
የኢፌዴሪ ባህልና ስፖርት ሚኒስቴር በጥናት ግኝቶች ላይ የተመሠረተና የስፖርቱን ስብራቶች ለመጠገን ያስችላሉ ያላቸውን የተለያዩ አሠራሮች ተግባራዊ እንደሚያደርግ ጠቆመ።
ሚኒስቴሩ “አብሮነታችን ለሀገር ግንባታ” በሚል ርዕስ ጉባኤውን ትናንትና ከትናንት በስቲያ በሀዋሳ ያካሄደ ሲሆን፤ የተጠሪ ተቋማቱ የስድስት ወራት አፈጻጸም ቀርቧል:: በዚህም በስፖርቱ ዘርፍ በተለይ የስፖርት ፖሊሲ፣ የሕግ ማሕቀፎች ክለሳና ማሻሻያዎች ለማከናወን የሚያስችሉ ችግር ፈቺ የጥናትና ምርምር ሥራዎች ማከናወኑ ተጠቁሟል::
የስፖርቱን ስብራት ሊጠግኑ የሚችሉ ሁለት ሜጋ ጥናቶች ባለፉት ወራት መዘጋጀታቸው የተገለጸ ሲሆን፤ ይህንንም ወደ ሥራ ለመቀየር በዝግጅት ላይ እንደሚገኝ ተጠቁሟል:: ዘርፉ ለኢትዮጵያ ገጽታ ግንባታ ያለውን አቅም አሟጦ ለመጠቀም ሴክተሩ ራሱን በመፈተሽና ቅንጅታዊ አሠራሮችን በማጠናከር ለውጤታማነት ሚናውን ሊወጣ እንደሚገባም ሚኒስትሯ አሳስበዋል::
የኢፌዴሪ ባህልና ስፖርት ሚኒስትሯ ሸዊት ሻንካ፣ ባለፉት ስድስት ወራት ከፌዴራል አንስቶ በሁሉም ክልሎች የተሳካ ሥራ ማከናወን መቻሉን ጠቁመው፤ የስፖርት ልማት ቀጣይነትን ለማረጋገጥ በጥናት የተገኙ ግኝቶችን መሠረት ያደረገ ስትራቴጂክ ዕቅድ መዘጋጀቱን ገልጸዋል። በዚህም የተለያዩ አዋጆች፣ ሕጎችና አሠራሮች በቀጣይ ተግባራዊ እንደሚደረጉ አስረድተዋል።
በባህልና ስፖርት ሚኒስቴር የስፖርት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ መኪዩ መሃመድ በበኩላቸው፤ ያለፉ ወራት ክንውኖችና ቀጣይ የትኩረት አቅጣጫዎችንም አመላክተዋል:: ስፖርት ማህበራትን ጨምሮ ስፖርቱ ላይ የሚነሱ ችግሮችን ለመፍታት የሚያስችሉ አሠራሮችን በጥናት በመለየት የፖሊሲ ለውጥ እንዲደረግ በፍትህ ሚኒስቴር በኩል አልቆ አሁን ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ደርሶ የመጨረሻ ውሳኔ እንዲሰጥበት ወደ ሚኒስትሮች ምክር ቤት የሚሰጥ መሆኑን አስረድተዋል። ይህም በስፖርቱ ዘርፍ የሚታየውን ውስብስብ ችግር መፍታት ያስችላል የሚል ተስፋ እንደተጣለበት ገልጸዋል። በስፖርት ማህበራት ውስጥ የሚታዩ ክፍተቶችን ለመፍታት የሚያስችሉ አሠራሮችን መተግበር አስፈላጊ በመሆኑም በቀጣይ ስድስት ወራት በትኩረት የሚሠራበት እንደሚሆን አክለዋል::
በጉባዔው በስፖርቱ ዘርፍ ባለፉት ስድስት ወራት የተከናወኑ አበይት ጉዳዮች ቀርበው ውይይት የተደረገባቸው ሲሆን፣ ውድድር ከሌለ ስፖርት የማይታሰብ እንደመሆኑ ተቋርጠው የቆዩ ሀገር አቀፍ ውድድሮችን ማስጀመር መቻሉ አንዱ ስኬት ነው ተብሏል:: ለረጅም ዓመታት ተቋርጠው የቆዩ ውድድሮችን (የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት፣ የታዳጊ ወጣቶች ስፖርት ምዘና የተመለሱት ባለፈው ስድስት ወራት ሲሆን፤ በቀጣይም የሚከናወኑ እንደሚኖሩ ተጠቁሟል:: በቅርቡም የባህል ስፖርትና ፌስቲቫል የሚካሄድ ሲሆን፤ በዓመቱ መጨረሻ ደግሞ የመላ ኢትዮጵያ ጨዋታዎች እንደሚደረግ ተገልጿል::
በስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎችን በሚመለከትም በተለይ ብሄራዊ ስታዲየምን ለማጠናቀቅ ርብርብ እየተደረገ መሆኑ የተገለጸ ሲሆን፤ በዘርፉ የሚነሱ ሌሎች ችግሮችም በሂደት እንደሚፈቱ ተጠቁሟል:: የስፖርት መልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመፍታት ከሚኒስቴሩ አንስቶ በክልሎችና የስፖርት ማህበራት ጋር በጋራ መሥራት አስፈላጊ መሆኑንም አመላክተዋል::
የአፍሪካ ዋንጫን በ2029 ለማዘጋጀት የሚያስችል ስትራቴጂክ ሰነድ ዝግጅት የተደረገ ከመሆን ባለፈ ዲፕሎማሲያዊ ቅድመ ዝግጅቶችም ተከናውነዋል:: ይኸውም የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን እንዲሁም የፊፋ አመራር ወደ ኢትዮጵያ የመጡበት ነው::
በዓለም አቀፍ ውድድሮች የሀገርን ስም ማስጠራት ለቻሉ የስፖርት ባለሙያዎች ማበረታቻ በማበርከት፣ የስፖርት አደረጃጀቱን በማዘመንና የስፖርት ማህበራትን በመደገፍ፣ በማስ ስፖርት እንቅስቃሴ እንዲሁም በማዘውተሪያ ስፍራዎች ላይም የተለያዩ ሥራዎች መከናወናቸው በቀረበው ሪፖርት ተመላክቷል::
በመድረኩ መልካም ተሞክሮ ያላቸው ክልሎች አፈጻጸምም ቀርቧል:: ከስድስት ዓመታት መቋረጥ በኋላ በቅርቡ ወደ ውድድር እንዲመለስ የተደረገው የታዳጊ ወጣቶች የምዘና ውድድር በቀጣዩ ዓመት ለማዘጋጀት የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ጥያቄውን ያቀረበ ሲሆን፤ ይሁንታም አግኝቷል:: ከጉባኤው ባሻገር የሲዳማ ክልል በስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች እያከናወናቸው የሚገኙ ሥራዎች ላይ የመድረኩ ተሳታፊዎች የመስክ ምልከታ አድርገዋል።
ብርሀን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ቅዳሜ የካቲት 8 ቀን 2017 ዓ.ም