ፕሬዚዳንት በሽር አልአሳድ ከሥልጣን ይውረዱ በሚል እ.አ.አ. በ2011 የተጀመረው ተቃውሞ መልኩን ቀይሮ ባልተጠበቀ መንገድ እርስ በርስ የሚጋጩ ፍላጎቶች ያሏቸው ባላንጣዎችን የውክልና ጦርነት በመከሰት ‹‹የመካከለኛው ምሥራቅ ገነት›› ስትባል የነበረችውን ጥንታዊቷንና ታሪካዊቷን ሶርያ ላለፉት ስምንት ዓመታት የደምና የሰቆቃ ምድር እንድትሆን አድርጓታል፡፡
በተለይ አሜሪካ እ.አ.አ.ከ2015 ጀምሮ ጦሯን ወደ ሶርያ በማዝመት ከምዕራባውያን አጋሮቿ ጋር በመሆን ሲሻቸው አንድ ላይ፤ ሲያሻቸው ደግሞ ለየብቻቸው እየሆኑ ፕሬዚዳንት በሽር አልአሳድን ከሥልጣን ለማስወገድ፣ ሩሲያና ኢራን በአንፃሩ አል አሳድን በሥልጣን ለማቆየት አይኤስን ለመዋጋት በማለት የገጠሙት የእጅ አዙር ጦርነት፣ ቀጣናው ዘግናኝ ዓመታትን እንዲያሳልፍ ዋነኛ ምክንያት ሆነዋል፡፡
አገራት በሶርያና አስተዳደሯ ላይ ያላቸው የየቅል አመለካከትም በተደጋጋሚ እርስ በርስ ሲያወነጃጅልና ሲያፋጥጣቸው ቢቆይም፣ ዶናልድ ትራምፕ ልዕለ ኃያሏን አገር ለመምራት ነጩን ቤተ መንግሥት ከተረከቡ ወዲህ ግን ትንቅንቁ በአንፃራዊነት ጋብ ብሎ ተስተውሏል፡፡ ለዚህ ደግሞ ትራምፕ በሶርያ ላይ ያላቸው አቋም ከቀድሞው መሪ ባራክ ኦባማ አስተዳደር የተለየና ጠንካራ አለመሆን በምክንያትነት ይጠቀሳል፡፡
እንደ ትራምፕ እምነት አገራቸው በመካከለኛው ምሥራቅ ጦርነት ምክንያት 8 ትሪሊዮን ዶላር ወጪ አድርጋለች፡፡ ይህ ሁሉ ሀብት ወጥቶም፣ የበርካታ ወገኖች ሕይወት ተቀጥፎም አሁንም የቀጣናውን ሰላምና ደህንነት አስተማማኝ ማድረግ አልተቻለም፡፡
ከዚህ ባሻገር አሜሪካ በሶርያ ውስጥ በነበራት ተሳትፎ፤ ‹‹ከማንም በላይ ሩሲያ፣ ኢራንና ሶሪያ ተጠቃሚዎች ሆኖዋል›› ብለው የሚያምኑት ፕሬዚዳንት ትራምፕ፣ ይህን አመክንዮ ዋቢ በማድረግ ከሰሞኑ የአገራቸውን ወታደሮች ከሰሜን ሶርያ የማስወጣት ውሳኔ አሳልፈዋል፡፡
ይህ ውሳኔም ከሁሉም በላይ በሰሜን ምሥራቅ ሶርያ ለሚገኙትና በአላሳድ አስተዳደር መወገድ ላይ ከአሜሪካ ጋር ለወገኑት የኩርድ ወታደሮች ዱብ ዕዳ ሲሆንባቸው፣ ኩርዶችን እንደ ሽብርተኛ ለምትቆጥረው ቱርክ ደግሞ ያልተጠበቀ ብስራት ሆኖላታል፡፡ ከሁሉም በላይ ግን ሩሲያ በዓለም ፖለቲካ ያላትን ተደማጭነት በአዲስ መልክ ለመገንባት የጀመረችውን ጥረት ይበልጡን ያጠናከረ ነው ተብሎለታል፡፡
በዚህ አብይ ጉዳይ ላይም የተለያዩ መገናኛ ብዙኃንና የፖለቲካ ተንታኞች ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከሶርያ ምድር የአገራቸውን ወታደሮች ለማስወጣት መወሰናቸው ለምንጊዜም ተቀናቃኛቸው ሩሲያ ትልቅ ድል ስለመሆኑ በማስረዳት ተጠምደዋል።
በዚህ ረገድ ሰፊ ሃተታቸውን አሾሽየትድ ፕሬስ ላይ ያሰፈሩት፣ ሼሊ ኤድለርና ዴብ ሪችማን፣ ‹‹ፕሬዚዳንቱ የአገራቸው ወታደሮችው ከሰሜን ሶርያ እንዲወጡ ውሳኔ ማሳለፋቸውን በገለፁ ማግስት ያልተረዱት ነገር ቢኖር ለዋንኛ ተቀናቃኛቸው ሩሲያ ቀጣናውን ማስረከባቸውንና ጡንቻዋን ማፈርጠማቸውን ነው›› ብለዋል፡፡
አሜሪካ ወታደሮቿን ለማስወጣት በወሰነች ቅጽበት በሶርያ ምድር የነበራትን ሁለንተናዊ የበላይነት ለሩሲያ፣ ለቱርክና ኢራን ማስረከቧን ከተስማሙት የፖለቲካ ምሁራን አንዱ የሆኑት ሲዝ ጆንስ፣ ውሳኔው በቀጣዮቹ ዓመታት የቀጣናው ዋነኛ ፈላጭ ቆራጭ አሜሪካ ሳትሆን ሩሲያ እንድትሆን በሩን ወለል አድርጎ የከፈተ ነው ሲሉ አስተያየታቸውን አጋርተዋል፡፡
የፕሬዚዳንቱን ውሳኔ በውጭ ብቻም ሳይሆን በራሳቸው አስተዳደር አመራሮችም የተወደደ አልመሰለም። የሪፐብሊካን ሴናተር ሊንድዚ ግራሃም የፕሬዚዳንቱ ውሳኔ መደገፉን ጠቅሰው፣ ቀጣዩ ግን እጅጉን እንደሚያሳስባቸው መናገራቸውም ለዚህ ምስክር ሆኖ ቀርቧል፡፡
‹‹አገራችን በሶርያ ምድር ከአጋሮቿ ጋር በመሰረተችው ወታደራዊ ጥምረት በተለይ የአይ ኤስን የሽብር ቡድን ለመቆጣጠርና ዳግም እንዳያንሰራራ ለማድረግ ወሳኝ ሚና አበርክቷል›› የሚሉት ሴናተሩ፣ ይህን ዘላቂ በማድረግ ሶርያን ከሽብርተኞች መፍልፈያነት በመታደግ ሂደት ሩሲያ፣ ቱርክና የአሳድ መንግሥት አቅሙ አላቸው ብለው እንደማያምኑም አስረድተዋል፡፡
ዴቪድ ሊግናተየሰ የተባለው ጸሐፊ በበኩሉ ዋሽንግተን ፖስት ባሰፈረው ሀተታ፣ «ምስጋና ለዶናልድ ትራምፕ ይሁንና ሩሲያ በመካከለኛው ምሥራቅ አሸናፊ ሆናለች›› ሲል ቢፅፍም፣በሞስኮ ዓለም አቀፍ ግንኙነት ኢንስቲትዩት መምህር የሆኑት ማክሲም ሹኮቭ ,በአንፃሩ፣ ሩሲያ ቀድሞውንም ቢሆን መልካም ተግባርና ምኞቷን የሚያንጸባርቅ ገጽታዋን በቀጣናው አሰራጭታ እንደነበር መዘንጋት እንደማይገባ አብራርቷል፡፡
በእርግጥም ፕሬዚዳንት ብላድሚር ፑቲን አገራቸውን በመካከለኛው ምሥራቅ ይበልጡን በመንሰራፋት በኢኮኖሚው በተለይ በኃይልና በወታደራዊ ግብአት አቅርቦት ቀልጠፍጠፍ ያለ ተግባራቸውን መከወን ከጀመሩ ዋል አደር ብለዋል። እዚህ ላይ የነጩ ቤተ መንግሥት አስተዳደር በቀጣናው ምህዋር ላይ የነበረውን ዙረት ማቀዝቀዙ ሲደምር ደግሞ የሞስኮን ጉዞ አልጋ በአልጋ ማድረጉ የሚያከራክር አይሆንም፡፡
አንዳንድ ጸሐፍትና መገናኛ ብዙኃን በሌላ በኩል አሜሪካ ከሰሜን ሶርያ ለመሸሽ የፈለገችው፣ በደመነፍስ ሳይሆን በተጠና መልኩ ነው ሲሉ አመላክተዋል። ይህን ሃሳብ የሚጋራው የኒውስ ዊክ ጸሐፊው ቶም ኦክኖርም፣ ውሳኔው ብልጠት በተሞላበት መልኩ የመካከለኛውን ምሥራቅ የኃይል ሚዛን ለማመጣጠን የተቀመረ ነው›› ሲል አስረድቷል፡፡
የኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲው ሳሙኤል ራማኒ፣ ምንም እንኳን ሩሲያ የሶርያንና መካከለኛው ምሥራቅን ዕጣ ፈንታ ብትረከብም፣ የደህነነት ዋስትናው ግን በቀጣይም ካለምንም ጥርጥር በአሜሪካ ስር እንደሚሆን መጠራጠር ሞኝነት ስለመሆኑ አብራርቷል፡፡ ከሰሞኑን የአሜሪካ ልዩ ኃይል ወታደሮች በሰሜን ምዕራብ ሶርያ ባካሄዱት የጸረ ሽብር ዘመቻ የአይ ኤስ የሽብር ቡድን መሪ አቡባከር አል ባግዳዲን መግደላቸው ደግሞ ለዚህ እሳቤ አንድ ማሳያ ሊሆን ይችላል፡፡
በአሁኑ ወቅት አሜሪካ ወታደሮቿን ከሰሜን ሶርያ ለማስወጣት መወሰኗ በዚህ መልክ የተለያዩ እሳቤዎችን መፍጠር ቢችልም፣ ሩሲያ በዓለም ፖለቲካ ውስጥ ያላትን ተደማጭነት በአዲስ መልክ ለመገንባት የጀመረችውን ጥረት ማጠናከሩ ግን በርካታ ወገኖችን አስማምቷል፡፡ ፕሬዚዳንት ብላድሚር ፑቲንም የመካከለኛው ምሥራቅ ንግስናቸውን ተረክበዋል፡፡
አዲስ ዘመን ጥቅምት25/2012
ታምራት ተስፋዬ