
በኢትዮጵያ በመንግሥትም ሆነ በግሉ ዘርፍ የሚከናወኑ የኮንስትራክሽን ሥራዎች በዓይነትም በብዛትም እየጨመሩ መጥተዋል። የኮንስትራክሽን ዘርፉ እንደቀደሙት ጊዜያት በድምሩ ህንጻዎችን፣ መንገዶችን እና የመሳሰሉ ብቻ አይደለም እየገነባ ያለው:: ረዣዥም /ሰማይ ጠቀስ/ እንዲሁም ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያላቸው ህንጻዎች፣ የፍጥነት መንገዶች፣ የባቡር ሃዲዶች ወዘተ እየተገነቡበት ነው:: እንደ ዓባይ ግድብ ያሉ ግዙፍ ፕሮጀክቶችን መገንባት የተቻለበትም ነው።
በአሁኑ ወቅትም በመላው ሀገሪቱ በስፋት እየተከናወነ ባለው የኮሪደር ልማት የከተሞች መልሶ ልማት በስፋት እየተካሄደ ይገኛል:: ልማቱ ስማርት ከተሞችን እውን ማድረግንም ጭምር ያካተተና፣ በከተሞች ሲታይ የቆየው ስር የሰደደ የመሠረተ ልማት ችግር የሚፈታበትና የተቀናጀ መሠረተ ልማት ግንባታ የሚካሄድበት ነው:: ዘርፉ እያደገ እንደሚመጣ ከሚጠበቀው የሀገሪቱ ኢኮኖሚ ጋር በተያያዘ በቀጣይም ሰፊ ሥራ ይጠብቀዋል::
ዘርፉ ኃላፊነቱን ለመወጣት የዘርፉን መልካም እድሎች መጠቀም እንዳለበት ሁሉ የዘርፉ መሰናክሎች ተብለው ለተለዩትም መፍትሔ ማመላከት ያስፈልጋል:: የዘርፉ ተግዳሮቶች ከተባሉት መካከል ለኮንስትራክሽን ሥራዎች ግብአትነት የሚውሉ ምርቶች ከውጭ ሀገራት የሚመጡበት ሁኔታ ይጠቀሳል።
እነዚህ ግብአቶች ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ የሚጠይቁ ከመሆናቸው ባሻገር በወቅቱ ባለመድረሳቸውም ሌላ ችግር አለባቸው፤ ይህም በፕሮጀክቶች ላይ በየወቅቱ የዋጋ ጭማሪ ያስከትላል፤ ከፍተኛ የጥራት መጓደል እየታየ ያለበት ሁኔታም ዘርፉ በጀመረው ጉዞ ላይ አሉታዊ ተጽእኖ እያሳደረ መሆኑ ይገለጻል።
የኮንስትራክሽን ግብአት ፍላጎትን በሀገር ውስጥ ምርት ለመሸፈን በሀገሪቱ ምቹና አስቻይ ሁኔታዎች ቢኖሩም፣ ትግበራው አሁንም ብዙ ርቀት የተጓዘ አይደለም።
የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስቴርም ይህንን ችግር ለመሻገር በሥሩ ከሚገኙ ተጠሪ ተቋማት ጋር በመሆን በርካታ ሥራዎችን እያከናወነ ይገኛል። ከትናንት በስቲያም የሚኒስቴሩ ተጠሪ ተቋም የሆነው የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ማኔጅመንት ኢንስቲትዩት የኮንስትራክሽን ግብአቶችን በሀገር ውስጥ ምርት ለመሸፈን የሚያስችሉ ጥናቶችን በማካሄድ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ተወያይቷል።
በውይይቱ ወቅት በኢንስቲትዩቱ የሥልጠናና ብቃት ማረጋገጫ መሪ ሥራ አስፈጻሚ ኢንጂነር ቅድስት ማሞ እንዳብራሩት፤ ችግሩ ለዘርፉ መሰናክል መሆኑ ከተለየ ቆይቷል። በመንግሥት በኩልም በሀገሪቱ ያለውን የኮንስትራክሽን ግብአት ፍላጎት እስከ 2022 ዓ.ም 80 በመቶውን በሀገር ውስጥ ምርት ለመሸፈን እቅድ ተይዞ እየተሠራ ይገኛል። ይሁንና አሁንም አብዛኛው ጥቅም ላይ እየዋለ ያለው ግብአት ከውጭ ሀገራት የሚመጣ ነው።
ችግሩ ረዥም ዓመታትን ማስቆጠሩን ኢንጂነሯ ጠቅሰው፣ ለመፍትሔው በጥናት ላይ ተመርኩዞ መሥራት እንደሚያስፈልግ አስታውቀዋል፤ ለዚህም የዘርፉ ባለሙያዎችና ባለድርሻ አካላት ሃሳብም ያስፈልጋል ብለዋል።
በዘርፉ የሚስተዋሉ ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት ከተጠሪ ተቋማት ማለትም ከኢኮኖሚክስ ባለሙያዎች ማህበር፤ ከኢትዮጵያ አርክቴክቸር፤ ህንጻ ግንባታና ከተማ ልማት ኢንስቲትዩት ጋር ጥናቶችን ሲያካሂድ ቆይቷል። በአሁንም ኢንስቲትዩቱ ከኢትዮጵያ ኢኮኖሚክ ባለሙያዎች ማህበር ጋር በመተባበር በኮንስትራክሽን ዘርፍ የሀገር ውስጥ ምርቶችን በመጠቀም ረገድ የሚታዩ ክፍተቶችን የሚለይ ጥናት አከናውኗል።
ከጥናቱ የሚጠበቀውም 80 በመቶ የኮንስትራክሽን ግብአቶችን በሀገር ውስጥ ምርት ለመሸፈን መንግሥት በእቅዱ ያስቀመጠውን በሚቀጥሉት ስድስት ዓመታት ለማሳካት የሚያስችሉ ግኝቶችን ማፍለቅ ነው።
በጥናቱ ውጤትም የሀገር ውስጥ ምርቶችን በመጠቀም ረገድ የሚታዩት ክፍተቶች በአምራቾችም ሆነ በተጠቃሚዎች በኩል እንዲለዩ ተደርጓል ሲሉም ጠቅሰው፣ ይህንንም መሠረት በማድረግ ለቀጣይ የመፍትሔ አቅጣጫ ሊሆን የሚችል የአሠራር ሥርዓት ለመዘርጋት የሚያስችሉ ግኝቶችም ተመላክተዋል ብለዋል።
እነዚህን ግኝቶች መሠረት በማድረግ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመወያየት ከፖሊሲ ጀምሮ መሰናክል የሚሆኑ ችግሮችን በማስወገድ የሀገር ውስጥ የኮንስትራክሽን ግብአት ምርት ተጠቃሚነትን ለማሳደግ የተጀመረው ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።
በመድረኩ ጥናታዊ ጽሑፍ ያቀረቡት የዘርፉ ተመራማሪ ሲሳይ ደበበ (ዶ/ር) በበኩላቸው በአሁኑ ወቅት እየተመረቱ ያሉት የሀገር ውስጥ የኮንስትራክሽን ግብአቶች ሀገሪቱ ካላት አጠቃላይ አቅም ከ22 እስከ 40 በመቶ ብቻ መሆናቸውን ይጠቅሳሉ። ለዚህም እንደ ምክንያት የሚቀመጠው የመሬት፣ የኤሌክትሪክ፣ የውሃ፣ የላብራቶሪ፤ የቴክኖሎጂ ተደራሽነትና የሀገር ውስጥን ምርት ያለመጠቀም ልምድ መስፋፋት ከቀዳሚ ችግሮች መካከል እንደሚጠቀሱ አመላክተዋል።
እሳቸው እንዳሉት፤ የሀገር ውስጥ ምርት ተጠቃሚነትን ማሳደግና ከውጭ የሚገቡትን መቀነስ እንደሚገባ ይታወቃል። ጥያቄ ሆኖ የተቀመጠው ግን የሀገር ውስጥ ምርቶችን በጥራትና በብዛት በማቅረብ ከውጭ የሚገቡትን እንዴት መቀነስ ይቻላል የሚለው ነው። ለግንባታ ግብአትነት የሚውሉ ቁሳቁስ ሲታሰቡ የመጀመሪያ መዳረሻ የሚሆነው የተፈጥሮ ሀብት ማለትም ማዕድን ይሆናል። እነዚህንም በሁለት በሁለት ተከፍለው ይታያሉ። አንደኛው እንደ አሸዋ፣ ድንጋይና ጠጠር ያሉትን የሚካትት ሲሆን፣ እነዚህም በቀጥታ ለግንባታ መዋል የሚችሉ ናቸው።
በሁለተኛው ክፍል የሚገኙት ደግሞ እንደ ብረትና ሲሚንቶ ያሉት ናቸው:: ለእነዚህ ምርቶች የሚያስፈልጉት ማዕድናት ቢኖሩም፣ ፋብሪካ ገብተው ወደሚፈለገው ምርት ለመቀየር ብዙ ሂደትን ማለፍ ይኖርባቸዋል:: በዚህ የምርት ሂደት ደግሞ ለግብአትነት የሚያገለግሉ በሀገር ውስጥ የማይገኙ ግብአቶች አሉ:: እነዚህን የኮንስትራክሽን ግብአቶች ለማምረት የሚያስችሉ ግብአቶችም ከውጭ ሀገራት እየገቡ ይገኛሉ። ካለቀላቸው ምርቶች ባልተናነሰ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ በማውጣት ከውጭ ሀገራት እንዲገቡ እየተደረጉ ያሉትም እነዚሁ ናቸው። ይህ የሚያመላክተው ስለ ኮንስትራክሽን ግብአት ምርቶች ሲታሰብ በርካታ ባለ ድርሻ አካላትን የሚነካ የመሆኑ ጉዳይ ነው።
እስካሁን ባለው ኢትዮጵያ ወደ ውጭ የምትልከው ዋናው ምርት ቡና ነው። ከዚህና ከሌሎች ጥቂት ምርቶች የምታገኘውን የውጭ ምንዛሬ በአግባቡ ለተመረጡና ቅድሚያ ለሚሰጣቸው ጉዳዮች ብቻ ልትጠቀምባቸው ይገባል። ለዚህም በሀገር ውስጥ ሊመረቱ የሚችሉ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ማምረት ቀዳሚ መፍትሔ ነው ሲሉም ያብራራሉ።
በኮንስትራክሽን መስክም ለምሳሌ እንደ ሴራሚክ፤ ማርብል፤ ግራናይት የመሳሰሉትን በሀገር ውስጥ ለመተካት የሚያስችል በቂ አቅም አለ። በጥናቱ የተዳሰሱትም እነዚህን በሀገር ውስጥ ሊመረቱ የሚችሉት ናቸው።
በጥናቱም በአሁኑ ወቅት በዚህ መስክ የተሠማሩት ምን ያህል የገበያ ተደራሽነት አላቸው የሚለው ተፈትሿል ሲሉ ጠቅሰው፣ በዚህም እስካሁን እንደ ሀገር እየተጠቀምን ካለው 55 በመቶው በሀገር ውስጥ ምርት የተሸፈነ ሲሆን ቀሪው ከውጭ እየገባ ነው ሲሉ አስታውቀዋል።
ለኮንስትራክሽን ግብአት የሚውሉ ምርቶችን በሙሉ በሀገር ውስጥ መሸፈን ይቻላል ማለት አይደለም ሲሉም ጠቅሰው፣ ለምሳሌ ቢቱሚን የሚባለው ለአስፋልት ሥራ የሚውል ግብአት አሁን ባለው ሁኔታ በምንም መልኩ ልንተካው አንችልም፤ ከውጭ ማስገባታችን አይቀረም ብለዋል።
እሳቸው እንዳስታወቁት፤ እንደ ሴራሚክ፤ ማርብል፤ ግራናይት፤ መስታወት፣ ቀለምና የመሳሰሉትን የግንባታ ማጠናቀቂያ /ፊኒሺንግ/ ግብአቶችን አቅምን አሰባስቦ በመሥራት መተካት እንደሚቻለው አመልክተዋል::
እስካሁንም እንደ ሲሚንቶ፣ ጂብሰም ባሉት ምርቶች ላይ የሀገር ውስጥ አቅም ተፈትሾ እንደሚቻል ለማረጋገጥ ተችሏል ሲሉም ገልጸው፣ ይህም ቢሆን ሀገሪቱ እያስመዘገበች ካለችው ለውጥ አኳያ በየወቅቱ በከፍተኛ ደረጃ ማደግ እንደሚጠበቅበት አስገንዝበዋል።
ዶክተር ሲሳይ እንዳመለከቱት፤ ይህም ሆኖ የሀገር ውስጥ ምርትን በመጠቀም ረገድ እንደ ክፍተት የተለየው ግንባታ በሚያካሂዱ አካላት ተመራጭ የሚሆነው ከውጭ የሚገባው ምርት መሆኑ ነው፤ ለዚህም እንደ ምክንያት ከሚነሱት መካከል የሀገር ውስጥ ምርቱ ጥራት ደረጃውን የጠበቀ አይደለም ጥንካሬ የለውም ፤ የዋጋ ውድነት ይታያል የሚሉት ናቸው።
ይህም ከሁለት ወገን የሚነሳ ነው። አንደኛው ራሱ ኮንትራቱን የሚሰጠው አካል ግንባታው ከውጭ በሚገቡ እቃዎች እንዲከናወንለት ሲጠይቅ ነው፤ ሁለተኛው ግንባታውን የሚያካሂዱ አካላት ሥራቸውን በአግባቡ ለመሥራት በዘላቂነት የሚያገኙት ከውጭ የሚገባውን በመሆኑ ግብአቱን ምርጫቸው ያደርጉታል።
‹‹የሀገር ውስጥ የኮንስትራክሽን ግብአት አምራቾች የግንባታ ምርቶችን በጥራት ለማምረት የተሻለ እድል አላቸው›› ያሉት ተመራማሪው፣ በመሆኑም ለሀገር ውስጥ አምራቾች የቴክኖሎጂ ድጋፍ ማድረግ፤ የኮንስትራክሽን ጥሬ እቃዎች ግብአቶች አቅርቦት ችግሮችን መፍታት፣ የሀገር ውስጥ ምርቶች አጠቃቀም ፍላጎትን ማሳደግ እንደሚገባ ጠቁመዋል:: እንዲሁም አመራረታቸውን በቴክኖሎጂ ማስደገፍና ዘርፋን ለማሳደግ የተደነገጉ ፖሊሲዎችንና ስትራቴጂዎችን በአግባቡ ተግባራዊ ማድረግ እንደሚያስፈልግም አመላክተዋል።
ከተለያዩ የውጭ ሀገራት በገፍ እየገቡ ባሉት የኮንስትራክሽን ግብአቶች ላይም ቁጥጥር ማድረግ እንደሚገባም አስገንዝበዋል። ትላልቅ ፕሮጀክቶች በሀገር ውስጥ ምርቶች እንዲገነቡ ለማድረግ አቅጣጫ ማስቀመጥም ሌላው መፍትሔ ብለውታል::
የከተማ ልማት ሚኒስቴር የ30 ዓመት ፍኖተ ካርታ ማዘጋጀቱንና የአስር ዓመት የልማት እቅድም አሰናድቶ እየሠራ መሆኑን ጠቅሰው፣ በዚህ ጥናት የተለዩት ችግሮችና የተቀመጡት የመፍትሔ ሃሳቦችም ይህንን መሠረት አድርገው የተዘጋጁ መሆናቸውን ተናግረዋል:: በመፍትሔ ሃሳቦቹ ላይ አስፈላጊውን ማሻሻያ በማድረግ ወደትግበራ መግባት እንደሚጠበቅ ጠቁመዋል።
ሌላው ተመራማሪ ሰለሞን እንድርያሰ (ዶ/ር) በበኩላቸው « የኮንስትራክሽን ግብአቶችን በሀገር ውስጥ ምርት ለመተካት 38 የሚደርሱ ባለ ድርሻ አካላት አሉ» ሲሉ ይገልጻሉ። ጥናቱን ለመተግበር የሚዘረጋው የአሠራር ሥርዓት ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱንና በሥሩ ያሉትን ተጠሪ ተቋማት ብቻ የሚያካትት እንዳልሆነም ይጠቁማሉ። ከእነዚህ በተጨማሪ እንደ ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ፤ ንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር፤ ማዕድን ሚኒስቴርና የመሳሰሉትን ተቋማት ተሳትፎም ይጠይቃል ብለዋል::
እሳቸው እንዳሉት፤ ከ38ቱ ተቋማት ውስጥ አብዛኛዎቹ የመንግሥት ተቋማት ሲሆኑ፣ የተቀሩት ደግሞ የግል ተቋማትም ናቸው። በጥናቱ የእነዚህ ተቋማት ተሳትፎ በምን መልኩ ሊሆን እንደሚገባ በዝርዝር የተመላከተ ሲሆን፣ በዋናነት የሶስት ተቋማት ሥራ ግን ዋናውን ሚና የሚይዝ ይሆናል።
ከእነዚህም ውስጥ አንደኛው ባለቤት የሆነው የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር ነው። ሚኒስቴሩ ሲቋቋም በአዋጅ ከተሰጡት ኃላፊነቶች መካከል አንደኛው የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪውን ተወዳዳሪነትና ዘለቄታዊነት ማረጋገጥ የሚያስችሉ ፖሊሲዎችን ስትራቴጂዎችን ማዘጋጀት የሚለው ነው። በሁለተኛነትም በሀገሪቱ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ የሆነ የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ እንዲኖር ምቹ ሁኔታዎችን የመፍጠርና የሀገር ውስጥ የኮንስትራክሽን ግብአቶች ጥራታቸውና ዓይነታቸው እንዲያድግ ጥናት የማካሄድና አጠቃቀምን የማበረታታት ኃላፊነትም አለበት።
ሁለተኛው ተቋም የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ነው፤ ሚኒስትሩ በማኑፋክቸሪንግ ዘርፉ ሊያሠሩና ምርትን ሊጨምሩ የሚችሉ ፖሊሲዎችንና ስትራቴጂዎችን የመቅረጽ ኃላፊነት ተሰጥቶታል፤ የዘርፉን ንኡስ ዘርፎች የመደገፍ ኃላፊነት አለበት:: በዚህም በኮንስትራክሽን ግብአት ረገድ እንደ ብረት ሲሚንቶ ማምረቻ ላሉት ልዩ ትኩረት ሊሰጥ እንዲሚገባ ተመላክቷል።
ከዚህም ባለፈ በዋናነት ለኮንስትራክሽን ግብአትነት የሚውሉ ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ለመተካት የመሥራት ኃላፊነት አለበት። ለዚህም በዚህ መስክ የተሠማሩ ማኑፋክቸሪዎችን በጥራትና በብዛት እንዲያመርቱ መደገፍና አቅም ማሳደግ ይጠበቅበታል።
ሶስተኛው ተቋም የማዕድን ሚኒስቴር ነው። ለኮንስትራክሽን ሥራ ግንባታ የሚውሉ ግብአቶች የሚመረቱት በተፈጥሮ ከሚገኙ ማዕድናት ነው። እነዚህን ማዕድናት ከሀገር ውስጥ ማቅረብ ካልተቻለ ዞሮ ዘሮ በውጭ ምርቶች ላይ ጥገኛ መሆኑና ከውጭ በማስገባት ሂደት የሚደርሱ ጉዳቶችን መሸከሙ አይቀርም ማለት ነው።
የዘርፉን ግብአቶች ሰማኒያ በመቶ በሀገር ውስጥ ለማምረት እቅድ ሲያዝ የሥራ እድል ፈጠራ፤ የውጭ ምንዛሬ መቀነስና ሌሎችም ከግምት የገቡት ጥሬ እቃውንም ከሀገር ውስጥ መጠቀምን ታሳቢ በማድረግ መሆኑ ተጠቁሟል።
በመሆኑም ለኮንስትራክሽን ምርት ግብአት የሚሆኑ ማዕድናት በአግባቡና በሚጠበቀው ደረጃ እንዲገኙ የማድረግ ኃላፊነት የማዕድን ሚኒስቴር ይሆናል ነው። ይህም የት እንዳሉ ማመላከት ብቻ ሳይሆን አስፈላጊውን ድጋፍና ቁጥጥር በማድረግ ለገበያ እስኪቀርቡ ድረስ ባለው ጉዞ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ዋናውን ድርሻ ሊወስድ ይገባል።
በዚህ ዓይነት ሶስቱን የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች ጨምሮ 38ቱ ባለድርሻ አካላት መቼ ? እንዴትና በምን ዓይነት ሁኔታ የሚጠበቅባቸውን ሊወጡ እንደሚገባ በጥናቱ ተመላክቷል። እነዚህም በሁለት ዓይነት መንገድ ይተገበራሉ::
አንደኛውን የጉዳዩ ዋና ባለቤት የሆነው የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር ብቻውን የሚሠራው መሆኑን ጠቅሰው፣ ሁለተኛውን ደግሞ ከተዘረዘሩት ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት የሚሠራው መሆኑን አመልክተዋል። እነዚህ ተግባራት የተቀመጡትም ኢትዮጵያ እንደ ሀገር ያስቀመጠችውን የአስር ዓመት እቅድና የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱን የአስር ዓመት እቅድ መነሻ በማድረግ ዋና ዋና የኮንስትራክሽን ግብአቶችን መተካት በሚያስችል መልኩ መሆኑን ጠቁመዋል።
በመሆኑም አሁን ይፋ የተደረጉት ጥናቶች ባስቀመጡት አቅጣጫ መሠረት ተግባራዊ ሲደረጉ፤ በ2022 ዓ.ም በእቅድ የተቀመጠውን የሀገር ውስጥ የኮንስትራክሽን ፍላጎትን 80 በመቶ በሀገር ውስጥ ምርት መሸፈን የሚለውን እውን ለማድረግ እንደሚቻል አስረድተዋል።
ራስወርቅ ሙሉጌታ
አዲስ ዘመን ቅዳሜ የካቲት 8 ቀን 2017 ዓ.ም