በወቅቱ የማይጠናቀቁ ሕንጻዎች የሚያስከትሉት ኪሳራ

ዜና ሀተታ

አዲስ አበባን ጨምሮ በበርካታ ከተሞች በጅምር ዓመታትን ያሳለፉ ሕንጻዎችን ማየት የተለመደ ነው። አንዳንዶቹ መሠረታቸው ተጀምሮ የቀሩ ሲሆን፤ ብዙዎቹ ደግሞ ወደማጠናቀቂያቸው ቢደርሱም ለዓመታትን በቆርቆሮ ታጥረው ይገኛሉ። የእነዚህ ጅምር ሕንጻዎች ያለመጠናቀቅ ብዙ ጉዳቶችንና ኪሳራዎችን ከማስከተላቸው ባሻገር የከተሞች ማራኪነት የሚያሳጡ መሆናቸው ባለሙያዎችና የሥራ ኃላፊዎች ያስረዳሉ::

በኮንስትራክሽን ማኔጅመንት ኢንስቲትዩት የኮንስትራክሽን ማኔጅመንት የማማከርና አሠራር ማሻሻያ መሪ ሥራ አስፈጻሚ ኢንጅነር ጎረምስ በቀለ እንደሚያስረዱት፤ ሕንጻዎች ተጀምረው ላለመጠናቀቃቸው የተለያዩ ምክንያቶች ሊኖሩ ይችላሉ:: ከእነዚህም መካከል ብዙ ጊዜ የሚጠቀሰው ከፍርድ ቤቶች ጋር የተያያዘ ነው። ነገር ግን ምክንያቱ ምንም ይሁን ምን ተጀምሮ ለረጅም ዓመታት ግንባታው የቆመ ሕንጻ የጥራትና ሌሎች ችግሮች እንዲከሰቱ ማድረጉ አይቀርም። የሚደርሰው ኪሳራም ሆነ ሌሎች የጥራት ችግሮች የሚመለከቱት ደግሞ የሕንጻውን ባለቤትና ሥራ ተቋራጩን ብቻ ሳይሆን ሕንጻውን የሚገለገልበትንም አካል ጭምር ነው ይላሉ።

በአሠራር ደረጃም ቢሆን የአንድ ሕንጻ ግንባታ ተቋርጦ የሚጀመር ከሆነ በቅድሚያ ፍተሻ ይደረግበታል። በተለይም የላይኛው አካል ጣራ ሳይለብስ ወይንም ተገቢው የውሃ ስርገት መቆጣጠሪያ ሳይደረግለት ከቆየ፣ የሕንጻው ጥራት ላይ የሚያስከትለው ጉድለት ይኖራል። በመሆኑም ብረቶች አለመዛጋቸው፤ እንዲሁም አጠቃላይ የሕንጻው ደረጃ ምን ያህል እንደተጠበቀ እና ግንባታው ማሻሻያ ሳይደረግበት የመቀጠል እድሉ ምን ያህል እንደሆነ ለመወሰን የላቦራቶሪ ምርመራን ጨምሮ ሌሎችም ፍተሻዎች መደረግ ይኖርበታል ነው ያሉት።

በተጨማሪም የሕንጻ ግንባታ ሲዘገይ የዋጋ ጭማሪ ማስከተሉ አይቀሬ ነው። የዚህን ተጨማሪ ወጪ የሚሸፍነው ደግሞ በተዘዋዋሪ የመጨረሻ ተገልጋዩ መሆኑ አይቀርም። በመንግሥትም በኩል በከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ከውጭ የሚያስገባቸው የግንባታ እቃዎች በወቅቱ ጥቅም ላይ ካልዋሉ እንደሀገር የሚያስከትሉት ኪሳራ ይኖራል።

እንደ ኢንጅነር ጎረምስ ማብራሪያ፣ አንድ ግንባታ ሲከናወን በሕንጻ አዋጁ መሠረት መቼ ተጀምሮ መቼ ሊጠናቀቅ እንደሚገባ የሚቀመጥለት ጊዜ አለ። ይህ የጊዜ ገደብ በባለቤቱ፣ በአማካሪውና በሚቆጣጠረው አካል ይታወቃል። የማንኛውም ሕንጻ ግንባታ ሲከናወን ለግንባታው ፈቃድ የሚሰጠውና በዚያ መሠረት እየተከናወነ መሆኑን የሚከታተልና የሚቆጣጠር፤ ሲጠናቀቅም የመጠቀሚያ ፈቃድ የሚሰጥ አካል አለ። ሕንጻው ለረጅም ዓመታት የቆየ ከሆነ የተሻሻሉ የሕንጻ ኮድ መሠረት በማድረግ ዲዛይኑንም መፈተሽን ያካትታል። ቁጥጥሩ የሚደረገውም በየደረጃው ነው።

ይህ እንደ ከተማ ሲሆን እንደ ፌዴራል ግን የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር ተጠሪ የሆነው የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ባለሥልጣን የሕንጻ አዋጁን ለማስፈጸም የተለያዩ መመሪያዎችንና ደንቦችን በማውጣት ረገድ ይሠራል። ቁጥጥር የሚያደርገው አካል ይህንን ምርመራ ለማድረግ የሚያስችል የሠለጠነ ብቃት ያለው ባለሙያና የላቦራቶሪ መሣሪያ እጥረት ቢገጥመው እንኳ ከዩኒቨርሲቲዎች ጋር በመቀናጀት ሊሠራ እንደሚችል ይገልጻሉ።

በቅርቡ ከተጀመረው ከኮሪደር ልማት ጋር በተያያዘ በየቦታው በጅምር የቀሩ ሕንጻዎችን አገልግሎት እንዲሰጡ በማድረግ ረገድ የተጀመሩ ሥራዎች መኖራቸውን አመልክተው፤ ይህ ሕግን መሠረት ባደረገና የባለቤትነት ድርሻና መብትን ባከበረ መልኩ ተጠናክሮ ሊቀጥል የሚገባውና በአዲስ አበባ ብቻ ሳይሆን በመላው ሀገሪቱ ሊተገበር የሚገባውም እንደሆነም ይገልጻሉ።

በኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ባለሥልጣን የኮንስትራክሽን ፕሮጀክቶች ግንባታ ቁጥጥር መሪ ሥራ አስፈጻሚ ኢንጂነር በረከት ተዘራ በወቅቱ ያልተጠናቀቁ ፕሮጀክቶች ደረጃቸው ቢለያይም ችግር መፍጠራቸው እንደማይቀር ይገልጻሉ። ግንባታቸው ተጀምሮ ለረዥም ጊዜያት የቆሙ ፕሮጀክቶች ከሚያስከትሏቸው ችግሮች መካከል የወጪ መጨመር፣ የጥራት መጓደል እና ለማህበረሰቡ መስጠት ያለባቸውን አገልግሎት በወቅቱ አለመስጠት ይጠቀሳሉ። የትኛውም የሕንጻ ግንባታ ወይንም ፕሮጀክት በተቀመጠለት የጊዜ ገደብ ካላለቀ የዋጋ ጭማሪ መኖሩ አይቀርም። ለዚህ ምክንያት የሚሆነው ባለቤቱ ግንባታውን የሚያካሂደው አካል ወይንም አማካሪው ሊሆን ይችላል ይላሉ።

በዋጋ ረገድ የሚከሰተው ጭማሪ በቀጥታ ግንባታውን የሚያከናውነውን አካል ላይመለከት ይችላል። ለምሳሌ አንድ የጋራ መኖሪያ ቤቶችን የሚገነባ አካል ግንባታውን ለረጅም ጊዜ ሲያቆየው የሚከሰተውን የዋጋ ጭማሪ ሕንጻውን በሽያጭም ሆነ በኪራይ ወደ ሚያስተላልፍላቸው አካላት መሄዱ አይቀርም የሚሉት ባለሙያው፤ በተጨማሪም እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ለግንባታ አገልግሎት የሚውሉ ከውጭ የሚገቡ ቁሳቁሶች ጥቅም ላይ ይውሉ ስለነበር እንደ ሀገር በውጭ ምንዛሬ ላይ የሚያሳድረው ተጽእኖም ነበር። በአሁኑ ወቅት ግን ከውጭ የሚገቡ ግብዓቶችን በሀገር ውስጥ ምርት ለመተካት የሚያስችል ፖሊሲ ተቀርጾ በሀገር አቀፍ ደረጃ እየተተገበረ ይገኛል ነው ያሉት።

ከውጭ የሚገቡ የኮንስትራክሽን ግብዓቶችን ሊተኩ የሚችሉ ደረጃቸውንና ጥራታቸውን የጠበቁ ምርቶች በኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ባለሥልጣን በኩል ግምገማ ይደረግባቸዋል። በዚህም መሠረት እንደ ሴራሚክ፤ የኤሌክትሪክ ገመድ፤ የፍሳሽ ማስወገጃ ቱቦ (ፒፒሲ) የመሳሰሉት መስፈርቱን አሟልተው ሲገኙ በአስገዳጅ ጥቅም ላይ እንዲውሉ እየተደረገ በመሆኑ በዚህ ረገድ ያለው ችግር ከሞላ ጎደል መፍትሄ እያገኘ እንደሆነ ያብራራሉ።

ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ የትኛውም ግንባታ ሲከናወን የዋጋ ግሽበት ሊኖር ስለሚችል በአዋጅ የተቀመጠ የክፍያ ማስተካከያ ሥርዓት በመኖሩ በዚያ መሠረት ማስተካከያ ይደረጋል። ይህ የዋጋ ማስተካከያ ተደራሽ የሚያደርጋቸው ፕሮጀክቶች ግን ከአንድ ዓመት በላይ የቆዩ ነገር ግን የተሰጣቸውን ሥራ በአግባቡ ለሚሠሩ ተቋራጮች ብቻ የሚሠራ ነው። ሌሎቹን ግን የዋጋ ማስተካከያው አይመለከታቸውም ብቻ ሳይሆን ግንባታውን በወቅቱ ካላጠናቀቁ ተጨማሪ ቅጣት ተጥሎባቸው የቀረውን አካክሰው ሥራውን እንዲጨርሱ የሚደረግ እንደሚሆንም ነው የጠቆሙት።

የጥራት መጓደል በሕንጻዎች በወቅቱ አለመጠናቀቅ ምክንያት የሚመጣ ሌላው ጉዳት ነው። ጥራትን በተመለከተ በግንባታ ወቅትም ይሁን ግንባታው ከተቋረጠ በኋላ የተቀመጠለትን የዲዛይን ደረጃ ያላሟላ ፕሮጀክት በአስገዳጅነት እንዲቋረጥ እንደሚደረግ ገልጸው፤ በተለይም የሕንጻው ግንባታ ለዓመታት ተቋርጦ ከቆየና ሕንጻው የተገነባባቸው ብረቶች በተገቢው መንገድ ካልተሸፈኑ ዝናብና አየር በቀላሉ ስለሚያገኛቸው ጥንካሬያቸውን ማጣታቸው አይቀርም። በመሆኑም በማንኛውም ሁኔታ ግንባታው ተቋርጦ የቆየ ሕንጻ እንዲቀጥል ከተፈለገ የጥራት ፍተሻ ይደረግለታል። በዚህም ግንባታው ችግር ከተገኘበት እንደገና ፈርሶ ተስተካክሎ እንዲሠራ ይደረጋል ነው ያሉት።

ከላይ የተነሱት ችግሮች በቀጥታ ከሕንጻው ጋር በተያያዘ የሚከሰቱ ችግሮች ሲሆኑ በተጨማሪ የከተማ ውበት መበላሸት፤ መሬት ያለ አገልግሎት መያዝ እና በአንዳንድ ቦታዎች በሰዎች ላይ የሚከሰቱ አካላዊ አደጋዎችም ይኖራሉ። መስጠት የሚኖርበትን ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ማሳጣት ሌላው ችግር ነው:: ከዚህ መነሻነት የሕንጻ ግንባታ ቁጥጥር ሥራ የሚከናወነው እነዚህን ሁሉ ጉዳዮች ከግምት ባስገባ መልኩ እንደሚሆን አመልክተዋል።

በቅርቡ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የጸደቀው የንብረት ታክስ አዋጁ ዓላማው ጥቅም ላይ ያልዋለን ሀብት ጥቅም ላይ እንዲውል በማድረግ ለሀገሪቱ ልማትና እድገት አስተዋጽኦ እንዲያበረክት ማስቻል ነው:: ሰፊ ቦታ ይዘው ያለሥራ ያስቀመጡና ግንባታቸው ለረጅም ጊዜ ተቋርጦ የቆዩ ሕንጻዎች፣ ሕንጻ ገንብተው ሳያከራዩ ያስቀመጡ ሰዎች ከፍተኛውን የንብረት ታክስ ክፍያ እንዲከፍሉ የሚያደርግ መሆኑ ታውቋል::

ራስወርቅ ሙሉጌታ

አዲስ ዘመን ቅዳሜ የካቲት 8 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You