
አዲስ አበባ፡- እንደ ሀገር የነበሩትን 48 የደም ባንኮች ወደ 54 በማሳደግ በበጀት ዓመቱ ስድስት ወራት የተሰበሰበው የደም መጠን ከባለፈው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር ጭማሪ እንዳሳየ የብሔራዊ ደምና ህብረህዋስ ባንክ አገልግሎት አስታወቀ::
የብሔራዊ ደምና ህብረህዋስ ባንክ አገልግሎት ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ሀብታሙ ታዬ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት፤ በተያዘው በጀት ዓመት በኦሮሚያ እና ሶማሌ ክልሎች ስድስት ባንኮችን በመጨመር ቀደም ሲል የነበሩትን 48 የደም ባንኮች 54 ማድረስ ተችሏል:: በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያው ግማሽ ዓመት 240 ሺህ ዩኒት ደም ለመሰብሰብ ታቅዶ 217 ሺህ ዩኒት ደም ተሰብስቧል:: በዚህም ተቋሙ የእቅዱን 90 በመቶ ማሳካት ችሏል::
በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያዎቹ ስድስት ወራት የተሰበሰበው የደም መጠን ከባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ48 ሺህ ዩኒት ደም ብልጫ እንዳለውም ገልጸዋል፤ ከአዲስ አበባ ከተማ ብቻ 55 ሺህ ዩኒት ደም እንደተሰበሰበና ይህም ከባለፈው ዓመት አንጻር 10 ሺህ ዩኒት ብልጫ እንዳለው አስረድተዋል::
የተሰበሰበው ደም ከባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት አንጻር ሲታይ ብልጫ እንዲኖረው ያስቻለው አንዱ ምክንያት በሀገር አቀፍ ደረጃ የነበሩት የደም ባንኮችን ቁጥር መጨመር በመቻሉ እንደሆነ ጠቅሰዋል:: የሰላምና ጸጥታ ሁኔታው ከባለፈው ዓመት በተወሰነ መልኩ መሻሻል ማሳየቱ እና የኅብረተሰቡን ግንዛቤ ለማሳደግ የተሠራው ሥራ ለተሰበሰበው ደም መጨመር በተከታታይነት የሚጠቀሱ አስቻይ ምክንያቶች እንደሆኑም ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ ተናግረዋል::
በበጀት ዓመቱ በአጠቃላይ ለመሰብሰብ የታደው 513 ሺህ ዩኒት ደም መሆኑን የገለጹት አቶ ሃብታሙ፤ ከተቀመጠው እቅድ አንጻር ለመሰብሰብ የሚቀረው የደም መጠን በርካታ ነው ብለዋል:: ቀጣይ የጾም ወራት መሆናቸውን ተከትሎ የደም ለጋሾች ቁጥር ሊቀንስ እንደሚችል ጠቅሰው፤ በቀሪ ጊዜያቶች የቅስቀሳ ሥራው ተጠናክሮ እንዲቀጥል አቅጣጫ መቀመጡን አመላክተዋል::
በጾም ወራት ምክንያት የደም እጥረት እንዳይከሰት ለአንድ ወር የሚቆይ የጎዳና ላይ ቅስቀሳ እንደሚደረግ ጠቁመው፤ ማህበረሰቡ የዓብይ እና የረመዳን የጾም ወቅቶችን በደም ልገሳ እንዲያሳልፍ መልእክት አስተላልፈዋል::
የማህበረሰቡ የግንዛቤ ደረጃ እንዲያድግ የተለያዩ ቅስቀሳዎችና የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርቶች እየተሰጡ ስለመሆኑም ተናግረዋል:: በትምህርት ቤቶች፣ በሚዲያ አማራጮች እና በወጣቶች ማህበር በኩል በርካታ ሥራዎች እየተሠሩ እንደሚገኙም ጠቅሰው፤ በዚህም ምክንያት የደም ለጋሾች መጠን ከቀን ወደ ቀን እየጨመረ ይገኛል ብለዋል:: በገጠሩ ማህበረሰብ ዘንድ ሰፊ ግንዛቤ በመፍጠር የደም ልገሳን እንደ ሀገር ባህል አድርጎ ለመቀጠል ግምገማ እየተደረገ ተጨባጭ ለውጥ እንዲመጣ ጥረት እየተደረገ ስለመሆኑ አስረድተዋል::
ደም ከሰው ልጅ የሚገኝ ሕይወት አድን የሕክምና ግብዓት ነው ያሉት ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ፤ ማህበረሰቡ በራሱ ፈቃድ ደም በመለገስ ወገኖቹን እንዲታደግ ጥሪ አቅርበዋል::
ዓመለወርቅ ከበደ
አዲስ ዘመን ቅዳሜ የካቲት 8 ቀን 2017 ዓ.ም