ዜና ሐተታ
“በዓል ሲደርስ ጎረቤቶቻችን በግና ዶሮ ሲገዙ የእኔ ልጆች እማዬ መቼ ነው ዶሮ የምንገዛው ይሉኛል” ያሉት ወይዘሮ ሸዋዬ ገመቹ፤ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለበዓል በሚያደርገው ድጋፍ የልጆቻቸው ጥያቄ መልስ ማግኘቱ እንዳስደሰታቸው ይናገራሉ።
ከተማ አስተዳደሩ ለበዓል የሚያደርገው ድጋፍ በዓሉን በደስታ እንዳከብር አድርጎኛል ያሉት ወይዘሮ ሸዋዬ፤ ከኮሮና ወረርሽኝ በኋላ ከተማ አስተዳደሩ በየበዓላቱ በሚያደርገው የማዕድ ተግባር ተጠቃሚ መሆናቸውን ገልጸው፤ “እኛን ያሰቡትን ሁሉ ፈጣሪ ዓመት ከዓመት ያድርስልን ሲሉ መርቀዋል።
ወይዘሮ ሸዋዬ ገመቹ የንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ነዋሪ እና የሦስት ልጆች እናት ናቸው። ሁለቱ ልጆች የራሳቸው ሲሆኑ፤ ሦስተኛዋ ግን የእህታቸው ልጅ እንደሆነች ተናግረዋል። የሦስተኛዋ ልጅ እናትና አባት በህይወት የሉም። ነገር ግን እንደልጃቸው እየተንከባከቧት እንደሆነ ነው የተናገሩት።
እነዚህን ልጆች በኪራይ ቤት ውስጥ ማሳደግ እየፈተናቸው እንደሆነ ገልጸው፤ በፊት ሰፊ የሥራ እድል ስለነበር እግዚአብሔር ይመስገን የሰው ፊት አላይም ነበር ብለዋል። አሁን ግን ኑሮ በጣም እየከበዳቸው በመምጣቱ አደባባይ ወጥተው የሰው ፊት እያዩ መሆኑን ተናግረዋል።
ኑሯቸውን የሚመሩት ማታ ማታ ድንች ቅቅል በመሸጥ እና በየሰው ቤቱ ልብስ በማጠብ መሆኑን የገለጹት ወይዘሮ ሸዋዬ፤ የተደረገልኝ የማዕድ መጋራት አመራሩ ደሃውን ሕዝብ እያየ መሆኑን ያሳያል። ማዕዱን ያጋራ ሁሉ እግዚአብሔር ይስጠው ሲሉ መርቀዋል።
በአዲስ አበባ ለቡ ሀና በሚባል አካባቢ የሚኖሩት ወይዘሮ ራሄል መስፍን በበኩላቸው፤ የሁለት ልጆች እናት መሆናቸውን ገልጸው፤ ከተማ አስተዳደሩ በዓሉን ምክንያት በማድረግ ማዕድ ያደረገላቸው የበዓሉ የደስታ ምንጭ እንደሆነላቸው ይገልጻሉ።
የመጀመሪያ ልጃቸው አሥር ዓመት የሞላው ሲሆን፤ ሁለተኛ ልጃቸው ደግሞ በሶስት ዓመቷ የልብ ታማሚ መሆኗን ገልጸው፤ ከተማ አስተዳደሩ ያደረገላቸው የአምስት ሊትር ዘይት እና የሃያ አምስት ኪሎ የዳቦ ዱቄት ከበዓል አልፎ ለተጨማሪ ቀናት ስንቅ እንደሚሆናቸው ገልጸዋል።
የልብ ታማሚ ልጃቸውን በመንከባከብ ረጅም ጊዜያቸውን እንደሚያሳልፉ ተናግረው፤ ይህም ሰርተው ገንዘብ እንዳያገኙ እንቅፋት እንደሆነባቸው ተናግረዋል። በዚህም በኢኮኖሚ ራሳቸውን እንዳይችሉና ከቀን ወደ ቀን ችግራቸው እየከፋ መምጣቱን ነው የገለጹት።
ልጃቸውን ተሸክመው ልብስ በማጠብ ህይወታቸውን እየመሩ መሆኑን ገልጸው፤ በወረዳ ያሉ አመራሮች የልብ ታማሚ ልጃቸውን በትንሹ እየደገፏት መሆኑን ይገልጻሉ፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ ልጃቸውን እንዲያድንላቸው ጠይቀዋል።
በአዲስ አበባ ሰፈረ ሰላም አካባቢ የሚኖሩ ወይዘሮ ሌንሴ ደሜ ደግሞ ለሁሉም ማዕድ አጋሪዎች ሁሉ ፈጣሪ እድሜ ይስጣቸው ብለው መርቀዋል። የተሰጣቸው ማዕድም በዓሉን በደስታ እንዲያከብሩ ያደረጋቸው መሆኑን ገልጸዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከ500 ሺህ በላይ ለሚሆኑ አቅመ ደካሞች እና የሀገር ባለውለታዎች እንዲሁም አነስተኛ ገቢ ላላቸው የመንግሥት ሠራተኞች አዲሱን ዓመት በደስታ እንዲቀበሉ ማዕድ አጋርቷል፡፡ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ልበ ቅን የሆኑ ባለሀብቶች፣ ወጣቶችና ተቋማትም በዚህ በጎ ተግባር እየተሳተፉ ይገኛል።ይህ ለወገን በችግር ጊዜ አለሁ ባይነት ባህል እየሆነ ሊመጣ ይገባል፡፡
ሳሙኤል ወንደሰን
አዲስ ዘመን መስከረም 8 ቀን 2017 ዓ.ም