አዲስ አበባ፡- በኦሮሚያ ክልል ለ2017 የትምህርት ዘመን 12 ነጥብ ስድስት ሚሊዮን ተማሪዎች ተመዝግበው ትምህርታቸውን መከታተል መጀመራቸው ተገለጸ።
የኦሮሚያ ክልል ትምህርት ቢሮ በሸገር ከተማ አስተዳደር ፉሪ ክፍለ ከተማ በከራቡ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት በክልል ደረጃ የ2017 የትምህርት ዘመን የማስጀመሪያ መርሀ-ግብር ትናንት አካሂዷል።
የክልሉ ትምህርት ቢሮ ምክትል ኃላፊ ቡልቶሳ ሂርኮ(ዶ/ር) ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ በተያዘው የትምህርት ዘመን በክልሉ 12 ነጥብ ስድስት ሚሊዮን ተማሪዎች ተመዝግበው ትምህርታቸውን መከታተል ጀምረዋል።
በቅድመ አንደኛ ደረጃ 15 ሺህ 58፣ በአንደኛ ደረጃ 15 ሺህ 315 እና በሁለተኛ ደረጃ አንድ ሺህ 300 በድምሩ በ31 ሺህ 673 ትምህርት ቤቶች 12 ነጥብ ስድስት ሚሊዮን ተማሪዎች ተመዝግበው ትምህርት መጀመራቸውን ገልጸዋል።
ትምህርትን በቴክኖሎጂ ለመደገፍ በየወረዳዎች አይሲቲ ፓርክ የመክፈት፣ በአዳሪ እና ልዩ ትምህርት ቤቶች ውስጥ የስማርት ክፍሎች የመፍጠር እንዲሁም በሁሉም የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ኮምፒውተር እንዲሁም ኢንተርኔት እንዲዳረስ ለማድረግ እየተሰራ ነው። በተጨማሪም በተለያዩ ትምህርት ቤቶች እድሳት መደረጉን አመልክተዋል።
በክልሉ ከባለፈው ክረምት ጀምሮ ሦስት ሚሊዮን መጽሐፍት አትሞ ወደ ትምህርት ቤቶች ማሰራጨት መቻሉን የጠቀሱት ኃላፊው፤ ከዚህ በፊትም የገጠሙት የተለያዩ ችግሮችን ለመፍታት ብዙ ጥረቶች እየተደረጉ መሆኑን ጠቁመዋል።
እንደ ቡልቱሳ(ዶ/ር) ገለጻ፤ በ2017 የትምህርት ዘመን በቅድመ አንደኛና አንደና ደረጃ የሚገኙ አጠቃላይ ከአስር ሚሊዮን በላይ ተማሪዎችን የምገባ አገልግሎት ለመስጠት ታቅዷል። በ2016 በጀት ዓመት የትምህርት ምገባ መርሀ ግብር ስምንት ሚሊዮን ታቅዶ ወደ አምስት ነጥብ ስምንት ሚሊዮን ተማሪዎች የምገባ አገልግሎት መስጠት ተችሏል።
ልጅዓለም ፍቅሬ
አዲስ ዘመን መስከረም 8 ቀን 2017 ዓ.ም