ከ20 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን ዝግጅቱን ጀምሯል

የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ወንዶች ብሔራዊ ቡድን የአፍሪካ ዋንጫ የሴካፋ ዞን ማጣሪያ ውድድር ከማድረጉ በፊት የዋና እና ረዳት አሰልጣኞች መሾማቸውን የኢትዮጵያ እግር ካስ ፌዴሬሽን ከትናንት በስቲያ ይፋ አድርጓል። በዚህም መሰረት ስዩም ከበደ የወጣት ቡድኑ ዋና አሰልጣኝ በመሆን የተሾመ ሲሆን ዓቢይ ካሳሁን እና አምሳሉ እስመለዓለም በምክትል አሰልጣኝነት ተሹመዋል።

በቅዱስ ጊዮርጊስ የወጣት ቡድን አሰልጣኝ በመሆን የአሰልጣኝነት ህይወትን የጀመረው ስዩም በዋናው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንም በምክትል አሰልጣኝነት አገልግሏል። ብዙ ልምድ ካላቸው አሰልጣኞችም አንዱ ሲሆን፣ ኢትዮጵያ ከ31 ዓመታት በኋላ ለአፍሪካ ዋንጫ ስታልፍ የአሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው ረዳት በመሆን አገልግሏል። በክለብም በትልቅ ደረጃ መስራት የቻለ ሲሆን ፋሲል ከነማን፣ መቻልን እና ሲዳማ ቡናን ማሰልጠን ችሏል።

የአሰልጣኞቹን ሹመት ተከትሎ አሰልጣኝ ስዩም ለ38 ተጫዋቾች ጥሪ ያደረጉ ሲሆን፤ ከትናንት ጀምሮ በካሌብ ሆቴል በመሰባሰብ ለማጣሪያ ውድድሩ ዝግጅታቸውን ጀምረዋል።

አሰልጣኝ ስዩም በሁሉም የሜዳ ክፍሎች ለበርካታ ተጫዋቾች የመጀመሪያ ጥሪ ያደረጉ ሲሆን በጊዜያዊነት አምስት ግብ ጠባቂዎችን በቡድናቸው ውስጥ አካተዋል። አብዩ ካሳዬ ከድሬዳዋ ከተማ፣ አማኑኤል ደስታ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣ ታምራት ቅባቱ ከመቻል፣ እንዳሻው ኡርጋ ከኢትዮጵያ ቡና እና አብነት ሀብቴ ከወላይታ ድቻ በግብ ጠበቂነት ተመርጠዋል። አብዱልሰመድ የሱፍ፣ ኪሩቤል ዳኜ፣ እስራኤል ሰማያት፣ ድልአዲስ ገብሬ፣ ፍፁም ፍትሕአለው፣ ዋንጫ ቱት፣ ቢንያም በቀለ፣ ብሩክ ታረቀኝ፣ አበበ ሸኖ፣ ዮናስ ለገሰ እና ተመስገን ታደሰ በመሃል ተከላካይነት መካተት ችለዋል።

በአማካኝና አጥቂ ክፍሉም ብዙ ተጫዋቾች በጊዜያዊነት ሲያዙ ሚኪያስ ፀጋዬ፣ ሚራጅ ሰፋ፣ ያሬድ ብሩክ፣ ዣቪር ሙሉ፣ አንዋር በድሩ፣ መላኩ አየለ፣ ቃለአብ ፈለቀ፣ ዮሃንስ መንግስቱ፣ ሚኪያስ በዳሶ፣ ቴዎድሮስ ባንቴ እና ሰለሞን ገመቹ በአማካኝ ክፍሉ የተካተቱ ናቸው። ቸርነት መንግስቱ፣ ፀጋ ከድር፣ አብነት ዓባይነህ፣ የአብስራ ተስፋዬ፣ ዮናታን ኤልያስ፣ ዳግም አወቀ፣ ዳዊት ዮሃንስ፣ አንተነህ ተፈራ፣ ሄኖክ ኤርሚያስ፣ ሀብታሙ ጉልላት እና ሚሊዮን ኃይሌ በአጥቂ ክፍሉ የተካተቱ ወጣት ተጫዋቾች ሆነዋል።

በታንዛንያ አስተናጋጅነት በሚካሄው ከ20 ዓመት በታች አፍሪካ ዋንጫ የሴካፋ ዞን ማጣሪያ ውድድር ላይ የሚሳተፈው የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ወንዶች ብሔራዊ ቡድን ዘጠኝ የዞኑ ሀገራትን በሚያሳትፈው የማጣሪያ ውድድር ዞኑን በመወከል በአፍሪካ ዋንጫ ከሚሳተፉ ሁለት ሀገራት አንዱ ለመሆን ይፋለማል።

የምሥራቅና መካከለኛው አፍሪካ የእግር ኳስ ማህበራት ምክር ቤት(ሴካፋ) የማጣሪያ ድልድል ባለፈው ሳምንት በዳሬሰላም ይፋ ማድረጉ ይታወሳል። የአፍሪካ ከ20 ዓመት በታች ዋንጫ ማጣሪያ በስድስት ዞኖች ተከፍሎ የሚካሄድ ሲሆን 48 ሀገራት እንደሚሳተፉበት የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን(ካፍ) አስታውቋል። የሴካፋ ዞን የማጣሪያ ውድድር በሁለት ምድቦች ተደልድሎ የሚካሄድ ሲሆን ዘጠኝ ሀገራት ለዋንጫው ለማለፍ ይፎካከራሉ። ኢትዮጵያ በምድብ ሁለት ከዩጋንዳ፣ ደቡብ ሱዳን እና ቡሩንዲ ተደልድላ ውድድሯን ታከናውናለች። በሴካፋ ዞን ማጣሪያ በምድብ አንድ ታንዛንያ፣ ሩዋንዳ፣ ሱዳን፣ ጅቡቲ እና ኬንያ ተደልድለዋል። የማጣያ ውድድሩ በጥቅምት መጀመሪያ በታንዛኒያ አስተናጋጅነት ከተከናወነ በኋላ ዞኑን ወክለው የሚሳተፉ ሁለት ሀገራት ይለያሉ።

25ኛው የአፍሪካ ከ20 ዓመት በታች ዋንጫ ውድድር እአአ በ2025 ጥር ወር ላይ በደቡብ አፍሪካ አስተናጋጅነት የሚካሄድ ሲሆን 12 ሀገራትም ይሳተፋሉ። በአፍሪካ ከ20 ዓመት በታች ዋንጫ የሚሳተፉ እና ግማሽ ፍጻሜ የሚገቡ ሀገራት ቺሊ ለምታዘጋጀው የዓለም ከ20 ዓመት በታች ዋንጫ በቀጥታ ያልፋሉ።

ዓለማየሁ ግዛው

አዲስ ዘመን መስከረም 8/2017 ዓ.ም

 

 

 

 

Recommended For You