የደረሱ ሰብሎችን በወቅቱ ወደ ጎተራ

የግብርና ሥራን ውጤታማ ሊያደርጉ ከሚችሉ የሥራ ሂደቶች ውስጥ አንዱ የድህረ ምርት አሰባሰብ ነው። በተለያዩ የሀገራችን አካባቢዎች የሚገኙ አብዛኛዎቹ አርሶ አደሮች በተለይም ከጥቅምት እስከ ጥር ባሉት ወራት የመኸሩን ምርታቸውን ወደ ጎተራ ያስገባሉ። ኢትዮጵያ ከፍተኛ የግብርና ምርት የምታገኘውም በዚሁ የመኸር ወቅት ነው። በምርት መሰብሰቡ ሂደት በሚያጋጥሙ ተፈጥሯዊና ሰው ሠራሽ ችግሮችም ከፍተኛ የምርት ብክነት ሊፈጠር እንደሚችል ጥናቶች ያመላክታሉ።

ከሰሞኑ “ከረሀብ ነፃ ዓለም” ዓለም አቀፍ ጉባዔ በአዲስ አበባ ከተማ በተካሄደበት ወቅት የግብርና ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ መለሰ መኮንን (ዶ/ር) የጥናት ውጤቶችን መሠረት አድርገው ሲያብራሩ በኢትዮጵያ በየዓመቱ 46 ሚሊዮን ዜጎችን መመገብ የሚችል ምርት በድህረ ምርት ሂደት ይባክናል። የድህረ ምርት ብክነት የሚደርሰው ከምርት መሰብሰብ ጀምሮ እስከ መጠቀም ባለው ሂደት እንደሆነ ተናግረው ይህም በዓመት ከ12 ሚሊዮን ቶን ምርት በላይ ይገመታል ብለዋል።

እንደ ጥናቱ ማብራሪያ ከረሀብ ነፃ ዓለም ለመፍጠር ሲታሰብ በሀገርም ይሁን በዓለም ደረጃ የድህረ ምርት ብክነትን መቀነስ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ ጉዳይ ነው። ዶክተር መለሰ በድህረ ምርት የሚባክን ምርትን ማስቀረትና መቀነስ ቢቻል በሀገር ደረጃ የምግብ ዋስትና ያልተረጋገጠለት ወይም የዕለት ቀለብ የሚሰፈርለት ዜጋ እንደማይኖር፤ በሀገርና በቤተሰብ ደረጃም የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ እንደሚቻል ያረጋግጣሉ።

ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ ፣ የአንበጣ ወረርሽኝ፣ ግጭት ወይም ጦርነት፣ ጥንቃቄ የጎደለው የምርት አሰባሰብ እና ሌሎችም ጉዳዮች ለድህረ ምርት ብክነት በምክንያትነት ልንጠቅሳቸው የሚችሉ ናቸው። በግብርና ሥራ ውስጥ ላብን ጠብ አድርጎ፣ አቅምን እና ቴክኖሎጂን አሟጦ በመጠቀም አዝመራን ቶሎ ሰብስቦ ወደ ጎተራ ማስገባት ያስፈልጋል።

የደረሰ ሰብል እንዳይባክን ከፍተኛ ጥንቃቄና አጣዳፊ ሥራ ሰርቶ በሰዓቱ ወደ ጎተራ ማስገባት ቢቻል ምርታማነት የበለጠ ያድጋል፤ በምግብ ራስን የመቻል ህልማችንም እውን ይሆናል።

ከዚህ አንጻር ለአርሶ አደሮቻችን ግንዛቤ የማስጨበጡ ጉዳይ ጊዜ የሚሰጠው ሊሆን አይገባም። ሌላው ቀርቶ አርሶ አደሮቻችን የብሔራዊ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት በየጊዜው የሚሰጣቸውን ወቅታዊ መረጃዎች እየተከታተሉ ለሥራቸው በሚያግዝ መልኩ ጥቅም ላይ የማዋል ልምዳቸው አናሳ ነው ተብሎ የሚገለጽ ብቻ ሳይሆን ከዚያም የወረደ ነው።

ኢትዮጵያ በታሪኳ ለመጀመሪያ ጊዜ በመኸር አዝመራ ከፍተኛ ሄክታር መሬት በዘር የሸፈነችው በዘንድሮው የመኽር ወቅት መሆኑን የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር) ከሰሞኑ መግለጻቸው ይታወሳል። የግብርና ሚኒስቴር መረጃም በዘንድሮው ዓመት የግብርናው ዘርፍ 6 ነጥብ 1 በመቶ እድገት የሚያስመዝግብ መሆኑን አመላክቷል።

ይህ ግምት እውን የሚሆነው እያንዳንዱ አርሶ አደርም ይሁን የሚመለከተው ባለድርሻ አካል ተስፋ የተጣለበትን መስክ ላይ ያለ ሰብል ለብክነት ተጋላጭ ሳይሆን ታጭዶና ተወቅቶ ለጎተራ እንዲበቃ ማድረግ ሲችል ነው።

ብሔራዊ የሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት ከሰሞኑ በሰጠው የአየር ትንበያ መረጃ የመኸር ሰብል አብቃይ በሆኑ በመካከለኛው፣ በምሥራቅ እና በሰሜን ምዕራብ የሀገሪቱ አካባቢዎች ከጥቅምት 7 እስክ ኅዳር 23 ቀን 2017 ዓ.ም ወቅቱን ያልጠበቀ ከቀላል እስከ መካከለኛ መጠን ያለው ዝናብ እንደሚኖር ጠቁሟል። የመኸር ሰብል አብቃይ በሆኑት በነዚህ አካባቢዎች ሊኖር የሚችለው ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ በተለይም በደረሱና በመሰብሰብ ላይ በሚገኙ ሰብሎች ላይ ተጽዕኖ ሊያሳድር ስለሚችል አርሶ አደሮች እና የሚመለከታቸው አካላት በየጣልቃው የሚኖሩትን ደረቃማ ቀናት በመጠቀም የደረሱ ሰብሎችን በወቅቱ መሰብሰብ እንዲችሉም አሳስቧል።

የሀገሪቱ የግብርና ምርታማነት እያደገ የመጣው በተለይም መንግሥት ከዓመታት በፊት የግብርናውን ክፍለ ኢኮኖሚ ከአምስቱ የኢኮኖሚ ማሻሻያ ዘርፎች አንዱና ዋነኛው አድርጎ በትኩረት እየሠራ በመሆኑ ነው። የከተማ ግብርና፣ የበጋ ስንዴ፣ የሌማት ትሩፋትን የመሰሉ ንቅናቄዎች ለግብርናው ዘርፍ ምርታማነት ጉልህ አስተዋጽኦ እያበረከቱ ያሉ እንግዳ የሥራ ባሕሎቻችን ናቸው። አርሶ አደሩ የግብርና ፓኬጆችን እንዲጠቀም፣ የኩታ ገጠምና የሜካናይዜሽን አስተራረስ ዘዴን እንዲከተል መደረጉም ለምርታማነቱ አስተዋጽኦ እንዳበረከተለት የዘርፉ ባለሙያዎች ይናገራሉ።

እንደ ግብርና ሚኒስቴር መረጃ በ2016/17 ምርት ዘመን የመኸር እርሻ በእቅድ ከተያዘው ውስጥ 20 ነጥብ 5 ሄክታር መሬት በዘር ተሸፍኗል። ከዚህም 608 ሚሊዮን ኩንታል ምርት እንደሚገኝ ይጠበቃል። ከ15 ሚሊዮን ሄክታር በላይ በባሕላዊ መንገድ፤ ከ5 ሚሊዮን ሄክታር በላይ ደግሞ በሜካናይዝሽን ወይም በትራክተር ታርሷል። የግብርናው ዘርፍ መነቃቃት በምርት እድገት ላይ የፈጠረው ለውጥ የሚደነቅ ቢሆንም በብዙ ድካምና ልፋት ለጥሩ ፍሬ የበቃውን ሰብል ለብክነት አጋላጭ ከሆኑ ነገሮች ጠብቆ ለጎተራ የማብቃቱ ጉዳይ ግን ገና ብዙ ሊሠራበት የሚገባ ነው።

የሀገራችን ግብርና ዛሬም ድረስ ከኋላ ቀር አሠራርና ከበሬ ትከሻ ያልተላቀቀ ነው፤ በዘንድሮው መኸር ወቅት በትራክተር የታረሰው መሬታችንም ከአንድ አራተኛ የሚበልጥ አይደለም። ግብርናችን ከዚህም በላይ መዘመን ቢችል የምርታማነታችን መጠን የቱን ያህል ሊያድግ እንደሚችል የዘንድሮው ውጤት ምስክር ነው። በግብርና ሥራ ላይ የተጀመረውን ንቅናቄ አጠናክሮ መቀጠል ቢቻልና አርሶ አደሩን ከዚህም በላይ መደገፍ ቢቻል በምግብ ራስን የመቻል ህልማችንን እውን አድርገን ቀሪ ምርታችንን ለውጭ ገበያ ማቅረብ የሚያስችል ትልቅ አቅም እንዳለን የተረዳንበት አጋጣሚ ነው።

ከሰሞኑ “ከረሃብ ነፃ ዓለም” ዓለም አቀፍ ጉባዔ በአዲስ አበባ ከተማ በተካሄደበት ወቅት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ባደረጉት ንግግር የምርጥ ዘር አቅርቦት እጥረትና የግብርና ግብዓት አቅርቦት እጥረት ፈተና ቢሆኑም ኢትዮጵያ ባለፉት ስድስት ዓመታት ረሀብን በመዋጋት ረገድ ውጤት አምጥታለች።

ባለፉት ጥቂት ዓመታት ኢትዮጵያ በግብርና ማሻሻያ ላይ ትኩረት ሰጥታ መሥራቷንና ድርቅን መቋቋም የሚችሉ ሰብሎችን በመዝራት ምርታማነትን ማሳደግ መቻሏንም ተናግረዋል።

ዓለምን የተፈታተኑ ታላላቅ ችግሮች ቢኖሩም ጥረትን በእጥፍ በመጨመር፣ ፈጠራ የታከለባቸውን ሥራዎች በመተግበርና ዘመናዊ የግብርና ሥራን በመከተል ፈተናዎችን ተቋቁሞ ምርታማነትን ማሳደግ ስለመቻሉም ጠቅሰዋል። በርግጥም ኢትዮጵያ ከተረጂነት ወጥታ ራሷን ለመቻል የምታደርገው ጥረት ውጤት እያስመዘገበ መሆኑን ለማወቅ የዛሬ ሰላሳና አርባ ዓመታት ጥቂት ሕዝብ ይዛ እጇን ለምጽዋት የዘረጋችበትን እና አሁን እጆቿን ሥራ ላይ አውላ ከ120 ሚሊዮን በላይ ዜጎቿን የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ እያደረገች ያለውን ጥረት አይቶ መረዳት ይቻላል። ይህን እኛ ልብ ላንለው እንችል ይሆናል፤ ነገር ግን ዓለም አይቶ ምስክርነት የሰጠበት ሀቅ ነው።

‹‹ከረሃብ ነፃ ዓለም›› ጉባኤ ላይ የተገኙት የአፍሪካ ህብረት ሊቀ መንብር ሙሳ ፋቂ በንግግራቸው ያረጋገጡትም ይህንኑ ነው። አፍሪካ የተፈጥሮ ሀብት ብዝሀነት ያላት አህጉር ብትሆንም አሁንም ድረስ የምግብ ሉዓላዊነትን ማረጋገጥ አልቻለችም ያሉት ሙሳ ፋቂ ረሀብን ከአፍሪካ ምድር የማጥፋት ጉዳይ የነገ ሳይሆን የዛሬ ተጨባጭ ሥራ ሊሆን ይገባል ነው ያሉት። የአፍሪካን የምግብ ሉዓላዊነት ለማረጋገጥ ጥራት ያለው የግብርና ሥራ በመተግበር ምርታማነትን ማስፋፋት ያስፈልጋል፤ ከዚህ አንጻር ኢትዮጵያ እየተገበረች ያለችው ሞዴል የግብርና ትራንስፎርሜሽን ሥራ የሚበረታታ እና ለሌሎች ምሳሌ መሆን የሚችል ነው ሲሉ አወድሰዋል።

ሞዴል የግብርና ሽግግር ምርት ማምረትን ብቻ ሳይሆን የምርት ብክነት መቀነስንም የሚመለከት ነው። ሰብሎች በጥሩ ክትትልና እንክብካቤ ተይዘው ፍሬያማ ከሆኑ በኋላ ታጭደውና ተወቅተው ወደ ጎተራ በሚገቡበት በመጨረሻው ሰዓት በሚፈጠሩ አንዳንድ ሁኔታዎች ከፍተኛ ብክነት ይፈጠራል። ብዙውን ጊዜ ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ እና ጥንቃቄ የጎደለው የምርት አሰባሰብ ሂደት ለድህረ ምርት ብክነት በምክንያነት ቢጠቀሱም የአንበጣ ወረርሽኝ፣ ጦርነትና ጦርነትን ተከትሎ የሚከሰት ስደት በምርት መሰብሰብ ሂደት ላይ ተጽዕኖ የሚፈጥሩ ተጨማሪ ችግሮች ናቸው።

ከዚህ አንጻር ከሀገራችን ተሞክሮ ተነስተን ብዙ ማሳያዎችን መጥቀስ እንችላለን። ለምሳሌ፤ ከሶስትና አራት ዓመታት በፊት በሀገራችን የተከሰተው የአንበጣ ወረርሽኝ በደረሱ ሰብሎች ላይ ምን ያህል አደጋ አስከትሎ እንደነበር የተመለከትነው ሀቅ ነው። በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል የነበረው የእርስ በእርስ ግጭት የደረሱ ሰብሎች በሥርዓት ተሰብስበው እንዳይገቡና ምርታማነታችን በሚፈለገው ደረጃ ከፍ እንዳይል ተጽዕኖ መፍጠሩም የሚታወስ ነው። ዛሬም በአንዳንድ የሀገራችን አካባቢዎች የሚስተዋሉት ግጭቶች እርሶ አደሩ ተረጋግቶ ሥራውን እንዳይሠራ በማድረግ በምርታማነታችን ላይ አሉታዊ ጥላ ማጥላታቸውን እያየን ነው። ግብርናችን እነዚህን ሁሉ ችግሮች ተቋቁሞ ምርታማ መሆኑም የሚያስደንቅ ነው።

የምርት ብክነትን በየአንዳንዱ አርሶ አደር ወይም በግለሰብ ደረጃ ስንመለከተው ትንሽ ሊመስለን ይችላል፤ ነገር ግን በምርት መሰብሰብ ሂደት እያንዳንዱ አርሶ አደር ላይ የሚፈጠረው የምርት ብክነት ሲደማማር ከፍተኛ የሆነ ሀገራዊ ጉዳት የሚያስከትል እንደሆነ ቀደም ባለው የጥናት ውጤት መረዳት ችለናል። አርሶ አደሩ በብዙ ኩንታል የተመናቸውና በብዙ ብር የለካቸው በቁም ያሉት ሰብሎች፤ ታጭደው ወደ ጎተራ ከመግባታቸው በፊት በተለያዩ ሰው ሠራሽና ተፈጥሯዊ ችግሮች ምክንያት የመባከናቸው ጉዳይ መፍትሔ ካላገኘ ምንጊዜም ቢሆን ምርታማነታችን ላይ ተጽዕኖ መፍጠሩ የማይቀር ነው።

ከሰሞኑ እየተመለከትነው ያለነው ደመናማ የአየር ፀባይም ምርታማነታችንን ጥያቄ ውስጥ እንዳይከተው ብርቱ ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል። ከቀበሌ እስከ ፌዴራል መንግሥት ያሉ አመራሮችም ለጉዳዩ ትኩረት ሰጥተው ሕዝብን በማንቀሳቀስ የደረሱ ሰብሎች በወጉ ታጭደውና ተወቅተው ወደ ጎተራ እንዲገቡ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል።

ከሳምንታት በፊት በቆላማና ከፊል ደጋማ አካባቢዎች የመኸር አዝመራው እየተሰበሰበ እንደሚገኝ እና እስከዚያን ጊዜ ድረስ በአምስት ነጥብ ሦስት ሚሊዮን ሄክታር መሬት ላይ የተዘራ ሰብል መሰብሰቡን የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ ዶ/ር መግለጻቸው ይታወሳል። በአሁኑ ሰዓትም የዚህ መረጃ አሀዝ በወቅቱ ከተጠቀሰው በላይ ከፍ ሊል እንደሚችል ይታመናል።

እንደ ሚኒስትሩ ገለጻ በደጋና በአብዛኛው ወይና ደጋ አካባቢዎችም የሰብል አዝመራው በጣም ጥሩ ቁመና ላይ ይገኛል፡ በቀጣይም አዝመራን የመሰብሰቡ ሂደት ተጠናክሮ የሚቀጥል እንደሚሆንና ይህም ለአምራቹ ብቻ የሚተው ሳይሆን የሁሉንም ተሳትፎና ጥረት የሚጠይቅ መሆን እንደሚገባው አሳስበዋል።

ኢትዮጵያ ያለማችውን ከፍተኛ ምርት ሙሉ ለሙሉ እውን ማድረግ የምትችለውና ምርትን ከብክነት መታደግ የሚቻለው ክረምቱን ሁሉ ርብርብ ሲደረግበት የነበረውን ሰብል በወቅቱና በጥራት መሰብሰብ ሲቻል እንደሆነም አስምረውበታል።

በየደረጃው ያሉ የመንግሥት አመራሮች፣ አርሶ አደሮች እና አርብቶ አደሮች ሁሉንም የሰብል መሰብሰቢያ ቴክኖሎጂዎች እንዲጠቀሙና ምቹ ሁኔታዎችን እንዲፈጥሩ፤ የመንግሥት ሠራተኞች፣ ተማሪዎች እንዲሁም የመንግሥት ፀጥታ አካላት በልዩ ሁኔታ ድጋፍ እንዲያደርጉም ጥሪ ማቅረባቸው ይታወሳል።

ይነስም፤ ይብዛም የኢትዮጵያን ሕዝብ እየመገበ ዘመናትን ያሻገረው የአርሶ አደሩ ብርቱ ክንድ ነው። የሕዝብ ቁጥር እያደገ በመጣ ቁጥር የማምረት አቅማችንም በዚያው ልክ ማደግ ካልቻለ ኑሯችን ውሃ ቅዳ ውሃ መልስ የመሆኑ ጉዳይ የማይቀር ነው። በልመና እና በርዳታ ስንዴ የኖርብትን ዘመን ታሪክ ለማድረግ መንግሥት በግብርናው ዘርፍ የወሰዳቸው ርምጃዎች አስደናቂ ልውጦች ተመዝግበውበታል። ምርታማነታችን ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መጥቶ ከዛሬ ሃምሳ ዓመት በፊት ከነበረው ሕዝብ በእጥፍ ያደገውን ሕዝባችንን እየመገበ ነው። ይህ ቀጣይነት እንዲኖረው እያንዳንዱ ዜጋ ግብርናውን ውጤታማ ለማድረግ የተቀረጹ አዳዲስ አሠራሮችን ማለትም፤ የከተማ ግብርናን፣ የሌማት ትሩፋትን፣ የበጋ ስንዴን የመሳሰሉ ፕሮግራሞችን ከመተግበር ባለፈ አርሶ አደሩን በሁሉም ዘርፍ መደገፍና ማገዝ ይጠበቅበታል።

አሁንም የደረሱ ሰብሎች ለብክነት እንዳይዳረጉና የተገመተውን ምርት ወደ ጎተራ አስገብተን በምግብ ራሳችንን የመቻል ህልማችንን እውን እንድናደርግ አርሶ አደሮቻችን እንደ ጅጊ ፣ ወንፈል እና ደቦን የመሳሰሉ የመረዳዳት ባሕሎቻችንን ተጠቅመው አዝመራቸውን መሰብሰባቸው ሳይዘነጋ ሁላችንም በያለንበት ቦታ ሁሉ ከአርሶ አደሩ ጎን ቆመን የደረሱ ሰብሎችን የመሰብሰብ የውዴታ ግዴታችንን ልንወጣ ይገባል።

ኢያሱ መሰለ

 አዲስ ዘመን ህዳር 17/2017 ዓ.ም

 

Recommended For You