ከምርጫ 97 በኋላ ኢትዮጵያ ውስጥ የነበረው አንጻራዊ ሠላም ወደመደፍረስ አመራ፡፡ ሞቅ በረድ ቢልም መንግሥትን በኃይል መቃወም የተጀመረው ምርጫውን ተከትሎ ቀውሶች ከመጡ በኋላ ነው ማለት ይቻላል፡፡ በተደራጀና ባልተደራጀ መልክ ሕዝብ መንግሥት ላይ የእንቢተኝነት ትግል በይፋ የጀመረው ከዚህ ጊዜ በኋላ ነው፡፡ በተለይ ኢህአዴግ እና አጋሮቹ መቶ በመቶ አሸንፈናል ባሉበት የ2007 ሀገር አቀፍ ምርጫ ማግስት ጀምሮ ባሉት ዓመታት ትግሉ በከፍተኛ ደረጃ በመቀጣጠሉ የህወሓት/ኢህአዴግ መንግሥትን ሳይወድ በግድ ለውጥን እንዲቀበል አስገድዷል፡፡
ለውጡንም ተከትሎ ወደሥልጣን የተሳቡት እነ ዶ/ር ዐብይ አሕመድ ወንበሩ ላይ በቆዩበት ያለፉት 19 ወራት የማይናቁ ለውጦችን ማስመዝገብ ቢችሉም የሀገሪቱን ሠላምና መረጋጋት በአስተማማኝ መልኩ መመለስ ግን አልቻሉም፡፡ ዛሬም እዚህም እዚያም በሚነሱ ግጭቶችና ጥቃቶች ወገኖቻችን ለሞት፣ ለመፈናቀል እና ለንብረት ውድመት አደጋዎች መጋለጣቸው ጋብ አላለም፡፡
በተለይ ከጥቅምት 12 ቀን 2012 ዓ.ም ወዲህ በኦሮሚያ አንዳንድ ከተሞች የተፈጠረው አዲስ ቀውስ ጋር ተያይዞ መንግሥት ሕግና ሥርዓትን አክብሮ እንዲያስከብር የሚደረገው አዎንታዊ ጫና ከወትሮው በተለየ መልኩ አድጓል፡፡ ጠ/ሚኒስትር ዐብይ አሕመድም ባለፈው እሁድ በሰጡት መግለጫ «መንግሥት የፖለቲካ እና የዴሞክራሲ ምህዳሩን ለማስፋት በማሰብ ሆደ ሰፊነቱን አብዝቶ ሲያስታምም ከርሟል» ብለዋል።
አያይዘውም ‹‹…መንግሥት ከኃይልና ጉልበት ይልቅም፤ ትምህርት እና ምክክር ይሻላል ብሎ መታገሱን፣ ይህ ትእግሰቱ ግን ፍርሃት፤ ማስታመሙ ድካም፣ የመሰላቸው ካሉ ተሳስተዋል። አንዳንዶች እንዲማሩ ተብሎ ሰፊ ልብ እና ትከሻ ሲሰጣቸው አጋጣሚውን ሳይጠቀሙበት ቀርተው የዜጎች ሕይወት ለአደጋ የሚጋለጥበት ምክንያት ተፈጥሯል›› በማለት መንግሥት የዜጎችን እና የተቋማትን ደህንነት ለመጠበቅ የሀገሪቱ ሕግ ባስቀመጠው መሠረት እንደሚሰራም አስታውቀዋል።
የቅርብ መረጃዎች እንደሚያሳዩትም ኢትዮጵያ በሕግ የበላይነት መለኪያ ከ126 የዓለም ሀገሮች 118ኛ ደረጃ ይዛለች፡፡
በዓለም የፍትሕ ፕሮጀክት በተሠራውና በአሜሪካ ዋሽንግተን ዲሲ ባለፈው ዓመት አጋማሽ ይፋ በተደረገው ጥናት ኢትዮጵያ ከ126 አገሮች 118ኛ ደረጃን መያዟ ታውቋል፡፡
በዓለም የፍትሕ ፕሮጀክት የተሰራው ጥናት ለሕግ ተገዥነትን በዓለም አቀፍ ደረጃ ለመለካት 120 ሺ የቤት ለቤትና የሦስት ሺ 800 ባለሙያዎችን አስተያየት መነሻ በማድረግ የዳሰሳ ጥናት አድርጓል፡፡
ኢትዮጵያ ከሰሃራ በታች ካሉና በጥናቱ ከተካተቱ 30 አገራት 27ኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች። 20 አነስተኛ ገቢ ካላቸው አገራት ደግሞ ኢትዮጵያ 18ኛ ደረጃ ላይ እንደምትገኝ ጥናቱ አመልክቷል፡፡
በዚህ ጥናት መሠረት ከፍተኛ የሕግ የበላይነት ነጥብ በማስመዝገብ ዴንማርክ፣ ኖርዌይና ፊንላንድ ከአንድ እስከ ሦስተኛ ያለውን ደረጃ ይዘዋል፡፡ ኮንጎ፣ ካምቦዲያና ቬኒዝዌላ ደግሞ የመጨረሻዎቹ ሦስቱ ሀገራት ናቸው፡፡
ለመሆኑ ሕግና ሥርዓት ማስከበር ማለት ምን ማለት ነው?
በኢትዮጵያ ሕገመንግሥት የሕግ የበላይነትን የሚገልፀው መንግሥት በሕግ ከተሰጠው ውጪ አልፎ ሥልጣን መጠቀም እንደሌለበት፣ ሕግ ለሁሉም እኩል ተፈፃሚ መሆን እንዳለበት፣ ዜጎች በሕግ ፊት እኩል መሆናቸው፣ በሕግ በእርግጠኝነት ውጤቱም ተገማች እንዲሆን ነው። በአጭሩ ሀገሪቱ በየደረጃው ያወጣችው ሕግና ሥርዓት ለዜጎች በእኩል ደረጃ ተፈጻሚ መሆናቸውን የማረጋገጥ ጉዳይ ነው፡፡
የሕግ የበላይነት በለውጡ ውስጥ ምን ትርጉም አለው?
በለውጥ ሂደት ላይ እንገኛለን፡፡ በፖለቲካው፤ በኢኮኖሚው፤ በማህበራዊውና በባህላዊው ሕይወት ዘርፎች በመንግሥት ብዙ ነገር ታቅዶ እየተፈጸመ፤ የሚታይ የሚጨበጥ ለውጥም እያስከተለ ይገኛል፡፡ በፖለቲካው ዘርፍ የሕግ የበላይነት ለማስፈን በመጣር የዜጎች ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች እንዲረጋገጡ መንግሥት ረዥም ርቀት ተጉዞ በርካታ ማሻሻያዎችን አድርጓል፡፡ የመዋቅር፤ የአሠራርና የውንብድና ችግር የነበረበትን እና በከፍተኛ ቀውስ ላይ የሚገኘውን የአገሪቱን ምጣኔ ሀብት ከፓርቲና ከመንግሥት ሹመኞች መጫወቻነት በማላቀቅ በፍትሓዊና በሳይንሳዊ መንገድ ለማቃናት ቀን ከሌሊት መንግሥት እየጣረ ይገኛል፡፡
አብሮ በጋራ በመኖር አንድ የፖለቲካ ኢኮኖሚ ማህበረሰብ ለመመስረት ጠንቅ የነበረውና ለሚሊዮኖች መፈናቀል ሰበብ ሆኖ የከረመውን የጥላቻና የመጠፋፋት ግንብን በማፍረስ መንግሥት የትርክት (Narrative) ማቃናትን እና ተግባራዊ እርምጃዎችንም ወስዷል። እናም ለውጡ ሰፊና ጥልቅ ውጤት ያለው በመሆኑ ያለጥርጥር ታሪካዊ ነው፡፡ ኢትዮጵያ የታሪክ አገር ለመሆኗ ምናልባትም ይህ ለውጥ የቅርብ ጊዜ ምስክር ነው ብሎ መውሰድም ይቻላል፡፡ በኢትዮጵያ ረዥምና ደማቅ የማህበረሰቦች እና የአገረ-መንግሥትነት ታሪክ ውስጥ እንዲህ እንዳሁኑ በርካታ የታሪክ ምዕራፎች ተከፍተው ተዘግተዋል፤ አሊያም ተጀምረው እንዲሁ ሳይቋጩ እስካሁን ቀጥለዋል፡፡
ኢትዮጵያ ያሳለፈቻቸው የታሪክ ምዕራፎች ሁሉ በስፋትና በጥልቀታቸው ከምንም በላይ ደግሞ የበርካታ ዜጎች ሁለንተናዊ ሕይወት ላይ አዎንታዊና አሉታዊ ተጽእኖ በማሳረፋቸው የራሳቸውን ሥፍራ እንደሚይዙ የታወቀ ጉዳይ ነው፡፡ ከዚህ አንጻር የተያያዝነው ይህ ለውጥ በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ስላለው ሥፍራ በዚህ ጽሑፍ ሃሳቦችን መሰንዘር የዛሬን መሠረት ለመረዳትና የነገን አቅጣጫ ለማወቅ ይጠቅማል ብሎ መንግሥት ያምናል፡፡ የሩቁን ትተን የቅርብ ዘመን የኢትዮጵያን ታሪክ ስንፈትሽ መሠረታዊ የሆነ ሀቅ ነቅሰን ማውጣት እንችላለን፡፡
ይኸውም ኢትዮጵያ የልዩ ልዩ ሕዝቦች ዕድሜ ጠገብ ሥልጣኔዎች፤ የረቀቁና የመጠቁ ሕዝባዊ ባሕሎች፣ ቅርሶች፣ የአንጸባራቂ ነፃነት እና የማራኪ ተፈጥሮአዊ እና ማሕበራዊ ሀብቶች ባለቤት ሆና እያለ በዚህ ዘመን በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎቿና ሕዝቦቿ በቁሳዊና በመንፈሳዊ ሀብት እጦት የቆረቆዙ፣ የላሸቁና በዚህም ምክንያት የተዋረዱ መሆናቸው ነው፡፡ በታሪክ ሂደት ላይ ዘመናት ያስቆጠሩ ተቋማት ተመሥርተዋል፤ ይሁን እንጂ ዜጎች ለበርካታ አስርት ዓመታት የሚገባቸውን አገልግሎት ሳያገኙ ኖረዋል፡፡
ነፃ ሉዓላዊ አገረ-መንግሥት በተጋድሎ ተከብሮ ተጠብቋል፤ ይሁን እንጂ ዜጎችና ሕዝቦች ለዘመናት በፍትሕ እጦት ተንገላተዋል፣ታስረዋል፣ ተሳደዋል፣ ተገርፈዋል፣ ተገድለዋል፡፡ በኢትዮጵያ ለግምት የሚከብድ የሕዝብ ጉልበትና የተፈጥሮ ሀብት ተከማችቷል፤ ይሁን እንጂ ጠኔ፣ እርዛትና በሽታ ሚሊዮን ዜጎችን እስካሁን በማሰቃየት ላይ ይገኛል። መንፈሳዊና ቁሳዊ ባሕሎችና ቅርሶች በእያንዳንዱ ሕዝብ አጥቢያ ሞልቷል፤ ይሁን እንጂ ፈጠራና ንሸጣ (inspiration) ገና በአስተሳሰብ እስር ቤት ውስጥ ናቸው፡፡ ይህ የታሪካችን ተቃርኖ ነው። ተቃርኖ ብቻ ሳይሆን ተላምደነው ዓይናችን ውስጥ እንደተጋደመ ግንድ የማናየው ተቃርኖ ነው፡፡
ተላምደን የማናየው ተቃርኖ በመሆኑ፤ መፍትሔ የሚሻ ችግር መሆኑንም አልተገነዘብም፤ እናም ከወዲሁ መፍትሔ የሚሻ አሳሳቢ የታሪክ ተቃርኖ ነው፡፡ የተጀመረው ለውጥ በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ይህን ታሪካዊ ተቃርኖ እልባት ለመስጠት የሚጥር በመሆኑ የሚይዘው ሥፍራ በቀላሉ የሚታይ አይደለም፡፡ ከዘመናዊ የፖለቲካ ታሪካችን እንጀምር:: የዘመናዊነት ጽንሰ ሀሳብ አካዳሚያዊ ሙግት ያለበት እንደሆነ ሳይዘነጋ፤ ኢትዮጵያ በታሪኳ የቅኝ አገዛዝ የጭቆና እንቅስቃሴን የገታችና ነፃ ሉዓላዊ አገረ-መንግሥትነቷን በሕዝቦቿ መስዋዕትነት ያስከበረች ብቸኛዋ የጥቁር ዓለም ፈርጥ ስለመሆኗ ብዙ ብዙ የተባለለት ጉዳይ ነው።
ከዚህ የነፃ አገረ-መንግሥትነት ታሪኳ ጋር በተያያዘም አገር በቀልም ይሁን አዳዲስ የፖለቲካ ተቋማትን የመመስረትና የማስፋፋት ታሪኳም በቀላሉ የሚታይ አይደለም፡፡ በእያንዳንዱ ማህበረሰብ ውስጥ ለዘመናት የዳበሩትን አገር በቀል የፖለቲካ ተቋማትን ሳንዘነጋ፤ በኢትዮጵያ ዘመናዊ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች በአዲስ መልክ ከተመሰረተ እንኳን ከአንድ ክፍለ ዘመን በላይ ታሪክ ተመዝግቧል፡፡
ለምሳሌ የፍርድ ሚኒስቴር! በዝነኛው የ1888ቱ የአድዋ ድል የተጎናጸፍነው ነፃ መንግሥትነትም ይሁን በ1900 ዓ.ም. የተመሰረቱት ዘመናዊ የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች በዚህ ሁሉ ዘመን ውስጥ በተለይ ለሕዝቦችና ለዜጎች ዴሞክራሲያዊና ፍትሐዊ ጥያቄዎችን በማስተናገድ ረገድ እስካሁን ያበረከቱት ሰብዓዊና ቁሳዊ አስተዋጽኦ የሚያስመካ እንዳልሆነ በሕይወታችን የተመለከትነው ነው፡፡ በአድዋ ድል ነፃ መንግሥትነታችን ተረጋግጧል ብንልም፤ እንደፍርድ ሚኒስቴር ያሉ ዘመናዊ ተቋማት በአፍሪካ ቀድመን አቋቁመናል ብለን ብንኩራራም በተከታታይ መንግሥታት አገዛዝ ዘመን ለአብነት ያህል በማዕከላዊ እስር ቤትና በየድብቅ እስር ቤቶች ዜጎች ሰብዓዊነታቸው ተገፏል፡፡
የተጀመረው የለውጥ ሂደት በአንድ በኩል የሉዓላዊነትና የዕድሜ ጠገብ ተቋማት ባለቤትነትን፤ በሌላ በኩል ደግሞ «የአባይን ልጅ ውሃ ጠማው» የሚያሰኙ የፍትሕ እጦቶች በመኖራቸው የሚታየውን ተቃርኖ እልባት ለመስጠት የሚጥር በመሆኑ በታሪክ ውስጥ የሚኖረው ሥፍራ ከፍ ያለ ነው ብሎ መንግሥት ያምናል፡፡ የለውጡን ትርጉም በኢኮኖሚ ታሪካችን አውድ ውስጥ እንመልከተው፡፡
አሁንም ክፍለ ዘመናትን ያስቆጠረውን በመካከለኛው ምሥራቅና በሜዲትራኒያን ዓለም የነበረውን የማምረትና የግብይት ረዥም ታሪካችንን ለዘርፉ አጥኚዎች ትተን፤ የዘመናዊውን ዓለም ልምዳችንን እንመልከት፡፡ እንደ ባቡርና ሌሎች የምድር፤ የባሕርና የአየር መጓጓዣ ዘዴዎች መቀልጠፍን ተከትሎ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ከዓለም አቀፉ ዘመናዊ የኢኮኖሚ ሥርዓት ጋር መተሳሰር ከጀመረበት አንስቶ በተለያዩ ጊዜያት በልዩ ልዩ መልኩ እድገቶችን ቢያስመዘግብም አሁንም የጥገኝነት ደረጃውን አልለቀቀም፡፡ ረዥም ዘመን ያስቆጠረ ነፃ አገረ መንግሥት ባለቤት መሆናችን፤ በአስር ሚሊዮን የሚቆጠር ሕዝብ ጉልበትና ክህሎት መኖሩ፤ ሰፊ መሬትና ልዩ ልዩ የተፈጥሮ ሀብቶች መኖራቸው አሁንም ከኢኮኖሚ ጥገኝነት ሊያስጥለን አልቻለም፡፡
ምንም እንኳን በጥቁሩ ዓለም ነፃ አገር መሆናችንን እኛም ብንለፍፍ፤ ባእዳንም ቢመሰክሩ ሌላው ቀርቶ በዘመናዊው ዓለም ከሞላ ጎደል የምጣኔ ሀብት ዕጣ ፈንታችን በ1930ዎቹ በእንግሊዝ፣ በ1940ዎቹ በአሜሪካ፣ በ1950ዎቹና 60ዎቹ በአሜሪካ፣ በዩጎዝላቪያና በስዊድን፣ በ1980ዎቹ በሶቭየት ሕብረት፣ በቀጣዮቹም ዘመናት በምዕራባውያን በሩቅና ቅርብ ምሥራቅ ወዳጅ አገራት እንዲሁም በኃያላኑ በሚመሩ የልማት አጋር በሆኑ ልዩ ልዩ ዓለም አቀፍ ተቋማትና የፋይናንስ ደጀንነት እንዲያም ሲል መቋሚያነት እየተንገዳገደ የቆመ፤ ግን እስካሁን ድረስ የአገር ውስጥ ዋስተጠሪ ኖሮት መጽናት ያልቻለ እንደሆነ የአደባባይ ምስጢር ነው፡፡
በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንዲሉ በእንቅብ መጠን አምርተን የጎተራ ያህል መብላትና ማባከናችን ዕዳና ቀውስ ውስጥም ጨምሮናል፡፡ ለሥራ አጥነት፤ ለዋጋ ንረት፤ ለኑሮ ውድነት፤ ከምንም በላይ ደግሞ ለሕዝብ ሀብት ዘረፋ ምላሽ ለመስጠት በአዲሱ አመራር ቁርጠኝነትና እልህ የተጀመረው የለውጥ ሂደት ትናንትም ዛሬም በጥገኝነት ለተሸበበው ቁሳዊ የኢኮኖሚ ታሪካችን ተቃርኖ እልባት ይሰጣል ተብሎ ታምኖበታል፡፡ እናም የሚይዘው ታሪካዊ ሥፍራ ከፍ ያለ ነው ብሎ መንግሥት ያምናል፡፡
የተጀመረውን ለውጥ በማሕበራዊና ባሕላዊ ታሪካችን አውድ ውስጥ ስንቃኘው ከሁሉ ከሁሉ ዕድሜ ጠገብ የቁሳዊና መንፈሳዊ ሥልጣኔ ባለቤት መሆናችን፤ የማያቋርጥ የሕዝብ ከቦታ ቦታ የመነቃነቅ፤ የግላዊና የወል ፍልሰት፤ ሰላማዊ የዝምድናና የትስስር ሕይወታችን ጎልቶ ይታያል፡፡ የምንገኝበት የዓለም ክፍል ለዚህ ያበረከተው አስተዋጽኦ በቀላሉ የሚታይ አይደለም፡፡ ቀጣናውን ልብ ብለን ካስተዋልነው፤ የጥቁር አፍሪካ፤ የአረብና የሜዲትራኒያን ዓለም፤ የነዚህ የሦስቱ ሥልጣኔና ባሕል መቀነት እንደቀስተደመና ዞሮ የሚያልፍበት ሥፍራ ነው።
እናም እንደመናኸሪያነቱ አንጸባራቂ የሕዝቦች ሰላማዊ ትስስር ታሪክ ሲያስተናግድ ኖሯል፡፡ በርግጥ እንደማንኛውም ማሕበራዊና ባህላዊ ክስተት አልፎ አልፎ ቁርሾና መቋሰል ያስከተሉ ልሂቃዊና ሕዝባዊ ግንኙነቶች እንደነበሩ አይካድም:: ይሁን እንጂ የማህበራዊና ባሕላዊ መሥተጋብር ታሪካችን ቁልጭ አድርጎ የሚያሳየው ቤተሰባዊ ስሜት ላይ የተመሰረተ መስተንግዶን፤ የባህል መወራረስንና ለፈጠራና ለአጎራባች ሀሳብና የኑሮ ዘይቤ ክፍት መሆንን ነው፡፡ በየገጠሩ ያለውን ይህን የታሪክ ገጽታና መልክ ሳንዘነጋ፤ በኢትዮጵያ ነባርና አዳዲስ ከተሞች ውስጥ ለዘመናት የቆየው የቅይጥነት፤ የተወራራሽነትና የመከባበር ታሪክ አደጋ ላይ ወድቆ ዛሬ በተቃራኒው ባይተዋርነትን የተንተራሰ የማሳደድና የደመኝነት አዝማሚያ ተስፋፍቷል፡፡
«ከክልሌ፣ ከዞኔ፣ ከወረዳዬ፣ ከቀበሌዬ ውጡ!» የሚለው አቋምና ድርጊት የአንድ መንደር ነዋሪዎችን በታሪክ የተፈተነ ጥበብ የሞላበት የሰላም ልምድ ይቅርና በሺህ የሚቆጠሩ ዓመታት ያስቆጠረውን የሦስቱን ዓለማት (የጥቁር አፍሪካ፤ የአረብና የሜዲትራኒያን) የመናኸሪያነት ታሪክን የሚጻረርና ትውፊቱንም የሚያፈርስ ነው፡፡ የጀመርነው ለውጥ በመደመር ፍልስፍና ለዚህ ታሪካዊ ተቃርኖ መልስ በመስጠት ሂደት ላይ ስለሚገኝ በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ የሚኖረው ሥፍራ በቀላሉ የሚታይ አይሆንም፡፡
ለማጠቃለል መንግሥትና ሕዝብ የጀመሩት ለውጥ በጥቁሩ ዓለም ውስጥ የተጎናጸፍነውን የነፃነት ካባ ከዜጎችና ከሕዝቦች ፍትህ ማጣት ጋር ያለውን ተቃርኖ እልባት በመስጠት አገራዊ አርነታችን በየፍርድ ቤቶችና በየአገልግሎት መስጫ መስሪያ ቤቶች ትርጉም እንዲኖረው የምንታገልበት በመሆኑ ታሪካዊ ሥፍራው የላቀ ነው ብሎ መንግሥት ያምናል፡፡
እንደመውጫ
ዕውቁ ደራሲ ሰለሞን ደሬሳ «አንዳንድ ጥያቄ አለ፣ አሥር ጊዜ ተጠይቆ፣ አሥር ጊዜ ተመልሶ፣ እንደገና አሥር ጊዜ የሚጠየቅ» እንዳለው የሕግ የበላይነት ይከበር ጥያቄም በሁሉም ወገኖች ዘንድ ተደጋግሞ ይነሳል፡፡ የሕግ የበላይነት ይከበር ሲባል በአጭር አነጋገር «ፍትሕ ይስፈን፣ በሕግና ሥርዓት እንዳኝ፣ ሥርዓት አልበኝነት ይቁም» ማለታችን ነው። ምንም እንኳን የሕግና ሥርዓት ይከበር ጥያቄ ዛሬ የተነሳ ባይሆንም በተለይ ሰሞኑን ከ86 በላይ ሠላማዊ ዜጎቻችንን ከነጠቀን አሰቃቂ ክስተት ጋር ተያይዞ ጥያቄው ጎላ ብሎ መሰማት ጀምሯል፡፡ መንግሥትም ኃላፊነቱን ለመወጣት ቃል ከመግባት አልፎ ዜጎችም እንዲደግፉት ጥሪ አቅርቧል፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብም ከምንጊዜው በላይ መንግሥት የገባውን ቃል በተግባር ለማየትና ሠላሙን መልሶ ለማግኘት ጓጉቷል፡፡
(ማጣቀሻዎች፡- ኢትዮጵያ አዲሲቷ የተስፋ አድማስ፡- በጠ/ሚ ቢሮ የተዘጋጀ የውይይት መድረክ ላይ የቀረበ ጥናት፣ አዲስ ዘመን ጋዜጣ፣ የተለያዩ ድረገጾች…)
አዲስ ዘመን ጥቅምት26/2012