
የጨንቻው ልጅ …
መስፍን ጩበሮ የአርባምንጭ ‹‹ጨንቻ›› ፍሬ ነው:: እንደ እኩዮቹ ልጅነቱን በሰፈር መንደሩ አሳልፏል:: አርባምንጭ ለእሱ ሁሌም የውስጠቱ ውልታ ናት:: በትዝታ ይቃኛታል:: በናፍቆት ያስባታል:: መስፍን ዕድሜው ከፍ እንዳለ የትውልድ ሀገሩን ርቆ ሊሄድ ግድ አለው:: የተሻለ ኑሮ፣ ያማረ ሕይወት ሲያስብ ቆይቷል:: እንደወጣ አይቀርም :: አንድ ቀን ወደነበረበት እንደሚመለስ ያውቃል::
አዲስ አበባ ሰፈረ – ሽሮሜዳ የሀገርቤት ሰዎች አሉ:: የቅርብ ዘመድና የሥጋ ቤተሰቦች ጭምር:: መስፍን እጀ ወርቅ ሸማኔ ነው:: ጥበቡን አሳምሮ ማስዋቡን ያውቅበታል:: ቀጭን ኩታው፣ ጋቢ ነጠላው ተደውሮ የሚሸመነው በእጁ ላይ ነው:: ሙያው ለእሱና ለቤተሰቡ ብርቅም፣ ሩቅም አይደለም:: ቀደምት መሠረቱ ከአያት ቅድመ አያቱ ይመዘዛል::
መስፍንና ሽሮ ሜዳ መልካቸው በሥራ ተዋዝቷል:: ሰርቶ በማግኘት መለወጥን የወጠነው ወጣት ዓላማውን አልሳተም:: ከትምህርቱ ሳይናጠብ፣ ከሥራው እጁ ሳይዝል ሽመናውን ቀጠለ:: አዲስ አበባ ለመስፍን ሁለተኛ ቤቱ ሆነች:: ሌት ተቀን እየተጋ ያሰበውን አሳካ:: አሁንም የአርባምንጭ ትዝታ ከውስጡ ነግሷል:: አንድ ቀን ተመልሶ እንደሚሄድ ማሰብን አልተወም::
የመስፍን ሕይወት በሥራ ብቻ አልቆመም:: ወጣትነቱ በዕድሜ ቢያበስለው ግራ ጎኑን ፈለገ:: ተሳካለትም:: ጎጆ ቀልሶ ትዳሩ እንደሞቀ ቤቱ በልጅ ስጦታ ተባረከ:: እሱና ባለቤቱ የመጀመሪያዋን ሴት ልጅ ታቅፈው ሳሙ:: አሁን የመስፍን ህልም ዕውን መሆን ይዟል:: ሀገሩ የመመለስ ዕቅዱን ሊያሳካ የልቡን ምኞት ሊሞላ ነው::
ሁለተኛው ሲሳይ …
መስፍን በአዲስ አበባ ሕይወት ክፉ ደጉን አይቷል፣ በሥራ ብዛት ደክሟል፣ በላቡ ጠብታ መልካም ፍሬን አፍሷል:: ከሰው ተግባብቶ ዕውቀት ሸምቷል:: ሽሮሜዳ የእንጀራ ቤቱ፣ የትዳር መሠረቱ ናት:: አሁን ደግሞ ሁለተኛ ልጁን ሊስም፣ ሊታቀፍ ነው:: ይህ ዕውነት ይበልጥ ወደ ዕቅዱ መርቶታል:: ከዚህ ቀጥሎ መንገዱ ሀገሩ ላይ ይቀጥላል:: በትውልድ ቦታው ዳግም ሕይወት፣ መዝራት፣ ኑሮን መምራት ህልሙ ነው::
ነፍሰጡር ባለቤቱ ህክምናዋ አልጎደለም:: ተገቢውን ክትትል፣ የጤና ምርመራን አታጎድልም:: መውለጃዋ ሲቃረብ መስፍን ወደ ሀገርቤት ተመላልሶ ጓዙን አደረሰ:: በአዲስ ሕይወትና ቤት አዲሱን ልጅ ሊቀበለው አስቧል:: አሁን ጨንቻ ላይ የቀለሳት ጎጆ የቤተሰቡ መኖሪያ፣ የእሱ ልብ ማረፊያ ሆናለች:: መስፍን ከዓመታት በፊት ከሀገሩ ሲርቅ ይህ ህልም ውስጡ ነበር:: አሁን ሃሳቡ ሰምሯል፣ ህልሙ ተፈቷል::
በአዲሱ ቤት እግሯ ቀድሞ የገባው ሚስት ለመውለድ የአስራአምስት ቀን ጊዜ አላት:: ሕይወትን በራስ አቅም በራስ ጎጆ መምራት ትርጉሙ ይለያል:: በጥንዶቹ ውስጠትም ይህ እውነት ውሎ ካደረ ቆይቷል:: ጥቂት ቆይቶ አባወራው ከአዲስ አበባ ጠቅልሎ ከአርባ ምንጭ ደረሰ::
ከቀናት በኋላ አዲሱ ጨቅላ እንግዳ ሆኖ ቤተሰቡን ተቀላቀለ:: አጋጣሚዎች መልካም ሆኑ:: ትንሹ ልጅ ትርጉም ያለው ስም ተቸረው:: ከልፋት ድካም በኋላ እፎይታን ያወጀ ዕድለ መልካም ሆኗል :: ለዚህ እውነታም መጠሪያውን ‹‹ተመስገን ›› ሲሉ ሰይመውታል:: ‹‹ተመስገን›› የሀገርቤት መግቢያ መንገድ፣ የአዲስ ሕይወት ገድ ነው:: ባልና ሚስት ከሁለት በአራት ተቆጥረው ደስታቸውን አጣጥመዋል::
እነሆ! ሕይወት በአርባምንጭ ጨንቻ ላይ ዳግም ተጀምሯል:: መስፍን ባለቤቱን ከሁለት ልጆቹ ይዞ ቤቱን እያሟላ ግቢውን እያደረጀ ነው:: ትልቋ ልጅ ትምህርት ጀምራለች:: ትንሹ ተመስገንም በእናቱ እቅፍ ሆኖ የልጅነት ወጉን ይዟል:: ተመስገን ገና ጨቅላ ነው:: ከትልቋ ይበልጥ ትኩረትን ይሻል:: አባወራው ቤቱን እየመራ ግዴታውን ይወጣል::
የእናት እጆች …
የቤት እመቤቷ ወይዘሮ ልጆች መንከባከብ ፣ ጓዳ ኑሮዋን መመልከት ግዴታዋ ነው:: የእናት ሃላፊነት ከብዙ ያደርሳል:: የቤት የደጁን ታስባለች::
ሠርቶ የሚገባ ባሏን፣ ተጫውተው የሚውሉ ልጆቿን ትቃኛለች:: ሕይወት በአዲስ ቤት አዲስ ሆኖ ተጀምሯል:: ለአባወራው አጋጣሚው መልካም ሆኖለታል:: ከዓመታት በፊት ትቷት የወጣውን ጨንቻን ዳግም አግኝቶ ታድሷል::
አሁን ትንሹ ተመስገን ዕድሜው ጨምሯል:: ከግዜያት በኋላ እንደ እኩዮቹ ትምህርት ቤት ገብቶ ፣ ቀለም ፣ ዕውቀት ይቀስማል:: ቦርሳውን አዝሎ፣ ፊደል ቆጥሮ ሲመለስ የወላጆቹ ዓለም ይሞላል:: ዛሬ ተመስገን በአባቱ ትውልድ ሀገር አድጎ ፣ተምሮ ሊለወጥ ነው::
ከቀናት በአንዱ እናት የልጇን ገላ ለማጠብ ልብሶቹን አወለቀች:: እንደ ሁልጊዜው ሁሉ ጀርባውን እያሸች፣ እጅ እግሮቹን ዳሰሰች:: ልጇን በፈገግታ፣ በልዩ ፍቅር እያየችው ነው:: በእናቱ እጅ ያለው ህጻን ዛሬም ደስታው ከፊቱ ይነበባል:: ጸጉሩን አጥባ ፣ አንገቱን አሽታ ወደ ብብቱ ስትዘልቅ ከእጆቿ መሀል አንዳች ነገር ተሰማት::
ለእናት ይህ ጉዳይ አዲስና ያልተለመደ ነው:: ክፉኛ ደነገጠች:: በፍራቻ መለስ ብላ የብብቱን ላይና ሥር ነካችው፣ እየፈራች ዳሰሰችው:: ዕብጠቱ ለእጅ በሚለይ ምልክት ቦታው ላይ እንዳለ ነው::
ጥቂት ቆይቶ አባት መስፍን የሚስቱን ስጋት ተጋራ:: ትንሹ ልጅ ብብት ሥር በግልጽ የሚታይ ዕብጠት አለ:: በዓይኑ ያስተዋለውን እውነት በዋዛ ሊያልፈው አልፈለገም:: ጥንዶቹ ስለልጃቸው አዲስ ጉዳይ በሃሳብ ተከዙ:: ውሎ ሲያድር ሥጋታቸው ጨመረ:: ጥቂት ቀናት እንዳለፉ እናት ልጇን ይዛ ወደ ሆስፒታል አቀናች::
በሆስፒታሉ …
እናትና ልጅ ከሆስፒታል ደርሰው ከሀኪም ፊት ቀረቡ:: ሀኪሙ የህጻኑን ምርመራ አጠናቆ የደም ናሙናውን ከአንድ የግል ሆስፒታል እንዲሰጡ አዘዛቸው:: እንደተባሉት የታዘዙትን ፈጸሙ:: ከቀናት በኋላ የበብቱ ሥር ዕብጠት በቀዶ ህክምና እንደሚወገድ ሰሙ :: እናት አባት ስለ ትንሹ ልጃቸው ደነገጡ:: ሁለቱም ስለህመሙ ምንነት ዝም አላሉም:: ቀረብ ብለው ሀኪሞችን ጠየቁ:: በቀላሉ የሚድን መሆኑንና በተለምዶ ‹‹ንፍፊት›› የሚባለው ችግር መሆኑ ተነገራቸው:: የሰሙት ውጤት መልካም ቢሆንም ምርጫ አልነበረም:: በተያዘው ቀነ- ቀጠሮ ሁሉም በጊዜው ተከውኖ ቀዶ ህክምናው ተጠናቀቀ::
አሁን ተመስገን ላይ የታየው ምልክትና የቤተሰቡ ሥጋት ተወግዷል:: ህጻኑ ህከምና ካገኘ ወዲህ ሁሉም በእፎይታ ‹‹ተመስገን›› እያለ ነው:: ትንሹ ልጅ ደስተኛ ሆኗል :: ከቀናት በኋላ የመጀመሪያውን ፊደል ሊቆጥር ከትምህርት ገበታው ይገኛል:: አባት መስፍን ወደ ጉዳዩ ገብቷል:: እናት ወደቤት ጓዳዋ ተመልሳለች::
ከሁለት ወራት በኋላ …
ከሁለት ወራት በኋላ የቤተሰቡ ስጋት ዳግመኛ አገረሸ:: ቀድሞ በሆስፒታሉ ምርመራ የቀዶ ህክምና ያገኘው ተመስገን አሁንም ብብቱ ሥር ምልክቱ ታይቶበታል:: ይህ እውነት የመላው ቤተሰብ ድንጋጤ ሆነ:: ሁሉም በትካዜ አንገቱን ደፍቶ ከረመ:: አስቀድሞ ‹‹ቀላል ነው አይተካም›› የተባለው ዕብጠት አሁን በተቃራኒው ሆኗል:: መስፍን ይህን ካወቀ ወዲህ ስለልጁ ጤና እረፍት አልባ ሆነ::
ዳግመኛ የተሠራው ናሙና ወደ አርባምንጭ ሆስፒታል መላክ ነበረበት:: በሥፍራው ያገኛቸው ባለሙያዎች የመጣውን ናሙና ካዩ በኋላ ለአባት መስፍን ቀድሞ መሠራት የነበረበት በዚህ ሆስፒታል እንደነበር ነገሩት:: አባት በሃሳብ መለስ ብሎ ያለፈበትን የህክምና መስመሮች አስታወሰ::
ከወራት በፊት ከአንድ የግል ህክምና ልጁ ቀዶ ህክምና ተሰርቶለታል:: አሁን የሚሰማው ግን ‹‹ፓቶሎጂ›› የተባለው ምርመራ መካሄድ የነበረበት ከፍ ካለ ሆስፒታል መሆኑን ነው:: መስፍን በልጁ ላይ ስህተት መፈጸሙን ባወቀ ጊዜ ልቡ ተሰበረ:: ለመፍትሔ ብሎ የወሰደው ፈጣን ውሳኔ በውጤቱ ስህተት እንዳለው ሲረዳ ቁጭት አንገበገበው::
የአባት መስፍን ውስጠት አልተረጋጋም:: በእጁ ላይ ያለው የልጁ ውጤት ካንሰር መሆኑ ተነግሮታል:: ከዚህ ቀድሞ ስለህመሙ ግንዛቤ የለውም:: በሰማው እውነትና ሰዎች ባስረዱት ልክ ግን የትንሹ ልጅ ችግር ቀላል አለመሆኑን ተረድቷል:: ተመስገን አስቸኳይ የሆነ ከፍተኛ ህክምና ያሻዋል:: እንዲህ ይሆን ዘንድ ከአርባምንጭ አዲስአበባ መሄድ ግድ ሆኗል::
አባት ተመስገን አሁንም ፈጥኖ ለመወሰን ደጋግሞ አላሰበም:: ስለ ልጁ ጤና የተባለውን ማድረግ አለበት:: ትናንት ብዙ ዕቅዶች ይወጥን ነበር:: ለዓመታት የቆየበትን የከተማ ኑሮ ትቶም ወደ ሀገርቤት ተመልሷል:: ዛሬ ግን ያለመው የጨንቻ ላይ አዲስ ሕይወት እንዳሰበው አልሆነም ::ልጁ ታሞበታል:: እሱን አሳክሞ ፣ማዳን ፣ ፈገግታውን መመለስ አለበት::
አዲስ አበባ …
አዲስ አበባና መስፍን ዳግም ተገናኝተዋል:: አዲስ አበባ የኖረበት፣ የተማረበት ከተማ ነው:: በሽሮሜዳ ሸማውን እየሠራ ፣ጥበቡን አሳምሯል:: ደንበኞችን አውቆ ወዳጅ ዘመድ አፍርቷል:: የዛኔው አዲስ አበባና የዛሬው ኑሮ ግን በእጅጉ ይለያል:: ዛሬ ብቻውን አይደለም:: ትንሹ ተመስገን አብሮት አለ:: አሁን ዞሮ የሚገባበት፣ ውሎ የሚመለስበት ጎጆ የለውም:: ሳይወድ በግድ የከተማዋ እንግዳ ሆኗል::
ልጁ ህክምና በጀመረ ጊዜ ለዕለት ወጪው ፣ ለመድሃኒት መግዣው ፣ ለትራንስፖርትና ለሌላም ብዙ ገንዘብ አስፈለገው:: ጨንቻ ላይ የመጀመሪያ ሴት ልጁና ባለቤቱ ቀርተዋል:: እሱ ደግሞ የአዲስ አበባ እንግዳ ሆኖ ላይ ታች ማለት ይዟል::
ሕይወት እንደ ትናንቱ አልሆነም:: አባወራው ስለ ልጁ መዳን ታገለ:: አሁን ስለሁሉም ብዙ ያስፈልገዋል:: ቀድሞ የተወውን ሽመና ሊመለስበት አሰቦ በአቅሙ ቤት ተከራየ:: እንደትናንቱ በቋሚ ሥፍራ ተረጋግቶ መሥራት አይችልም:: በሙያ ኪራይ እጁን አሳይቶ ሥራውን ጀመረ::
ሁኔታዎች እንዳሰበው አልሆኑለትም:: የልጁ ህክምና በአጭር ጊዜ፣ በቀላል ወጪ የሚቋጭ አይደለም:: ዕለት በዕለት በቂ ምግብ፣ የሀኪም ክትትልና መድሃኒት ያስፈልጋል:: ትንሹ ተመስገን የተሻለ ማረፊያና ምቹ ዕንቅልፍ ማግኘት አለበት::
በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ኬሞ ቴራፒው በተጀመረ ጊዜ ለመድሃኒቱ መገኘት መሯሯጥ ከቀርብ ሆኖ መከተታተል ግድ አለው:: ይህኔ አባት መስፍን ለመትፍሄ ሲል የመረጠው የግል ጥረት ዳር እንደማይደርስ ተረዳ ::
ጅምር ሥራውን ትቶ፣ ከሽመና ጉድጓዱ ወጣ:: ሙሉ ጊዜው ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ሆነ:: የመልካም ሀኪሞች ዓይን የጥሩ ሰዎች ልቦና አልራቀውም:: ችግሩን ያስተዋሉ ቀርበው አዋዩት:: ስለልጁ ጤና ስለራሱ ሁኔታ ሳይደብቅ ተናገረ::
በሆስፒታሉ ዶክተር ሃይለእየሱስ ባገኙት ጊዜም መልካም ተስፋን አሰጨበጡት:: ትንሹን ተመስገንን እያዩ ህመሙ ለክፉ እንደማይሰጠው፣ ወደፊትም የሚተካ ሆኖ ስጋት እንዳማይሆን አበሰሩት:: አባት በመልካሙ፣ በትሁቱ ዶክተር ንግግር ልቡ ሞላ :: ስለ ነገም አሻግሮ ማሰብ ያዘ::
መስፍን መልካሙን ነገር በሰማ ማግስት በልጁ ላይ ሌላ ነገር መከሰቱን አስተዋለ:: ትንሹ ተመስገን እግሩን ሸምቅቆ ይዞታል:: ያለፈበት ህክምናና በእሱ ላይ የሆነበት ህመም ክፉኛ እንደጎዳው ተረዳ:: አንስቶ ለማቀፍ አቅፎ ለማስተኛት ይቸግረው ያዘ:: አሁን ጉልበቱ ላይ መሰራጨት የጀመረው ህመም አፋጣኝ ህክምና ያሻዋል::
መስፍን ዛሬ ላይ ሆኖ በልጁ ላይ ያለፈውን ስቃይ ሲያስታውስ ቀድሞ የተሠራውን የህክምን ክፍተት ተጠያቂ ያደርጋል:: ተመስገን ውሎ አድሮ የከፈለው ዋጋም የጥቂት ባለሙያዎች ግዴለሽነት መሆኑ ይሰማዋል:: አንዳንዴ ‹‹እንዲህ ባይሆን ኖሮ…›› ይሉት ቁጭት በውስጡ ውሎ ያድራል::
እንዲህ በሆነ ጊዜ አብዝቶ ይፈተናል:: ወዲያው ደግሞ በተመስገን ቆሞ መሄድ ፈጣሪውን አመስግኖ ከልቡ ይጽናናል:: ትንሹ ልጅ እስካሁን ለሁለት ጊዚ ኬሞ ቴራፒ ወስዷል:: ህመሙን ተቋቁሙ ለማለፍ እየሞከረ ነው :: ስቃዩ እንደሌሎች ባለመሆኑ መስፍን ደስ ይለዋል::
አባወራው ከትንሹ ልጅ ዓይኑን ባነሳ ቁጥር ትቷቸው የመጣውን ቤተሰቦቹን ያስባል:: እነሱ ሁሌም ከሃሳቡ አይጠፉም:: ብድግ ብሎ እንዳይሄድ የልጁ ጤና ይጎድል ቢመስለው ትካዜ ይገባዋል:: ‹‹በቃ! ይቅር›› እንዳይል ደግሞ የሚሆን አይደለም:: ህክምናው ብዙ እንደሚቆይ አላጣውም:: ልቡ ለሁለት ተከፍሏል::
አሁንም ወጥኖት ስለመጣው ጅምር ሥራ፣ ድንገት ከፍቶት ስለቀረው ጎጆና ስለሌላም እያሰበ ነው:: ትናንት በሽመና የሚያሳድራት ባለቤቱ ዛሬ ከእሱ አንዳች አትጠብቅም:: ሥራ የላትምና ከእጇ ብዙ እንደሚጎድልባት ያውቃል::
ዛሬን…
አባት መስፍን ቤት ጎጆውን፣ ሰፈር ቀዬውን ትቶ አዲስ አበባ ከከተመ ቆይቷል:: የልጁ ህክምና ይቀጥላልና ፈጥኖ መሄድ አልቻለም:: አሁን ላይ እንደትናንቱ በቤት ኪራይ፣ በምግብና የመድሃኒት ግዢ አይቸገርም:: በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ሳለ ያገኛቸው የማቲዎስ ወንዱ ኢትዮጵያ ካንሰር ሶሳይቲ አካላት ለጥያቄው መልስ ሆነዋል::
ዛሬ አባትና ልጅ የእፎይታን ዓለም እያዩ ነው:: የት እናድራለን? ምን እንበላለን? ብለው አያስቡም:: የትንሹ ልጅ ህክምና በወጉ ቀጥሏል:: መድሃኒቱ፣ ክትትሉ ፤ ልዩ ምርመራው ሁሉ ተጓድሎ አያውቅም:: ቤተሰብ በሆኑበት የፍቅር ግቢ ሰሀን ገበታቸው በእኩል ቀርቧል::
አባት መስፍንን ከመሰናበቴ በፊት መልዕክቱን ልቀበለው ግድ ብሎኛል:: ደጋግሞ ቅር ስለተሰኘባቸው ክፉ አጋጣሚዎች ሊደብቀኝ አልፈለገም:: አንዳንዴ በግዴለሽነት ስህተት የሚሰሩ የህክምና ባለሙያዎች ጉዳይ ዝም ሊባል አይገባም ባይ ነው::
እሱ ስለልጁ ብዙ ዋጋ ከፍሎ እዚህ ደርሷል:: ሌሎች ደግሞ በርምጃው ተለክተው እንዳይጓዙ ይፈልጋል:: ባለፈበት ክፉና ደግ አጋጣሚዎች ዕንባውን ያበሱለት፣ ጩኸቱን የሰሙለትን ባለውለታዎች ፈጽሞ አይረሳም:: በተለይ ደግሞ ለማቲዎስ ወንዱ ኢትዮጵያ ካንሰር ሶሳይቲ የተለየ ቦታና አክብሮት ይሰጣል:: ጠንካራው የልጅ አባት መስፍን ጩበሮ::
መልካምሥራ አፈወርቅ
አዲስ ዘመን ቅዳሜ የካቲት 8 ቀን 2017 ዓ.ም