እንደመግቢያ
ምን አለሽ ተራ ከመርካቶ ደቡባዊ ክፍል የሚገኝ ሥፍራ ሲሆን፤ በተለያዩ አካባቢዎች ተፈልጎ የጠፋ ቁስ በዚህ ስፍራ የሚገኝ በመሆኑ ምንም የማይጠፋበት ስፍራ እንደሆነ ለማመላከት የተሰጠ ስያሜ እንደሆነ ሰዎች ይናገራሉ። አንዳንዶች እንደሚሉት ደግሞ፤ በደርግ ዘመን ነዋሪዎች ከቀበሌ ዘይትና ስኳር ይሰጣቸው ነበር። ታዲያ ከቤተሰባዊ ፍጆታ የሚተርፋቸውን ይዘው ወዲህ ሥፍራው ወጣ ይሉ ነበር። ገዥዎችም ‹‹ምን አለሽ?›› ወይንም በእጅሽ ምን ይዘሻል፣ ምንስ ይዘሃል? ሲሉ ይጠይቋቸውና ይገበያዩ ነበር ይላሉ። በዚህም የተነሳ አካባቢው ‹‹ምን አለሽ ተራ›› እንደተባለ ይናገራሉ።
ምንም እንኳን በስያሜው አሰጣጥ በእርግጠኝነት መደምደም ባይቻልም በአሁኑ ወቅት ወደስፍራው የሚያቀና ሰው ለስፍራው የተሰጠው ስያሜ ለክርክር እንደማይቀርብ ይገነዘበዋል። ይህ አካባቢ ከእሁድ እስከ እሁድ ሁሌም ሥራ፣ ሁሌም ሩጫ፣ ሁሌም ግፊያ፣ ሁሌም እንደ አቂሚቲ ሰርቶ ማግኘት፤ ማትረፍ፤ መክሰር ወዘተ ትዕይንቶች የሚታይበት ስፍራ እንደሆነም ነዋሪዎች ይናገራሉ።
ሰዎች በምንአለሽ ተራ
ጉራጌ ዞን የተወለደው አቶ ሰፋ ያሲን ሥራ ፍለጋ ከ30 ዓመት በፊት ወደ አዲስ መምጣቱን ያስታውሳል። ከዚያም ሳያስበው የኑሮ መልህቁን ከ‹‹ምንአለሽ ተራ›› ጣለ። ያረጁ ቢላዎች፣ ሚስማር፣ የጀሪካን ክዳን፣ ወስፌ፣ ብሎን መፍቻዎችንና ሌሎች የቤት ዕቃዎችን እየገዛ ለፈላጊዎች ይሸጣል። በዚህ ሥራውም ግን ሁለት ልጆቹን አሳድጓል፤ ማህበራዊ ሕይወቱን መርቷል እየመራም ይገኛል።
ታዲያ እርሱ በ‹‹ምን አለሽ›› ተራ ኪራይ ባይከፍልም የቤት ጣሪያ ተከራይተው እቃ የሚያስቀምጡ በርካታ ጓደኞች አሉት። በወር እስከ አምስት ሺህ ብር እየከፈሉ እቃቸውን ከጣሪያ ላይ ያኖራሉ። በምን አለሽ ተራ ከቤት ወለል በላይ የቤቱ ጣሪያ ዋጋውም ተፈላጊነቱም ከፍ ያለ ነው።
አንማው ገደፋዬ በጎጃም መርዓዊ ተወልዶ በ2004 ዓ.ም የእንጀራ ጉዳይ ዘወር ዘወር፤ ሸከርከር አድርጋው ከዋና ከተማዋ ከአዲስ አበባ አስቀመጠችው። ከአራት ዓመት በፊት ደግሞ ከምን አለሽ ተራ ጋር በሰፊው ተዋወቁ። ከዚያም ደንበኝነቱን ጠበቅ እያደረገ መጣ። ሥራ አይመርጥም። በድርጅቶች ውስጥ ሥራ ሲገኝ ከባለሃብቶች ጋር ይሠራል። በተሽከርካሪዎች ላይ እንደ ረዳት ሆኖ ያግዛል። አልፎ አልፎ ‹‹ከምን አለሽ›› ተራ ወጣ ይልና ሌላ ስራ ሠርቶ ይመለሳል።
ነገር ግን ከዚህ ሥፍራ እስመጨረሻው ሊለያይ አይፈልግም። በስምንት ዓመት የአዲስ አበባ ቆይታው በርከት ያሉ አካባቢዎችን ተዘዋውሮ ቢሠራም እንደ ምንአለሽ ተራ ለድሃ አሳቢ ተንከባካቢ አላየሁም ባይ ነው። በአካባቢውም ሰውም እቃም፣ ሻጭም ገዥም የሚባዘበት ነው። በዚያው ልክ ደግሞ ግጭትም የሚበዛበት ሥፍራ መሆኑን ይናገራል። በዚህ አካባቢ ያረጀ ስፖንጅም ይዘህ ብትመጣ ገዥ በጥያቄ ያጣድፉሃል ይላል። ‹‹አንድ ሰው ባዶ ኪሱን ወደዚህ መንደር ካመራ ከደቂቃዎች በኋላ ለዕለት ጉርስ የሚሆን ሳንቲም አያጣም።›› ስለዚህ ከአዲስ አበባ መንደሮች ይለያል ሲል አንማው ለምናለሽ ተራ ያለውን ፍቅር ይገልፃል።
እርሱም በምን አለሽ ተራ ውስጥ ብዙ ክፍልፍሎችና መጠሪያዎች እንዳሉ እየነገረኝ ‹‹ጋዝ ተራ፣ ቀለም ተራ፣ ጠርሙስ ተራ፣ ቆርቆሮ ተራ፣ መሶብ ተራ፣ ቡና ተራ፣ ሚስማር ተራ፣ ጫማ ተራ፣ በርሜል ተራ፣ ዶሮ ተራ፣ ሽንኩርት ተራ…›› ዞር ዞር ብለን ጎበኘነው።
አገልግሎት የጨረሱ በርሜሎች እንደ አዲስ ገበያ ላይ ወጥተው ግዙኝ ብለው ይገማሸራሉ። አረጀሁ፤ ዕድሜ በቃኝ ብለው ከአንዱ ጥግ አይቀመጡም በበርሜል ተራ። ‹‹ጣሳ ተራ›› በዓይነትና በብዛት ጣሳ ይሸጥበታል። አዳዲስ የሆኑ ጣሳዎች ወደ ክፍለሀገር ለሌላ ግልጋሎት ይላካሉ። በርካታ የመድሃኒት ብልቃጦችም በዚህ ሥፍራ ድጋሜ አገልግሎት እንዲሰጡ ገበያ ላይ ይወጣሉ። ማር ማስቀመጫና ሌሎች ጣፋጭ ነክ ነገሮችን ለማስቀመጥ የሚውሉ ዕቃዎች ከጣሳ ተራ ይገኛሉ።
በቀለም ተራ አጃዒብ የሚያስብሉ ሥራዎች ይከናወናሉ። ሰዎች የቤት ቀለም ቀብተው የቀለም ማስቀመጫውን ቆርቆሮ ይዘው ወደዚህ ስፍራ ይመጣሉ። ታዲያ በዕቃው ውስጥ ትንሽ ቀለም እንኳን ቢኖር እንዲሁ አይጣልም። ቀለሙ የደረቀ እንደሆነ በኬሚካል ነካ! ነካ! ተደርጎ ከጣሳው ላይ ይፋቃል። ቀለሞች በየዓይነታቸው በዕቃ ይቀመጡና አንድ ላይ ይሞላላሉ። ከዚያም ታሽጎ ለሽያጭ ገበያ ላይ ይቀርባል፤ ቤትም ያስውባል።
በምን አለሽ ተራ አንድ ሜትር በአንድ ሜትር የሆነች ሱቅ ኪራይ እስከ 5ሺህ ብር እንደሆነ ወጣት አንማው ይናገራል። ሱቅ ውስጥ የሚቀመጡት ውድ የሆኑና ከፍተኛ ክብደት ያላቸው ቁሳቁሶች ብቻ ናቸው። ከዚያ ውጭ ያሉት ግን ከሱቋ ጣሪያ ላይ እንደ ዳሽን ተራራ ይቆለላሉ። አከራዮችም የሚደራደሩት በሱቋ ወለል ስፋት ሳይሆን በጣሪያው ስፋት፣ ጥንካሬ እና ምቾት ነው። ይህ ክስተት በኢትዮጵያ ውስጥ የቤት ጣሪያዎች እረፍት አልባ ሆነው ዘርፈ ብዙ አገልግሎት የሚሰጡበት በመሆኑ ልዩ ክስተት ነው ሲል አንማው በአግራሞት ይናገራል። የተወለደበትን የጎጃም ቤቶችን ጣሪያ ‹‹ከምን አለሽ›› ጣሪያዎች ጋር እያነፃፀረ በአድናቆት እራሱን ይነቀንቃል።
ላለፉት 40 ዓመታት በምንአለሽ ተራ ፕላስቲኮችን በመግዛትና በመሸጥ ኑሩዋቸውን መርተዋል-አቶ ጌታቸው ቱርፊ። እርሳቸው አካባቢውን በቁጭትም በስስትም ይመለከቱታል። አዲስ አበባ በአራቱም ማዕዘናት እያደገች እየተለወጠች ስትምጣ እርሳቸው የሚኖሩበት መንደር ‹‹አለሁ እንዳለሁ›› ብሎ መኖሩ ቁጭት ፈጥሮባቸዋል። ለመሆኑ መቼ ይሆን እንደ አዲስ አበቤዎች አምረን፤ እንደ አዲስ አበባም ደምቀን ለዕይታ ዓይነ ግቡ የምንሆነው ብለው በቁጭት ይጠይቃሉ። መሃል ከተማ ሆኖ ሰውም አካባቢም በሚገባ ያለመለወጡ ያስቆጫቸዋል።
በሌላ ጎኑ ደግሞ በዚህ ስፍራ ኖረው በዚሁ ሥራቸው ቤተሰባቸውን ያስተዳደሩበት፣ ማህበራዊ ሕይወት የተዋዋሉበት፣ ክፉና በጎውን ያዩበት በመሆኑ በሥሥት ይመለከቱታል። በዚህ ሥራም አራት ልጆቻቸውን አስተምረው ለቁምነገር አብቅተዋል።
አቶ ጌታቸው አሮጌ ጀሪካኖችን ይገዛሉ፤ ይሸጣሉ። ከ‹‹ውሃ ሽንት›› እቃዎች ጀምሮ የማልገዛው ነገር የለም ይላሉ። ግን የእቃው ብዛትና፣ የቦታው ጥበት ባለመመጣጣናቸው የሚበዛውን ንብረታቸውን ከቤቱ ጣሪያ ላይ ያስቀምጣሉ። አንድ ሜትር በአንድ ሜትር በሆነችው ሱቅ ጣሪያ ላይ የጀሪካን ድርድሮች ለዕይታ በሚያስፈራ መልኩ ወደ ላይ ተቆልሏል። ታዲያ ብዙ ጊዜ ይህ የተቆለለው በራሱ ጊዜ እየፈረሰ አደጋም እያደረሰ መሆኑን ይናገራሉ።
በ1981 ዓ.ም እና በ1987 ዓ.ም አካባቢው የዕሳት አደጋ ተከስቶ ብዙ ንብረት መውደሙን ያስታውሳሉ። ታዲያ አካባቢው የስራ ብቻ ሳይሆን የሥጋት ስፍራም እንደሆነ ያስረዳሉ። ከሥራው ክብደትና አደጋ መብዛት የተነሳም ወደ አካባቢው ቤተሰቦቻቸው እንዲመጡም አይፈቅዱም።
ከመንግስት ለተከራዩዋት ሱቅ 300 ብር ወርሃዊ ክፍያ ይፈፅማሉ። 7000 ብር ደግሞ ዓመታዊ ግብር ይከፍላሉ። በእርሳቸው አባባል ‹‹እኔ እየከፈልኩ ያለሁት ለወለሉ ሳይሆን ለጣሪያው ነው ይላሉ።›› ከወለሉ በበለጠ ጣሪያው ጥሩ ጥቅም እንዳስገኘላቸው ለመግለጽ ሲሉ ነው ይህንን አባባል መጠቀም የፈለጉት።
30 ዓመታት በዚሁ ሥፍራ ሲሠሩ ቆይተዋል ስማቸውን መናገር የማይልጉት የጠርሙስ ነጋዴ። ከግለሰቦች ጀምረው ‹‹ቆራሊዮ›› ብለው ዞረው ጠርሙስ ከሚለቅሙ ሰዎች ላይ ጠርሙስ ይገዛሉ፤ ከዚያም ፈላጊ ሲመጣ ይሸጣሉ። አንድ ጠርሙስ እስከ ሦስት ብር ከሃምሳ ሳንቲም ይገዛሉ። በጠርሙስ የጎደለባቸው፣ የጠፋባቸው፤ የተሸረፈባቸው ደግሞ ከእራሳቸው ዘንድ ሄደው ይገዛሉ። አጠብ አጠብ አድርገውም ለጉዳያቸው ይጠቀሙበታል። የታሪክ ቅርስ የሚሆኑ ጠርሙሶችም አልፎ አልፎ እንደሚመጡ ይናገራሉ።
አሁን ለሚሠሩበት ቤት በየወሩ 300 ብር ኪራይ ይከፍላሉ። ታዲያ ከመንግስት የተከራዩት ሱቅ ስፋቱ አንድ ሜትር በሁለት ሜትር ነው። ሱቋ ጠባብ በመሆኗም በርካታ እቃዎችን ከቤቱ ጣሪያ ላይ ይደረድሩታል። በዚህ ስፍራ አንዱ የአንዱን ዕቃ የማይነካ በመሆኑ ይጠፋብኛል የሚል ሥጋት የለባቸውም፤ ከአጠገባቸው የሚሰሩ ባልደረቦቻቸውም እንዲሁ።
መልዕክት
የሆነው ሆኖ ‹‹ምንአለሽ ተራ›› ለበርካቶች ህይወት መለወጥና የዕለት ጉርስ ማግኛ ሥፍራ ሆኗል። አካባቢው በተሻለ ደረጃ እንዲለማም ይሻሉ። ለዚህም በአክሲዮን ተደራጅተው ለመንግስት ጥያቄ አቅርበዋል። ዳሩ ግን ፈቃድ ማጣታቸውን ይናገራሉ። ልጆቻቸውን ያሳደጉበት፤ የዕለት ጉርስ ያገኙበት ስፍራ በበለጠ ለማልማት ከመሻት ውጭ ሌላ አካባቢ አይናፍቃቸውም። መንግስትም ይህን እዲገነዘብላቸው ይፈልጋሉ።
አዲስ ዘመን ጥቅምት22/2012
ክፍለዮሐንስ አንበርብር