ተደጋግሞ በሚተረክ አንድ ስዕላዊ ይዘት ባለው አጭር ታሪክ ልንደርደር፡፡ በርከት ያለ ቁጥር ያላቸው ሰዎች አንድ ትልቅ ግንድ በትከሻቸው ላይ ተሸክመው ወደሆነ ቦታ እንዲያደርሱ ተልዕኰ ይሰጣቸዋል፡፡ ሁሉም የቡድኑ አባላት በተቀራረበ ርቀት ያንን ፈታኝ ግንድ በትከሻቸው ላይ ተሸክመው ላባቸው ጠብ እያለ ጉዞው ይጀመራል፡፡ ጥቂት እንደተጓዙ በጓደኞቹ መሃል ላይ የተሰለፈው አንዱ ተሸካሚ እንጣጥ ብሎ ግንዱ ላይ በመውጣት ተደላድሎ ተቀመጠ፡፡ አላዩትም፡፡
ይሄን ጊዜ ሸክሙ ግንድ ብቻ መሆኑ ቀርቶ አንድ ሰው ተጨመረበት ማለት ነው፡፡ ተሸካሚዎቹ ጥቂት ምዕራፍ እንደተጓዙ ሌላው ሰው ሸክሙን ከትከሻው ላይ አውርዶ በሁለት እጆቹ ግንዱ ላይ በመንጠልጠል ራሱን ከሸክሙ ነፃ አድርጎ ሌሎቹ ጓደኞቹ በሸክሙ ጫና ላባቸው እየተንቆረቆረ ሲቃትቱ እርሱ ግን መዝናናቱን ቀጠለ። አይተው እንዳላዩ ሆኑ፡፡ ሦስተኛውም ሰው እንዲሁ ቀስ ብሎ ሸክሙን ከትከሻው ላይ አውርዶ ግንዱን በእጁ የደገፈ በማስመሰል ሙሉው ሸክም ኋላና ፊት ባሉት ተሸካሚዎች ላይ ብቻ እንዲያርፍ እያሾፈ በጓደኞቹ ስቃይ ይዝናና ጀመር፡፡ ከንፈራቸውን እየመጠጡ ጉዟቸውን ቀጠሉ፡፡ ሌሎችም እንዲሁ ቀስ በቀስ ሸክማቸውን ሁለቱ ምስኪን ተሸካሚዎች ትከሻ ላይ በማሳረፍ ራሳቸውን ከሸክሙ ነፃ በማድረግ በሌሎች ስቃይ መዝናናቱን ቀጠሉ፡፡
የዛሬዋ ሀገሬ አንዳንድ ወቅታዊ ጉዳይ ከዚህ ገላጭ ስዕል ጋር የሚቀራረብ ይመስለኛል፡፡ በዚህቺ አሳረኛ እናት ዓለም መድረክ ላይ የሚተወኑት የዋዘኞች ኮሜዲያዊ ክስተቶችና ትራዤዲያዊ ተውኔቶች ግማሽ እንባ፣ ግማሽ ሣቅ የተቀላቀለባቸውን ስሜቶች እያስተናገዱ እንዳለ ማስተዋል ከጀመርን ሰነባብተናል፡፡
ከአሁን ቀደም የወተወትኩባቸውንና የቆዘምኩ ባቸውን አንዳንድ ጽሑፎቼን መላልሼ ሳነብ አንዳንዱ እውነታ ለኃላፊው ወቅት ብቻ ሳይሆን የዛሬውንም አሳራችንን ቁልጭ አድርጎ ስለሚያሳይ ጥቂት ሃሳቦችን እየተዋስኩ አመነዥካለሁ፡፡ ለመከራ የጣፈው ቢነግድ አይተርፈው እንዲሉ፡፡ ሀገሬ በለውጥና በነውጥ ማዕበል ሳትንገላታና ሳትላጋ የኖረችባቸውን የተረጋጉ ዘመናትንና ዓመታትን እንዲጠቁሙን የታሪክ መዛግብትንና የዕድሜ ባለጠጎችን ብናማክር ወደ የትኛው የታሪካችንና የዘመናችን አቅጣጫ እንደሚጠቁሙን ለመገመት በእጅጉ ያዳግት ይመስለኛል፡፡
ብዙ የአውሮፓ ሀገራት ወርቀ ዘቦ አልብሰው እንደሚኳሹት ዓይነት «ሰላማዊና ወርቃማ ዘመናችንን» እንዳናደንቅ የታወርን እስኪመስለን ድረስ ግራ እንደተጋባን አለን፡፡ ይህንን የምለው የሀገሬን ታሪክ በሙሉ ለማንኳሰስ ሳይሆን በከበረው ታሪካችን ላይ ዘመን ወለድ ግራ ገቦች እያሳረፉበት ያለውን ጉድፍ ለመጠቆም ብቻ ነው፡፡
ዘመነ አክሱምም ይሁን ዘመነ ላሊበላ ወይንም ምሥራቁ፣ ምዕራቡ፣ ደቡቡና ማዕከላዊው የሀገራችን ክፍሎች ወደ አስመዘገቧቸው ቀደምት ታሪኮች በምልሰት ወደ ኋላ ብናፈገፍግ ሁሉንም ጎራ የሚያስማማ ሀገራዊ «የወርቃማ ዘመን» ምሳሌ ለመጠቆም እንድንቸገር የተዘራው ዘር ዛሬ ጎምርቶ እያየን ነው፡፡ እውነታዎችን በሙሉ እንዳንቀበል አእምሯችንን ዘግተን ያልኖርንበትን ዘመን የምንረግምና «ከሟች ታሪካችን ላይ ሞራ ገፈን የምናነብ» ብጤ ሥነ ልቦና የተላበስን «ሕዝቦች» እንድንሆንም ተፈርዶብናል፡፡ ምክንያቱም አዘውትረን ከምንዘምርላቸው የሥልጣኔዎቻችን ቀለመ ደማቅ ገፆች መካከልም ቢሆን ጥቋቁር ነቁጦችን በመንቀስና ህልው በማድረግ ለፍልሚያ መገባበዙን ስለተካንበት ነው፡፡
የግል የንባብ ፍቅሬና በዘመነ ፍሬሽማን የወሰድኩት የታሪክ ኮርስ ዕውቀቴ ከዚህ መንደርደሪያ በላይ «እንድተርክ» ስለማይፈቅድልኝ ወደ ተነሳሁበት ዓላማዬ ማቅናቱ የተሻለ ይመስለኛል፡፡ የትኛውም ሀገር ቢሆን ያለ መራር ነውጥ ለውጥ አላመጣም፡፡ ነውጥና ለውጥ በመንትያ የባህርይ ተመሳስሎ አንዱ የአንዱ ገፊ ምክንያት ሆኖ ዘመን መሻገሩን በብዙ ማስረጃ መፈተኑ አይከብድም። ለውጥ እና ነውጥ እንደ ነፍስና ሥጋ የተዋሃዱ መሆናቸው እውነት ቢሆንም በታሪካችን ያስተናገድናቸው የእኛዎቹ በርካታ ነውጠኛ የለውጥ ሱናሚዎች ግን በየዘመናቱ አውዳሚ ወጀቦችና ማዕበሎችን በማስነሳት እንደምን ሲያተራምሱን እንደኖሩ ምስክር መፈለግ አያሻውም። ለእንቆቅልሼ ጥያቄ «ምን አውቅልህ» ባይ መላሽ አገኝ እንደሆን በማለትም እነሆ ውሉ ጠፍቶብን እየተወሳሰበ ግራ ባጋባን በሀገሬ ወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ለመቆዘም ይህንን ርዕስ መርጫለሁ፡፡
ካቻምና ትምህርት አልሰጥ ብሎን፣ የአምናውን ልምድም ማስታወስ ተስኖን፣ የዘንድሮንም ክስተቶች እንደዘበት እያለፍናቸው ሀገሬ ነጋ ጠባ የመልህቋ ገመድ እንደተበጠሰባት ጀልባ በሁሉም የሕይወታችን ዐውዶች በአውሎ ነፋሶች ስትንገላታ ማየት በእጅጉ ቅስምንም ልብንም ይሰብራል፡፡ «ዐይታው በማታውቀው ዓለም አቀፋዊ እውቅናና ማዕረግ ከፍ ለማለት እየደመቀች ቢሆንም» የዛሬይቱ ኢትዮጵያ ዝንጉርጉር መልክ ግን መነሻቸው በተወሳሰበ የበረቱ ወጀቦች ዕለት በዕለት ሲናወጥ ማየቱ የዘወትር ምሳ እራታችን ከሆነም ሰነባብቷል፡፡
የሰላማዊ ምህዳር አየር ሽታ እየናፈቀንም በየቤታችን እንደየእምነታችን ቀኖና በክራሊያሶ አራራይ ዜማ ወደፈጣሪ ለመቃተት ተገደናል፡፡ የሚያሳዝነውና ለሰሚው ግራ የሆነው የጓዳችን ብሔራዊ ገበናም ከእኛ «ትልልቅ» ተብዬዎች አልፎ ተርፎ ነፍስ ወዳላወቁት እንቦቀቅላ ሕፃናቶቻችን ሳይቀር መዛመቱም ገበናችንን ይበልጥ እያመሳጠረው «ወየው ለነገ ትውልዳችን» እያልን እንባችንን እንድናንዠቀዥቅ ሰበብ ሆኖናል፡፡
የእናቶች እንባ፣ የአባቶች ሰቀቀን፣ የሕፃናቶቻችን መበርገግ፣ የሃይማኖት መሪዎች እዮታ የምድራችንን አየር በክሎ በልባችን ውስጥ የተራራ ሸክም ካሸከመን ውሎ አድሯል፡፡ እነዚያ በመንደርደሪያዬ ላይ የጠቀስኳቸው ግንዲላ ተሸካሚዎች ወቅታችንን በአግባቡ ይገልጻሉ ያልኩትም ስለዚሁ ነው፡፡ አንዳንዶች ከፊት ለፊታችን ተገሽሮ አላላውስ ያለንን የመከራ ሸክም ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ተረባርበው ሊያስወግዱ ሌት ተቀን እየቃተቱ ሲንገዳገዱ አንዳንዶች ደግሞ የመከራውን ጫና ለማክበድ ተግተው ሸክም በመሆን ሲሰሩ ይስተዋላል። ሸክሙን ለመሸከም ባይፈቅዱም ተሸካሚዎቹ በተሸከሙት ሸክም ላይ ፊጥ በማለት የተሸካሚዎቹን አናት እየወገሩ ለስቃይ ይዳርጓቸዋል። ሸክም ብቻ ቢሆኑማ ደግ፤ ችግሩ የክፋታቸው ልክ በስጋ ክብደት ብቻ ሳይሆን በውስጣቸው የታጀለው መርዘኛ ሃሳባቸው በራሱ ከሸክማቸው ገዝፎ ማስማጡ ላይ ነው፡፡
እነዚህን መሰል የትውልድ እዳዎች ቅዱስ መጽሐፍ «የበግ ለምድ የለበሱ ተኩላዎች» ናቸው ይላቸዋል፡፡ ከእሾህ ወይን ከኩርንችትም በለስ አይለቀምም እያለም ይገልጻቸዋል፡፡ መልካም ዛፍ ክፉ ፍሬ ማፍራት፣ ወይንም ክፉ ዛፍ መልካም ፍሬ ማፍራት አይችልም በማለትም ባህሪያቸውን በሚገባ ያስተዋውቃል፡፡ እነርሱ በጣታቸው ለመሸከም የማይፈቅዱትን ሸክም ሌሎችን ያሸክማሉ እያለም እኩይ ተግባራቸውን ያመላክተናል፡፡
የሀገራችንን ለውጥና ነውጥ እያባባሰ ያለው የፖለቲካ ቡድኖችና ቡድንተኞች ሱናሚ የዘመናችን ልዩ ክስተት ከሆነ ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ የማይስማሙ ፖለቲከኞቻችን «ጨዋታ ፈረሰ ዳቦ ተቆረሰ» እየተባባሉ የሕፃናት ልጆቻችንን ጨዋታ ከነጠቋቸውም ሰነባብቷል። በእያንዳንዱ የፖለቲካ ጓዳ ውስጥ ትልቋን ኢትዮጵያንና የተከበሩ ብሔረሰቦቿን በልዩነታቸው ኅብር አቀራርቦ ከማስዋብ ይልቅ ልዩነታቸውን በማጉላት ብቻ በጎጠኝነት ሰበካ ላይ እየባዘኑ እንዳሉም እያስተዋልን ነው፡፡ ፖለቲከኞቻችን ለውጣቸው በነውጥ፣ ኅብረታቸው በእኸኝነትና በእኔ አውቃለሁ ባይነት ብቻ ሲፈረካከስም እያስተዋልን ነው፡፡ የራስን ዝናና ጥቅም ካማከለ አስተሳሰብ መቼ እንደሚላቀቁ አዋቂው ራሱ እግዜሩ ብቻ ነው፡፡
የሰሞኑ መከራችን ግን በአጭሩ ካልተቀጨ በስተቀር ከትውልድ ትውልድ ተቀጣጥሎ እየፈነዳ የሚሸጋገር ድማሚት እንዳይፀንስብን ስጋታችን ከፍ ያለ ነው፡፡ እስከዛሬ የፋፋው ሽልም በውርጃ እስካልመከነ ድረስ ጦሱ እንዲህ በቀላሉ የሚታሰብ አይመስለኝም፡፡
ይህን ያህል ሰው ሞተ ወይንም ተጎዳ፡፡ ይህን ያህል ንብረት ወደመ ወይንም ሺህ በሺህ ዜጎች ተፈናቀሉ የሚለው ዜናስ «የፕራይም ታይም» ወሬዎቻችን ርዕሰ ጉዳይ ሆኖ እስከ መቼ ይዘለቃል፡፡
መቼም ደጋግመን እንደወተወትነው ብሔራዊ መግባባትም ይባል ብሔራዊ ዕርቅ ማስፈን እስካልተሞከረ ድረስ የሀገራችን ዘርፈ ብዙ ነውጥ ይገታል ብሎ ለማመን ይከብዳል፡፡ የሃይማኖት ቤተሰቦች፣ ወጣቶች፣ እናቶች፣ ፖለቲከኞች፣ የሀገሪቱ አዛውንቶችና ምሁራን ዐውዳቸው በሚፈቅደው ልክ በሀገራዊ መግባባት ላይ በጋራ ሥራዬ ብለው መንቀሳቀስ እስካልቻሉ ድረስ አንዱ ሲሰፋ አንዱ እየቀደደ፣ አንዱ ሲጠግን አንዱ እየሸነቆረ ሀገር ሀገር አትሆንም፡፡ በውጥር የተያዝንበት ሀገራዊ ችግርም ፋታ ሊሰጠን ስለመቻሉ እርግጠኛ መሆን አይቻልም፡፡
ኡኡታ የበዛበት የፌዴራሊዝም ሥርዓታችን መዋቅር ቢፈተሽ፣ የልማታዊ ዴሞክራሲያዊ ፍልስፍናችን ቢገመገም፣ የክልል ሽንሻኖ ልምዳችን ለውይይት ቢቀርብ ምፅዓትን የቀረበ በማስመሰል ማንባረቅ ለማን ይጠቅማል። የተሻለ መስሎ ከታየን በአሸናፊነት እልል ብለን እናስቀጥለዋለን። ህፀፅ ካለበትም ይታረማል። ያለበለዚያ ግን የሚቀጥለውን ከማስቀጠል፣ የሚለወጠውን ከመለወጥ፣ የሚታረመውን ከማረም፣ የሚሻሻለውን ከማሻሻል ይልቅ አንዳች የተለየ ሃሳብ በተነሳ ቁጥር የራስ ወገንን ዝመት ተዋጋ እያሉ ማቅራራት ምን ይረባል፡፡
በችግሮች ሥርና መሠረት ላይ በሚገባ ተወያይቶና የበቀልን መንፈስ አርቆ መነጋገር ጀግንነት እንጂ የተሸናፊነት ምልክት አይደለም፡፡ እጅግ የሚያስገርመውና የሀገሬን እንቆቅልሽ ካመሳጠሩት መሪ ጉዳዮች መካከል ተቀዳሚ ተጠቃሹ «በድል አጥቢያ ጀግንነት» ላይ ያነጣጠረው የእኔ እበልጣለሁ ጉዳይ እንደሆነ ከገባን ሰንብቷል፡፡ ሲሞቅ በማንኪያ፤ ሲቀዘቅዝ በእጅ መጉረስ የለመዱ ምንዱባን ድርጊትም ህመም ሆኖብናል፡፡
የዝናቡ ወራት ሲያባራ ብቅ እንደምትለው እንደ መስቀል አበባ በሀገር ላይ መከራ ሲዘንብ በደጋጎች ሀገር ተሸሽገው፤ ብራማ ቀን ሲወጣላቸው ጠብቀው እንደ «አደይ» ምድሩን ካላፈካን እያሉ ለሚጨፍሩት «የድል አጥቢያ አርበኞች» መፍትሔ ቀድሞ ባለመሰጠቱ እነሆ እኛ ዜጎች ለመከራ፤ መሪዎች ደግሞ ለመሳቀቅ ሊዳረጉ ግድ ሆኗል፡፡
የድምጻቸውን ጉልህነት፣ የረብጣ ገንዘባቸውን እብጠት፣ የሸንጋይ ምላሳቸውን መርቀቅ፣ የከበባቸውን ጀማ ብዛት፣ የቴክኖሎጂውን ፍጥነት እየተጠቀሙ ሀገር የሚያምሱት «የክፋት ጀግኖች!» ሃይ ባይ በማጣታቸው ለእኛ ተራ ዜጎች መርዶ፣ ለእነርሱ ግን እልልታ እየሆነ እንደምን በአንድ ሀገር መኖር እንደሚቻል እንቆቅልሻችንን አመሳጥሮብናል፡፡
እነርሱ አንደኛ፤ አሳረኛው ሕዝብ ኋላ። ተንደላቃቂዎቹ እነርሱ፤ ርሃብተኛው ወገን ሌላ። ተሞጋሾቹ እነርሱ፤ ዳፋ ቀማሹ ሕዝብ፡፡ ኧረ ጎበዝ እየተያየን፡፡ እነርሱ ለምድር ለሰማይ በከበደ ቤት ውስጥ «ነፍሴ ሆይ ደስ ይበልሽ!» እያሉ ሲቀማጠሉ በድሃ ጎጆ የድሃ ልጅ አስከሬን ተዘርግቶ በእዬዬ ሲለቀስለት፣ የኀዘን ማቅ አውልቃ የማታውቀው የኢትዮጵያ እናት ዛሬም እንደ ትናንቱ የተረፋት መሪር ኀዘን እንጂ ድሎትማ ተረቷ ነው፡፡
ሰሞኑን በሀገሬ አንደኛው ክፍል ለመገኘት ችዬ ነበር። ያ ሰፊ የወገኔ ምድር ኀዘን አጥልቶበት፣ የመከራ ጉም እንዣቦበት ስመለከት ነፍሴም ስጋዬም ያለቀሱት እኩል ነው፡፡ እጅግ የገረመኝ ነገር በዚያ ሰፊ የሀገሬ ክልል ውስጥ የልኳንዳ ቤቶች በሙሉ ለቀናት ተዘግተው ማየቴ ነበር፡፡ ነገሩ ግራ ቢገባኝና በሽሮ ብቻ እንግዶቻቸውን የሚያስተናግዱትን ቤተሰቦችና ሆቴሎችን ምክንያቱን እንዲገልፁልኝ ስጠይቅ የሰጡኝ መልስ በእጅጉ ኀዘኔን አበርትቶታል፡፡
ለካንስ በዚያ ምድር ክርስቲያን ወገኖች በሥጋ ምግቦች ላይ ማዕቀብ በመጣል በፆም በፀሎት ሱባዔ ላይ ነበሩ፡፡ ሙስሊም ወገኖችም የእምነታቸው ቀነኖ በሚፈቅደው መሠረት ከወንድሞቻቸው ጋር ሱባዔውን ተጋርተዋል፡፡ ጠግቦ አይበላም፡፡ በሥጋና በቅቤ ማዕዱ አይሞላም፡፡ ለምን? ለሀገራቸው መከራ፣ ለሕዝባቸው አሳር ፈጣሪ እንዲታረቃቸው እናቶች በእንባ፣ አባቶች በጸሎት፣ ሕፃናት በመንበርከክ ይቃትታሉ፤ ያነባሉ፡፡
በሌላኛው ቤት ጮማ እየተቆረጠ፤ ውስኪ እንደ ውሃ እየተንቆረቆረ ይዶለታል፡፡ ሀገር ስለምትተራመስበት ሁኔታ ሤራ ይጎነጎናል፡፡ ወገን ስለሚተላለቅበት ሁኔታ ዘዴ ይዘየዳል፡፡ እስትራቴጂ ይነደፋል፡፡ በሶሻል ሚዲያ የጦርነቱ ፊሽካ ይነፋል፡፡ የዕለት እንጀራ ላረረበት ወጣት «ተነስ! ዝመት! ተዋጋ!» እየተባለ መመሪያ ይሰጣል፡፡
ሀገሬ ይህቺ ነች፡፡ ወቅታዊ ሁኔታችን ይህንን ይመስላሉ፡፡ ጀንበራችንን ያጠቆረው ደመና ከብዷል። ሕዝብ ግራ ተጋብቷል፡፡ አቅጣጫው ተወሳስቧል። ኢትዮጵያ እያለቀሰች ነው፡፡ ወገኔ ሆይ የሀገርን እንባ የምናብሰው እንደ ክፉዎች የክፋት ዲዲቲ በመነስነስ ሳይሆን ለሰላም ዘብ በመቆም ነው፡፡ የክፉዎችን ሰይፍ የምንሰበረው የሕግ የበላይነትን በማስቀደም በእርጋታ እያስተዋልን ነው፡፡ መከራው በዝቶብናል፡፡ ከመከራው ባሸገር የምትወጣው ደማቅ ፀሐይ ግን የምታጓጓ ነች። ስለዚህ ከክፉዎች ሤራ ጋር ላለመተባበር እምቢዮ ብለን በጋራ ልንቆምና ልንተባበር ይገባል፡፡ ጊዜያዊ መከራችን ቢከብድም ተስፋችን ግን የገዘፈ ነው፡፡ ተባብረን እንቁም። እጅ ለእጅ ተያይዘን የክፉዎችን ሤራ እናክሽፍ። ሰላም ይሁን!!
አዲስ ዘመን ጥቅምት26/2012