ፋሲል ከነማ የአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫን አነሳ

የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አንድ ጊዜ ማንሳት የቻለው ፋሲል ከነማ በተጋባዥነት የተሳተፈበትን የ2016 ዓ.ም የአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ ማሸነፍ ችሏል፡፡ ፋሲል አምስት ክለቦችን ባሳተፈው የአዲስ አበባ ዋንጫ በፍፃሜ ጨዋታ ኢትዮ- ኤሌክትሪክን በመርታት ቻምፒዮን ሆኖ አጠናቋል፡፡

18ኛው የአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ ከነሐሴ 28/2016 ዓ.ም ጀምሮ በአዲስ አበባ አበበ ቢቂላ ስታድየም ሲካሄድ የቆየ ሲሆን ከትናንት በስቲያ ፍጻሜ አግኝቷል፡፡ አፄዎቹ በውድድሩ በተጋባዥነት ቀርበው የአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫን ማንሳት ከቻሉ ክለቦች ተርታ ያሰለፋቸውን ታሪክ መጻፍ ችለዋል፡፡ አፄዎቹ በፍጻሜው ጨዋታ ከአንድ ዓመት የከፍተኛ ሊግ ቆይታ በኋላ ዘንድሮ ወደ ኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ያደገው ኢትዮ-ኤሌክትሪክን ገጥመው 2 ለምንም በመርታት ነው ዋንጫው የወሰዱት፡፡ ለፋሲል ከነማ የማሸነፊያ ጎሎቹን ማርቲን ኩዛ በ24ኛው እና አፍቅሮት ሰለሞን በ63ኛ ደቂቃ ማስቆጠር ችለዋል፡፡

አፄዎቹ የመጀመሪያ የምድብ ማጣሪያ ጨዋታቸውን የፕሪሚየር ሊጉን ጠንካራ ክለብ ኢትዮጵያ መድንን 2 ለ 1 በሆነ ጠባብ ውጤት በመርታት የጀመሩ ሲሆን፣ በሁለተኛው የምድብ ጨዋታ ከዋንጫው ተፋላሚ ክለብ ጋር ነጥብ ተጋርተዋል፡፡ አፄዎቹ የፕሪሚየር ሊጉን ቻምፒዮን ኢትዮጵያ ንግድ ባንክን 3 ለ 1 በመርታትም የፍጻሜ ተፋላሚ ሆነዋል። የዋንጫው ተፋላሚው ኢትዮ-ኤሌክትሪክ በበኩሉ በምድብ ጨዋታዎች ከፋሲል ከነማ ጋር ነጥብ ሲጋራ ኢትዮጵያ መድንን እና መቻልን ረቶ ለፍጻሜ በቅቷል፡፡ ኢትዮ-ኤሌክትሪክ የአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫን ብዙ ጊዜ ካነሱት የመዲናዋ ክለቦች አንዱ ቢሆንም በምድብና በጥሎ ማለፍ ያሳየውን ጥንካሬ በፍፃሜው ላይ መድገም ሳይችል ቀርቶ ዋንጫውን አጥቷል፡፡

በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ፣ በኢትዮጵያ ዋንጫ እና በአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ ብዙ ድሎችን ያሳካው ኢትዮ-ኤሌክትሪክ ከውጤት ርቆና ከሊጉ ወርዶ ከአንድ ዓመት ቆይታ በኋላ መመለሱ ይታወሳል፡፡ ኢትዮ-ኤሌክትሪክ በውድድሩ ለፍጻሜ ደርሶ ሲሸነፍ የመጀመሪያው ሲሆን ከዚህ ቀደም በሶስት አጋጣሚዎች ለፍጻሜ ደርሶ ዋንጫውን አንስቷል፡፡

የዘንድሮውን የአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ በማሳካት የ2017 የውድድር ዘመን ጉዛቸውን የጀመሩት አፄዎቹ፣ ከአዲስ አበባ ክለቦች ውጭ ይህን ዋንጫ ማንሳት ከቻሉ ጥቂት ክለቦች አንዱ ለመሆን በቅተዋል፡፡ አምና ሃዲያ ሆዕሳና ተጋባዥ ክለብ በመሆን ኢትዮጵያ ቡናን አሸንፎ የአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ ቻምፒዮን እንደነበር አይዘነጋም፡፡ ውድድሩ መካሄድ ከጀመረ አሥራ አራት ዓመታትን ማስቆጠር የቻለ ሲሆን አብዛኛው የከተማዋ ክለቦች ዋንጫውን በማንሳት የበላይነት አላቸው።ኢትዮጵያ ቡና እና ቅዱስ ጊዮርጊስ ብዙ ጊዜ ለፍጻሜ መድረስ የቻሉ ክለቦች ሲሆኑ ፈረሰኞቹ ስምንት ጊዜ ለፍጻሜ ደርሰው አምስቱን በማሸነፍ ዋንጫውን አንስተዋል።

ውድድሩ እንደተጀመረ የመጀመሪያውን ዋንጫ ያነሱትና የአምናው የፍጻሜ ተፋላሚ የነበሩት ቡናማዎቹ ስድስት ጊዜ የፍጻሜ ተፋላሚ በመሆን ማሳካት የቻሉት ሁለት ዋንጫ ብቻ ነው። ኢትዮ-ኤሌክትሪክ ሶስት ዋንጫዎችን የወሰደ ሌላኛው የከተማው ክለብ ሲሆን፣ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አንድ ዋንጫ አሳክቷል፡፡ የ2016 የአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ አሸናፊ ፋሲል ከነማ፣ ዳሽን ቢራ እና ሃድያ ሆሳዕና በተጋባዥነት ዋንጫውን ካነሱት ክለቦች ውስጥ ይጠቀሳሉ፡፡

ኢትዮጵያ ቡና እና ቅዱስ ጊዮርጊስ የወዳጅነት ጨዋታ ለማድረግ ወደ አሜሪካ በማቅናታቸው በውድድሩ ያልተሳፉ ሲሆን፣ አምስት ክለቦች የውድድሩ ተሳታፊ ነበሩ፡፡ ኢትዮ- ኤሌክትሪክ፣ መቻል፣ ኢትዮጵያ መድን፣ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና ተጋባዡ ፋሲል ከነማ በውድድሩ የተሳተፉ ክለቦች ናቸው፡፡

ከፍጻሜው ጨዋታ ቀደም ብሎ በተካሄደው የደረጃ ጨዋታ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክና መቻል በመደበኛ የጨዋታ ሰዓት 1 ለ 1 አጠናቀው በመለያ ምት 5 ለ 3 በሆነ ውጤት ንግድ ባንክ አሸንፎ የሶስተኝነት ደረጃን ሲይዝ፣ መቻል አራተኛ ደረጃን በመያዝ ውድድሩን አጠናቋል፡፡ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በነበረበት የአፍሪካ ቻምፒዮንስ ሊግ የሁለተኛ ዙር የመጀመሪያ ጨዋታ ምክንያት በሁለተኛ ቡድኑ ተሳታፊ የሆነው፡፡

 ዓለማየሁ ግዛው

 አዲስ ዘመን መስከረም 7/2017 ዓ.ም

 

Recommended For You