አዲስ አበባ በጉብዝና ዘመኗ በልምላሜ ከብራ የሚያልፍባትን ሁሉ በውበቷ ታስደምም ነበር።አዲስ አበቤም በየደረሰበት ኮለል ካለ ምንጭ ይጎነጭ ነበር።እዚህም እዚያም በሚንፎለፎለው ፍል ውሃ ይጠመቅ ነበር።አሁን ግን ይህ የአዲስ አበባ ዝና ሽግግር ላይ ነው፤ ተረት ለመሆን።ዛሬ የከተማው ሰው «ምንጭ ምንድን ነው?» ተብሎ ቢጠየቅ «ገቢ ማግኛ» ብሎ የሚመልስ ይመስለኛል።
እዚች ጋር አንዲት ቀልድ ትዝ አለችኝ።ሕንፃና ኮብልስቶን ሳንዱች አድርገው እያስጨነቋት በእግሯ ሳይሆን በዓይኗ ቦርቃ ያደገች አንዲት አዲስ አበቤ ሕፃን በመምህርቷ አንድ ጥያቄ ቀረበላት።«ወተት ከምን ይገኛል?» ልጅት በየቀኑ ሲታለብ ታይ ነበርና አሳምራ የምታውቀውን ነገር በመጠየቋ ደስ እያላት «ከፍሪጅ ነዋ!» ብላ እርፍ።
ምን ታድርግ … አይደለም ላሞች ልጆች የሚቦርቁበት መስክ ማግኘት ህልም ነው። በተገኘው ክፍት ቦታ ላይ ሁሉ ሕንፃና ኮብልስቶን ሆኗል የሚተከለው።ችግኝ እንደሆነ በዘመቻ ነው የሚተከለው።ሊያውም ተፈልጎ በሚገኝ ተራራና የመንገድ አካፋይ ላይ።ተራራው ላይ የሚተከልበት ምክንያት አፈር እንዳይሸረሸር ለመከላከል ሲሆን፤ የመንገድ አካፋዩ ደግሞ ለውበት ነው። ሙቅ ለጉንፋን፤ እግረ መንገድ ለሆድ በሚል ካላሰላነው በስተቀር እንደሚለፈፈው የካርበን ልቀትንና ምንትስን አስመልክቶ አይደለም።
እንዲያውም ከሰሞኑ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከ20 ሺህ በላይ የጋራ መኖሪያ ቤቶችን ለመገንባት የመሠረት ድንጋይ ካስቀመጠባቸው ቦታዎች አንዱ በሐምሌ ወር በመላ አገሪቱ በተከናወነው የችግኝ መትከል ዘመቻ በርካታ ችግኞች የተተከሉበት ቦሌ አየር ማረፊያ አጠገብ የሚገኝ ቦታ ነው።ችግኞቹ በአራት ወራቸው ተነቃቅለው ቦታው ለኮንዶሚኒየም ግንባታ ተመቻችቷል።
የከተማው አስተዳደሩ ቤቶች ለመገንባት መሰል መስዋትነቶችን በመክፈል ባይታማም፣ አዲስ አበቤ ኮንዶሚኒየም ቤት የሚመዘገበው እንደሚደርሰው አምኖ ሳይሆን ተስፋ ለማድረግ ከሆነ ሰነባብቷል። ቤቱ ባይደርሰውም መመዝገቡ ብቻውን የሚፈይድለት ነገር አለ።ለምሳሌ በዘመናችን ትዳር ለመመስረት ያሰበ ሰው እጁ ላይ ያለ ነገር ሁሉ ይታያል፤ ተስፋው ሳይቀር።ቢያንስ ኮንዶሚኒየም ተመዝግቤያለሁ ካለ «መጪው ጊዜ ከኢህአዴግ ጋር ብሩህ ነው» እንደተባለው ለእርሱም ደግሞ ይባልለታል።የቤት ባለቤት ሊሆን እንደሚችል ታሳቢ ተደርጎ መጻዒ ቀኑ እንደ ጸሐይ ይቆጠርለታል።
ዕድሜያቸው በ30ዎቹ መጀመሪያ ላይ የሚገኝ አዲስ አበቤዎች ከተማዋ በድንጋይና ሲሚንቶ ከመወረሯ በፊት በአረንጓዴው መስክ ላይ አፈር ፈጭተው፤ ጭቃ አቡክተውና አባሮሽ ተጫውተው ያደጉ የመጨረሻዎቹ ትውልዶች ናቸው።በልጅነት ዘመናቸው በባዶ እግራቸው ሳር የሸፈነው ሜዳ ላይ አባሮሽ ሲጫወቱ ተባራሪው ሲደክመው አንድ ቦታ ላይ ይቆምና «ቤቴ ገባሁ ቁልፍ ቁልፍ» ብሎ ሳሩ ላይ ቁጢጥ ይላል።ሁለቱም ሰፊው መስክ ላይ ቢገኙም አባራሪው በጨዋታው ደንብ መሠረት ስትወጣ እይዝሃለሁ ብሎ አጠገቡ ቁጭ ይላል።
ተባራሪው በቂ እረፍት ካደረገ በኋላ ሩጫውን ይቀጥላል።አባራሪውም እንደምንም ደርሶበት ልብሱን አሊያም አንዱን የአካል ክፍሉን ነክቶ በተራው ተባራሪ እስኪሆን ድረስ በትጋት ማባረሩን ይቀጥላል።ዛሬም ይህ ትውልድ ከልጅነት ጨዋታው የተላቀቀ አይመስልም።የአባሮሽ ጨዋታውን ቀጥሎ ኮንዶሚኒየምን እያባረረ ነው።ግንባታው በየዳገቱ ላይ ተቋርጦ ባረፈ ቁጥር «ሲወጣ ይደርሰኛል» እያለ በተስፋ ይጠብቃል።እርሱ ከጉሮሮው እየነጠቀ በቆጠበው ገንዘብ ፍትሃዊ ባልሆነ መንገድ ካድሬዎችና ባለጊዜዎች የቤት ባለቤት ሲሆኑ እያየ አንጀቱ እያረረ ኖሯል።ግና አዲስ አበቤ ብሶቱን በቀልድ እያዋዛ ይውጠዋል እንጂ ፊት አይሰጠውም።
ይህን ስል ባለፉት ዓመታት የኮንዶ ሚኒየም ዕጣ በወጣ ቁጥር የምሰማት አንድ ቀልድ ታወሰችኝ።ከአንድ ክልል ተነስቶ ወደ አዲስ አበባ የሚጓዝ መንገደኛ መኪናው ከተማ ባቋረጠ ቁጥር «አዲስ አበባ ገባን?» እያለ ተሳፋሪውን በጥያቄ ሲያሰለች ቆይቶ ተለቅ ያለች ከተማ ሲመለከት «አሁን አዲስ አበባ ገባን» ብሎ ደመደመ።አንድ ተሳፋሪ ገና አዲስ አበባ አለመድረሳቸውን ነገረውና «ለመሆኑ ለምን ጉዳይ ነው የምትሄደው?» ሲል ጠየቀው።አዲስ አበባ መድረስን የናፈቀው ተጓዥም «ኮንዶሚኒየም ደርሶኝ» ብሎ እርፍ አለ፡፡
ከዚህ ቀደም «ቆጠሚንየም» በሚል ርእስ ባቀረብኩት አንድ መጣጥፍ እንደጠቀስኩት ለአዲስ አበቤ ኮንዶሚኒየም ዝም ብሎ መጠሪያ አይደለም።በዓመታት ጠብ የሚልን ርቆ የተሰቀለ መና ወካይ ረቂቂ ስም ነው:: የተመዘገቡ ብቻ ሳይሆኑ ወደፊት ተመዝግበን እናገኘዋለን ብለው የሚያልሙ ህልመኞች የቀን ከሌሊት ቅዠት ነው:: ሚሊዮኖች ከጉሮሯቸው ነጥቀው የሚሞሉት ሆድ ነው:: አንዳንዴም ከቆመበት ቦታ ድንገት የሚሰወር መንፈስ ነው::
የከተማዋ አስተዳዳሪዎች ይህን ረቂቅ ስም በጠሩ ቁጥር የአዲስ አበቤዎች የልብ ምት ይጨምራል።ከሰሞኑ በ2012 በጀት ዓመት በመሃል ከተማ በተለያዩ አማራጮች የ500 ሺህ መኖሪያ ቤቶች ግንባታ ለመጀመር ዝግጅት ማጠናቀቁ መገለጹን ተከትሎ የተስ ፋው አቧራ ዳግም መብነን ጀምሯል፡፡
በተለያየ አማራጭ ይገነባሉ ከተባሉት ቤቶች ውስጥ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር 150 ሺህ ቤቶችን በ20/80 እና 40/60 ፕሮግራም ተመዝግበው ለሚገኙ ቆጣቢዎች እንደሚገነባ አስታውቋል።በሁለት ክፍለ ከተሞች የተተገበሩ የፓይለት ፕሮጀክቶችን ተሞክሮ በማስፋት በ10ሩም ክፍለ ከተሞች በሚገኙ ያረጁ የቀበሌ ቤቶች ይዞታዎች ላይ 25 ሺህ ኪራይ ቤቶችን ለመገንባት ማቀዱንም ይፋ አድርጓል።በተጨማሪም በግንባታ ላይ የሚገኙ ከ 139 ሺህ በላይ ቤቶችን ግንባታ አጠናቅቄ ለነዋሪዎች አስተላልፋለሁ ብሏል።
ይህን ዜና ተከትሎ ዕጣ ከወጣባቸው በኋላ ለነዋሪዎች ሳይተላለፉ በቀሩት የኮዬ ፈጬ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ምክንያት ትርጉም አጥቶ የነበረው ኮንዶሚኒየም ይደርሰኛል የሚል ተስፋ አሁን ዳግም ማንሰራራት ጀምሯል።አዲስ አበቤ ወደቀድሞ ተስፋው ተመልሷል።ከእንግዲህ በመልሶ ማልማት ሰበብ ስትኖር ከነበርክበት ቦታ እንደ አረም ተነቅለህ ጠረፍ ላይ አትጣልም፤ በነበርክበት መልሰህ እንድትሰፍር ትደረጋለህ መባሉ ለልጅ ልጁ ሊደርስ የሚችለውን ኮንዶሚኒየም በጽናት እንዲጠብቅ ኃይል ሰጥቶታል።
እርግጥ ነው ባለፉት ዓመታት ከፍተኛ ቁጥር ያለው የከተማዋ ኗሪ የቤት ባለቤት ሆኗል።ለዚህም መንግሥት ሊመሰገን ይገባዋል።ነገር ግን ከተማዋ ላይ ካለው የቤት ፍላጎት አንጻር ሲታይ ተጠናቀው ለኗሪዎች የተላለፉት ቤቶች ቁጥር አነስተኛ ነው።የአዲስ አበባ ቤቶች ግንባታ ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት በ1996 ዓ.ም በአዋጅ ቁጥር 15/1996 ከተቋቋመበት ጊዜ አንስቶ ባለፉት 15 ዓመታት ውስጥ ግንባታቸውን አጠናቆ ለኗሪዎች ባስተላለፋቸው ቤቶች ተጠቃሚ የሆኑት ተመዝግበው ከሚጠባበቁት አዲስ አበቤዎች ሩብ ያህሉ ናቸው።ይህም ግንባታው በኤሊ ፍጥነት እንደሚከናወን ያሳያል።
ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤቱ በ2020 በአዲስ አበባ ከተማ ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው ነዋሪዎች ጥራትና ደረጃቸውን የጠበቁ ቤቶችን በመገንባት የመኖሪያ ቤት ባለቤት የማድረግ ራዕይ እንዳለው ቢገልጽም የሚያልመውን ማሳካት የሚችልበት ቁመና ላይ አለመሆኑን የእስከዛሬው አፈጻጸሙ ያሳብቅበታል። ከዚህ ግዙፍ ችግሩ ያልተላቀቀው ይህ ተቋም 100 ሺህ ቤቶችን ለመገንባት ስምንት ዓመት እንደፈጀበት ዘንግቶ የተጀመሩ 139 ሺህ ቤቶችን እያጠናቀቅኩ ጎን ለጎን 175 ሺህ ቤቶችን በሁለት ዓመት ውስጥ እገነባለሁ ማለቱ ግር ያሰኛል።
በሌላ በኩል በአዲሱ የግንባታ መርሃ- ግብር የዲዛይን ክለሳ ተደርጎ አዲስ አበባን የሚመጥኑ ቤቶች ይገነባሉ መባሉና በሂደቱም የመንግሥት ሚና ከክትትልና ቁጥጥር ያለፈ እንደማይሆን መገለጹ ተስፋ ሰጪ ነው።
አዲስ ዘመን ጥቅምት26/2012
የትናየት ፈሩ