ስልጠናው የእናቶችና የጨቅላ ሕፃናት ሞት ለመቀነስ የሚደረገውን ጥረት የሚያግዝ ነው

አዲስ አበባ፦ የእስራኤል የህክምና ቡድን በአለርት አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የጨቅላ ሕፃናት ህክምና ላይ እየሰጠ ያለው ስልጠና እንደሀገር የእናቶችና የጨቅላ ሕፃናት ሞት ለመቀነስ የሚደረገውን ጥረት እንደሚያግዝ ተገለጸ፡፡

በስልጠናው ወቅት በሆስፒታሉ የህክምና አገልግሎት ሜዲካል ዳይሬክተር ፀጋዬ ገብረአናንያ(ዶክተር) እንደገለጹት፤ በህክምና ቡድን አባላቱ እየተሰጠ የሚገኘው ስልጠና በኢትዮጵያ እንደሀገር የተያዘውን የእናቶችና የጨቅላ ሕፃናት ሞት ለመቀነስ የሚደረገውን ጥረት የሚያግዝ ነው፡፡

የህክምና ቡድኑ ለሶስት ቀናት የሚቆይ የተሟላ የተግባር ስልጠናና የህክምና ቁሳቁስ ድጋፍ እንደሚያደርግ የጠቆሙት ዳይሬክተሩ፤ የጨቅላ ሕፃናት ሞትን ለመከላከል የሚያስፈልገው የሰለጠነ የሰው ኃይል፣ የተሟላ የህክምና አገልግሎት መስጫ ቦታና መሳሪያ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

እነኝህ ምክንያቶች ለጨቅላ ሕፃናት ሞት መጨመር ምክንያት መሆናቸውን ጠቅሰው፤ ስልጠናው የዘርፉ ባለሙያዎችን አቅም የሚያሳድግና ተጨማሪ እውቀት የሚገኝበት መሆኑን ፀጋዬ( ዶክተር) ገልጸዋል።

እንደ ፀጋዬ (ዶክተር) ገለጻ፤ የጨቅላ ሕፃናት የህክምና አገልግሎት በተለይም እድሜያቸው ሳይደርስ የተወለዱትን፣ በተለያዩ እንፌክሽኖች የተጠቁ ሕፃናትን ማከም የሚችል የሰለጠነ ባለሙያ እንዲኖር እንደእነኝህ አይነት ለየት ያሉ ስልጠናዎች አስፈላጊ ናቸው፡፡ ሰልጣኞቹ በጤና ሚኒስቴር አማካኝነት ከተለያዩ ተቋማት የተመረጡ መሆናቸውን በመግለጽ፤ ስልጠናው በቀጣይ ቀናት ተጠናክሮ የሚቀጥል ነው፡፡

በኢትዮጵያ የእስራኤል ምክትል አምባሳደር ቶሜር ባር ላቪ በበኩላቸው፤ የህክምና ቡድን አባላቱ በተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት ተንቀሳቅሶ ለዘርፉ ባለሙያዎች ስልጠና በመስጠት የጨቅላ ሕፃናት ሞትን ለመቀነስ ጥረት እያደረጉ መሆኑን አንስተው፤ ከስልጠናው በተጨማሪ ለተለያዩ ሆስፒታሎች የህክምና ቁሳቁስ ድጋፍ መደረጉን ጠቁመዋል።

እንደ ምክትል አምባሳደሩ ገለጻ፤ ሁለቱ ሀገራት ከሚተባበሩባቸው ዘርፎች ውስጥ አንዱ የጤና ዘርፍ ተጠቃሽ ነው፡፡ የእስራኤል የህክምና ልዑካን አባላት በአዲስ አበባ እና በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች በመንቀሳቀስ ህሙማንን በማየትና ለኢትዮጵያውያን የጤና ባለሙያዎች በጨቅላ ሕፃናት፣ አጥንት፣ ዓይንና በሌሎችም የህክምና ዘርፎች ስልጠና ይሰጣሉ፡፡

በአሁኑ ወቅት እስራኤል የዜጎቿን ደህንነት ለማስጠበቅ በምታደርገው ጥረት ከባድ ጊዜ እያሳለፈች መሆኑን በማንሳት፤ ኢትዮጵያና እስራኤል ታሪካዊ ግንኙነት ያላቸው ሀገራት መሆናቸውን ማሳያ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

መሰል ድጋፎችና የትብብር ሥራዎች የእስራኤል እና ኢትዮጵያ ግንኙነት የበለጠ እንደተጠናከረ ማሳያ መሆናቸውንና ሀገራቱ በቀጣይ በቴክኖሎጂ፣ በጤና፣ በትምህርትና በሌሎች ዘርፎች የሚደረገው ትብብር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ጠቁመዋል።

ቃልኪዳን አሳዬ

አዲስ ዘመን  መስከረም 8 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You