
የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በወሰዱት ጊዜያዊ የርዳታ ማቆም ርምጃ በሃምሳ ሀገራት የኤች አይቪ ሕክምናን ጨምሮ በዓለም ዙሪያ በቢሊዮን የሚቆጠሩ የኤች አይ ቪ፣ የፖሊዮ፣ ኤምፖክስ እና የወፍ ጉንፋን በሽታን ለመከላከል የሚከናወኑ ተግባራት መስተጓጎላቸውን የዓለም ጤና ድርጅት አስታወቀ፡፡
ተመራጩ ፕሬዚዳንት ትራምፕ ከበዓለ ሲመታቸው ጀምሮ አነጋጋሪ ውሳኔዎችን ሲወስኑ እንደነበር ይታወቃል፡፡ የዚህ ውሳኔ አካል ከሆነው ውስጥ የዩኤስ ኤይድ ርዳታ ማቆም አንዱ ነው፡፡ ትራምፕ በርዳታ ድርጅቱ ውስጥ የሚሠሩ አስር ሺህ የሚደርሱ ሠራተኞችን ከመቀነስ ጀምሮ ተቋሙ ይሰጣቸው የነበሩ ዓለም አቀፍ ርዳታዎችን እንዲያቆም ትዕዛዝ ማስተላለፋቸው አይዘነጋም፡፡
ይሄን የትራምፕ ውሳኔ ተከትሎ በዓለም አቀፍ ደረጃ የጤናው ሁኔታ አስጊ ወደ መሆን መምጣቱ ሲገለጽ የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም የተከሰተውን ችግር በመረዳት ሌሎች አማራጮች እስኪገኙ ድረስ የትራምፕ አስተዳደር ድጋፍ ማድረጉን እንዲቀጥል ጥሪ አድርገዋል፡፡ ዋና ዳይሬክተሩ ረዕቡ እለት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፤ በሃምሳ ሀገራት ሲሰጡ የነበሩ የኤች አይቪ ሕክምናን ጨምሮ ሌሎች የጤና አገልግሎት መቋረጣቸውን ተናግረዋል፡፡
ዩኤስ ኤይድ መቋረጥን አስመልክቶ ለመጀመሪያ ጊዜ በጄኔቫ በተካሄደ መግለጫ፤ ‹‹የአሜሪካ መንግሥት እየወሰዳቸው ያሉ ርምጃዎች አሉ፡፡ እነኝህ ርምጃዎች እኛን ስጋት ውስጥ መክተት ብቻ ሳይሆን በዓለም አቀፉ የጤና ሁኔታ ላይ ከፍተኛ ጫና እያሳደሩ ነው›› ሲሉ ተደምጠዋል፡፡ ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም አያያዘውም ለነፍስ አድን አገልግሎት ሲደረግ የነበረው ድጋፍ እንዳይቋረጥ የተደረገው ተማጽኖ ፍሬ አልባ መሆኑንም አንስተዋል፡፡
አሜሪካ በወሰደችው ርምጃ በአሁኑ ሰዓት ክሊኒኮች ተዘግተዋል፡፡ የጤና ባለሙያዎች እረፍት ወጥተዋል፡፡ ርዳታ በመቋረጡ በሽታ ሊስፋፋ እንደሚችል፣ በሂደት ላይ የሚገኙ ተስፋ ሰጪ ክትባቶች እና ምርምሮች ሊስተጓጎሉ እንደሚችሉ፣ አዳዲስ የሕክምና ጥናቶች ቀጣይነት እንዳይኖራቸው ሊያደርግ እንደሚችል የዓለም ጤና ድርጅት ስጋቱን ገልጿል፡፡
ትራምፕ በበኩላቸው፤ ዩኤስ ኤይድን ‹‹ብቃት የሌለው እና ሙሰኛ ነው›› በማለት ሲወርፉት፤ የፕሬዚዳንቱ የቅርብ ወዳጅ እንደሆነ የሚነገርለት ቢሊየነሩ ኢሎን መስክ በበኩሉ ‹‹ወንጀለኛ ድርጅት ነው›› ሲል ተናግሯል፡፡ ሆኖም ሁለቱ ግለሰቦች ተቋሙን እንዲህ ለማለታቸው እስካሁን ምክንያት አላቀረቡም፡፡ ትራምፕ በዚህ ሳያበቁ ሀገራቸው አሜሪካ ከዓለም ጤና ድርጅት አባልነት እንድትወጣ ግፊት እያደረጉ እንደሚገኙም ይታወቃል፡፡
ዩኤስ ኤይድ በዓለም አቀፍ ደረጃ የጤና አገልግሎቱን ለመደገፍ እና ለሰብዓዊ ርዳታ ሲባል እስከ አርባ ቢሊዮን ዶላር የሚጠጋ ገንዘብ የሚያወጣ ሲሆን፤ ይሄም ከጠቅላላው የአሜሪካ መንግሥት ዓመታዊ ወጪ 0.6 በመቶ የሚይዝ ነው፡፡ በቀድሞው ፕሬዚዳንት በባይደን ዘመን አሜሪካ የዚህ ተቋም ዋነኛ ለጋሽ ሀገር ስትሆን፤ በፈረንጆቹ 2023 ከተቋሙ አጠቃላይ በጀት ውስጥ አንድ አምስተኛ የሚሆነውን መሸፈኗ ተገልጿል፡፡
አብዛኛው የተቋሙ የርዳታ ገንዘብ በኢሲያ፣ ከሰሀራ በታች በሚገኙ የአፍሪካ ሀገራት እንዲሁም በአውሮፓ የሚውል ሲሆን፤ አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ በይበልጥ በዩክሬን ውስጥ ባለው ችግር ለሰብዓዊ ድጋፍ እየዋለ እንደሚገኝ ይነገራል፡፡ የአሜሪካ መንግሥት የፌዴራልን ወጪ ለመቀነስ ባስቀመጠው አዲስ መመሪያ መሠረት ዓለም አቀፉ የርዳታ ድርጅት በጊዜያዊነት እንዲቆም መደረጉ አይዘነጋም፡፡
የፕሬዚዳንቱን ውሳኔ ተከትሎ በዓለም የጤና መዋቅር ላይ ከፍተኛ ጫና መድረሱ የታወቀ ሲሆን፤ ይሄንንም ለማርገብ አሜሪካ ውሳኔዋን ዳግም እንድታጤነው ጥሪ ቀርቧል፡፡ የመረጃ ምንጫችን ቢቢሲ ነው፡፡
ዘላለም ተሾመ
አዲስ ዘመን ቅዳሜ የካቲት 8 ቀን 2017 ዓ.ም