
የአፍሪካ አንድነት ድርጅት በ1963 ዓ.ም እውን ሲሆን፣ “አሕጉሩን ከቅኝ እና ከአፓርታይድ አገዛዞች ፈፅሞ ማላቀቅ፤ በአፍሪካ ሀገራት መካከል አንድነትን እና ወዳጅነትን ማጠናከር፤ ለልማት የሚደረገውን ትብብር ማጠናከር፤ የአባል ሀገራትን ሉዓላዊነት እና የግዛት አንድነት እንዲሁም ዓለም አቀፍ ትብብር ማጠናከር፤” የሚሉ አንኳር ዓላማዎችን ይዞ ነበር::
የወቅቱ 32 ነጻ ሀገራትን ያሳተፈው የአፍሪካ አንድነት ምሥረታ ሂደት፤ ለቀናት ከፍ ያለ ውይይት የተደረገበት ሲሆን፤ በወቅቱም በሁለት ጎራ ተከፍሎ የነበረውን የአፍሪካ ሀገራት ጉዳይ ወደ አንድ እንዲመጣ ያደረጉት የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት አጼ ኃይለሥላሴ፣ የወቅቱ የሊቀመንበርነት መንበሩ በሙሉ ድምጽ ነበር የተሰጣቸው:: በተደረገው ትልቅ ውይይት እና በወቅቱ ሊቀመንበር ከፍ ያለ ሚናም ግንቦት 25 ቀን 1963 ዓ.ም የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ቻርተር በመሪዎች ተፈርሞ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ተመሠረተ።
በጊዜውም የአፍሪካ አንድነት ድርጅት 32 ነፃ ሀገራት መሪዎች እና ተወካዮች በተገኙበት አዲስ አበባ ላይ ሲመሠረት ንግግር ያደረጉት አፄ ኃይለሥላሴ፣“ከጥቂት ዓመታት በፊት የአፍሪካ ችግሮች ከአፍሪካ ውጪ አፍሪካውያን ባልሆኑ ወገኖች ውሳኔ ይሰጥበት ነበር፣ ዛሬ አፍሪካውያን ጉዳያቸውን በራሳቸው የሚመክሩበት እድል በዚህ ኮንፈረንስ ተፈጥሯል::” ሲሉ ተደምጠው ነበር::
ይሄ የአጼ ኃይለሥላሴ ንግግርም ሆነ በመመሥረቻ ሰነዱ ላይ የተመላከቱት አንኳር ዓላማዎች ታዲያ፤ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት አፍሪካዊ ተቋም ሆኖ እንዲገለጥ የማስቻል ከፍ ያለ ርዕይን የሚያመላከቱ ናቸው:: ይሄ አፍሪካዊ ተቋም ደግሞ ለአፍሪካውያን ነጻነት፣ ሕብረትና ልዕልና የሚተጋ እንዲሆን፤ አፍሪካውያንም በተቋማቸው ታግዘው ከጭቆና ወደ ነጻነት፤ ከመከፋፈል ወደ አንድነት፤ ከመናጠቅና ከመጣላት ወደ መተባበርና ፍቅር፤ ከድህነት ወደ ብልጽግና፣… እንዲሸጋገሩ የማስቻል ሕልምና ርዕይ ነው::
ለዚህ ደግሞ በመሠረታዊነት አራት ጉዳዮችን እንመልከት:: አንደኛው፣ አፍሪካን ከቅኝ እና ከአፓርታይድ አገዛዞች ፈፅሞ ማላቀቅ ነው:: በዚህ ረገድ፣ ዛሬ ላይ አንድም አፍሪካዊ ሀገር በቅኝ ገዢዎች መዳፍ ውስጥ አለመኖሩን ማረጋገጥ ይቻላል:: ምክንያቱም ኢትዮጵያ ባቀጣጠለችው ወራሪዎችን ድል የመንሳት ብርሃን ተመርተው፤ በአፍሪካ አንድነት ድርጅት ሕልም ታግዘው አፍሪካውያን ዛሬ ላይ ነጻ ሀገርነታቸውን አረጋግጠዋል:: ይሄን ሕልም ከማሳካት አኳያ ተቋማዊ ጉዞው የተሳካ ነበር::
ሁለተኛው ጉዳይ፣ የአባል ሀገራትን ሉዓላዊነት እና የግዛት አንድነት እንዲሁም ዓለም አቀፍ ትብብር ማጠናከር የሚለው ሲሆን፤ ይሄም ከመጀመሪያው ጉዳይ እምብዛም የተለየ ሳይሆን፣ ሀገራቱን ከቅኝ ግዛት ቀንበር ከማላቀቅ ባሻገር ወደተሟላ ሉዓላዊነት እና የግዛት አንድነት እንዲሸጋገሩ ማስቻልን ታላሚ ያደረገ ነው:: ይሄኛው ሀገራቱን ከቅኝ ገዥዎች ነጻ እንደማውጣቱ ይሄኛው ቀላል አልነበረም::
ምክንያቱም፣ በአንድ በኩል የግዛት አንድነት ጉዳይ አለ:: ይሄ ደግሞ በተለያዩ ፍላጎቶች (በውስጥም በውጪም) ምክንያት አፍሪካውያን ዛሬም ድረስ የጠነከረ የግዛት አንድነታቸውን ማስከበር ያልቻሉ ሀገራት ጥቂት አይደሉም:: ዛሬም ድረስ ከአንድ ወደ ሁለት እየተከፈሉ፤ በውጭ ኃይሎች ጣልቃ ገብነት እየተሸራረፉ ያሉ ሀገራት ተበራክተዋል:: በየቦታው የጦር መሣሪያ ድምጽ የሚያጓራባት አሕጉር የሆነችውም ይሄንኑ የግዛት አንድነት በማጽናትና በመናድ መካከል በሚደረግ ትግል ነው::
የሉዓላዊነት ጉዳይም እንዲሁ ነው:: ሉዓላዊነት አንድ ዘርፍ አይደለም:: ሉዓላዊነት ከድንበር፣ ከፖለቲካ አስተሳሰብ፣ ከኢኮኖሚ፣ ከማህበራዊ ጫና፣ ከሥነልቡናዊ ልዕልና፣ ከፖሊሲ ጥገኝነትና ሌሎችም ጉዳዮች ጋር በተያያዘ ነጻ መሆንን ይመለከታል:: የቀደምቶቹም የሉዓላዊነት እሳቤ ከዚሁ ጋር የተቆራኘ ነው:: እናም አፍሪካ ከቅኝ ገዢዎች ነጻ ብትሆንም፤ ከፖለቲካ አጀንዳ ተሸካሚነት፣ ከፖሊሲ ጉዳዮች ፈጻሚነት፣ ከኢኮኖሚ ጥገኝነትና ሌሎችም የሉዓላዊነት ጉዳዮች ያልተላቀቀች መሆኗ እሙን ነው::
አፍሪካ እና አፍሪካውያን ቀደምቶቻችን እንዳሰቡት ሁሉ የአባል ሀገራቱን ሉዓላዊነት እና የግዛት አንድነት እንዲሁም ዓለም አቀፍ ትብብር በማጠናከር ውስጥ የሚመጣ ምሉዕ የሆነ ሉዓላዊነትን እንዲጎናጸፉ ያስፈልጋል:: ምክንያቱም ምሉዕ ሉዓላዊነትን ያልተጎናጸፈ ሀገር ምንጊዜም ቢሆን ነጻ ሊሆን ስለማይችል፤ የአፍሪካውያን ቀጣይ እጣ ፈንታና ልዕልና ይሄን እውን ማድረግ በመቻል እና ባለመቻል ውስጥ የሚወሰን ይሆናል:: ምክንያቱም ነጻ ሀገርና አሕጉር ነው ዓለምአቀፍ ትብብርና ዲፕሎማሲያዊ ስኬቶችን እንዲሁም ተጽዕኖ ፈጣሪነትን መላበስ የሚችለው::
ይሄን እውን ከማድረግ አኳያ ሌላው የሚነሳው ሦስተኛው ጉዳይ ደግሞ፣ በአፍሪካ ሀገራት መካከል አንድነትን እና ወዳጅነትን ማጠናከር የሚለው ነው:: ይሄኛ ገና ከመጀመሪያው የሞኖሮቪያ እና ካዛቭላንካ በሚል ጎራ ለይቶ የሚግባባ የማይመስለውን አፍሪካዊ የቅኝ ግዛት እሳቤ ታሳሪነት ነጻ የማውጣት የኢትዮጵያን ሚና ታሳቢ ያደረገ ነው:: ከድርጅቱ ምሥረታ በኋላም መሰል መከፋፈሎች እንዳይኖሩ፣ አፍሪካውያን የአንድ አሕጉር ሕዝቦች፣ የጋራ የልማትና ብልጽግና ሕልውና ያላቸው ሀገራት መሆናቸውን ተገንዝበው፤ ሀገራቱ በወንድማማችነት እና ወዳጅነት ስሜት በአንድ እንዲቆሙ፤ ጠንክረውም እንዲታዩ ማድረግ ሕልም ነው::
ከዚህ አኳያ፣ አፍሪካውያን ወንድማማችነታቸውን አምነው እንዲቀበሉ ማድረግ ተችሏል:: ወዳጅነታቸውም እንዲጠናከር ከፍ ያሉ ሥራዎች በወቅቱ ተሠርተዋል:: ይሁን እንጂ ይሄ የአንድነትና ወዳጅነት ሕልም የቀደሙቱ የአንድነት ድርጅቱን የመሠረቱት መሪዎች ባስቀመጡት ልክ አፍሪካውያን ተላብሰውታል ለማለት ግን ልብ የሚሞላ አይሆንም::
ለዚህም ነው ዛሬ አፍሪካውያን በአንድም በሌላ መልኩ እርስ በእርስ መገፋፋት፤ መዋጋት፣ በዙፋን ነቅናቂነትና ተነቅናቂነት መንፈስ (ገዢና አማጺ ስሜትና ተግባር) ውስጥ መዳከር መገለጫቸው የሆነው:: ለዚህም ነው አፍሪካ ዛሬም ድረስ የጦርነት እና የስደት ማዕከል ሆና የምትገለጠው:: ለዚህ ነው ዛሬም፣ አንግሎ ፎን፣ ፍራንኮ ፎን፣… እየተባለ በሕብረቱ መድረክ ሳይቀር ከአንድነቱ ይልቅ ልዩነትን ለማጉላት ሲሞከር የሚስተዋለው::
ይሄ ወዳጅነትና አንድነቱ በሚፈለገው ልክ ያለመጠናከሩ፤ አፍሪካውያን እንደ ሕዝብ አፍሪካም እንደ አሕጉር ዛሬ ላይ በዓለም መድረክ ጠንካራ ሕዝብ እና አሕጉር ሆነው እንዳይታዩ አድርጓቸዋል:: የዚህ አብይ ማሳያ መጥቀስ ካስፈለገም፣ የአፍሪካና አፍሪካውያን ጠንካራ ሆኖ አለመውጣት በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ውስጥ ሳይቀር ይሄ ነው የሚባል ተጽዕኖ መፍጠር የሚያስችል ቦታ አላገኙም::
በፀጥታው ምክር ቤት ውስጥ እንኳን ቢሆን አፍሪካ በአፍሪካ ሀገራት በየተራ ከሚደርሳቸው የተለዋጭ አባልነት ያለፈ ቦታ የላትም:: ለዚህም ነው ዛሬ ላይ አፍሪካ በምክር ቤቱ ውስጥ የቬቶ ፓወር ባለቤትነቷ ቀርቶ የቋሚ መቀመጫን ቦታ ለማግኘት እንደ አዲስ ገቢ እንግዳ በመማጸን ላይ የምትገኘው::
በአራተኛነት የሚታየው አንኳር ነጥብ፣ አፍሪካን እንደ አሕጉር ለማበልጸግ በሚደረገው ጥረት ውስጥ ለልማት የሚደረገውን ትብብር የማጠናከር ጉዳይ ነው:: ቀደም ሲል የተጠቀሱት ጉዳዮችን ለማጠናከርና ለማጽናት የሚያስችል መሠረታዊ መርህና የቀደምቶቹ ሕልም ነው:: ምክንያቱም፣ ነጻነትም የሚጸናው፣ ሉዓላዊነትም ምሉዕ የሚሆነው፣ ዓለምአቀፋዊ ትብብርና ግንኙነቱም ሚዛን የሚጠብቀው እንደ አሕጉር ያለንን አቅም አስተባብሮ የልማት አቅም ማድረግና መበልጸግ ሲቻል ነው::
ከዚህ አኳያ ጅምሮች የጭላንጭል ያህል ይታዩ ይሆን እንጂ የተሠራ ሥራ አለ ብሎ መናገር አያስችልም:: ይሄ ባለመሆኑም ነው ዛሬ ላይ አፍሪካ ከአንድ ነጥብ ሦስት ቢሊዮን በላይ (ያውም ከ 70 በመቶ የሚልቀው አምራች የሆነ የወጣት ኃይል) ሕዝብ ይዛ፣ እምቅ የተፈጥሮ ሀብትና ፀጋን ተጎናጽፋ ስታበቃ በድህነት ገጿ የምትሳለው፤ ለልመናና ርዳታም እጆቿን የምትዘረጋው::
ይሄ የሆነው ደግሞ በሀገራቱ መካከል የትብብር መንፈስ ያለመፈጠሩ ነው:: ምክንያቱ ደግሞ አፍሪካውያን በቅኝ ገዥዎች አካላዊ ግዞት ነጻ ወጡ እንጂ ዛሬም የተሟላ ነጻነታቸውን ተጎናጽፈዋል በሚያስብል ደረጃ ባለመገለጻቸው ነው:: ይሄ የተሟላ ነጻነት ያለመኖሩ ደግሞ ሀገራቱ በራሳቸው ፍላጎትና ውሳኔ እርስ በእርሳቸው እንዲተባበሩና እንዲያድጉ የሚችሉበትን ልዕልና ነጥቋቸዋል::
ለዚህም ነው አፍሪካውያን ለመተባበርና አብሮ ለመሥራት ያልቻሉት:: ለዚህም ነው የቀድሞ ቅኝ ገዥዎቻቸው የእጅ አዙር ጥቅምና ፍላጎት ተጭኗቸው የሚታዩት:: ለዚህም ነው በቅኝ ግዛት ውሎች ማዕቀፍ ውስጥ ራሳቸውን ቀንብበው ሊገኙ እና የራሳቸውን ዘመን ሕግና አሠራር ፈጥረው ለመራመድ ሲቸገሩ የሚታዩት:: ለዚህ ነው አይደለም በጋራ ሀብትና አቅምን አሰባስቦ ለማልማትና ለመጠቀም ቀርቶ፤ ለራስ እንኳን አልምቶ ለመጠቀም በሚያደርጉት ጥረት በተለያየ ምክንያት በሚፈጠር ጫና እግር ተወርች በሚያስር ችግር ውስጥ እንዲገቡና ከልማት ፊታቸውን እንዲያነሱ እየሆኑ ያሉት::
በዚህ መልኩ አያሌ ምክንያቶችንና ማሳያዎችን መጥቀስ ይቻላል:: ግን ጉዳዩ ችግሮችን መዘርዘር ሳይሆን ከችግሮቹ መውጫውን መጠቆምና ማስገንዝቡ ይሆናል:: ሆኖም የችግሩ መውጫ መንገድ አፍሪካውያን የአንድነት ድርጅታቸውን ሲመሠርቱ በፈረሙት የስምምነት ሰነዳቸው ላይ አስፍረው አኑረውታል:: እናም እሱን ማየት እና ማላቅ የችግሩ መውጫ መንገድ ይሆናል::
ለምሳሌ፣ ኢትዮጵያ እንደ ሀገር ቀደም ሲል የነበራትን የነጻ አሕጉርና ሀገር እውን የማድረግ ሚና አሁንም አስቀጥላ ትገኛለች:: ይሄ ማለት አፍሪካውያን ነጻነታቸው ምሉዕ እንዲሆን፤ ትብብርና ወንድማማችነታቸው ከፍ ብሎ እንዲገለጥ፤ ሀብትና ፀጋቸውን ተጠቅመው እንዲበለጽጉ የማድረግ ከፍ ያለ ኃላፊነትን እየተወጣች ትገኛለች::
በዚህ በኩል፣ በቅኝ ገዢዎች ውል መሠረት ብቻ እንዲጓዝ እና የወል ሀብት የሆነውን የዓባይ ወንዝ የተፋሰሱ ሀገራት የበይ ተመልካች የሆኑበትን አካሄድ በመቀየር ሁሉም ከውሃው ተጠቃሚ የሚሆኑበትን መንገድ ቀይሳ አሳይታለች:: በዚህም ዓባይ የጥቂቶች ሳይሆን የሁሉም የሚሆንበትን አዲስ ምዕራፍ ከፍቷል:: ለኢትዮጵያም ለአካባቢውም መብራት መሆን ጀምሯል:: ይሄ አንዱ ለልማት መተባበርን አስፈላጊነት የሚያሳይ ነው::
ከዚህ በተጓዳኝ፣ በመሠረተ ልማት (በመንገድ፣ በባቡር፣ በውሃ፣…) የማስተሳሰርና የቀጣናው ብሎም የአሕጉሪቱ ሕዝቦች በጋራ የሚበለጽጉበትን ከፍ ያለ ሥራ እያከናወነች ነው:: በዚህ በኩል እንደ አፍሪካ ሕብረት የተቀመጠ የአጀንዳ 2063ን ከማሳካት አኳያ ጉልህ አበርክቶ ያላቸውን ሥራዎች ነው እየከወነች ያለችው:: የባሕር በር የማግኘት ሕልምና ጅምር ስኬቶቿም የዚሁ የባከኑ ሀብቶችን በጋራ አልምቶ የመልማት የቀደምቶች እሳቤ ውጤት ነው::
እነዚህ እና ሌሎችም የሕብረቱ ጅማሬ በአንድነት ድርጅቱ እሳቤ ውስጥ የተጠነሰሱ፤ በዓመታት ሂደትም እየተሞካከሩ የቀጠሉ ናቸው:: ዛሬም ከአንድነት ድርጅቱ የተላለፈውን አደራ በሕብረቱ የአጀንዳ 2063 ግቦች ታግዞ ለማሳካት ወጥኖ ወደ ትግበራ የገባባቸው ናቸው:: ይሁን እንጂ በተቀመጠው ግብ ልክ እየተጓዘ ነው ለማለት አፍን ሞልቶ የሚያናግር አይሆንም::
ምክንያቱም ብዙ ግብ ተቀምጦላቸው እንዲሳኩ የታሰቡ ጉዳዮች ሳይሳኩ ቀርተዋል:: ለምሳሌ፣ አፍሪካን ከጥይት ድምጽ ነጻ የማድረግ ግብ ተቀመጠ፤ ግን ሳይሳካ እነሆ ጊዜው አልፏል:: ሌላው ቀርቶ የሕብረቱ ኮሚሽን ዛሬም ድረስ ራሱን በራሱ በጀት ደጉሞ መሥራት የሚችልበትን ግማሽ አቅም እንኳን መፍጠር አልቻለም::
እነዚህን እና ሌሎች ነጥቦችን መመልከት ከተቻለ ደግሞ፣ የአፍሪካ ሕብረት እንደ ተቋም፤ የአፍሪካውያን መሪዎችም እንደ መሪ በቀጣይ አሕጉሪቱን የሚመጥን፤ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ምሥረታ ያስቀመጠውን ዓላማ የሚያሳካ ተግባርን መከወን ይጠበቅባቸዋል:: ከዚህ አኳያ 38ኛ የሕብረቱ ጉባዔ ዘርፈ ብዙ አጀንዳዎችን አንስቶ ከፍ ያሉ ውሳኔዎችን ማስቀመጥና ለተግባራዊነቱም መተባበርን ያስቀደመ መንገድ መቀየስ ይኖርበታል::
ምክንያቱም፣ የአንድነት ድርጅቱ መሥራቾች የአሁኑ የሕብረቱ መሪዎች አባቶች ናቸው:: ሕልምና ግብ ደግሞ አንድ ቦታ ተጀምረው አንድ ቦታ የሚያልቁ አይደሉም:: ይልቁንም ከፍ ያሉ ሕልሞች በዓመታት ውስጥ የሚፈቱ፤ የትውልዶችን ያልተቆራረጠ አረዳድና ትግበራ የሚፈልጉ ናቸው:: የአፍሪካ አንድነት ድርጅት መሥራች አባቶችም ሕልምና ትልሞች እንዲሁ ናቸው::
በእነሱ ከፍ ያለ እሳቤ አፍሪካንና አፍሪካውያንን ሙሉ ነጻነትና ሉዓላዊነትን የማጎናጸፍ ግብን አስቀመጡ:: ጊዜና እድሜ የፈቀደላቸው ድረስ ተጉዘውም አፍሪካን ከቅኝ አገዛዝ ነጻ አወጡ፤ ሉዓላዊ ወሰንና የግዛት አንድነትንም አስጠበቁ:: ግና የኢኮኖሚ ነጻነትን ከማጎናጸፍ፤ የማህበራዊና ዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ሂደትን ሳያጠናቅቁ ጊዜና እድሜ ቀደማቸው:: እናም ዓላማቸውን እንዲያሳኩ፤ ሕልማቸውን እንዲፈቱላቸው ለተተኪዎቻቸው አደራውን አኑረዋል::
ለዚህም ነው ዛሬ ላይ የአፍሪካ ሕብረት ከፍ ያለ የቀደምቶቹ አደራን የመወጣት ኃላፊነት አለበት የሚባለው:: የአንድ ገጹ ያጠናቀቁትን ነጻነት ወደ ሙላት ማሸጋገር፤ የዴሞክራሲ እና ማሕበራዊ ሥርዓት ግንባታን እውን ማድረግ፤ አፍሪካውያን ሕልውናቸውና ብልጽግናቸው ከውጭ የሚቸራቸው ሳይሆን፤ በራሳቸው አቅምና ሥራ ልክ የሚወሰን መሆኑን ተገንዝቦና አስገንዝቦ መሥራት ከዛሬዎቹ መሪዎች፤ ከዛሬውም አፍሪካዊ ተቋም ይጠበቃል::
ኢትዮጵያም እንደ እስካሁኑ ሁሉ በአፍሪካ አንድነት ድርጅት ምሥረታ የነበራትን ታሪካዊ የመሪነት ሚና ማጎልበት፤ አፍሪካውያን የነጻነትና ሉዓላዊነት አርነታቸውን እውን የሚያደርጉት በማንም ምንዳ ሳይሆን በራሳቸው ፀጋ መሆኑን የማስገንዘብ እና ለዚሁ ዓላማ የማስተባበር ድርሻን ልታጠናክር ይገባል:: ለዚህም ከቅኝ ግዛት እንዲላቀቁ የአሸናፊነት ምሳሌ እንደሆነች ሁሉ፤ አሁንም የኢኮኖሚ ነጻነታቸውን እንዲያረጋግጡ በዓባይ ግድብ እና በሌሎችም ያሳየችውን ስኬት አብነት አድርጋ መሥራት ይኖርባታል::
አሁን ላይ ከፍ አድርጋ የያዘችው የባሕር በር ባለቤትነት ጥያቄዋ መልስ ማግኘትም የሚኖረውን ቀጣናዊ ብሎም አሕጉራዊ አበርክቶ ማብራራት ይጠበቅባታል:: ምክንያቱም ይሄን መሰሉ አካሄድና አሠራር ለአፍሪካ እና አፍሪካውያን ልዕልና ከሚመኝና ከሚተጋ ኃይል የሚጠበቅ ነው:: እናም የአፍሪካ ሕብረት በጉባዔውም የቀደምቶቹን (የአፍሪካ አንድነት ድርጅትን) ሕልሞች በልካቸው ተገንዝቦ፤ የኢትዮጵያንም መንገድ ተረድቶ ለአህጉሪቱ ሉዓላዊነት ምሉዕ መሆን በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ አተኩሮ መሥራት ያስፈልጋል::
በየኔነው ስሻው
አዲስ ዘመን ቅዳሜ የካቲት 8 ቀን 2017 ዓ.ም