«ሰው ምንድነው?» ፡-
ለዳዊት ጥያቄ የተሰጠ ምላሽ
በዓለማዊውም ይሁን በመንፈሳዊው እሳቤ ብንመረምረው ሰውነት ከሁሉም በላይ ከፍ ብሎ የተቀመጠ ቀዳማዊ ኃልዮት ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ ሰው ሆኖ መፈጠርም ከፍጥረታት ሁሉ በላይ የሆነ ታላቅ ክብርን የሚያቀዳጅ የታላቁ ፈጣሪ ልዩ ስጦታ ነው፡፡ የሰውን አፈጣጠር በተመለከተ መንፈሳዊው ወይም ሥነ ፍጥረታዊው ዕይታ እንደሚያስረዳው ፈጣሪ ይህን ዓለም በውስጡ የሚኖረውን ፍጥረት በፈጠረበት ወቅት ሌሎችን ፍጥረታት በሙሉ ሥራው ይታወቅበትና ይደነቅበት ዘንድ ለአንክሮና ለተዘክሮ የፈጠራቸው ሲሆን፤ ሰውን ግን “ስሙን ለመቀደስ፣ ክብሩን ለመውረስ ፈጠረው” ይላል። ይህም ለሰው ልጅ ምን ያህል ክብር እንደተሰጠው የሚያሳይ ነው፡፡ በተለይም “ክብሩን ለመውረስ” የሚለው ቃል ሰው በአግባቡ ተፈጥሮውን አውቆ ከተንቀሳቀሰ ከምድራዊ ፍጥረታት በልጦ መገኘት ብቻ ሳይሆን እንደ እግዚአብሔር የመሆን ዕድል እንዳለውም ያሳያል፡፡
እንደዚሁ የሰውን አፈጣጠር አስመልክቶ በታላቁ መጽሃፍ ላይ እንደተገለጸው እግዚአብሔር ሌላውን ፍጥረት ሁሉ “ይሁን” እያለ በቃሉ ብቻ የፈጠራቸው ሲሆን፤ ሰውን ግን በቅዱስ “ኑ ሰውን እንደ አምሳላችን እና እንደ አርዓያችን እንፍጠር” በማለት ከአራት ባህርያተ ሥጋና ከሦስት ባህርያተ ነፍስ በአጠቃላይ ከሰባት ባህርያት አዋህዶ በቅዱስ እጆቹ አበጅቶታል፡፡ በግዕዙ “ሰብዕ” የሚለው ቃልም ይህንኑ የሚያመለክት ሲሆን፤ ትርጓሜውም ሰባት ባህርያት ያሉት ማለት እንደሆነ ሊቃውንት ያስረዳሉ፡፡ ይህም የሰው ልጅ ሁሉን በሚችለው አምላክ አምሳያ የተፈጠረ ብቸኛ ታላቅ ፍጡር መሆኑን ያረጋግጥልናል፡፡
ስለ ሰው ልጅ አፈጣጠርና አመጣጥ የሚያትተው የሳይንሱ ክፍልም ቢሆን አጠቃላይ ህይወት ያላቸው ነገሮች ህይወት ከሌላቸው ቁስ አካላት መገኘታቸውንና የሰው ልጅም ከጦጣ መሰል ፍጡር መምጣቱን ይናገራል። ይሁን እንጂ በዝግመተ ለውጥ አማካኝነት በርካታ ችግሮችን እያሸነፈ የመጣና በሂደት ተፈጥሮን በቁጥጥሩ ስር ማድረግ የቻለ ከፈጣሪው በታች ማንኛውንም ነገር ለማድረግ የሚችል ኃያል ፍጡር መሆኑን ይመሰክራል፡፡
ይህም ብቻ አይደለም ሰው የተፈጠረው ከእርሱ ውጭ ያሉ በምድር ላይ የሚኖሩ ሌሎች ፍጥረታትን ሁሉ “ይገዛ” ዘንድ ታላቅነትን ብቻ ሳይሆን አለቅነትንም ጭምር ይዞ የተፈጠረ መሆኑን በፍጥረታዊው(Creationist) የሥነ ፍጥረት እሳቤ ዘንድ ዋነኛ ማጣቀሻ ሆኖ የሚያገለግለው መጽሃፍ ቅዱስ በማያሻማ ቋንቋ በግልጽ መዝግቦት ይገኛል፡፡
ከዚህ አኳያ የሰው ልጅ አፈጣጠርን በተመለከተ የዚህ ጽሁፍ አቅራቢም “ሰው ከጦጣ መሰል እንስሳ የተገኘ ነው” ብሎ ከሚያምነው የዝግመተ ለውጣዊው እሳቤ ይልቅ ሁሉን በሚችል አምላክ ፈቃድ “በእግዚአብሔር አምሳል ተፈጠረ” በሚለው የማምን መሆኔን ለመግለጽ እወዳለሁ። ምነው ቢሉ በግሌ “ከጦጣ ይልቅ እግዚአብሔርን መምሰል” የሰውን ማንነት የበለጠ ይገልጸዋል ብዬ ስለማስብ ነው፡፡ ከፈጣሪ በታች ከፍጥረታት በላይ ሆኖ የተፈጠረው፣ ታላቁ ፍጥረት ሰው ካልሰነፈ በቀር ከፀሃይ በታች የሚፈልገውን ለማድረግ የሚሳነው የለም፡፡ ይህ ምኞት ብቻ ሳይሆን በተግባርም የተፈጸመ ለመሆኑ የራሱ የሰው ልጅ ታሪክ ይመሰክራል፡፡
አዕምሮ፡- የሰውነትና የታላቅ ፍጡርነት ሚስጥር
ሁሉን የሚችለው ፈጣሪ ሰውን የዚች ምድር ታላቅ ፍጡር አድርጎ ሲፈጥረው ታላቅ እንዲሆን ያስቻለውን ታላቅ ኃይል መቀመጫ እንዲሆን አድርጎ የመረጠው የሰውነት አካል ከአካል ክፍሎች ሁሉ በላይ የሚገኘውን ጭንቅላትን ነው፡፡ እናም ዝም ብሎ ለታዘበው ሰው አዕምሮ የሚገኝበት የአካል ክፍል በራሱ ስለ አዕምሮ ታላቅነት ሚናገረው ትልቅ ሚስጥር አለ፡፡ እጅ፣ እግር፣ ደረት፣ ሆድ ዕቃ፣ ወይንም ሌሎች የሰው አካል ክፍሎች ለምን የአዕምሮ መገኛ አልሆኑም? ነገር ግን አዕምሮ የሚገኝበት የአካል ክፍል ጭንቅላት ነው፡፡ ይህ አዕምሮ የሚሉት ተዓምር መፍጠር የሚችል ታላቅ ኃይል ከአካል ክፍሎች ሁሉ መርጦ ከሁሉም የአካል ክፍሎች በላይ ከፍ ብሎ ከሚገኘው ጭንቅላት ላይ ተቀመጠ፡፡
ሰው የምድራችን ታላቁ ፍጥረት እንዲሆን ያስቻለውና ከሁሉም ፍጥረታት በላይ ከፍ ብሎ በክብር እንዲቀመጥ ያደረገው ሚስጥራዊ ኃይል ከሁሉም በላይ ከፍ ብሎ መቀመጥ ይገባዋልና! እናም የሰው የታላቅነቱ ሚስጥር የሆነው ታላቁ ሰብዓዊ ኃይል አዕምሮ በማስተዋል ለተመለከተው እንኳንስ ውስጠ-ተፈጥሮው አካላዊ አቀማመጡ በራሱ ሚስጥር ነው፡፡ ለዚህም ነው በሰው ልጆች አካላዊ መዋቅር(Anatomy) ውስጥ ቀዳሚ ቦታ ይዞ በሚገኘው ጭንቅላት ውስጥ ሚገኘው አዕምሮ ሰውን ከሁሉም ፍጥረታት በላይ ከፍ ብሎ እንዲቀመጥና ታላቅ ሆኖ እንዲገኝ አደረገ፡፡
ይሁንና አዕምሮ የሚገኘው ጭንቅላት ውስጥ ከሆነ፤ ጭንቅላት ደግሞ በሰዎች ብቻ ሳይሆን በሌሎች እንስሳት አካላዊ መዋቅር ውስጥም የሚገኝ ስለሆነ ሌሎች እንስሳትስ አዕምሮ ሊኖራቸው አይችልም ወይ? የሚል ከፊል-ምክንያታዊ የአመክንዮ ጥያቄ ሊያስነሳ ይችላል። እርግጥ ነው ሰዎች ብቻ ሳይሆኑ ሌሎች እንስሳትም ጭንቅላት አላቸው፡፡ እንስሳት ጭንቅላታቸው ውስጥ አንዳች ነገር አላቸው ከተባለም ያላቸው “አንጎል” እንጅ “አዕምሮ” አይደለም፡፡ በእርግጥ የ“አንጎል” ና “አዕምሮ”ን ልዩነት በግልጽ ማስቀመጥ የሚከብድ መሆኑን ብዙዎች የሳይንስ ተመራማሪዎች ይስማሙበታል፡፡
ለብዙሃኑ በሁለቱ መካከል ልዩነት የለም፡፡ ይሁን እንጂ “አዕምሮ” እና “አንጎል” የተለያዩ ነገሮች መሆናቸውን አዕምሮዬ የነገረኝን ልንገራችሁ፡፡ ሁለቱን እሳቤዎች በተመለከተ ከማንም ተሽሎ ወይም እንዳለ ያልተወሰደ(neither adopted nor adapttd) የራሴን ኦሪጅናሌ ትርጓሜ ያዘጋጀሁ መሆኔንም በዚህ አጋጣሚ ልገልጽላችሁ እወዳለሁ፡፡ ስለሆነም በእኔ ትርጓሜ መሰረት፡- ሁለቱ የተለያየ ትርጉም ላቸው ሲሆን፤ አንጎል ማለት በእንስሳት ጭንቅላት ውስጥ ሚገኝ ግልጽ፣ ውስብስብ ያልሆኑ፣ ማሰብ፣ ማመዛዘን፣ ማሰላሰልና መተንተን የማያስፈልጋቸው መረጃዎችን መሰረት በማድረግ የእንስሳውን አጠቃላይ እንቅስቃሴ የሚመራ፣ በአካልነትና በመንፈስነት መካከል የሚገኝ ነገር ግን አካላዊነት የሚያመዝንበት እንስሳዊ ተፈጥሮ ነው፡፡
አዕምሮ ደግሞ በሰው ልጆች ጭንቅላት ውስጥ የሚገኝ፣ ማሰብ፣ ማሰላሰል፣ ማመዛዘንና መተንተን የሚስፈልጋቸው እጅግ በጣም ጥልቅና ውስብስብ መመሪያዎችን መሰረት በማድረግ ያለፈውን፣ የአሁኑንና የወደፊቱን ሳይቀር ለመረዳት የሚሞክር፣ ሥጋዊ፣ ደመ ነፍሳዊ፣ መንፈሳዊና መለኮታዊ ባህርያትን አንድ ላይ አጣምሮ የያዘ፣ የሰዎችን አጠቃላይ ህይወት የሚመራ፣ በታላቅ ሚስጥራዊ ኃይል የተሞላ ሰብዓዊ ተፈጥሮ የሚል ትርጉም ሰጥቸዋለሁ፡፡ በዚህም አዕምሮ በተፈጥሮው በያዘው ታላቅ ኃይል የተነሳ እንስሳን ጨምሮ ከሌሎችም ምድራዊውን ፍጥረታት የበለጠ ሰውን በተለየ ታላቅ ኃይል ሊያጎናጽፈው ችሏል፡፡
ታላላቆቹን ለመብለጥ የሚያስችል ኃይል
ከሰማይ በታች ምድር በተባለችው ፕላኔት ላይ እንዲኖሩ ከተፈጠሩ ፍጥረታት ሁሉ ግዙፉ ፍጡር የአየር ንብረት ለውጥን መቋቋም አቅቶት ከሺ ዓመታት በፊት ዝርያው እንደጠፋ የሚነገረው ዳይኖሶር የሚባለው እንስሳ ነው፡፡ ታላቅነቱ ከሰው እንደማይበልጥ ግን መጥፋቱ በራሱ ምስክር ነው፡፡ ሰው ግን የአየር ንብረት ለውጥን ብቻ ሳይሆን ከዚያም በላይ ሊያጠፉት የሚችሉ ሌሎች ብዙ ፈተናዎችን አልፎ ዛሬም ምድር ላይ ለዚያውም በ “በለጠ ምቾት” ውስጥ ሆኖ መኖሩን ቀጥሏል፡፡
አሁን ምድር ላይ አሉ ከሚባሉ ሌሎች ትልልቅ ፍጥረታት መካከል አንደኛው ዝሆን መሆኑን መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡ የሰው ልጅ ግን ከእርሱ በብዙ ሺ እጥፍ የሚገዝፈውን ታላቁን እንስሳ ዝሆንን እንደ በግ አስሮ መጠበቅ፣ እንደ አህያ ጭኖ መንዳት ይችላል(ዝሆንን በማላመድ ለጭነት አገልግሎት በመጠቀም የሚታወቁትን ህንዳውያንን ልብ ይሏል)፡፡ የእንስሳት ንጉስ በመባል የሚታወቀው ኃያሉ እንስሳ በተፈጥሮው ከእርሱ በላይ በጣም ግዙፍና ጉልበታም የሚባሉ እንስሳትን ሰባብሮ ለመብላት የሚያስችል ኃይልና የአሸናፊነት መንፈስ የታደለ ነው፡፡ የሰው ልጅ ግን የእንስሳ ፍጥረት ሁሉ የሚርበደበዱለትን፣ አስፈሪውንና አደገኛውን ኃያሉን አውሬ፣ በሰፊው ግዛቱ ያለማንም ከልካይ የፈለገውን እያደረገ በፍጹም ነጻነት መኖር የለመደውን የጫካውን ዓለም ገዥ አንበሳን ህጻናት ሳይቀር እንደሚያዟቸው እንደ ምስኪን ለማዳ የቤት እንስሳት በጠባብ በረት ውስጥ ታጉሮ እንዲኖር ማድረግ ይችላል፡፡
በአፈጣጠራቸው ምክንያት በአየር ላይና በባህር ውስጥ በፍጥነት መጓዝ የሚችሉ ፍጥረታት አሉ። በመሆኑም ወፎች ክንፎቻቸውን በመጠቀም በአየር ላይ በፍጥነት ይንቀሳቀሳሉ፣ ዓሶችም እንደዚሁ ተፈጥሮ የሰጠቻቸውን ክንፎቻቸውን በመጠቀም በባህር ውስጥ በፍጥነት በመዋኘት ይታወቃሉ፡፡ ሆኖም የሰው ልጅ ግን በተፈጥሮ በተሰጠው ሳይሆን ራሱ በፈጠረው “ክንፉ”(በአውሮፕላን) ከማንኛውም ወፍ የበለጠ በአየር ላይ መብረር ችሏል፡፡ ከማንኛውም ዓሳ ያልተናነሰም በባህር ውስጥ መዋኘት የሚያስችል ሰርጓጅ መርከብ ፈጥሯል፡፡ ይህም ብቻ አይደለም በባህር ውስጥ ብቻ ሳይሆን በባህር ላይም መብረር በመቻል ከዓሳም በላይ ሆኗል፡፡
ተራሮችን ከግዝፈታቸውና ከክብደታቸው የተነሳ በአንዳች ልዕለ ኃያል ተፈጥሯዊ ኃይል(ለምሳሌ የመሬት መንቀጥቀጥ) ካልሆነ በስተቀር ማፍረስ ይቅርና ማንቀሳቀስ እንኳን የሚችል ኃይል የለም፡፡ የሰው ልጅ ግን ሲፈልግ በድማሚት እያፈራረሰ መንገድና ከተማ ይሰራባቸዋል፡፡ ውቅያኖስ እጅግ ሰፊና ጥልቅ ነው፡፡ የሰው ልጅ ግን ስፋቱ ሳይገድበው ጥልቀቱ ሳይመልሰው ጥልቁ ድረስ ገብቶ በውስጡ ስላሉ ፍጥረታት ይመራመራል፣ ሲፈልግም በዚያ የሚገኙ ውድ ሃብቶችን አውጥቶ ጥቅም ላይ ያውላል፡፡ ጠፈር የማይደረስበት ሩቅ፣ መንገዱም አስቸጋሪና የማያልቅ ነው፡፡ ሰው ግን ጠፈር ላይ ከመድረስ አልፎ የተወሰኑም ቢሆን በላዩ ላይ የሚገኙ አካላትን መመርመርና ማወቅ ችሏል፤ ይህም ብቻ ሳይሆን እንደ ምድር ሁሉ ጠፈር ላይም አገር ለመመስረት፣ ከተማም ለመቆርቆር ወደ ሥራ ከገባ ሰንበትበት ብሏል፡፡
ከዚህ ቀጥሎ የሚመጣው መሰረታዊ ጥያቄ “ከሌሎች የምድር ፍጥረታት በተለየ በሌሎች ፍጥረታት ለማድረግ ያልተቻሉ ታላላቅ ጉዳዮችን ማከናወን የቻለው የሰው ልጅ ይህንን ታላቅ ኃይል ከወዴት አኘው? እንደተባለው ከእርሱ በብዙ ሚሊዮንና በብዙ ሺ የሚበልጡ ሌሎች ታላላቅ የምድራችን ፍጥረታት እንኳን ያልቻሉትን ሰው ማድረግ የቻለበት ምክንያቱስ ምን ይሆን? በአጠቃላይ የሰው የታላቅነቱ ሚስጥር ምንድር ነው? የሚለው ነው፡፡
የእነዚህ ጥቄዎች መልስ የሚገኘው አሁንም አፈጣጠሩ ላይ ነው፡፡ ማለትም የሰው ልጅን አፈጣጠር በተመለከተ ጠቅለል ባለ መልኩ ከላይ በመግቢያዬ ላይ ለማሳየት እንደሞከርኩት ከሌሎች ፍጥረታት በተለየ ሁኔታ ሰው ታላቅ ሆኖ ነው የተፈጠረው፡፡ አሁን ደግሞ ታላቅነቱ ምኑ ላይ እንደሆነ ዘርዘር አድርገን እንመለከታለን፡፡
ከላይ የተጠቀምንበትን ንጽጽር በድጋሜ እንጠቀመው፡፡ በግዝፈተ አካል ከሆነ ሰው የዳይኖሰርን ይቅርና የዝሆንን አንድ እግሩን እንኳን አያክልም። የምድራችን ታላላቅ ፍጥረታት ብለን የጠቀስናቸው እንደ ዳይኖሰርና ዝሆን የመሳሰሉ እነዚህን ፍጡራን ያየን እንደሆነ የታላቅነታቸው ምክንያት “አካላዊ ግዝፈት” ነው፡፡ ሰው ግን በአካሉ ትንሽ ሆኖ እያለ ታላላቆቹን ፍጥረታት ለመግዛት የሚያስችለውን እንዲህ ዓይነቱን ኃይል ከየት አገኘው የሚለው ላይ ነው ሚስጥሩ ያለው። ሰውን ከምድር ፍጥረታት ሁሉ በላይ ታላቅ እንዲሆን ያስቻለው ይህ ታላቅ ኃይል መገኛው አካላዊ ግዝፈት ሳይሆን አዕምሯዊ ልህቀት ነው፡፡ ይህ ነው የሰው ልጅ የታላቅነቱ ሚስጥር፣ አካሉ ሳይሆን አዕምሮው!
ሰው ሰውነቱን ማወቅ ሲያቅተውስ?
ሰው ይህን ያህል ታላቅ ተፈጥሮውን፣ ኃያል ማንነቱን ማወቅ ተስኖት ከሰውነት ወርዶ ሰው መሆን አቅቶት ሲገኝስ? ለእርሱ ብቻ ተዳልቶ በተሰጠው በታላቁ አዕምሮው ምክንያት የምድራችን ታላቁ ፍጡር መሆን የቻለው ሰው ስጦታውን ማወቅ ሳይችል ቀርቶ ሰው መሆን ባልቻለ ጊዜስ? ሰው ከሁሉም የከፋውን ጥፋት አጥፍቷልና ከምድር ፍጥረታት ሁሉ የሚያንስ ፍጥረት ይሆናላ! ክፉና በጎን፣ ስህተትና ትክክልን፣ እውነትና ሀሰትን፣ ልማትና ጥፋትን፣ ሞትና ህይወትን ወዘተ… የተሻለውን አመዛዝኖ እንዲመርጥበት ከፍጥረት ሁሉ ተዳልቶ “አዕምሮ” የተባለ ውድ ስጦታ የተሰጠው የሰው ልጅ ይህንን ታላቅ ስጦታውን ማወቅ የተሳነው(ወይም ማወቅ ባልፈለገ ጊዜ) ያኔ ከሁሉም ማነሱን ይወቀው።
ከዚህ በተቃራኒው ሰው ይህንን ታላቅነቱን ረስቶ ያለተፈጥሮው መኖር ከጀመረ፣ በራሱ ስህተት ከታላቁ የሰውነት ባህሪው ከጎደለ፣ ሰው ሆኖ ሰውን ከበደለ፣ በፍቅር ፋንታ ጥላቻን ከመረጠ፣ በበጎነት ፋንታ ክፋትን ካስበለጠ፣ ከሰላም ይልቅ ጦርነትን ከናፈቀ ያኔ ሰው ከሰውነቱ ብቻ ሳይሆን ታናሽ ከሚባሉ ፍጥረታትም በታች አንሶ የሚገኘው፡፡ ማሰብ ማሰላሰል ማመዛዘን ከማይችለው፣ አንጎል እንጅ አዕምሮ ከሌለው ከእንስሳም በታች እንስሳ ሆኗል፡፡ በተለይም በቅርቡ ባስተዋልነው የእርስ በርስ ውዝግብ የተከሰተው የመጎዳዳት ተግባር ከላቀው የሰውነት ጎዳና የሚያወጣን ሆኖ ታይቷል፡፡
ሰው ሰውነቱን አለማወቁና ወደ ጥፋት ማምራቱ ከስህተቶች ሁሉ የከፋ ስህተት ፣ ወንጀልና ኃጢአትም ነው። ሰው ሰው መሆኑን ባለማወቁ ምክንያት ለሚፈጽመው ለዚህ ክቡድ ስህተቱም ከራሱ ውጭ ማንንም ተወቃሽ ሊያደርግ አይችልም፡፡ ለዚህ ዓይነት ወንጀል መፈጸምም መንግስትም ቢሆን ተጠያቂ ሊሆን አይገባውም፡፡ ምክንያቱም ሰው መሆንን፣ ሰውነትን ለማወቅና ይህንን ለማክበርና ለማስከበር ህግም አስፈላጊ አይደለምና ነው፡፡ ሰው መሆንን ለማሳወቅ ፖሊስ አይሰማራም፡፡
ሰውነትን በመዘንጋት ከሰሞኑ በሃገራችን እንዳየነው ዓይነት ጥፋትና ወንጀል ለመዳን ሰው ሆኖ መፈጠር ብቻ በቂ ነው! አሁን ላይ በአገራችን እየተፈጠረ ያለው አሳዛኝ ክስተትም የዚሁ ሰው ሰውነቱን ያለማወቅ ጥፋት ያስከተለው ውጤት ነው፡፡ እናም ሰው ሰው መሆኑን ማወቅ አቅቶት ለፈጸመው ለዚህ ዘግናኝ ወንጀልም ይቅርታና ምህረት ሊደረግለት አይገባም፡፡ ምድር ላይ ከዚህ የበለጠ ጥፋት ሊኖር አይችልምና!
አዲስ ዘመን ጥቅምት26/2012
ይበል ካሳ