አዲስ አበባ:– ለሀገር ውስጥ ኢንሹራንሶች የቴክኒክ እና የፋይናንስ ድጋፍ በማድረግ የመድንና የጠለፋ መድን ሙያ በኢትዮጵያ እንዲጎለብት አስተዋጽኦ ማድረጉን የኢትዮጵያ የጠለፋ መድን አክሲዮን ማህበር ገለጸ።
ኩባንያው ያለፉት ስምንት ዓመታት አፈጻጸሙን አስመልክቶ ትናንት በሰጠው መግለጫ፤ የኩባንያው ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ዳዊት ገብረአማኑኤል፤ የመድንና የጠለፋ መድን ሙያ በኢትዮጵያ እንዲጎለብት አስተዋጽኦ ማድረጉን አመልክተዋል።
ለኩባንያዎች የተለያዩ ስልጠናዎች መስጠቱን በማመልከት፤ በተለይም የሳይበር ሴኪዩሪቲ፣ የኤሌክትሪክ መኪና ኢንሹራንስ፣ የግብርና ኢንሹራንስ እና ሌሎችንም ዘርፎች ጨምሮ በዓመት ከ16 በላይ ስልጠናዎችን እየሰጠ እንደሚገኝም ተናግረዋል።
ሰባት ከሚሆኑ ኩባንያዎች ጋር የስትራቴጂክ ፓርትነር ሺፕ ስምምነት መፈራረሙን በማመልከት፤ ስምምነቱ የሀገር ውስጥ ኩባንያዎች በዘርፉ ለእውቀት እና ቴክኖሎጂ ሽግግር እገዛ ለማድረግ ጉልህ አስተዋጽኦ እንዳለው ተናግረዋል።
የሕይወት፣ የንብረትና የሕጋዊ ኃላፊነት መድን ሽፋን እየሰጠ እንደሚገኝ በመጠቆም፤ በመንግሥት እና ከግሉ ዘርፍ በተውጣጡ ባለአክሲዮኖች በአንድ ቢሊዮን ብር የተቋቋመው ኩባንያው አሁን ካፒታሉ ሁለት ነጥብ አምስት ቢሊዮን ብር መድረሱንም አመልክተዋል። በአቪየሽን እና በባህር ኢንሹራንስ ዘርፉ ድርሻ እንዳለውም ተናግረዋል።
በጠለፋ መድን ሥራ ባለፉት ስምንት ዓመታት በአረቦን ክፍያ መልክ ከሀገር ይወጣ የነበረን 50 ሚሊዮን ዶላር የውጭ ምንዛሬ ማስቀረት ተችሏል ብለዋል። ትግበራው 30 በመቶ ሽፋን እንዳለውም አቶ ዳዊት ጠቁመዋል።
10 በሚሆኑ የአፍሪካ ሀገራት ውስጥ እየሠራ በመሆኑም የውጭ ምንዛሬ ማስገኘቱንም ነው የጠቆሙት። ኩባንያው ታዋቂ ከሆኑ ገማቾች (AM Best) ኤ ኤም ቤስት በተባለው ዓለም አቀፍ ገማች እውቅና ማግኘቱን ተከትሎ በተለያዩ ሀገራት ገብቶ ለመሥራት ተቀባይነት የሚያገኝ መሆኑም ተጠቁሟል።
ስራው ስጋት ላይ የተመሰረተ እንደመሆኑ ከኢትዮጵያ ውጭ የት የት አካባቢ መስራት እንዳለበት ጥናት እየተደረገ እንደሚገኝም አመልክተዋል።
ኩባንያው 127 ባለአክሲዮኖች እንዳሉት በመጠቆምም፤ 102 ግለሰቦች፣ ሰባት ባንኮች እና 18 የኢንሹራንስ ኩባንያዎች የተካተቱበት መሆኑንም ነው አቶ ዳዊት የጠቆሙት። የመንግሥት ድርሻ 40 በመቶ ሲሆን፤ ግለሰቦች፣ የኢንሹራንስ ተቋማትና ባንኮች 60 በመቶ እንደሚሸፍኑ አመልክተዋል።
የስትራቴጂና ቢዝነስ ዴቨሎፕመንት ኤክስኪዩቲቭ ኦፊሰር አቶ ፍቅሩ ጸጋዬ በበኩላቸው፤ ጠንካራ የሆነ የአደጋ ስጋት የመሸከም አቅም እንዲዳብር ማድረጉን ተናግረዋል። ዘላቂ የሆነ ገቢ ማግኘትና ዓለም አቀፍ የአይቲ ቴክኖሎጂ መዘርጋት መቻሉንም ተናግረዋል። በተደረገው ጥናትም የደንበኞች ርካታ 94 በመቶ ማድረስ መቻሉን ማረጋገጡን ነው የጠቆሙት።
የጠለፋ መድን ሥራ ሲቋቋም በዋናነት ከሀገር በአረቦን ክፍያ መልክ ይወጣ የነበረውን የውጭ ምንዛሬ ለማስቀረት መሆኑን ያስታወሱት አቶ ዳዊት፤ በሌሎች ሀገራት ተመሳሳይ ኩባንያዎች ሲቋቋሙ ግብር አይከፍሉም ወይም የታክስ ቅነሳ ያደርጋሉ፤ በኢትዮጵያ ይህ የለም ብለዋል።
ዘላለም ግዛው
አዲስ ዘመን መስከረም 8 ቀን 2017 ዓ.ም