800 አባወራዎችን ተጠቃሚ የሚያደርግ ፕሮጀክት ወደ ሥራ ሊገባ ነው ተባለ

አዲስ አበባ፡- 800 ስደተኛና ተፈናቃይ አባወራዎችን እንዲሁም ተቀባይ ማህበረሰቦችን ተጠቃሚ የሚያደርግ “ምኞቴ” የተሰኘ የሁለት ነጥብ አንድ ሚሊዮን ዩሮ ፕሮጀክት ሊገባ መሆኑ ተገለጸ፡፡ ፕሮጀክቱ ከኔዘርላንድ ኤምባሲ በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ልማትና ክርስቲያናዊ ተራድኦ ኮሚሽን እና በኢየሩሳሌም የሕጻናት እና ማህበረሰብ ልማት ድርጅት በአዲስ አበባና በደብረ ብርሃን ከተማ እንደሚተገበር ተጠቁሟል፡፡

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ልማትና ክርስቲያናዊ ተራድኦ ኮሚሽን ኮሚሽነር ይልቃል ሽፈራው ፕሮጀክቱ ትናንት ይፋ ሲደረግ በመድረኩ ላይ እንደገለጹት፤ ፕሮጀክቱ ከኔዘርላንድ ኤምባሲ በተገኘ ሁለት ነጥብ አንድ ሚሊዮን ዩሮ ለሁለት ዓመታት ይተገበራል፡፡ በዚህም 800 ስደተኛና ተፈናቃይ አባወራዎች ተጠቃሚ ይሆናሉ ብለዋል፡፡

አንድ ነጥብ አምስት ሚሊዮን ዩሮ በላይ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በለሚ ኩራና ላፍቶ ክፍለ ከተሞች የሚገኙ 500 አባወራዎች ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ጠቁመው፤ 520 ሺህ ዩሮው በደብረ ብርሀን ከተማ ሦስት ክፍለ ከተሞች የሚገኙ 300 አባወራዎችን ተጠቃሚ ያደርጋል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ልማትና ክርስቲያናዊ ተራድኦ ኮሚሽን በተለያየ የሀገሪቱ ክፍሎች የተለያየ የልማት ድጋፍ ትግበራን እንደሚያከናውን ጠቁመው፤ ምኞቴ የተሰኘው ፕሮጀክትም በስደትና መፈናቀል ምክንያት ለችግር የተጋለጡ ወገኖችን ሕይወት ለመለወጥ ትልቅ አቅም ይፈጥራል፡፡ ይህ እውን እንዲሆን ድጋፍ ላደረገው በኢትዮጵያ የኔዘርላንድ ኤምባሲ ምስጋና አቅርበዋል፡፡

በኢትዮጵያ የኔዘርላንድ አምባሳደር ክሪስቲን ፒሬን በበኩላቸው፤ ፕሮጀክቱ በኢትዮጵያ ለስደተኞች እና ለተፈናቃዮች የሚያስፈልጋቸውን ድጋፍ በማድረግ በዘላቂነት የወደፊት ሕይወታቸውን ለመገንባት አስተዋጽኦ ያደርጋል።

ኢትዮጵያ ከአንድ ሚሊዮን በላይ ስደተኞችን ተቀብላ እያስተናገደች መሆኑን ጠቅሰው፤ በተጨማሪ በግጭት እና በአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖ ምክንያት ተፈናቃዮች አሏት፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥትም ስደተኞችን ተቀብሎ ከለላ መስጠቱ የሚያስመሰግነው ነው ብለዋል፡፡

የሀገር ውስጥ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ፕሮጀክትን በሚተገብሩበት ጊዜ አቅም ማሳደግን ይጠይቃል ያሉት አምባሳደሯ፤ የሀገር ውስጥ ድርጅቶች ከተባበሩት መንግሥታት ኤጀንሲዎች እና ከዓለም አቀፍ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ይልቅ ፕሮግራሞችን የመተግበር አቅም እንዳላቸው መተማመን ያስፈልጋል ነው ያሉት።

በአዲስ አበባ እና በደብረ-ብርሃን የሚገኙ ስደተኞችን፣ ተፈናቃዮችን እና ተቀባይ ማህበረሰቦችን አቅም ለማሻሻል የሚያግዘውን ምኞቴ ፕሮጀክት በአግባቡ እንደሚሳካ ያላቸውን እምነት ገልጸው፤ ለፕሮጀክቱ የሚደረገው ድጋፍ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አምባሳደሯ አስታውቀዋል።

ፋንታነሽ ክንዴ

አዲስ ዘመን ቅዳሜ የካቲት 8 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You