ከትምህርት ጋር በተያያዘ ያላነሳነው መሰረታዊ ጉዳይ እንደ ሌለ ሁሉ፤ የማናነሳውም መሰረታዊ ጉዳይ አይኖርም። በመሆኑም፣ ስለ ትምህርት የሚመለከታቸውን ባለድርሻ አካላት ሁሉ እግር በእግር እየተከተልን የምንችለውን ሁሉ እንላለን።
የዛሬ ትኩረታችን የትምህርት ሚኒስቴርን የ2016 ዓ•ም አመታዊ ክንውን (አፈፃፀም) የያዘችውና የ2017ን እቅድ የምታመላክተው ወቅታዊዋ (ነሀሴ 2016 ዓ•ም ለህትመት የበቃችው) “የትምህርት ገጽ፣ ቁጥር 3” መጽሔት ነች።
መጽሔቷ “ጉባኤው በትምህርት ሴክተሩ አንድ አይነት አረዳድ እንዲኖርና የቀጣይ የትኩረት አቅጣጫ ላይ የጋራ መግባባት ለመፍጠር ያለመ መሆኑ፤ የትምህርት ማህበረሰቡ በ2016 ዓ•ም በትምህርቱ ዘርፍ የተከናወኑ ተግባራትን መለስ ብሎ የሚያይበት፣ በእውነት ላይ ተመስርቶ የሚገመግምበት እና የመጪውን አመት ስራችን አቅጣጫ” ማሳየት የሚቻልበት መሆኑ በትምህርት ሚኒስትሩ በተነገረለት 33ኛው ሀገር አቀፍ የትምህርት ጉባኤ፣ በአጠቃላይም የ2016 ዓ.ም ትምህርት ዘርፍ አፈጻጸም፣ የ2017 ዓ.ም ዕቅድ ዋና ዋና የትኩረት አቅጣጫዎችና የትምህርት ዘርፉ ሪፎርም ላይ ያተኮረች ህትመት ነች።
በመጽሔቷ የመጀመሪያ ክፍል ሽፋን ያገኘው የሚኒስትር ብርሀኑ ነጋ ንግግር ሲሆን፤ ሚኒስትሩ የ2016ን አፈፃፀም (በአብዛኛው የተሳካ አፈፃፀም ያላቸው ናቸው) በመግለፅ የ2017ን እቅድ አስተዋውቀዋል።
የትምህርት ጥራትና ፍትሐዊነት እንዲረጋገጥ የትምህርት ሴክተሩን በሪፎርም መለወጥ የምርጫ ጉዳይ አይደለም እንዳሉት፤ የትምህርት ዘርፉን በሪፎርም በመለወጥ በፍጥነት እየተቀየረ ያለውን ዓለም ተቋቁሞ ሀገርን ሊያስቀጥል የሚችል ትውልድ ማፍራት የሚገባ መሆኑን እንደ ተናገሩት እንደ ሚኒስትሩ ንግግር ከሆነ፤ መስሪያ ቤታቸው ያለፈው አመት ስኬቶቹን አጠናክሮ ለማስቀጠል፣ አጋጥመው ከነበሩ ስህተቶችና ችግሮች በመማር አሻሽሎ ለመሄድ ዝግጅቱን አጠናቋል።
በዚሁ መሰረትም፣ ለ25 ቀናት የቆየ የሙያ ማሻሻያ ስልጠና ለ52ሺህ 300 የሁለተኛ ደረጃ መምህራን እና ለ8ሺህ 70 ርእሰ መምህራን የተሰጠ ሲሆን፤ በ2017 የሴት ርእሰ-መምህራንን የአመራር ተሳትፎ ድርሻ ከፍ የማድረግ ስራዎች ይሰራሉ።
በ2016 22•7 ሚሊዮን መጻሕፍት ታትመው 20•64 ሚሊዮን መጻሕፍት ለሁሉም ክልሎች የተሰራጩ ሲሆን፤ በ2017 ሙሉ በሙሉ መጻሕፍትን በሁሉም የትምህርት አይነቶች ለሁሉም ተማሪ በነፍስ ወከፍ ለማዳረስ 40•2 ሚሊዮን ዶላር በመመደብና 18 ሚሊዮን መጻሕፍትን በሁለት ዙር በማሳተም የአመቱ ትምህርት ከመጀመሩ በፊት ይሰራጫል፤ ለተማሪዎችም ተደራሽ ይደረጋል።
በትምህርት ለትውልድ እንቅስቃሴ 30 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ ታቅዶ 27•389 ቢሊዮን ብር በመሰብሰብ የትምህርት ቤቶችን መሰረተ ልማት የማሻሻል ስራዎች የተሰሩ ሲሆን፤ ይህም በ2017 ተጠናክሮ ይቀጥላል።
የትምህርት ቤት ምገባ፣ በችግር ውስጥ ያሉ የትምህርት ተቋማትን ትምህርት የማስጀመር ጥረት ወዘተ ተጠናክሮ ይቀጥላል።
በ2016 በከፍተኛ ትምህርት ዘርፍ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተቋማዊ ነፃነት ደንብ ፀድቆ ወደ ስራ የተገባ ሲሆን፤ ይህንን ተቋማዊ ነፃነት ወደ ሌሎች ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት (ዩኒቨርሲቲዎች) የማስፋፋት ስራዎች በ2017 ተጠናክረው ይቀጥላሉ።
የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የትምህርት ፕሮግራሞች ከተሰጣቸው ተልእኮና ልየታ አኳያ ተፈትሸው የመከለስ ስራዎች ይሰራሉ።
በ2016 የምርምርና ፈጠራ ስራዎችን ለማሳደግ በከፍተኛ ትምህርት ዘርፍ የቴክኖሎጂ እድገት፣ ሽግግር እና የማህበረሰብ አገልግሎቶችን ማጎልበት የሀገር በቀል እውቀትና ማህበረሰብ አቀፍ ስራዎችን ከማጠናከርና የትምህርት ተቋማት እና የኢንዱስትር ትስስርና የቴክኖሎጂ ሽግግርን ማሻሻል ትኩረት ተሰጥቷቸው ሲሠራባቸው የነበሩ ሲሆን፤ እነዚህ ተግባራት በ2017ዓ.ም ተጠናክረው የሚቀጥሉ ይሆናል።
ዋና አላማው ለዜጎች ተገቢና ጥራት ያለው ትምህርት መስጠት የሆነው የሪፎርም ስራ በ2017ዓ.ም ተጠናክሮ የሚቀጥልና ተጠናቅቆም ወደ ተግባር የሚገባበት ይሆናል።
በተቋሙ ውስጥ አስተዳደራዊ ስራዎች ላይ ማሻሻያን ማድረግ ሌላው የለውጡ ተግባር ሲሆን፤ ትምህርት ሚኒስቴርን እንደ ተቋም ለሠራተኞች እና ተገልጋዮች ውብ፣ ማራኪ፣ ምቹና ደህንነቱ የተረጋገጠ እንዲሆን የተጀመሩ አበይት ስራዎች ማለትም ለሠራተኞችና ተገልጋዮች አገልግሎት የሚሰጥ ደረጃውን የጠበቀ የምግብ አገልግሎት የሚሰጥ ካፊቴሪያ የመገንባት ስራዎች በ2017ዓ.ም ተጠናክረው ይቀጥላሉ፤ ተጠናቅቀውም ወደ ስራ ይገባሉ።
በሀገሪቱ ታሪክ የመጀመሪያ የሆነው የትምህርት ሙዚየም ግንባታ በ2017 እቅድ መሰረት የሚከናወን ይሆናል።
ሌላውና በ“የትምህርት ገጽ” ሽፋን የተሰጠው በኢፌዴሪ ትምህርት ሚኒስቴር የአጠቃላይ ትምህርት ልማት ዘርፍ ሚኒስቴር ዴኤታ ወይዘሮ አየለች እሸቴ ንግግር ሲሆን፤ ሚኒስትር ዴኤታዋ በዚሁ ጉባኤ ላይ እንደ ተናገሩት ከሆነ፤ እሳቸው በሚመሩት ዘርፍ በ2016 የተከናወኑ በርካታ ተግባራት ያሉ ሲሆን፤ በ2017ም ይከናወኑ ዘንድ በእቅድ የተያዙ ስራዎች አሉ።
በሌላ መድረክ ላይ “ተማሪዎች ከታችኛው እርከን ጀምረው የሥነ ምግባር ትምህርት እየተማሩ በመሆኑ ጥሩ ሥነ ምግባር የተላበሱና ምክንያታዊ እንዲሆኑ ተደጋግፎ መሥራት የሚገባ መሆኑን እንደተናገሩት፤ የክልል እና የከተማ መስተዳድሮች ለመምህራን ምቹ ሁኔታዎችን በመፍጠር ለትምህርት ልማት ስኬታማነት የበኩላቸውን ኃላፊነት እንዲወጡም እንደ ጠየቁት፤ እንደ ሚኒስትር ዴኤታዋ ማብራሪያ፤ የቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ለሁሉም ደረጃዎች መሰረት ነው። በመሆኑም በ2016 ሲሰሩ የነበሩ ስራዎች በ2017 ዓ.ም ተጠናክረው ይቀጥላሉ።
በ2016 በአጠቃላይ ትምህርት ዘርፍ ሲከናወኑ የነበሩት – የትምህርት ቤት ምገባ፣ የትምህርት ለትውልድ፣ የትምህርት ቤቶች ጥራትና ደረጃን ማሻሻል፣ የሥርአተ ትምህርት ለውጥ ትግበራ፣ የእንግሊዝኛ ቋንቋ ማሻሻያ፣ የመምህራንና የትምህርት ቤት አመራር የክረምት ስልጠና እና የሀገር አቀፍ ምዘና ሥርዓት ለማሻሻል የሚያስችል የዲጂታላይዜሽን ሥርዓት ግንባታ የለውጥ ፕሮግራሞችና አበይት ተግባራትን በመለየት፤ ከተሞክሮዎች በመማር የተማሪዎችን ውጤት ለማሻሻል የተሰሩ ስራዎች በ2017ዓ.ም ተጠናክረው ይቀጥላሉ።
በጉባኤው ላይ በትምህርት ለትውልድ መርሀ ግብር በአንድ አመት ውስጥ 27.4 ቢሊዮን ብር በማሰባሰብ ትምህርት ቤቶች እንዲገነቡ፣ እንዲጠገኑና ግብአቶችም እንዲሟሉ መደረጉን፤ እንዲሁም እሳቸው በሚመሩት ዘርፍ በ2016 ዓ.ም በትምህርት ዘርፉ የተከናወኑ ተግባራት ከትምህርት ጥራት፣ አግባብነት፣ ፍትሐዊነት፣ ተሳትፎና ተደራሽነት ጋር የተያያዙ በርካታ አመርቂ ውጤቶች መገኘታቸውን የተናገሩት ሚኒስትር ዴኤታ አየለች እሸቴ እንዳሉት፣ በ2017 ባሳለፍነው የትምህርት ዘመን (2016) ከአምስት ሚሊዮን በላይ በሰው ሰራሽ እና በተፈጥሮ አደጋዎች ምክንያት ከትምህርት ገበታ ውጪ የሆኑ ሕፃናትን ወደ ትምህርት ገበታቸው የመመለስ ስራዎች ይሰራሉ።
ሌላውና በመጽሔቷ የተካተተው የከፍተኛ ትምህርት ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ኮራ ጡሹኔ ንግግር ሲሆን፤ እሳቸው እንዳስረዱት በከፍተኛ ትምህርት ዘርፉ ላይ ከፍተኛ መዋዕለ ነዋይ በማፍሰስ በተደረገው ጥረት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን ተደራሽነት በማስፋት ከፍተኛ ውጤት ተመዝግቧል። የትምህርት ጥራትንም ለማጎልበት በትኩረት እየተሰራ ነው።
በዚሁ በማጠቃለያው ባለ 12 ነጥብ ውሳኔ የተላለፈበት ጉባኤ ላይ የዘርፋቸውን ሪፖርት ያቀረቡት ክቡር ሚኒስትር ዴኤታው አያይዘውም ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ባሉባቸው አካባቢዎች የዜጎችን ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ህይወት የሚያሻሽሉ ተግባራትን በማከናወን፤ እንዲሁም በሀገራዊ የልማት መስኮች አጠናክረው ማስቀጠል ይገባቸዋል።
ከመማር ማስተማርና ማህበረሰብ አቀፍ የምርምር አገልግሎት ከማከናወን በተጨማሪ በማህበረሰቡ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ላይ በስፋት መስራት ይጠበቅባቸዋል። ከዚሁ አኳያ የተቀረጹት የከፍተኛ ትምህርት የሪፎርም አጀንዳዎች ተግባራዊነት በ2017 ዓ.ም በተጠናከረ መልኩ መስራት አለባቸው።
እንደ ክቡር ሚኒስቴር ዴኤታው ማሳሰቢያ በ2017 የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ሥራዎቻቸውን በቁልፍ የአፈጻጸም አመላካቾች (KPI) በመለካት ለተሻለ ስራ መትጋት አለባቸው።
የ2016 ዓ.ም ዕቅድ አፈጻጸምና የ2017 ዓ.ም ዕቅድ፣ የአካዳሚክ ጉዳዮች፣ የምርምርና የማኅበረሰብ ጉድኝት፣ የአይሲቲና ዲጂታል ትምህርት፣ የአስተዳደርና መሠረተ ልማት የሪፎርም ሥራዎችን፣ የቁልፍ አፈጻጸም አመላካች ጉዳዮች ላይ ሪፖርቶችና የተለያዩ ጽሑፎች ቀርበው ውይይት በተካሄደባቸው በዚህ ጉባኤ ላይ በርካታ ጉዳዮች የተነሱ ሲሆን፤ አንዱም የከፍተኛ ትምህርት አጠቃላይ ይዞታችን ከሌሎች (ከሰሀራ በታች ካሉት ሀገራት ጭምር) ጋር ሲወዳደር ገና ብዙ የሚቀረን መሆኑ ነው።
የከፍተኛ ትምህርት ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር አቶ ኮራ ጡሹኔ በዚሁ ጊዜ እንደተናገሩት፤ የዩኒቨርሲቲ መምህራን በተቀራራቢ የብቃት ደረጃና የማስተማር ችሎታ ላይ እንዲደርሱ በቀጣይ ተከታታይነት የአቅም ግንባታ ስራዎችን መሥራት ይገባል።
እንደ ሚኒስትር ዴኤታ ኮራ ማብራሪያ ከሀገራችን በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተመዝግበው ትምህርታቸውን በመከታተል ላይ የሚገኙ ተማሪዎች ምጣኔ (Enrolment Rate)ን እንኳን ብንመለከት ገና 10-12% አካባቢ ሆኖ የምናገኘው ሲሆን፤ ይህ አሃዝ ከሰሃራ በታች ካሉ ሀገሮች አማካይ እምብዛም ያልዘለለ፤ ሌሎች ከደረሱበት አንፃር እዚህ ግባ የሚባል አይደለም። ከሰሀራ በታች ካሉ ሀገሮች በምዝገባ ምጣኔ በግንባር ቀደምትነት ከሚገኙ ከነሞሪሺስ (40%) እና ደቡብ አፍሪካ 20-25%)፣ እንዲሁም በዓለም አቀፍ ከፍተኛ ምጣኔ ካላቸው እንደነ ደቡብ ኮሪያ (95%) እና ፊንላንድ (94%) ጋር ስናነፃፅረው ገና ብዙ መስራት ይጠበቅብናል።
በዚሁ “ፍትሐዊና ጥራት ያለው ትምህርት ለሁሉም” በሚል መሪ ቃል በተካሄደው ጉባኤ ላይ ሚኒስትር ዴኤታው እንደተናገሩት፤ በተለምዶ የዩኒቨርሲቲዎችን ቁጥር በማብዛት ተደራሽነትን የማስፈጸም፣ ትምህርትን በአራት ግድግዳ ገድቦና በአካል እየተገናኙ ብቻ መስጠትና የከፍተኛ ትምህርት ማለት የዩኒቨርሲቲ ትምህርትና ዲግሪ ብቻ አድርጎ የማየቱን ጉዳይ እንደገና ልንመረምር ይገባል። ተቋማትን ከማስፋፋቱ ጎን ለጎን በቴክኖሎጂ ታግዞ ትምህርትን ማዳረሱና በቦታና በጊዜ ሳይገደብ ተደራሽ ማድረግ ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ ነው። በመሆኑም፣ 2017 በዚህ ላይ ትኩረት ተሰጥቶ የሚሰራ ይሆናል።
ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ኮራ ጡሹኔ እንደሚሉት፤ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት አካባቢዎች በርካታ ያልተሻገርናቸው ችግሮችና ፈተናዎች አሉ። እነዚህን ችግሮችና ፈተናዎች ለመፍታት በ2017 በተጠናከረ መልኩ የሚሰሩ ስራዎች ያሉ ሲሆን፤ ከትምህርት ተደራሽነትና ፍትሐዊነት፣ ከጥራትና አግባብነት፣ ከአሰራር ቅልጥፍናና ውጤታማነት፣ ከትምህርት ፕሮግራሞች ጥራትና አግባብነት፣ ከመልካም አስተዳደርና ስነምግባር፤ ከአመራር ብቃትና ክህሎት፣ በምርምር ቴክኖሎጂና ፈጠራ የማህበረሰቡን የቆዩ ችግሮችን ከመፍታት፣ የምሩቃን ስራ ፈጠራ እና ተቀጣሪነትን ከማሳለጥና መሰል ጉዳዮች አንፃር ክፍተቶች አሉ። በመሆኑም እነዚህን በአግባቡ በመረዳት በርካታ ስራዎችን መስራት ያስፈልጋል። በ2017 እነዚህን ባማከለ መልኩ ስራዎች ይሰራሉ።
እንዲሁም ከተቋሙ ሌሎች ምንጮች መገንዘብ እንደተቻለው:-
የስፖርት ሊግ በአግባቡ ከተመራ ሀገራዊ ሰላማችንና አብሮነታችንን ለማጠናከር ድርሻው የጎላ መሆኑ ታምኖበት፣ በ2017 የትምህርት ዘመን በሁሉም ት/ቤቶች የስፖርት ሊግ እንዲጀመር ከሁሉም ክልሎች ከተውጣጡ የቀጣና ኃላፊዎች ጋር የስምምነት ፊርማ ተደርጓል። ባለፉት ዓመታት እየተቀዛቀዘ የመጣውን የት/ቤቶች የስፖርት ውድድር “የስፖርት ሊግ” በሚል መርህ በአዲስ መልክ ለማጠናከር ይሰራል። ከምሥራቅ አፍሪካ ሀገራትና ከአውሮፓ ት/ቤቶች ስፖርትና ከትምህርት ቤቶች የስፖርት ፖሊሲ ተሞክሮዎች በመነሳት የሀገራችንን የትምህርት ቤቶች የስፖርት ውድድር በንቃት መምራት እንደሚገባም አቅጣጫ ተቀምጧል።
በትምህርት ቤቶች መካከል ወጥና ቅንጅታዊ አሰራርን በመፍጠር፣ ስፖርታዊ ልማትን በማስፋፋት፣ የስፖርት ትምህርት ጥራትን በማሻሻል ስፖርታዊ እንቅስቃሴን ባህሉ ያደረገ ንቁና ሁለንተናዊ ስብዕናው የተሟላ ተተኪ ትውልድን ለማፍራት ምቹ ሁኔታን መፍጠር የሚገባ መሆኑም ታምኖበት ከዚሁ አኳያ ስራዎች ሊሰሩ እንደሚገባ ተገልጿል።
በአጠቃላይ ከላይ በአጭሩ ዋና ዋና የሆኑትን በሀገር አቀፍ ደረጃ የተያዙትን እቅዶች በማቅረብ ወደ ሕዝብ ለማሻገር ጥረት አድርገናል። ይህ ማለት የተቋሙ የ2016 አፈፃፀምና የ2017 እቅድ እነዚህን ብቻ ነው የያዘው ማለት አይደለም፤ ፍፁም እንደዛ ማለት አይደለም። ተቋሙ ለ2017 በእቅድ ከያዛቸው መካከል እዚህ የጠቀስናቸው እጅግ ጥቂቶቹ ናቸው። ከዚህ አንፃር አንባቢያን ሌሎች ምንጮችን በመዳሰስ ሙሉ መረጃን መያዝ ይጠበቅባቸዋል። እዚህ የጠቀስናቸው ከገጻችን ውስንነት አኳያ ዋና ዋናዎቹን ብቻ ሲሆን፣ አላማውም በሚቀጥለው አመት ተቋሙን ስንመዝነው በእነዚህ መሰረት መሆኑን በጥቂቱም ቢሆን ለመጠቆም ነው።
ግርማ መንግሥቴ
አዲስ ዘመን መስከረም 6 ቀን 2017 ዓ.ም