እኒያ የደርጉና የኢሠፓ ሊቀ መንበር፣ የኢሕዲሪ ፕሬዚዳንትና የአብዮታዊ ጦር ጠቅላይ አዛዥ ሌተናል ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማርያም ‹‹በቆሎ በልቶ ያልጠገበ ሕዝብ ወንበር ይመኛል፤ ወደዳችሁም ጠላችሁም እዚህ ወንበር ላይ የሚቀመጠው አንድ ሰው ነው…›› ሲሉ መፈንቅለ መንግሥት ያሴሩባቸውን ጄኔራሎች በምሬት የተናገሩት የፖለቲካ ሽኩቻው በርትቶ ለሥልጣን ሲባል ለመግደል የሚያደባው በበዛበት ወቅት ነበር፡፡
ምንጊዜም ቢሆን ማናቸውም የፖለቲካ ኃይሎች የያዙት ሥልጣን ሳይበቃቸው ሌላ ለማግኘት በሴራም፤ ከሴራ ነፃ በሆነ መንገድም ይራመዳሉ።ይህንን መሰሉ የፖለቲካ አካሄድ የማይዋጥለት ገዢ መንግሥት ደግሞ ሥልጣኑን ላለማስነካት ያለ የሌለ ኃይሉን ስለሚጠቀም ተጎጂው በርካታ ይሆናል፡፡
ከዴሞክራሲ ጋር ለመለማመድ ቆርጠው የተነሱና በሥልጣን ጥም ያልቋመጡ በተግባራቸውና በቃላቸው መካከል ልዩነት አይኖርም፣ የፖለቲካ ትግሉ እልህ አስጨራሽ ቢሆንም ከፖለቲካው ንፋስ ጋር ሳይነፍሱ ጸንተው ይገኛሉ።
እርግጥ ነው አንዳንድ ጽንፈኛ ፖለቲከኞች አንድ ወንበር አንድ ሰው ብቻ እንደሚያስተናግድ እያወቁ፣ ወንበሩን ማግኘት የሚቻለውም በነፃ የምርጫ ሥርዓት ተወዳድሮ መሆኑን ልባቸው እየተገነዘበ አውቆ ባለማወቅ ዓይነት ከሕግ ያፈነገጠ ተግባር ሲፈጽሙ ማየት እየተለመደ መጥቷል፡፡
በአገራችን ቀዳማዊ ኃይለሥላሴን ከሥልጣን ከማውረድ ጀምሮ ደርግን ከሥልጣን እስከማሰናበት የተደረሰው በኃይል እርምጃ መሆኑ እስካሁን ላለው ትውልድ የመማሪያ መድረክና ታሪክ ሆኖ ሊያገለግል የሚችል ተደርጎ እየተወሰደ አይደለም።
በአገራችን ባለፉት ሁለት ዓመታት በተቃውሞ ጎራ በመሰለፍ ለሚሊዮኖች መፈናቀል፣ በሺዎች ለሚቆጠሩ ሕይወት መጥፋትና ለአካል ጉዳት የመዳረጉ መንስዔ የፖለቲከኞች በረጋ መንፈስ ለውይይት በራቸውን አለመክፈታቸውና ተከታዮቻቸውን የመምራት አቅም ያልገነቡ በመሆናቸው ነው፡፡
የፖለቲካ ትግል የሥልጣን ትግል መሆኑ ቢታወቅም ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ተግባራዊ መሆን በመታገል በሕዝብ ይሁንታ ሥልጣን መያዝን አማራጭ ካላደረጉ የሥልጣኑ ወንበር ለአንድ ሰው ብቻ ስለሚሆን ትግሉ የመጠላለፍ ሆኖ ሥልጣን የጨበጠውን ኃይል ዕድሜ በማራዘም የሚመኙትን ሳያገኙ መቅረት ይሆናል።
የሚደረገው ትግል ሁሉ ዓላማና ግብ ሳይኖረው ራስን በሥልጣን ላይ ለማስቀመጥ እንጂ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መመስረትን ያስቀደመና የአገር ግንባታን ያለመ ካልሆነ መስዋዕትነቱ መክኖ አገሪቱን ለከፋ አደጋ ይዳርጋታል። በተለይም በአሁኑ ወቅት በፖለቲከኞችና በተከታዮቻቸው መካከል ያለው ጉድኝት በአግባቡ ያልተያዘ በመሆኑ፤ ፖለቲከኞች ያለባቸውን አገራዊ ኃላፊነታቸውን መወጣት ያልቻሉበት ደረጃ ላይ መድረሳቸውን ማስተዋል ይቻላል፡፡
ከዚሁ በተጓዳኝ ፖለቲከኞቹ ደጋፊ የሆነው የኅብረተሰብ ክፍል በማህበራዊ ሚዲያ የሚያገኘውን መረጃ ትክክለኛነት ሳያረጋግጥ በስሜታዊነት እየተመመ የሚያደርሰው ጥፋት ሁሉም ነገር እንደታሰበው ሳይሆን እውነታው ሲገለጥ ጸጸትን ማስከተሉ አይቀሬ ነው።ስለዚህም የዴሞክራሲ ሥርዓት ለማስፈን፣ እውነተኛ ሕገ መንግሥትን ተግባራዊ ለማድረግ፣ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ በአገሩ ጉዳይ ያገባኛል የሚል እሳቤ እንዲኖረውና የሁሉም ዜጋ ተጠቃሚነት የሚገለጥበት የአገር ዕድገት እንዲኖር ፖለቲከኞች ተከታዮቻችሁን ለአገር በሚበጅ መልኩ ምሩ።ደጋፊዎችም ተቃውሞአችሁም ይሁን ድጋፋችሁ በእውነት ላይ በተመሰረተ መረጃና በሚዛናዊነት የተሞላ ይሁን፡፡
አዲስ ዘመን ጥቅምት 26/2012