ነጻነትን ምሉዕ የማድረጉ ትግል ብዙ አፍሪካውያን ጀግኖችን የሚጠይቅ ነው

ከ15ኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ አፍሪካውያን በቅኝ አገዛዝ እና በእጅ አዙር ቅኝ አገዛዝ የከፋ መከራ እና ስቃይ ውስጥ ለማለፍ ተገድደዋል። ምድራቸውን እንደ ቅርጫ ስጋ እጣ ተጣጥለው የተቀራመቱ ኃይሎች የአህጉሪቱን ሕዝቦች ሀብት እና ንብረት ያለከልካይ ከመዝረፍ ባለፈ ሰብዓዊ ማንነታቸውን የሚገዳደሩ ተግባራትን በአደባባይ ሲያደርጉ ቆይተዋል።

ይህ ከመጠን ባለፈ ራስ ወዳድነት የተቃኘው የምዕራቡ ዓለም የትናንት ተግባር እና ከዚህ ተግባራቸው የመነጨው ትርክት አፍሪካውያንን መልከ ብዙ ዋጋ አስከፍሏቸዋል። በገዛ ምድራቸው ተፈጥሮ ለሰጠቻቸው ጸጋዎች ባእዳን እንዲሆኑ አድርጓቸዋል። የተግባራቱ ትርክቶቹም አንገት ከማስደፋት ባለፈ በራሳቸው ተማምነው እጣ ፈንታቸውን እንዳይወስኑ ተግዳሮት ሆኖባቸዋል።

ይህንን የጭቆና ቀንበር ለመስበር ዓመታት ያስቆጠሩ የነጻነት ተጋድሎዎችን አካሂደዋል። ከሰሜን እስከ ደቡብ፣ ከምሥራቅ እስከ ምዕራብ የአህጉሪቱ ሕዝቦች ስለ ፍትህ እና ነጻነት ከሁሉም በላይ ስለሰብአዊ ክብር ከፍ ያለ መስዋዕትነት የጠየቁ ትግሎችን አካሂደዋል። በዚህም ለሞት፣ ለግዞት እና ለከፋ መከራም ተዳርገዋል። እውነታውን በጽናት ተጋፍጠው ነጻነት የሚጠይቀውን መስዋዕትነት ሁሉ ከፍለዋል።

አፍሪካውያን ዛሬ ላይ ያገኙት ያልተሟላ ነጻነት፣ የብዙ ትውልዶችን የመስዋዕትነት ቁርጠኝነት የጠየቀ፣ ብዙ ወጀቦች እና ፈተናዎች ውስጥ እየተንገጫገጨ ያለ ነው። በተለይም የነጻነት ትርጉም ዘርፈ ብዙ በሆነበት እና የባርነት መንገድ ረቂቅ እና ውስብስብ እየሆነ በመጣበት በዚህ ዘመን እውነታው ለአፍሪካውያን ቀልሎ የሚታይ አልሆነም።

የፖለቲካ ነጻነት በራሱ ከረቂቅ ግዞት መታደግ የማይችልበት፣ ዓለም አቀፍ እውነታው በብዙ መንገድ እና ቀለም ከፍ ባለ ራስ ወዳድነት በተያዘበት፣ ምድራችን ከሰብዓዊነት ባፈነገጡ እሳቤዎች የቀደሙ ማህበራዊ እና ፖለቲካዊ አስተሳሰቦች እየተሸረሸረች ፣ በጥቂቶች ፍላጎት ውስጥ ለማደር እየተገፋች ባለችበት በዚህ ዘመን የትናንት አባቶቻችን የነጻነት ትግል ብቻውን ዛሬን ሊያሻግረን የሚችል አልሆነም።

ትናንት በቅኝ ግዛት ዘመን እንደሆነው ሁሉ፤ ዛሬም ብዙ አፍሪካውያን ለሀገራቸው እና ለሀብታቸው ባዕድ የሆኑበት ሁኔታ ስለመኖሩ የአደባባይ ምስጢር ነው። በገዛ ሀብታቸው ለዘመናዊ ባርነት የተዳረጉ፤ ነጻነታቸውን ሙሉ ለማድረግ በሄዱበት የተገባ መንገድ ያልተገባ ዋጋ ለመክፈል የተገደዱ አፍሪካውያን ወንድም እና እህቶቻችን ጥቂት አይደሉም።

አፍሪካውያን ከግማሽ ምዕተ ዓመት በላይ የበለጸገ አፍሪካዊ አንድ የፖለቲካ እና የኢኮኖሚ ማህበረሰብ ለመፍጠር ባደረጓቸው እልህ አስጨራሽ ትግሎች ያጋጠሟቸው ፈተናዎች ችግሩ የቱን ያህል የደነደነ ስለመሆኑ በተጨባጭ የሚያመላክት ነው። ለሕዝባቸው ብሩህ ቀናት በማሰባቸው ብቻ መቃብር ውስጥ የገቡ አፍሪካውያን ወንድም እህቶቻችን ብዙ ናቸው ።

በየዘመኑ የአፍሪካውያን ወንድም እህታቸው ድምጽ ለመሆን የሞከሩ፣ አፍሪካውያን በብዙ መስዋዕትነት ያገኙትን የፖለቲካ ነጻነት ሙሉ ለማድረግ በጽናት እና ከፍ ባለ ድምፅ አደባባይን የሞሉ አፍሪካውያን በተለያዩ ሴራዎች በገዛ ወንድሞቻቸው ሳይቀር ለግፍ ሞት ተዳርገዋል። ታሪካቸው ከመቃብር በላይ ሕይወት እንዳይዘራም የመቀጣጫ ያህል ተደርገው ተስለው አልፈዋል።

የእውነታው አስከፊነት በነጻነት ትግሉ ከመስዋዕትነት በላይ ድምፁን አጥፍቶ አፍሪካውያንን ብዙ ዋጋ እያስከፈላቸው ነው። እንደ አንድ ትልቅ ተስፈኛ ሕዝብ የተስፋቸው ባለቤት እንዳይሆን እንደ ዓይነ ጥላ እየተከተላቸው ነው። በዚህም እንደ ሕዝብ ለዓመታት ድባቴ ውስጥ እንዲገቡ አድርጓል፤ በነጻነት ትግሉ ወቅት ፈጥረውት የነበረውን በራስ የመተማመን መንፈስ በብዙ ሸርሽሮታል ።

ይህም ለሁለንተናዊ ነጻነት የነበራቸውን መነቃቃት እና ቁርጠኝነት እያደበዘዘው፤ በብዙ ሴራ እና ያልተቋረጠ ጣልቃ ገብነት እየኖሩት ያለውን ያልተገባቸውን የድህነት እና የኋላ ቀርነት ሕይወት እጣ ፈንታቸው አድርገው እንዲቀበሉ ሆነዋል ። ይህንንም ማህበረሰባዊ ማንነታቸው አድርገው እንዲቀበሉ ብዙ ተሠርቶባቸዋል። ችግሮችን ሰባብረው እንዳይወጡም አቅመ ቢስነት ፈጥሮባቸዋል።

ይህ ለነጻነት የተደረገውን ትግል እና በብዙ መስዋዕትነት የተገኘውን ድል አልፋ እና ኦሜጋ አድርጎ ከመመልከት የመነጨ መዘናጋት፤ አፍሪካውያን ያገኙትን ድል በአግባቡ እንዳያጣጥሙ አድርጓል፤ በእጅ አዙር ተመልሰው የቀደሙት ጌቶቻቸው ፍላጎት ተገዥ የሆኑበትን የታሪክ ትርክት ፈጥሯል። የገዥ እና የተገዥ የባሪያ እና የሎሌ ትርክት ትንሳኤ እንዲያገኝ አድርጎታል።

አፍሪካውያን እንደ ትናንቱ ዛሬም ካሉበት የፖለቲካ ድባቴ የተነሳ ለሀብቶቻቸው ባዕድ ሆነዋል፤ ሰብአዊ ክብራቸው በተለያዩ ክስተቶች በሚፈጠሩ ማነሶች እየተሸራረፈ በማንነታቸው አንገት መድፋት ከጀመሩ ውለው አድረዋል። አዲሱ አፍሪካዊ ትውልድም የዚህ እውነታ ሰለባ ከሆነ አረፋፍዷል። ከእውነተኛ ማንነት መሸሽ እና መጣላት መገለጫው ሆኗል።

በዚህ ዘመን ያሉ አፍሪካዊ መሪዎች ትልቁ የቤት ሥራቸው ይህንን ትውልዱን የተጫነውን የፖለቲካ ድባቴ በአዲስ የፖለቲካ መነቃቃት መግፈፍ፣ ለዚህ የሚሆን ቁርጠኝነት እና መናበብ፤ በብዙ መስዋዕትነት ያገኙትን ያልተሟላ የፖለቲካ ነጻነት ሙሉ ማድረግ የሚያስችል ትግል ማድረግና የጋራ ተነሳሽነት መፍጠር ነው።

ትግሉ እንደ ቀደመው የነጻነት ትግል ብዙ አፍሪካውያን ጀግኖችን የሚፈልግ፤ የሁሉንም አንድነት እና የአቋም ጽናት የሚጠይቅ፤ በብዙ ፈተናዎች ማለፍና በፅናት መሻገር የሚያስችል ማንነት መገንባት የግድ የሚልበት ነው። ለሕዝብ ፍላጎት ራስን መስዋዕት ማድረግ ይገባል። ይህን ማድረግ የራስን የአፍሪካውያንን ነገዎች ብሩህ ከማድረግ ባለፈ ሰብዓዊ ማንነታቸውን በተጨባጭ በአደባባይ ማጽናት ነው።

ከመርደቂዮስ

አዲስ ዘመን ቅዳሜ የካቲት 8 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You