ሀገር ወዳዱ ሰው ፤-ኢንጂነር ታደለ ብጡል

ሀገራቸውን ከውጭ ወራሪና ጠላት በመከላከል አኩሪ ታሪክ የሠሩ፣ የሕዝባቸውን ደኅንነትና አንድነት እንዲጠበቅ ለማድረግ መስዋዕትነት የከፈሉና አንፀባራቂ ታሪክ የሠሩ ጥቂቶች አልበሩም። በደራሲነት፣ በሙዚቃ፣ በሥዕል፣ በስፖርት፣ በታሪክ፣ በሳይንስና በእምነት አስተምሮ፣ የኪነ ጥበብና የምርምር ሥራዎችም ኢትዮጵያን በዓለም የበለጠ እንድትታወቅ ያደረጉ ትናንትናም ዛሬም ደምቀው የሚታዩ ደማቅ ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያውያት ብዙዎች ናቸው።

አብዛኞች እንደዋዛ ጥለዋት በሚለይዋት ዓለም ጥቂቶች ከራሳቸው ለሌሎች የሚተርፍ አስተዋጽኦ አበርክተው ማለፉ ይሳካላቸዋል። በሚያልፍ ዕድሜ የማያልፍ ሥራ ሠርተው ስማቸው ሲወሳ ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያን መካከል አንዱ ከቀናት በፊት ከዚህ ዓለም ድካም ያረፉት ኢንጂነር ታደለ ብጡል አንዱ ናቸው።

ኢንጂነር ታደለ በሥነ ጥበብ፣ በታሪክ እና በቅርስ ጠባቂነት፣ በንግግር አዋቂነት፣ በድርሰት ሥራዎቻቸው፣ በላቀ የምህንድስን በሙያቸው እንዲሁም በበጎ አድራጊነት ሥራቸው ይታወቃሉ።

ታታሪነት እና ሀገር ወዳድነትን በተግባር ያሳዩን ሁለገብ ባለሙያ፣ ሁሉም በየዘርፉ እና በየአቅሙ ለሀገሩ ምን ማበርከት እንዳለበት ሠርተው ያሳዩ ሊቅ ናቸው።

መኖሪያ ቤታቸው የኢትዮጵያ ባለውለታ የሆኑ ታላላቅ ሰዎችን በሚዘክሩ ታሪካዊ እና ዕድሜ ጠገብ ሥዕላት፣ ምስሎች እና ፎቶግራፎች፣ ቅርጻ ቅርጾች እንዲሁም የኢትዮጵያን ታሪክ እና ቅርስ በተመለከተ በጽሑፎች፣ በሰነድ፣ በምስል፣ በድምፅ እና በቪዲዮ ያሰባሰቧቸው መረጃዎችና ቅርሶች የተሞላ እንደሆነ የቅርብ ወዳጆቻቸው ይመሰክራሉ።

ለኢትዮጵያ ታሪክ፣ ባሕልና ቅርስ ያላቸው ክብር እና ተቆርቋሪነት እንዲሁም ለሕዝባቸው ያላቸው ፍቅር እና ወገናዊነት በጣም ጥልቅ ነው ይባልላቸዋል።

ኢንጂነር ታደለ ብጡል ክብረት ታኅሣሥ 21 ቀን 1919 ዓ.ም አዲስ አበባ ከተማ ተወለዱ። የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን በቀድሞው ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ (የአሁኑ ኮከበ ጽባህ) ት/ቤት ተከታትለዋል። የከፍተኛ ትምህርታቸውን ደግሞ በአሜሪካ ዩኒቨርሲቲ ኦፍ ዊል ካስሰን እና ቺካጎ የተከታተሉ ሲሆን፣ በስዊድን ስቶክሆልም ደግሞ በስተረክቸራል ዲዛይን በሲቪል ኢንጂነሪንግ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን አግኝተዋል።

ወደ ውጭ ለትምህርት ከማቅናታቸው በፊት በመንግሥት ባንክ ለ8 ዓመታት ያገለገሉት ኢንጂነር ታደለ፣ ስዊድን ሀገር በጆንማትሰን ኩባንያ ተቀጥረው የቬኔግሬን የሪሰርች ማዕከል ግንባታ ላይ መሥራት ጀመሩ።

በስዊድን ሀገር በወቅቱ ረጅም በነበረው ባለ 25 ፎቅ ሕንጻ ሥራ ተቆጣጣሪ በመሆን፣ ኢራን ውስጥ በተሠራ የባንክ የምድር ቤት ገንዘብ ማስቀመጫ፣ ፖላንድ የሚገኝ ትልቅ ሆቴል ስትራክቸራል ዲዛይን ሥራዎችን ሠርተዋል።

ስዊድን እያሉ የ1953 ዓ.ም የእነ ጄኔራል መንግሥቱ ንዋይ መፈንቅለ መንግሥት ሙከራ በስዊድን የኢትዮጵያ ኤምባሲ አምባሳደር ከነበሩት ወዳጃቸው አቶ ተፈሪ ሻረው እና ከቅርብ ጓደኛቸው ኢንጂነር አሰፋ ብርሃነ ሥላሴ ጋር ሆነው ደግፈውት ነበር። የመንግሥት ግልበጣ ሙከራው ሲከሽፍም ሁሉም ፓስፖርታቸውን ተነጥቀው ለስደት ተዳረጉ።

ኢንጂነር ታደለ፣ ወደ ሀገራቸው ተመልሰው የግዮን ሆቴልን የመዋኛ ገንዳ የሠራው መሐንዲስ ጉስታቭለን ከሚሠራበት ሀዩስ ኮንሱልት ቢሮ ተቀጥረው ሁለት ዓመት ከሠሩ በኋላ የራሳቸውን የሪል ስቴት እና የግንባታ ድርጅት አቋቁመው ሥራ ጀመሩ። በዚህም አሮጌ ቤቶችን እየገዙ አድሰው በማከራየት ሥራ ተሰማሩ።

በ1966 ዓ.ም ኢትዮጵያ ውስጥ ድርቅ በመከሰቱ የሀገራቸውን ሕዝብ ለመርዳት ከስዊድን ሕዝብ ከስምንት ሚሊዮን ብር በላይ የሚያወጣ መድኃኒት፣ የሆስፒታል አልጋ፣ የኤክስሬይ መሣሪያዎች ስላገኙ የትራንስፖርቱን ወጪ ከራሳቸው ገንዘብ በመክፈል ቁሳቁሶቹን አምጥተው ለእርዳታ ማስተባበሪያ ኮሚሽነር አስረክበዋል።

በተለያየ ጊዜ እርዳታዎችን ከስዊድን ሀገር እያሰባሰቡ የበጎ አድራጎት አገልግሎት ሲሰጡ ቆይተዋል። የአቅመ ደካሞች መርጃ ድርጅት፣ የገበሬዎች ማኅበር እና ለዕድገት በህብረት ዘማች ተማሪዎች የድጋፎቻቸው ተቋዳሾች ናቸው። በአዲስ አበባም 300 ተማሪዎችን የሚያስተናግድ ትምህርት ቤት በገንዘባቸው ሠርተው አስረክበዋል።

በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት የማታ ትምህርትን ያስጀመሩት እርሳቸው መሆናቸውም ይነገራል። በታዋቂው አርበኛ የተሰየመውን ደጃዝማች ወንድይራድ ትምህርት ቤትንም ከሌሎች ሰዎች ጋር በመሆን ያቋቋሙት ኢንጂነር ታደለ ናቸው።

የአክሱም ሐውልት እና ሌሎች የኢትዮጵያ ቅርሶች ብሔራዊ አስመላሽ ኮሚቴ አባል በመሆንም የዜግነት ኃላፊነታቸውን ተወጥተዋል። የአክሱም ሐውልትን ለማስመለስ ከሌሎች ጋር በመሆን ከአሥራ ሰባት ዓመታት በላይ ታግለዋል። ሐውልቱን ለማስመለስ እንደ አርበኛም ጣሊያኖችን በመከራከር፣ እንደ ባለ ሀብት በገንዘባቸው፣ እንደ ምህንድስና ባለሙያነታቸው የሐውልቱን አመላለስ የምሕንድስና ጉዳዮች አጥንቶ እንዲተገበር በማድረግ ታሪካቸውን በወርቅ ቀለም ለመጻፍ በቅተዋል።

ኢንጂነር ታደለ ብጡል የተለያዩ ባሕላዊና ትውፊታዊ ቅርሶችን ከተለያዩ ክፍላተ ዓለማት በራሳቸው ወጪ በመግዛት በመሰብሰብም ይታወቃሉ። የሰበሰቧቸውን ቅርሶችም በኢትዮጵያ ውስጥ ለሚገኙ ልዩ ልዩ ሙዚየሞች በመለገስ ታሪካዊ አስተዋጽኦ አድርገዋል።

ኢንጂነር ታደለ በኢትዮጵያ ታሪክ ጉዳይ እረፍት የላቸውም። በተለያዩ ጊዜያት በአውሮፓና በአሜሪካ ስለ ኢትዮጵያ ታሪክ፣ ቅርስ፣ ባሕል፣ ነፃነትና ጀግንነት አስረድተዋል፣ ኢግዚቢሽኖችን አሳይተዋል። በአሜሪካ ኮሎምቢያ ዩኒቨርሲቲ ግብዣ ተደርጎላቸው ስለ አክሱም ሐውልት አወሳሰድ እና በኋላም ወደ ሀገሩ እንዲመለስ የተደረገውን ትግል በተመለከተ ሰፊ ቃለ መጠይቅ አድርገዋል።

አንጂነር ታደለ የምህንድስና ባለሙያ ብቻ ሳይሆኑ የተዋጣላቸውም ደራሲ ናቸው። ከድርሰት ሥራዎቻቸውም መካከል ማራዠት 1 እና 2፣ ሦስትዮሽ የግጥም ስብስቦች፣ ውለታ፣ ከበደ ሚካኤል ከልጅነት እስከ ዕውቀት፣ መጽሐፈ ውይይት ከከበደ ሚካኤል መኩሪያ ጋር የሚሉት ይገኛሉ።

በተጨማሪም በአፄ ቴዎድሮስ፣ በልዑል ዓለማየሁ፣ በሐኪም ወርቅነህ እሸቴ ዙሪያ ከጻፏቸው መጻሕፍት ሌላ የአማርኛ የምልክት ቋንቋ መዝገበ ቃላትን አዘጋጅተው አሳትመዋል። በአጠቃላይ ከአሥራ አምስት በላይ መጻሕፍትን እንዳዘጋጁ ታሪካቸው ያሳያል።

ኢንጂነር ታደለ ብጡል ለሀገራቸው በሠሩአቸው ሥራዎች በርካታ ሽልማቶች ተበርክተውላቸዋል። ከነዚህ ሽልማቶች መካከልም የአክሱምን ሐውልት ለማስመለስ በነበራቸው ሚና፣ ከኢፌዴሪ መንግሥት ፕሬዚዳንት ሙላቱ ተሾመ(ዶ/ር) እጅ የወርቅ ሜዳሊያ፣ ከትግራይ ክልል መስተዳድር ርዕሰ መስተዳድር የወርቅ ካባ፣ ከአክሱም ሕዝብ የአክሱም ሐውልቶች ቅርፅና ሐረግ ያለበት ከእንጨት የተሰራ ታጣፊ የፎቶግራፍ ማቀፊያ ተሸልመዋል።

በበጎ አድራጎት ሥራዎቻቸው፣ በግል ገንዘባቸው እና ሌሎችን አስተባብረው ለሠሩአቸው ትምህርት ቤቶች እንዲሁም ለኢትዮጵያ ቱሪዝም ዕድገት ላደረጉት አስተዋጽኦ በርከታ ሽልማቶችን ተሸልመዋል። የ2008 ዓ.ም የዓመቱ በጎ ሰው ድርጅት ሽልማት በቅርስና ባሕል ዘርፍ፣ ከንባብ ለሕይወት ድርጅት የዕድሜ ዘመን ታላቅ የጥበብ ባለውለታ ዋንጫ ከሽልማቶቻቸው መካከል ነው።

ከ2002 እስከ 2009 ዓ.ም የዲካ ትራቨል ኤንድ ሎጅስ አስጎብኚ ድርጅት የዳይሬክተሮች ቦርድ ሰብሳቢ በመሆን ለፈፀሟቸው ከፍተኛ ተግባራት ዋንጫ ተሸልመዋል። እንዲሁም ለያሬድ ሙዚቃ ትምህርት ቤት እና ለኢትዮጵያ መስማት የተሳናቸው ማኅበር ላደረጉላቸው ልዩ ልዩ ድጋፎችም ዕውቅና አግኝተዋል።

ከፊንላንድ ኤምባሲ ለምነው ባስገኙት 650 ሺህ ብር ባለ 2 ፎቅ ትምህርት ቤት በማሰራታቸውም ከኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት እጅ የተማሪዎች መመረቂያ የሆነ ውብ ሥዕል ተሸልመዋል።

የያሬድ ሙዚቃ ትምህርት ቤትን እና የአዲስ አበባ ዲዛይን ትምህርት ቤት ወደ ዩኒቨርስቲ ደረጃ ከፍ እንዲል በኮሚቴ አባልነታቸው ላደረጉት ከፍተኛ አስተዋፅኦ በሁለቱ ትምህርት ቤቶች ስም በዲዛይን ትምህርት ቤቱ ዳይሬክተር በአርቲስት በቀለ መኮንን እጅ የተሠራ ውብ ሥዕል ተሸልመዋል።

የኢትዮጵያ መስማት የተሳናቸው ማኅበር የሕፃናት ትምህርት ቤት እና የማኅበሩን የመሰብሰቢያ አዳራሽ ከፊንላንድ ኤምባሲ እና ከካናዳ ድርጅት ለምነው በአገኙት ገንዘብ ሙሉ እድሳት እንዲደረግ ላደረጉት አስተዋፅኦም ከማህበሩ ፕሬዚዳንትና ከፊንላንድ መስማት የተሳናቸው ማኅበር ዕውቅና ተሰጥቷቸዋል።

ከ15 በላይ የሚሆኑ መጻሕፍት በማዘጋጀት ለአንባቢ አበርክተዋል። በተጨማሪም በሰባ ስድስት ዓመታቸው የምልክት ቋንቋ በመማር የምልክት ቋንቋ መጽሐፍ ለመፃፍ ችለዋል። ከዚህ ሌላ “ኢትዮጵያ ጽናት” የሚል ፊልም ሰርተው የሀገራቸውን ታሪክ በመሰነድ ታሪክ ሰርተው ለሕዝብ አበርክተዋል።

ኢንጂነር ታደለ ብጡል ክብረት በሥነ ጥበብ፣ በታሪክና በቅርስ ጠባቂነት፣ በንግግር አዋቂነት፣ በበጎ አድራጊነት ሥራቸው ለእኛ ለኢትዮጵያዊያን ታታሪነትና ሀገርን መውደድ በተግባር ያሳዩን ትልቅ ሰው ነበሩ።

ኢንጂነር ታደለ ብጡል ክብረት አቃቂ ስታዲየምን መጀመሪያ የቀየሱ ሰው ነበሩ። አቃቂ ስታዲየም የእግር ኳስ ሜዳ ከመሆኑ በፊት ቀድሞ በዘመነ ደርግ “አብዮት አደባባይ” ተብሎ ሕዝባዊ ስብሰባ ይደረግበት የነበረ ሥፍራ ነው።

ደርግ በመጀመሪያዎቹ የስልጣን ዘመናት ሕዝባዊ ስብሰባውን ወደ እዚህ ሥፍራ ከማምጣቱ በፊት የቀድሞ 08 አሁን የውሀና ፍሳሽ ህንጻ የሚሰራበት ሥፍራ ላይ ነበር ሕዝባዊ ስብሰባ ሲያደርገበት የነበረው። በኋላም ቦታው አመቺ ሳይሆን በመቅረቱ ቀድሞ አብዮት አደባባይ በኋላም አቃቂ ስታዲየም ለስብሰባ የሚሆን መድረክ በመገንባት በማዘጋጀት ሕዝባዊ ስብሰባውን ወደ እዚህ ሥፍራ አዙሮታል።

በኋላም በአቃቂ ማዘጋጃ አማካኝነት በዘመኑ የነበሩት ስመ ጥር ኢንጂነር በማስመጣት ቅየሳ እንዲያደርጉ እና ለእግር ኳስ መጫወቻ ስታዲየም እንዲመች አድርገው ቀይሰውታል። የመጀመሪያው የስቴዲየም አጥር ግንባታም የተከናወነው ከመናገሻ አውራጃ ሥር ከነበሩ ወረዳዎች በተወጣ ገንዘብ ነበር።

እኚህ ታላቅ የሀገር ባለውለታ በተወለዱ በ97 ዓመታቸው ነሐሴ 28/2016 ዓ.ም ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል። ሥርዓተ ቀብራቸውም ነሐሴ 30/2016 ዓ.ም በመንበረ ጸባኦት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ተፈፅሟል።

እኛም በዚህ ለሕዝብና ለሀገራቸው መልካም ያደረጉና በተሰማሩበት ዘርፍ ሁሉ የማይነጥፍ ዐሻራ ማኖር የቻሉ ግለሰቦች ታሪክ አንስተን ለአበርክቷቸው ክብር በምንሰጥበት በዚህ የባለውለታዎቻችን አምድ እውቁን ኢንጂነር፣ ደራሲና በጎ አድራጊ ታደለ ብጡልን ላበረከቱት ዘመን ተሻጋሪ ሥራ አመሰግነናል። ቸር እንሰንብት!

ክብረአብ በላቸው

አዲስ ዘመን መስከረም 8/2017 ዓ.ም

 

 

 

 

Recommended For You