በወር በሚያገኙት ደመወዝ የመኖሪያ ቤት ተከራይቶ መኖር እንደ ዳገት የከበዳቸው ሠራተኞች የጠዋቷን ጀንበር ለመመልከት ቀስቃሽ የወፎች ጫጫታ አያሻቸውም። ይልቁንም አዳራቸውን በዕምነት ተቋማት ደጃፍና የእግር ጉዞ እያደረጉ ከጨረቃ ጋር ዓይን ለዓይን ሲተያዩ ወጋገኑ መንጋቱን ያበስራቸዋል። ሕይወትን እንዲህ የሚገፉ ሠራተኞች እንዳሉ የሠማ ታዲያ ጉዳዩን ከማመን ይልቅ ችግሩ ተጋንኖ የቀረበ ሊመስለው እንደሚችል ሥማቸው እንዲገለጽ ያልፈለጉ የቀድሞ ካርታ ሥራዎች ድርጅት በአሁኑ አጠራርሩ የጂኦስፓሻል ኢንፎርሜሽን ኢንስቲትዩት ሠራተኞች በሃዘን ይናገራሉ።
እንቅልፍ የተራቡ እኚህ ሠራተኞችን በቅርብ የሚያውቁ የተቋሙ የሥራ ባልደረቦቻቸው ከቤታቸው ምግብ ቋጥረው እንደሚያመጡላቸው የሚናገሩት ቅሬታ አቅራቢዎቹ፤ መሥሪያ ቤታቸው ከኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ አንድ ዲቪዥን (ክፍል) ጋር ውህደት እንደፈጠረ በሠሙ ጊዜ ታላቅ የምሥራች እንደሆነላቸው ይናገራሉ። ይሁን እንጂ ውህደቱ እንዳሰቡት ሳይሆን ቀርቶ መንግሥት ተቋማትን እንደ አዲስ ለማደራጀት ያከናወነው ተግባር ከጅምሩ ደስታን የፈጠረላቸው ሠራተኞች የኋላ ኋላ ግን ለከፍተኛ የስነልቦና ውድቀት እንደዳረጋቸው ነው የሚገልጹት።
ከዓመት በፊት በተደረገው ተቋማትን ዳግም የማዋቀር ተግባር ጂኦስፓሻል ኮሚሽን ኤጀንሲና የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ (ኢንሳ) አንድ ዲቪዥን (ክፍል) ውህደት ከፍተኛ ቅሬታ የፈጠረባቸው ሠራተኞችን የፍረዱኝ አቤቱታ እንዲህ ይዘንላችሁ ቀርበናል።
የቅሬታው መነሻ
ከኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ (ኢንሳ) አንድ የሥራ ክፍል ጋር የተደረገው ውህደቱ ቀድሞ የነበረባቸውን ችግር አጉልተው እንዲመለከቱ ያደረገና ከለውጥ ይልቅ ራሳቸውንና ተቋማቸውን የጎዳ እንደሆነም ነው የሚያስረዱት። ለአንድ ዓይነት ሥራ ተመሳሳይ የሥራ ልምድና የትምህርት ደረጃ የሚያገኙት ክፍያም ፍፁም ተቀራራቢ አይደለም። የቀድሞ ሠራተኞች ከነበራቸው አነስተኛ ደመወዝ የተነሳ የችግሩ መጠንና ስፋት ይለያይ እንጂ በየደረጃው ቅሬታ እንደነበረባቸው በማስታወስ፤ በአሁኑ ወቅት በአንድ ተቋም ይስሩ እንጂ ሠራተኞቹ በስነልቦናም ሆነ በደመወዝ እንደማይገናኙ በመግለጽም፤ በአንድ መሥሪያ ቤት ውስጥ የተለያየ የደመወዝ መክፈያ ሰነድ (ፔይሮል) ሊኖርስ ይችላልን? በማለትም ይጠይቃሉ።
ከኢንሳ ጋር ከተቀላቀሉ በኋላ ለተቋሙ ሠራተኞች አገልግሎት የሚሰጠው ካፍቴሪያ እንኳ ዋጋውን በእጥፍ ማሳደጉን በማንሳት፤ የዋጋ ጭማሪው የቀድሞውን ሳይሆን አዲስ የተቀላቀሉትን የኢንሳ ሠራተኞች ደመወዝ መነሻ ማድረጉን እንደ ማሳያ ያቀርባሉ። ችግሮቹም ተያያዥና ሰፊ እንደሆኑም ነው የሚያስረዱት።
ተቋማቱ ሲዋሀዱ ሠራተኞቹ ተቀላቅለው እንዳይሠሩ በየመሥሪያ ቤቱ በቡድን በቡድን መቀመጣቸው የዕውቀትና የቴክኖሎጂ ሽግግር እንዳያገኙ ማድረጉን ይገልፃሉ። ከደመወዝ ጋር በተያያዘም ከኢንሳ የመጡት ሠራተኞች ከፍተኛ የደመወዝና ሌሎች ጥቅማ ጥቅም ያላቸው ሲሆን፤ ይህ የደመወዝ ልዩነትም ሆነ የተለያዩ ጥቅማ ጥቅሞች ለሌላው የጂኦስፓሻል ሠራተኛ እንደማይከፈል ነው ቅሬታ አቅራቢዎቹ የሚያስረዱት።
ሠራተኛው በደመወዝ ልዩነቱ ያለበት ቅሬታ ሳይበቃ ቀደም ሲል በጂኦስፓሻል ወይም በካርታ ሥራ ላይ ይሠሩ የነበሩ ከፍተኛ ሙያ ያላቸው ሠራተኞች በምንም ጉዳይ ላይ እንዳይሳተፉ መገለላቸው ሁኔታውን በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንዳደረገው ያብራራሉ።
ከመቀላቀላቸው በፊት እንደነበረው ሁሉ የሥራ ጫናውን ሳያማርሩ የሚያከናውኑት የቀድሞ ሠራተኞች ቢሆንም፤ የተቋሙ የበላይ ኃላፊ ዋና ዳይሬክተሩ ግን ግንኙነታቸውን ከኢንሳ ከመጡት ሠራተኞች ጋር ብቻ ገድበውታል። በዚህም በተፈጠሩ ልዩነቶች በቀድሞ ሠራተኞች ዘንድ ከፍተኛ የሥነልቦና ውድቀት፣ የሥራ መቀዛቀዝና የሥራ ተነሳሽነት እንዲጠፋ እያደረገ መሆኑንም ቅሬታ አቅራቢዎቹ ይጠቁማሉ። ለሦስት አስርት ዓመታት በተቋሙ ያገለገሉና በቂ የሥራ ዕውቀት ያላቸው ሠራተኞች ቢኖሩም እየደረሰባቸው ያለው መገለል ብሎም የተለያዩ ልዩነቶች ግን ሁኔታውን ለመቋቋም ያላቸውን ጥንካሬ እየተፈታተነው ይገኛል።
የቀድሞ ሠራተኞች በአንድ በኩል በልዩ ስኬል የደመወዝ ማስተካከያ ሳይደረግላቸው በሌላ በኩል ደግሞ የጂኤጂ ተጠቃሚ ሳይሆኑ ጥያቄያቸው ምንም ዓይነት ምላሽ ሳያገኝ እነሆ ድፍን አንድ ዓመት እንደነጎደ የሚናገሩት ቅሬታ አቅራቢዎቹ፤ ጥያቄያቸውን ለተቋሙ የበላይ ኃላፊ ቢያቀርቡም ‹‹አትጠብቁ የሞተ ጉዳይ ነው›› የሚል ለውይይት ክፍት ያልሆነ ዝግ ምላሽ ማግኘታቸው ይበልጥ ተስፋቸውን እንዳጨለመው ይገልፃሉ።
ለአቤቱታቸው መፍትሔ ያመጣል ብለው ዕምነት ጥለውበት የነበረው ተቋማቱ ሲዋሀዱ የተሠራው መዋቅር በአንደኛው መሥሪያ ቤት የነበረና መዋቅሩን ከኢንሳ ሌላ ማንም ሊከታተለው የማይችል ከመሆኑም ባሻገር ከአንድ ዓመት በላይ የፈጀ እንደሆነ ይናገራሉ።
ቀድሞ ተሠርቶ የነበረው የጂኤጂ ደመወዝም ቢሆን ሠራተኛው ሊያገኝ አለመቻሉን የሚያነሱት ሠራተኞቹ፤ ለዚህ ደግሞ ተገቢውን ትኩረት ሰጥቶ የሚከታተልና ጉዳያቸውን ከዳር የሚያደርስ አካል አለመኖሩን እንደ ምክንያት ያነሳሉ። ለጥያቄያቸው ፈጣን ምላሽ አለመሰጠቱ ቅሬታቸውን አምኖበት የያዘ አካል ላለመኖሩ አመላካች እንደሆነ በመግለጽ፤ የሚመለከተው አካል እልባት እንዲሰጣቸው ይጠይቃሉ።
አዋጁ
በአዋጅ ቁጥር 1097/2011 አንቀጽ ዘጠኝ፤ በኢትዮጵያ ጂኦስፓሻል ኢንፎርሜሽን ኤጀንሲ እንደገና ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 1079/2010 ዓ.ም ለጂኦስፓሻል ኢንፎርሜሽን ኤጀንሲ እንዲሁም ጂኦስፓሻል ዴታና መረጃን በተመለከተ በኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ እንደገና መቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 860/2006 ዓ.ም ለኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ ተሰጥቶ የነበሩ ሥልጣንና ተግባራት ለጂኦስፓሻል ኢንፎርሜሽን ኢንስቲትዩት እንደተሰጠ ይደነግጋል። በ2010 ዓ.ም የጂኦስፓሻል ኢንፎርሜሽን ኤጀንሲ እንደገና ተቋቁሞ የነበረ ሲሆን፤ ከቆይታ በኋላ ደግሞ ከኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ ውስጥ የነበረ የጂኦስፓሻል ዲቪዥን በጋራ ኢንስቲትዩቱ መቋቋሙን እንዲሁም ተጠሪነቱ ለኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ሆኖ መቋቋሙን ያመለክታል።
የተቋሙ ሠው ሀብት
በቀድሞ የጂኦስፓሻል ኮሚሽን ኤጀንሲ በአሁኑ አጠራሩ የጂኦስፓሻል ኢንፎርሜሽን ኢንስቲትዩት የሠው ሀብት አስተዳደር ዳይሬክተር ወይዘሮ ገነት ለማ፤
የሠራተኞች ቅሬታ መኖሩን እንደሚያውቁ አምነው ተገቢ እንደሆነም አቤቱታውን ተጋርተውታል። በኢ.ፌ.ዴ.ሪ የፌዴራል አስፈፃሚ አካላትን ሥልጣንና ተግባር ለመወሰን በወጣው አዋጅ ቁጥር 1097 መሠረት፤ ከተዋሃዱ መሥሪያ ቤቶች መካከል አንዱ ቀድሞ የጂኦስፓሻል ኢንፎርሜሽን ኤጀንሲን እና ከመረጃ መረብ ደህንነት ኤጀንሲ የጂኦስፓሻል ዲቪዥን ወይንም ክፍል ጋር አንድ ላይ ተዋቅረው እንዲሰሩ መወሰኑን ያስታውሳሉ።
የሠራተኞቹን ቅሬታ ከፈጠሩ ምክንያቶች አንዱ የደመወዝ መለያየት ነው የሚሉት ወይዘሮ ገነት፤ ሁለቱ ተቋማት በተለያዩ ሁኔታዎች ውስጥ የነበሩ መሆናቸው ለቅሬታው መንስዔ እንደሆነ ይገልፃሉ። የኢንሳ ሠራተኞች ስለነበሩ የደመወዝ ወሰናቸው የተለየ መሆኑን በማብራራት፤ በተቋሙ ዝቅተኛው የደመወዝ ወለል ሰባት ሺህ አንድ መቶ ሃምሳ አራት ብር ሲሆን፤ ከፍተኛው ደግሞ እስከ 18 ሺህ ብር እንደሆነ ያረጋግጣሉ። በሌላ በኩል በተቋሙ ከፍተኛው የደመወዝ ጣርያ ሰባት ሺህ ስድስት መቶ አርባ ሰባት ሲሆን፤ ይህም ዋና ዳይሬክተር የሚያገኙትና ከኢንሳ ዝቅተኛ የደመወዝ ወለል ጋር ተቀራራቢ መሆኑን ያብራራሉ።
የደመወዝ መለኪያው የተለየ መሆኑን የሚጠቁሙት ዳይሬክተሯ፤ የሥራ መደባቸው አይሲኤፍ (ኢንሳ ኮምፒተንሲ ፍሬምዎርክ) እንደሚባል ያስረዳሉ። ይህም በመንግስት ውስጥ የሌለ መደብ ነው በማለት ተቋሙ የመንግሥት መሥሪያ ቤት ይሁን እንጂ የደመወዝ መለኪያው ግን የተለየና በመንግሥት መደብ ውስጥ የሌለ እንደሆነ ያስረዳሉ። በዚህ መሠረት ከተቋሙ የመጡ ሠራኞች ይዘውት የመጡት ደመወዝ ከፍተኛና ከቅሬታ አቅራቢዎቹ ሠራተኞች ደመወዝ ጋር የማይገናኝ መሆኑ ለቅሬታው አንዱ መነሻ እንደሆነ ይናገራሉ።
ሠራተኛው ቢሮ ተሰጥቶት ቢገባም በሥራም ሆነ በመንፈስ ግን አልተዋሃደም ሲሉ ዳይሬክተሯ ሁኔታውን ያብራራሉ። ሁለቱ ተቋማት ከመዋሃዳቸው አስቀድሞ የጂኦስፓሻል ሥራ ይሠሩ የነበረ ሲሆን ፤ ሲዋሃዱ ግን በዘፈቀደ እንጂ ምደባ አለመመደባቸውንም ያስረዳሉ። በዚህም ከኢንሳ የመጡት ሠራተኞች የሥራ ሪፖርት የሚያቀርቡት ከራሳቸው ለመጡ ኃላፊዎች ሲሆን፤ የተቋሙ ሠራተኞችም በበኩላቸው ለራሳቸው ኃላፊዎች ሪፖርት ያቀርባሉ። ይህም የተቀናጀና ወጥነት ያለው የመረጃ ፍሰት እንዳይኖር እያደረገው ይገኛል በማለት ልዩነቱ በተቋሙ ሥራ ላይም አሉታዊ ተፅዕኖ እያሳደረ መሆኑን ያስረዳሉ። ስለሁኔታው የሚናገሩት ወይዘሮ ገነት፤ ሠራኞቹ ለአንድ ዳይሬክተር ተጠሪ ሆነው እየሠሩ አይደለም።
የደመወዝ ልዩነቱ ከሚፈጥረው ቅሬታ ባሻገር ሥራዎችን ለተለያዩ ኃላፊዎች ሪፖርት ማድረግ ሥራዎች በተቀናጀ ሁኔታ እንዲሄድ ያስችላል ለማለት እንደሚያዳግት ነው የሚጠቁሙት። በፍጥነት ተዋህዶ ተጠሪነታቸውም ለተወሰነ አካል መሰጠት አለበት። ይህም የሥራ አፈፃፀም ጥራት ቁጥጥር ለማድረግም ያስችላል በማለት ይገልፃሉ። ከደመወዝ ጋር በተያያዘም ከተቋሙ ሠራተኞች ባሻገር ከኢንሳ የመጡት ሠራተኞች በተመሳሳይ ጥያቄ እንደሚያቀርቡ የሚናገሩት ወይዘሮ ገነት፤ ቃል ተገብቶላቸው እንደነበር እንደሚገልጹ ያስረዳሉ።
ቀድሞ በነበሩበት ተቋም በየዓመቱ የደመወዝ ማሻሻያ ይደረግላቸው የነበረ በመሆኑና በአሁኑ ወቅት በመቅረቱ ጥያቄ እያነሱ ይገኛሉ። ቀድሞ አይሲኤፍ በሚል ከአንድ እስከ ዘጠኝ የደረጃ ዕድገት እየተሰጣቸው ደመወዛቸውም የሚያድግ በመሆኑና በአሁኑ ወቅት በነበሩበት በመቆማቸው ጥያቄው ከሁለቱም ወገን እንደሆነ ያስረዳሉ።
የችግሩን ተያያዥነት የሚያስረዱት ወይዘሮ ገነት የደመወዝ ብቻ ሳይሆን የአበል መለያየት እንዳለም ነው የሚናገሩት። ለችግሩ እንደማሳያ ለተቋማችን ቃለምልልሱን ከመስጠታቸው ጥቂት ቀናት ቀደም ብሎ ለመስክ ሥራ ከአዲስ አበባ የወጡ ሠራተኞችን ጉዳይ አንስተዋል። በዚህም በቀን አምስት መቶ ብር የሚከፈላቸው ሲሆን፤ የተቋሙ ሠራተኞች ደግሞ በመንግሥት አበል አከፋፈል መመሪያ መሠረት ነው። በዚህም በእነርሱ በኩል 15 ሺህ ብር ሲወስዱ የተቋሙ ሠራተኞ ደግሞ አራት ሺህ ብር ብቻ ሊወስዱ ችለዋል።
ለተመሳሳይ ሥራ መስክ የወጡት ሠራተኞች ይህን መሰል ሰፊ ልዩነት ያለው የውሎ አበል አከፋፈልም በመስክ ሥራ ላይ የወጣውን ሠራተኛ ተመሳሳይ ቦታ እንዳይመገቡና እንዳያድሩ በማድረግ ከፍተኛ የስነልቦና ጉዳት እንደሚያደርስም ይገልፃሉ። ይህም ጥያቄ የሚነሳው በቅሬታ አቅራቢዎቹ ብቻ ሳይሆን ለተመሳሳይ ሥራ መስክ ወጥተው በቀን 147 ብር የተሠጠው የሥራ ባልደረባቸው በምን ተመግቦ? ምኑን ለአልጋ ከፍሎ ሥራውን ሊሠራ ነው? የሚል ጥያቄ የሚጭርባቸው መሆኑን ይናገራሉ።
ዳይሬክተሯ ችግሮቹን ሲያብራሩ፤ በመንግሥት አሠራር መሠረት በከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊነት ላይ የሚቀመጡ ኃላፊዎች ቤት ወይንም የቤት አበል ይሰጣል። ነገር ግን ከኢንሳ የመጡት ሠራተኞች ከኃላፊዎች ባሻገር እስከተወሰነ የሥራ እርከን ደረጃ ያሉ ሠራኞችም የዚህ ጥቅማ ጥቅም ተቋዳሾች በመሆናቸው ከስድስት ሺህ እስከ ስምንት ሺህ ብር ከደመወዛቸው በተጨማሪ ያገኛሉ። በተያያዘ ከዳይሬክተሮች አልፎ እስከ ቡድን መሪ ድረስ የተሽከርካሪ (መኪና) አገልግሎት አላቸው።
በተቋሙ የተሽከርካሪ እጥረት በመኖሩ ዳይሬክተሮች በቡድን የሚሄዱ ሲሆን፤ በግል መኪና ያላቸው ከሦስት ዳይሬክተሮች ያልበለጡ የሥራ ኃላፊዎች ብቻ ናቸው። ለእነርሱም የተሰጠው ሥራ አምሽተው ስለሚሠሩና በተያያዥ ምክንያት ቢሆንም ከኢንሳ የመጡት ሠራተኞች ግን ቀድሞ በነበሩበት ተቋም ይገለገሉባቸው የነበሩና ኪራይ የሚከፈልባቸው መኪናዎች አላቸው። ወደ ተቋሙ ሲቀላቀሉም ኪራያቸው እየተከፈለላቸው የመኪና አገልግሎታቸው ሊጠበቅ ችሏል በማለት ልዩነቱ ሰፊ እንደሆነ ንፅፅሩን በመግለጽ ያብራራሉ።
ከደመወዙ ባሻገር በተለያዩ ጥቅማጥቅሞች የተነሳ ልዩነቱ ሰፊ እንደሆነ የሚናሩት ዳይሬክተሯ፤ ቅሬታው በሠራተኞች ዘንድ የፈጠረውን አሉታዊ ተፅዕኖ መረዳት የሚቻለው በሥራ ተነሳሽነት ላይ ነው ባይ ናቸው። ሠራተኞች በተደጋጋሚ በቢሯቸው በመገኘት ለጥያቄያቸው ምላሽ የሚጠይቋቸው እንደሆነ በመግለጽም፤ በርካቶች የሥራ ልምድ እንደሚያፅፉና ፍልሰትም እንደጨመረ ይገልፃሉ። ይህም ሌላ የተሻለ አማራጭ እየፈለጉ መሆናቸውን ማሳያ ነው። ቀሪዎቹ በኢንስቲትዩቱ የሚገኙ ሠራተኞችም ቢሆኑ የሥራ ተነሳሽነታቸው ወርዷል።
ካፍቴሪያ በቀን አንድ ጊዜ መመገብ እንደማይችሉና በተቃራኒው በተመሳሳይ የሥራ መደብ ላይ ያሉ ከፍተኛ ተከፋዮች እስከ አራት ጊዜ የመመገብ አቅም እንዳላቸው በአደባባይ ዋና ዳሬክተሩ ባሉበት እንደተነሳ ያስታውሳሉ። ነገር ግን በወቅቱ የተሰጠው ምላሽ ‹‹እዚህ ደመወዝ ላይ አትደርሱበትም፤ አትጠይቁ›› የሚል ዝግ የሆነ ነበር። ይህም በርካታ የተቋሙን ሠራተኞች ያስከፋና ቅሬታን የፈጠረ ነበር። ምላሹም በእኩል ዓይን ባለመታየታቸውና ቅሬታቸውን ከቁብ የቆጠረው አካል ባለመኖሩ ፈጣን ምላሽ ሊሰጠው አለመቻሉን ይናገራሉ። ይህም ትክክለኛና ተገቢነት ያለው ቅሬታ ነው በማለት ያረጋግጣሉ። የሚመለከተው አካልም ምላሽ እንዲሰጥ ይጠይቃሉ።
ከአጠቃላይ ሠራተኛ ጋር በጉዳዩ ላይ ታስቦ የተዘጋጀ መድረክ ባይኖርም የሶሻል ኮሚቴ ለማቋቋም ሐምሌ 2011 ዓ.ም በተዘጋጀው መድረክ ላይ ግን ሠራተኞች ቅሬታቸውን አንስተው እንደነበር ያስታውሳሉ። በዚህ ልዩነት እንዴት መኖር እንደሚችሉ ሠራተኞች አቤቱታውን ያሰሙ ሲሆን፤ ልዩነቱ በአጭር ጊዜ እልባት እንደሚያገኝ በዋና ዳይሬክተሩ ምላሽ ተሰጥቶ ነበር። በመቀጠልም ነሀሴ 10 ቀን 2011 ዓ.ም የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ እንዲሁም ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት አምባሳደር አስቴር ማሞ በተገኙበት መድረክ ችግራቸውን እንዳስረዱ ወይዘሮ ገነት ያስታውሳሉ።
የደመወዝ ልዩነቱ የፈጠረውን ከፍተኛ ቅሬታ ምላሽ መስጠት የሚቻለው መዋቅር በመሥራት ማዋሀድ ሲቻል ነው የሚሉት ወይዘሮ ገነት፤ መዋቅር እየተሠራ እንደሆነ በተባራሪ ወሬ እንደሚሰሙ ይገልፃሉ። ነገር ግን ምንም ዓይነት ለውጥ ሳይጎበኛቸው ዓመት እንዳስቆጠሩም ነው የሚናገሩት። ጥምረታቸው ከጥቅምት ስድስት ቀን 2011 ዓ.ም ቢጀምርም ውጤት ግን አላገኙም። ዋና ዳይሬክተሩ ከመረጃ መረብ ደህንነት ኤጀንሲ ከመጡ ከተወሰኑ ኃላፊዎች ጋር በመሆን እየሠሩ እንደሆነ ቢሰማም ሠራተኛው አውቆት የመረጠው በግልጽ የተቋቋመ ኮሚቴ ግን የለም።
ዳይሬክተሯ የተቋሙን የሰው ሀብት የተመለከቱ ጉዳዮች መረጃ ሊኖራቸው ቢገባም ‹‹እየሠራን ነው›› ከሚለው የዋና ዳይሬክተሩ የቃል ምላሽ የዘለለ በፅሑፍ ያረፈ ምንም ማስረጃ እንደሌለና እንደማያውቁም ይናገራሉ። ነገር ግን የደመወዝ ልዩ ስኬል ወይንም ጣርያ እንዲፈቀድ እንደጠየቁም ዋና ዳይሬክተሩ በቃል እንዳሳወቋቸው ይገልፃሉ።
በአንድ ወቅት ጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ሊላክ በመሆኑ ቶሎ በሉ ተብሎ በፍጥነት አስተያየት ሰጥተውበት መላኩን ያስታውሳሉ። ከዛ በኋላ ግን በጉዳዩ ላይ የጠለቀ መረጃ እንዳሌላቸውም ይናገራሉ። ሥራው እየተሠራ ያለው ግልጽነት በተሞላበት መንገድ አለመሆኑም ለሠራተኞች ቅሬታ ሌላ መነሻ እንደሆነ ዳይሬክተሯ ይገልፃሉ። ከኢንሳ የመጡትን ሠራተኞች ደመወዝ መንካት ወይንም መቀነስ ባይቻልም መዋቅር በመሥራት የሠራተኛውን ደመወዝ ከፍ ማድረግና ቅሬታውን ማቃለል ይቻል እንደነበርም ይጠቁማሉ። ለዚህም ዓይነተኛ መፍትሔ የሚሆነው ልዩ ስኬል ፈቃድ ከተገኘ እንደሆነም ያመለክታሉ።
ተቋሙ ቀደም ሲል ሞዴል (የተሻለ) እንደነበር ዳይሬክተሯ ይናገራሉ። በፌዴራል ደረጃ ከተመረጡ ስምንት መሥሪያ ቤቶች አንዱ የነበረ ሲሆን፤ ከ2009 ዓ.ም ጀምሮ ሠራተኛው ከ2009 ዓ.ም ጀምሮ ምደባ ተሰጥቶት ነበር። ሠራተኛው የምደባ ደብዳቤውን ቢይዝም የጂኤጂ ደመወዝ ግን ሳይለቀቅ የቆየ በመሆኑና በዚህ መሀል ደግሞ አዲስ መዋቅር ተሠርቶ ስሙም ተጠሪነቱም በመቀየሩ ቀድሞ የተሠራው ምደባ ተግባራዊ ሊሆን አልቻለም። ሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽንን በዚህ ጉዳይ ላይ ያማከሩ ሲሆን፤ መዋቅር በመሥራት ልዩ ጥቅማ ጥቅሙን በመተው መዋቅር ሠርተው በማቅረብ በጂኤጂው ተጠቃሚ እንዲሆኑ የመፍጥሔ ሃሳብ ቀርቦላቸው እንደነበር ይገልፃሉ።
ነገር ግን በዋና ዳይሬክተሩ ልዩ ስኬሉ ቢፈቀድ ነው የተሻለ የሚሆነው የሚል አቋም በመያዛቸው እየተጠባበቁ እንደሆነ ይናገራሉ። በዚህ ምክንያትም የጂኤጂ ተጠቃሚ ሊሆኑ አለመቻላቸውን ይናገራሉ። ጂኤጂው አዲስ መዋቅር የሚፈልግ በመሆኑ መዋቅር ከተሠራ በኋላ ሲቪል ሠርቪስ ኮሚሽን ተሰጥቶት ካፀደቀ በኋላ ነው ተጠቃሚ ሊሆኑ የሚችሉት። በዚህም ሁለቱም ሳይሳካ መሀል ላይ እንደቀሩ ይናገራሉ።
የደመወዝ ልዩነቱን በተመለከተ ምንም ማድረግ አይቻልም የሚሉት ወይዘሮ ገነት፤ ከኢንሳ የመጡት ሠራተኞች በአዋጅ ይዘውት የመጡት በመሆኑ ደመወዛቸው አይነካም። ነገር ግን ይኸኛውን ከፍ ማድረግ ተገቢ ነበር። ነገር ግን ግልጽ የተቋቋመ ኮሚቴ ባለመኖሩ የሚደርሳቸው መረጃም ተባራሪ ከመሆን የዘለለ ባለመሆኑ ልዩ ስኬል (ጣርያ) ጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት እንዳልፈቀደ መስማታቸውን ይገልፃሉ። ልዩ ስኬል ካልተፈቀደ በጂኤጂ ተጠቃሚ እንዲሆን መዋቅሩ ተሠርቶ ለሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን እንዲቀርብ ሃሳብ ማቅረባቸውን ይናገራሉ። ነገር ግን ልዩ ስኬል መጠበቅ እንዳለባቸው አቋም መያዙን ይናገራሉ።
ኮሚሽኑ
በጉዳዩ ላይ የሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽንን አነጋግረን ባገኘነው ምላሽ፤ ጉዳዩ ከኮሚሽኑ አልፎ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የሚታይ ሳይሆን እንዳልቀረ ተገልፆልናል። በሌላ በኩል ኮሚሽኑ የሚያስተዳድራቸውን ተቋማት ግን መብታቸው፣ ግዴታቸውና አደረጃጀታቸውን እያፀደቀ ይሰራል። ነገር ግን ለቅሬታዎቹ ተገቢውን ምላሽና መፍትሔ ለመስጠት ሠራተኞቹን አግባብቶ ማሰራት ተገቢ በመሆኑ በጉዳዩ ላይ መወያየት አስፈላጊ ነው። ለዚህም ደግሞ በጉዳዩ ላይ የተቋሙ የበላይ ኃላፊ ምላሽ መስጠት ይኖርባቸዋል በሚል ተነግሮናል። እኛም ይህንኑ ተከትለን ዋና ዳይሬክተሩን ለማነጋገር ጥረት አድርገናል።
የተቋሙ ዋና ዳይሬክተር
የተቋሙ ሠራተኞች ከደመወዝ ባሻገር በእኩል ዓይን ያለመታየት ብሎም ቅሬታቸው ሰሚ ማጣቱን ያቀርባሉና በእነዚህ ቅሬታዎች ላይ ዋና ዳይሬክተሩ ምላሽ እንዲሰጡን ሙከራ አድርገናል። ኃላፊውን በጉዳዩ ላይ ለማነጋገር በአካል በቢሯቸው ብንገኝም ልናገኛቸው ግን አልቻልንም። ባደረግነው ተከታታይ ሙከራ ቀነ ቀጠሮ እንዲያዝልን አድርገን የነበረ ቢሆንም፤ ምንም ዓይነት ምላሽ ግን ሊሰጡን አልቻሉም። ስለ ሁኔታው በሥልክ ደውለን ስናነጋግራቸው መጀመሪያ መረጃ ሊሰጡን ፈቃደኛ ከሆኑ በኋላ ዳግም በሰጡን ምላሽ ግን ቅሬታው ተገቢነት የጎደለው ሲሉ ተችተው፤ የመመለስ ግዴታ እንዳሌለባቸው ገልፀውልናል።
አዲስ ዘመን ጥቅምት26/2012
ፍዮሪ ተወልደ