ሄለን ዜሊ በደቡብ አፍሪካ ፖለቲካ ውስጥ እንግዳ አይደሉም። እአአ ከ2007 እስከ 2015 ድረስ በአገሪቱ የዴሞክራቲክ ትብብር በሚል ስያሜ የሚታወቀውን የተቃዋሚ ፓርቲ በሊቀመንበርነት የመሩ ጠንካራ ሴት ተቃዋሚ ናቸው። እኚህ አንጋፋ ፖለቲከኛ ታዲያ ባለፈው ወር በፌዴራል ካውንስል የዴሞክራቲክ ጥምረት ሊቀመንበር ሆነው ዳግም ተመርጠዋል።
እኚህ ሴት በነጭ አክራሪ ፖለቲከኞች ዘንድ ከፍተኛ ድጋፍ እንዳላቸው ይነገራል። እሳቸውም ቢሆኑ አገሪቱ በነጭ የአፓርታይድ አገዛዝ ስር በነበረችበት ወቅት የተሻለ ኢኮኖሚ እንደነበራት በተደጋጋሚ ያነሳሉ። የዘር ጉዳይ ዋነኛ የአገራችን ጉዳይ ሊሆን አይገባም የሚል ሃሳብ በተደጋጋሚ የሚያነሱት ሄለን ዜሊ በተዘዋዋሪ የቀደመው የአፓርታይድ ዘመን እንደሚመለስ ከፍተኛ ጥረት እንደሚያደርጉ ግን የፓርቲያቸው አባላት ጭምር ይወቅሳሉ።
ሄለን ዜሊ በአዲሱ የስራ ጊዜያቸው በተፎካካሪ ፓርቲ ከፍተኛ የተባለ ስልጣን የተቆናጠጡ ሲሆን በስልጣን ጊዜያቸው ቀድሞ የነበሩ አሰራሮችን እንደማይከተሉና አለም አቀፍ ለውጥ ለማምጣት እንቅስቃሴ ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል። እንደሳቸው አባባል ከሆነ ቀድሞ ከነበረው የአመራር ዘይቤ ተለውጠው መምጣታቸውንና የወከሉትን ፓርቲ ጥቅም ለማስጠበቅ ይሰራሉ።
የሄለን ማሸነፍ የቀድሞ የዴሞክራሲ ጥምረቱ ፓርቲ አባላት እንዲለቁ ምክንያት እየሆነ መጥቷል። እአአ 2019 ጥቅምት 21 የጆሀንሰበርጉ ከንቲባ ሀርመን ማሼባ ፓርቲውን ለቀዋል። ለመልቀቃቸው ምክንያት በደቡብ አፍሪካ ላለው ድህነትና መድሎ ዘር አስፈላጊ አይደለም ብሎ ከሚያምን ቡድን ጋር መስራት አለመፈለጋቸው መሆኑን ተናግረዋል። ከሀርመን ማሼባ መልቀቅ ሁለት ቀናት በኋላ የዴሞክራቲክ ትብብር ፓርቲ የመጀመሪያው ጥቁር መሪ የነበሩት ሙሙሲ ማኢማኔ ከፓርቲው ለቀዋል።
እንደሳቸው አባባል፤ ፓርቲው ወደ ቀድሞ የነጮች የበላይነት የበዛበትና ሌሎቹን ወደ ማግለሉ ይመለሳል። በተመሳሳይ ቀን የቀድሞ የኔልሰን ማንዴላ ቤይ ከንቲባና የፓርቲው ሊቀመንበር አትሆሎ ትሮሎፒ ከፓርቲው እራሳቸውን አግልለዋል።
ሄለን ዚሊስ ወደ ስልጣን ከተመለሱ ከጥቂት ቀናት በኋላ ፓርቲው በእሳቸው አመራር እአአ 2008 ላይ ከአፓርታይድ ወቅት በኋላ ሊብራል አመራርነትን ለመከተል ሞክረው ህዝባዊ ተቃውሞ ገጥሟቸው እንደነበር ይታወሳል። አሁን በአዲሱ አመራር የዴሞክራሲ ትብብር ፓርቲ በግልጽ ካለፈው የመሻሻል ወደ ወግ አጥባቂ ነጭ አናሳ ትኩረት ወደተደረገ አጀንዳ ለመሄድ ተዘጋጅቷል። ይህ ለፓርቲውም ሆነ ለደቡብ አፍሪካ የፖለቲካ ሁኔታ ጥሩ እንዳልሆነ ፖለቲከኞች ይገልጻሉ።
የከሸፈ ለውጥ
ሙሙሲ ማኢማኔ እአአ 2015 የዴሞክራሲ ትብብር ፓርቲ ሊቀመንበር ሆነው በተመረጡበት ወቅት ፓርቲው አዲስ መንገድ እንደ ጀመረ ተገምቶ ነበር። በጀመሪያ ንግግራቸው የተለያዩ እድሎችን ለወጣቱ፣ ለስራ እጥ ጥቁር ህዝቦች መፈጠር እንዳለበት ተናግረዋል። በወቅቱ አፓርታይድ እንዳልተፈፀመ ማድረግ እንደማይቻልና በቀጣይ የተለያዩ ፖሊሲዎችን በማውጣት የቀድሞ ሁኔታ እንዳይፈጠር ማድረግ እንደሚገባ አፅንኦት ሰጥተው ተናግረዋል። ነገር ግን ሙሙሲ ማኢማኔ የፓርቲው ፖሊሲዎች ድህነት ወዳጠቃቸው ሰዎች፣ በታንክ ወደተጎዱ ዜጎችና ሌሎች ጥቁር መራጮች ላይ እንዲያተኩር አደረጉ። እአአ 2019 ግንቦት ወር ላይ ፓርቲው አብዛኛውን ደጋፊ ድምፅ አጣ።
የፓናል ውይይት ሪፖርቶች እንደሚያሳዩት የቀድሞ የፓርቲው መሪ የነበሩት ቶኒ ሊዮን እና ራይን ኮቴዝ ፓርቲው ባህላዊ በሆነ መንገድ በመንቀሳቀሱ፣ በነጭ አፍሪካ መራጮች እና ፓርቲውን በሚጠሉ ሰዎች ምክንያት በተደረገው ምርጫ ብዙ ጥቁር መራጮች እንዲሳተፉ መደረግ አለበት ሲሉ ተናግረዋል። የሄለን ዚሊ ማሸነፍ የተፎካካሪ ፓርቲዎች የመንግስት ስልጣን በደቡብ አፍሪካ መያዝ እንደሚያስችላቸው አንዱ ማሳያ ነው። የሄለን ፍላጎት በደቡብ አፍሪካ ዘርን መሰረት ያላደረገ ፖለቲካ ማምጣት ነው። የቀድሞው የፓርቲው አመራሮች በዚህ ጉዳይ ለውጥ ማምጣት እንዳቃታቸውና የጥቁርን መብት ብቻ ሲያራምዱ እንደነበር ተስተውሏል።
ሄለን የራሳቸው የአመራር ጥበብ በመከተል የሊብራሊዝም አስተሳሰብ በማራመድ ሁሉን አቀፍ ፖሊሲ የማምጣት ፍላጎት አላቸው። ለጥቁሮች የሚደረገውን ልዩ ድጋፍና የአቅም ግንባታ የሚቃውሙ ሲሆን ድጋፉ ምንም አይነት ለውጥ ያላመጣ እንደሆነ በድፍረት ይናገራሉ። እአአ 2017 ላይ ሄለን ዚሊስ ቅኝ መገዛት ሁል ጊዜ መጥፎ ክፍል ብቻ የለውም ብለው በመናገራቸው በጥቁር የፓርቲው አባላት ጥርስ ተነክሶባቸው ቆይቷል። ሄለን በትዊተር ገፃቸው ቅኝ መገዛት የደቡብ አፍሪካ ጥቁር ህዝቦችን ጠቅሟል። ያመጣውም ለውጥ ሊደነቅ እንደሚገባም በትዊተር ገፃቸው ማስፈራቸው ይታወሳል።
በዚህ መንገድ ሄለን ከቅኝ ግዛት ነፃነት በኋላ በደቡብ አፍሪካ የመጣውን ለውጥ መቀበል አይፈልጉም። እንደሳቸው አባባል ከሆነ በአፍሪካ ውስጥ የሚገነቡት ኢንዱስትሪዎች ከአውሮፓ ጋር ተወዳዳሪ መሆን አይችሉም። ለዚህም የአውሮፓ አገራት ሁል ጊዜም ለአፍሪካ ድጋፍ እንደሚያደርጉ ገልፀዋል። የሄለንን አተያይን በመቃወም ሰልፎች የተካሄዱ ሲሆን በዴሞክራሲ ትብብር ፓርቲ ውስጥም መከፋፈልን ፈጥሯል። በተለይ ጥቁር የፓርቲው አመራሮች ተቃውሟቸውን በግልፅ አቅርበዋል።
ከዚያ በኋላ እ.ኤ.አ. በግንቦት ወር 2019 ዜሊስ ህብረተሰቡ “ነጭነት” ን እያወገዘ እና “ጥቁር መብት” አለ በሚል በደቡብ አፍሪካ ውስጥ በመቶዎች ከሚቆጠሩ ሰዎች ቢሊዮን ብሮችን በመስረቅ መመረጥ አይቻልም ብለው በመናገራቸው ከፍተኛ ተቃውሞ ተነስቶባቸዋል። እንደዚህ አይነት አመራሮች በፓርቲው ውስጥ እየበዙ መምጣት የፓርቲውን ህልውና ተፈታትኖታል። ለሚፈጠሩ ችግሮች ደግሞ ፓርቲውን የሚመራው ሰው የበፊቱንና የአሁኑን ሁኔታዎች የመረዳት አቅም ያለው መሆን አለበት ሲሉም ፖለቲከኞች ይናገራሉ።
አዲስ ዘመን ጥቅምት24/2012
መርድ ክፍሉ