ታሪክ ሰርተው ታሪክ የሚያስቀጥሉ እጆች

ጀምበር ወጥታ እስክትገባ..

ለሀገር ክብር መባ

ነገ ሳልል አሁን

ዛፍ ልትከል፣ ሰው ልሁን።

የዛሬ ነፃ ሃ ሳቤን በስንኝ ጀምሬአለሁ።

ታሪክ ያለው ታሪክ ሰርቶ ታሪክ ለማስቀጠል በተሰናዳ አእምሮና ልብ ውስጥ ነው። ኢትዮጵያውያን በአንድነት ከተነሱ የሚያቆማቸው እንደሌለ በተለያየ ጊዜ አይተናል። ከነዚህም ውስጥ አንዱ በየዓመቱ የክረምት መግባትን ተከትሎ የሚከወነው የአረንጓዴ ዐሻራ መርሀ ግብር አንዱ ነው። በዘንድሮ ዓመትም አዲስ ታሪክ የሰራንበት በአንድ ጀምበር ከ600 ሚሊዮን በላይ ችግኞችን በመትከል ተባባሪ ክንዳችንን ለዓለም ያሳየንበት ሕዝባዊ ንቅናቄ ነው።

ነሐሴ 17/2016 ዓ.ም በአረንጓዴ ዐሻራ ዳግማዊ ድል የተቀዳጀንበት ቀን ነው። ጀምበር ወጥታ እስክትገባ ለሀገር ክብር ዐሻራችንን ያሳረፍንበት ብሔራዊ የኩራት ቀናችን ነበር። ከዚህ ቀን አስቀድሞ መግለጫ የሰጡት ጠቅላይ ሚኒስተር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አዋቂዎች ከ20 በላይ፣ ታዳጊዎች ከ10 በላይ ችግኝ በመትከል ለሀገራቸው ያላቸውን ፍቅርና ክብር ለትውልድም ያላቸውን ይሁንታ በተግባር እንግለጥ ማለታቸው ተከትሎ ሕዝቡ በነቂስ ወጥቶ የታቀደውን አላማ አሳክቷል።

በእለቱም የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ ሰላማዊት ካሳ ‹እለቱ ኢትዮጵያውያን ታላቅ ስጦታን የሚያበረክቱበት እለት ነው። ለነገው ትውልድ የሚተርፍ ታላቅ ሥራን የሚሰሩበት ለሀገራቸውም ስጦታን የሚያበረክቱበት ነው› እንዳሉትም ሕዝቡ ለልጆቹ ወደር የማይገኝለትን ስጦታ አበርክቷል።

አረንጓዴ ዐሻራ በየዓመቱ በድርቅ ሳቢያ መስዋዕት ለምትከፍል አፍሪካና የሰሀራ ሀገራት ብዙ ነገራችን ነው። የግብርና ምርታችንን የምናሳድግበት፣ በምግብ ራሳችንን የምንችልበት፣ ሁለት ሶስት ጊዜ አምርተን የምግብ ምርቶችን በርካሽ እንድናገኝ የሚያደርግ፣ የደን ሽፋንን ጠብቆ የአየር ንብረትን የሚያስተካክል፣ የመኖር ዋስትናችንን የሚያረጋግጥ ላቅ ያለ ፋይዳ ያለው ንብረታችን ነው። ነገር ግን ይህንን ስጦታ ተንከባክቦ ለቁም ነገር ለማብቃት፤ የተሰራ ታሪክን ለማቆየት አቅምና አቋም የሚጠይቅ ጉዳይ ነው።

ይህንን ስልም አንድ ወላጅ በስሙ የሚጠሩ ልጆቹን ከወለደ በኋላ መውለዱ ታሪክ ብቻ ሆኖ እንዳይቀር ማብላት፤ ማጠጣትና መንከባከብ አለበት። የተከልናቸው ችግኞችም እንደዚሁ ናቸው የኛን እንክብካቤ እና ትኩረትን ይሻሉ።

በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ሰፊውን ድርሻ የሚይዘው ‹ኢትዮጵያ ለምለሟ› የሚለው ታሪክ ነው። በብዙ ሀገረኛ ዜማዎቻችን ውስጥ ይሄ እውነት በኩራት እና በሞገስ ተጠቅሷል። አሁን ላይ ይሄ ስም ተረት ከመሆን ባለፈ በእውን የሚታይ አይደለም። ምክንያቱም የደን ሽፋናችን ከጊዜ ወደጊዜ በሰው ሠራሽ እና በተፈጥሮ አደጋዎች በመመናመኑ ነው። ያለፈ ታሪካችንን ለመመለስ እና አዲሷን ኢትዮጵያ ለመፍጠር የአረንጓዴ ዐሻራ ንቅናቄ የአንበሳውን ድርሻ ይወስዳል። በአረንጓዴ ዐሻራ የንቅናቄ ቀኖቻችን ለነገ ተስፋ የምንጥልባቸውን ልጆች እንደመውለድ ነው። እነዚህ ተስፋዎቻችን ደግሞ አድገው ለፍሬ እስኪበቁ የኛን ትኩረት ይፈልጋሉ።

‹ኢትዮጵያ ለምለሟ› ብለን ዳግም የምንጠራትን እና ዳግም የምናዜምላትን ሀገር መፍጠር የዚህ ትውልድ የቤት ሥራ ነው። ንቅናቄያችን ለውጥ እያመጣ እንደሆነ ያለፈውን ጊዜ ማየቱ በቂ ነው። ከራሳችን አልፈን ለአፍሪካና ለዓለም ምልክት የሆንበት የአረንጓዴ ዐሻራ ትግበራ ነበር።

እንዲህ ዓይነቱ ሕዝባዊ ንቅናቄ ችግኝ ከመትከል ባለፈ ሌላም ላቅ ያለ ትርጉም ያለው ነው። የእንችላለን መንፈስን ከመፍጠር ባለፈ ኢትዮጵያውያን በአንድነት ከተነሳን የሚያቆመን ኃይል እንደሌለ የሚያሳይ ነው። አንድነት አጥታ በዘርና በጎሳ ለተከፋፈለች ሀገር ይሄን መሰሉ ሕዝባዊ ተሳትፎ ጥሩ ማሳያ ነው።

የሰው ልጅ ጊዜውን እና እውቀቱን በአግባቡ መጠቀም ከቻለ ሁሌም ታሪክ መሥራት ይችላል። የታሪክ አብራኮች የአንድነት ጽንሶች ናቸው። ታሪክ ለመሥራት ተያይዘንና ተቃቅፈን ወደፊት ከመሄድ ባለፈ ሌላ ምርጫ የለንም። በአንድ ጀምበር 600 ሚሊዮን ችግኞችን መትከል ለዓለም ብርቅ ለእኛ ግን የተቻለ ድል ነው። ቢሆንም ድላችንን ለማስጠበቅ በተባበረ ክንዳችን የተከልናቸውን ችግኞች በህብረት ልንጠብቃቸው ይገባል።

የታሪኮቻችን ቀለሞቻችን የተዋሃድንባቸው ናቸው። እንደ አረንጓዴ ዐሻራ ተዘካሪና ተሞጋሽ ያደረጉን የህብረ ብሔራዊ ድሎቻችን በአንድ አስበን በአንድ የወሰንባቸው ጉዳዮቻችን መሆናቸው አያጠራጥርም። ባለፉት ዓመታት ውስጥ በአረንጓዴ ንቅናቄ በድል ላይ ድልን እያስመዘገብን የለውጥ እና የተሃድሶ መንፈስ ውስጥ ነበርን። በአንድ ቀን 500 ሚሊዮን በላይ ችግኞችን ተክለን ዓለም ጉድ ሲለን ነበር። በአንድነት ስንቆም እንዲህ ነን… ለዓለም መደነቂያ ነው የምንሆነው።

የተናቅነው እና ዝቅ ያልነው አንድነት ስላጣን ነው። ታሪክ በአንድነት እጆች የሚጻፍ የብዙሃነት እሳቤ ስለመሆኑ ብዙ ሰነዶች አሳይተዋል። በአረንጓዴ ዐሻራ ዓለም አቀፍ ውዳሴንና መደነቅን ያመጣነው በጋራ ስላሰብን ነው። በጋራ ማሰብ በጋራ ማደግ፣ በጋራ መልማት ነው። ሀገራችንን የምናገለግለው እንዲህ ባለው ሀገራዊ ንቅናቄ ላይ ተሳትፎ ስናደርግ እንደሆነ በርካታ ማረጋገጫዎች አሉን። እንዲህ ዓይነቱ አጋጣሚ ሀገሬን በምን ላግዛት ብሎ ለሚጠይቅ ጥሩ አጋጣሚ ነው።

ሀገሬ ለኔ ምን አደረገችልኝ? በሚል መጠይቅ ውስጥ ከስረንና አቅመቢስ ሆነን ከሰነባበትን ከርመናል። ራሳችንን ሳናይ፣ ለሀገር ያለን ዋጋ ሳይገለጥልን ጣት በመቀሰር ብቻ እንደ ዜጋ ተቆጥረናል። እንደ አረንጓዴ ዐሻራ ያሉ ተግባሮች ከዚህ መሰሉ መጠይቅ ወጥተን እኔ ለሀገሬ ምን አደረኩ? ለሕዝቤ፣ ለትውልዱ ምን ሰራሁ? ብለን የምንጠይቅበትና ጠይቀንም መለስ የምናገኝበት መልካም አጋጣሚ ነው። ስለሆነም የተከልናቸውን ችግኞች በመንከባከብ እና ለውጤት በማብቃት ለቀጣዩ ትውልድ ውድና ብርቅ የሆነ ስጦታችንን ልናበረክት ግድ ይላል።

ነሐሴ አስራ ሰባት ይሄን ጥያቄ የመለስንበት፣ ሀገሬ ለኔ ምን ሰራች ሳይሆን እኔ ለሀገሬ ምን ሰራሁ ያለንበት የተሳትፎ ቀናችን ነበር። ሕዝቡ የከበረበት፣ ሀገር ጸዐዳ የለበሰችበት፣ ምድር ራቁቷን የሸፈነችበት ቀን ነው። ጀምበር ወጥታ እስክትገባ እጆቻችን ከታሪክ እውነት ጋር ተሳስረዋል። ስለኢትዮጵያ ደክመን፣ ስለትውልዱ ሰርተን ስማችንን በዓለም አደባባይ በወርቅ ቀለም ጽፈናል። ይሄ ነው እኔ ለሀገሬ ምን ሰራሁ ማለት። ለሀገር መድከም ለራስ መድከም እንደሆነ፣ ለትውልድ መልፋት ለራስ መልፋት እንደሆነ በሥራችን ገልጠናል።

ሕይወት የሚገኘው ከአረንጓዴ ቀለም ውስጥ ነው። አረንጓዴ ምድር የሕይወት መብቀያ፣ የህላዊ ማፍሪያ ማህጸን ነው። ምድር ሕይወትን አምጣ የምትወልደው እንዲህ ባለው የተፈጥሮ ዝምድና ነው። ከዚህ እውነት በመነሳት አረንጓዴ ዐሻራ የመኖር እና ያለመኖር ጉልህ ጥያቄ እንደሆነ መረዳት እንችላለን። ምድርን በአረንጓዴ መሸፈን ሕይወትን ማስቀጠል ሲሆን በተቃራኒው ማራቆት ሕይወትን መግታት ነው። አያት ቅድመ አያቶቻችን ሕይወታቸውን ሰውተው ሉዓላዊት የሆነች ሀገር አውርሰውና። እኛ ደግሞ ለልጆቻችን ሕይወታቸውን የሚያስቀጥሉበትና የአየር ንብረት ለውጥን መቋቋም የሚችሉባቸውን እስትንፋሶች እናወርሳለን።

በአረንጓዴ አስተሳሰብ ከዓለም ፊተኛ ነን። ዓለም ፊቷን አዙራ እኛን እያየች እና እያደመጠች ትገኛለች። አምናና ካቻምና ያስመዘገብናቸው ድሎች ዛሬም በእኛ እጅ ውስጥ ናቸው። ዘንድሮም አዲስ ታሪክ አስመዝግበን በተጠንቀቅ ቆመናል። በርግጠኝነት ይሄንንም የሚሽር አዲስ ሪከርድ በሚመጣው ዓመት እንጠብቃለን። እስካሁን ድረስ በአረንጓዴ ዐሻራ በኩል የሚገዳደረን ጠፍቶ የራሳችንን ሪከርድ ራሳችን እየሰበርን ያለበት ሁኔታ ነው ያለው።

የአረንጓዴ ዐሻራ ፕሮግራም ችግኝ ተክለን የምናልፈው ብቻ አይደለም። ልዕልናው እና አሳታፊነቱ፣ አንድነቱና ህብረቱ ከሀገራችን ወቅታዊ ጉዳዮች ጋርም በበጎ ቢነሳ ባይ ነኝ። ከችግኝ ተከላ ባለፈ ችግሮቻችንን በጋራ እጆች እንዴት መርታት እንዳለብን ጥቁምታ የሚሰጥ ነው። መቶ ሃያ ሚሊዮን እጆች ኢትዮጵያን በዓለም አደባባይ ባለክብር እና ባለማዕረግ ማድረግ ከቻሉ ችግሮቻቸው ላይም መዝመት የማይችሉበት ምንም ምክንያት የለም።

ዓለም ሞክሮ ያልቻለው ግን ደግሞ በእኛ የተቻሉ ብዙ ነገሮች አሉ። እኚህ እውነታዎች በአንድነት ከተጓዝን የማንደርስበት እንደሌለ የሚጠቁሙን ናቸው። እናም የሚያዋጣንን እንምረጥ። የሚያዋጣን እንደ አረንጓዴ ዐሻራ በአንድነት ተሰልፈን የአንድነት ታሪክ መጻፍ ነው። አብዛኞቹ ታሪኮቻችን በአንድነት እጆች የደመቁ ስለሆኑ።

የዚህ ዓለም ትልቁ ጉዳይ የአየር ንብረት ለውጥ እንደሆነ ተደጋግሞ የተነሳ ጉዳይ ነው። ከትላንት እስከዛሬ የሰው ልጅ በዚህ ጉዳይ ላይ ብዙ መክሮ እና ዘክሮ ያውቃል። ስልጣኔና ዘመናዊነቱ ግን ሕይወቱን ወደ ሞት ከመውሰድ ባለፈ የፈየደለት የለም። አረንጓዴ ዐሻራ ደግሞ ለዚህ ስጋትና ተግዳሮት ትልቅ መፍትሔ ሆኖ ከፊት የሚሰለፍ የመፍትሔ አካል ነው።

የአየር ንብረት ለውጥ ስጋቱም ሆነ በረከቱ የማይደርስበት የምድር ክፍል የለም። እድገት እና ስልጣኔ፣ ድህነት እና ኋላ ቀርነት ከዚህ እውነት ጋር በእጅጉ የተቆራኙ ናቸው። ሌሎች መሠረታዊ መነሻዎች እንዳሉ ሆነው ለአፍሪካ በተለይም ደግሞ ለምስራቅ አፍሪካ ድህነት እና ተረጂነት መስፋፋት የአየር ንብረት ለውጥ የአንበሳውን ድርሻ ይወስዳል።

የአካባቢ ጥበቃ እንደ ሀገር ለተጋረጡብን ችግሮች፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ እየተስፋፋ ለመጣው የኑሮ መወደድ የአየር ንብረት ለውጥ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ አለበት። አሁን ላለብንም ሆነ ነገ ለሚፈጠሩ የመኖር እና ያለመኖር መሠረታዊ የህልውና ጥያቄዎች መልስ የሚሰጠን አረንጓዴ ዐሻራ ብቻ ነው። ዓለም በጥበቧ የዚህን ስጋት መድኃኒት አልፈጠረችም።

መፍትሔው በእውቀት እና በሳይንሳዊ ዘዴ የተመራ የአካባቢ ጥበቃ ንቅናቄ ነው። በአረንጓዴ አስተሳሰብ አረንጓዴ ምድር እስካልፈጠርን ድረስ ከችግሩ የምናመልጥበት ሌላ አቋራጭ መንገድ የለንም። ችግሩ ዓለም አቀፍ ነው። በተለየ መንገድ አፍሪካን የሚያጠቃ፣ ከአፍሪካም ምስራቅ አፍሪካን በተለየም ከሰሀራ በታች ያሉ ሀገራትን የሚያጠቃ መሆኑ ባለፉት ዓመታት በግልጽ የታየ ነው።

እንዲህ ዓይነቱ ስጋት በአረንጓዴ አስተሳሰብ የሚሽር፣ በአረንጓዴ ምድር የሚያገግም ሲሆን ሀገራችን ኢትዮጵያ ደግሞ በዚህ ረገድ ሕዝባዊ በሆነ ተሳትፎ በዓለም አቀፍ ደረጃ እውቅና ያገኘችበትን እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ ናት። ባለፉት ዓመታት ውስጥ የተከልናቸው ችግኞች ለውጥ እያመጡ እንደሆነ በተለያየ ጊዜ ካየነው እና ከሰማነው እውነት መረዳት ችለናል።

የአረንጓዴ ዐሻራ ትግበራ የአየር ንብረት ለውጥ ላይ ብቻ የሚቆም ሳይሆን ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያለው እንደሆነ የሚያጠያይቅ አይደለም። የአየር ንብረትን በማስተካከል ተስማሚና ምቹ ከባቢ እንዲኖር ማድረግ አንዱና ዋነኛው በረከቱ ሲሆን። ከዚህ ጋር ተያይዘው የሚመጡ ሌሎች ብዙ ጸጋዎችም አሉ።

በረሀማነትን በመከላከል ምርታማነትን ይጨምራል። ወቅቱን በጠበቀ ዝናብ ዘርተን እንድናበቅል፣ አጭደን እንድንበላ እድል ይሰጠናል። በተስተካከለና በተገባ የአየር ንብረት ከባቢ ራሳችንን በምግብ እንድንችል በማድረግ ድህነትን እንድንረታ ያደርጋል። ከዚህ ሁሉ በላይ ደግሞ በሕይወት እንድንኖር ዋስትና ይሰጠናል።

የቱሪዝም ኢንዱስትሪው እንኳን ይሄን እውነት ተከትሎ የሚነቃቃ ነው። ቱሪዝም መነሻው አካባቢ ነው። አካባቢ ስንል ዘርፈ ብዙ ቢሆንም ዋናው እና ትልቁ ግን ሳቢና ማራኪ ሥነ ምህዳር የሚለው ነው። የአረንጓዴ ዐሻራ በረከት ወንዝ ዳር እንዳለች ጽጌሬዳ አበባ ነው። ወንዝ ዳር የበቀለች ጽጌሬዳ አበባ ምን እንደምትመስ ለእናንተ ማስረዳቱ ለቀባሪ ማርዳት ነው።

አረንጓዴ ቀለም የሀገር ቬሎ ነው። ነጭ በነጭ ለብሰን ሀይሎጋ እንደሚባልልን የደስታ ቀናችን የኢትዮጵያ ሠርጓም አረንጓዴ ቀለም ነው። ሚዜዎቿ ደግሞ እኛ ልጆቿ ነን። በአረንጓዴ እሳቤ፣ በአረንጓዴ ቬሎ ሀገር እየዳርን አረንጓዴ ትውልድ እንፈጥራለን።

ለሀገር መድከም ፖለቲካዊ እሳቤ አይደለም። አንዳንዶች ሁሉን ነገር ከፖለቲካ ጋር አስተቃቅፈው ለምንም ነገር አስተዋጽኦ ሲጠየቁ ፖለቲካ ይመስላቸዋል። ፖለቲካና ሀገርን ማገልገል የተለያዩ አስተሳሰቦች ናቸው። ሀገርን ማገልገል የዜግነት ግዴታ ከመሆኑም በተጨማሪ የሁላችንም የጋራ ኃላፊነት ነው። አረንጓዴ ዐሻራ በምንም ዓይነት መልኩ ፖለቲካዊ እሳቤ ሊሆን አይችልም። ሀገር የመፍጠር፣ ትውልድ የማዳን የጋራ እውነት እንጂ።

እንደ አረንጓዴ ዐሻራ የመሰሉ ንቅናቄዎች የማንም ሳይሆኑ የኢትዮጵያ ሆነው ወደ ሕይወታችን የሚመጡበት አጋጣሚ ብዙ ነው። ኢትዮጵያ የምትደምቅበት፣ ትውልዱ የሚከብርበት ሀገራዊ ንቅናቄ ፖለቲካዊ እሳቤ ሊሆን አይችልም። እናም አረንጓዴ ዐሻራ የፖለቲካ ጉዳይ ሳይሆን የኢትዮጵያ ጉዳይ ነው የሚለው ሚዛን ደፍቶ እናገኘዋለን።

ሀገርን በማገልገል ውስጥ የእኔ የአንተ የሚባል የለም። ሀገር ማለት እኔ አንተ እና ለሌላው ሰው ነው ካልን በማገልገላችን ውስጥ የምንገለገለው ራሳችን ነን። እናም አረንጓዴ ዐሻራ የኢትዮጵያ ጉዳይ እንጂ የፖለቲከኞች ወይም የፖለቲካው ማቀንቀኛ አይደለም። ከሆነም እናዝናለን። ስለዚህም ታሪክ እየሰራን ነው ይህንንም ታሪክ በማስቀጠል ለፍሬ እናብቃው አልኩ የዛሬውን ነፃ ሃሳቤን እዘጋለሁ። ቸር ቆዩልኝ።

ቴልጌልቴልፌልሶር (የኩሽ አሸክታብ)

አዲስ ዘመን መስከረም 8/2017 ዓ.ም

 

 

 

 

Recommended For You