እሁድ መጋቢት 1 ቀን 2011 ዓ.ም ከጠዋቱ ሁለት ሰዓት ከ38 ደቂቃ ሲል፤ ከአዲስ አበባ ቦሌ ዓለም ዓቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ተነስቶ ወደ ኬንያ ዋና ከተማ ናይሮቢ በረራ የጀመረውና ንብረትነቱ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የሆነው ኢቲ 302 ቦይንግ 737 ማክስ 8 አውሮፕላን ከስድስት ደቂቃ በኋላ ችግር እንዳጋጠመው ፓይለቱ ሪፖርት ማድረጉንና በዚያው ቅፅበትም ከራዳር ውጭ በመሆን መከስከሱ ይታወቃል:: አውሮፕላኑ በአጠቃላይ ከ35 አገራት የተውጣጡ 149 መንገደኞችንና 8 የበረራ ሰራተኞችን አሳፍሮ የነበረ ሲሆን፤ የሁሉም ተሳፋሪዎችና የበረራ ሠራተኞች ህይወት ማለፉ ይታወሳል፡፡
ኢትዮጵያዊያንን ብሎም የመላውን ዓለም ህዝብ በእንባ ያራጨው ይህ አሳዛኝ ክስተት የተከሰተው በኦሮሚያ ክልል ቢሾፍቱ ከተማ አቅራቢያ ኤጄሬ በተባለ ስፍራ ሲሆን፤ አደጋው ከመከሰቱ ከአምስት ወራቶች በፊት “ላዮን ኤየር” የተሰኘ የኢንዶኔዢያ አየር መንገድ ንብረት የሆነ ተመሳሳይ ሞዴል አውሮፕላን ለበረራ በተነሳ በደቂቃዎች ውስጥ ተከስክሶ የ189 ሰዎች ህይወት ማለፉ ይታወሳል።
በዚህም ቦይንግ 737 ማክስ 8 አሜሪካ ሰራሽ አውሮፕላን በአምስት ወራቶች ውስጥ ሁለት ጊዜ የመከስከስ አደጋ የደረሰበት በመሆኑ፤ ኢትዮጵያን ጨምሮ የተለያዩ አገሮችና አየር መንገዶች ማክስ 8 አውሮፕላን እንዳይበር እገዳ ጥለዋል። ይህንንም ተከትሎ የቦይንግ ዓለም አቀፍ የገበያ ድርሻ እገዳው በተጣለ በሳምንታት ውስጥ 12 ነጥብ 9 በመቶ ያሽቆለቆለ ሲሆን፤ ካምፓኒው ሁለቱም አደጋዎች በቦይንግ 737 ማክስ አውሮፕላን የበረራ ሶፍትዌር ስህተት መከሰታቸውን በማመን የነበረውን ክፍተት የሚሞላ የተሻሻለ ሶፍትዌር ከወራት በፊት በማስተዋወቅ ዳግም ወደ ገበያ ለመግባት እየሰራ ይገኛል።
ቦይንግ አውሮፕላን አብራሪዎች እንዴት በተሻሻለው ሶፍትዌር መገልገል እንዳለባቸው መመሪያ አዘጋጅቶ ለፌዴራል አቪዬሽን አድሚንስትሬሽን (ኤፍኤኤ) ሰጥቶ እየተገመገመ ሲሆን፤ አየር መንገዶቹ የሙከራ በረራ ካደረጉ በኋላ የማረጋገጫ ሰርተፍኬት እንደሚያገኝም ይጠበቃል።
ነገርግን ቦይንግ የሶፍትዌር ማሻሻያ ባደረገባቸው 737 ማክስ አውሮፕላኖች 207 በረራ ማድረጉን ያስታወቀ ሲሆን፤ የኩባንያው ዋና ሥራ አስፈፃሚ ዴኒስ ሙለንበርግ ከትናንት በስቲያ ከሴኔቱ የንግድ ቋሚ ኮሚቴ ፊት ቀርበው ለሁለቱ አውሮፕላኖች መከስከስ መንስኤ የሆኑ ችግሮችን አብራርተዋል።
የአሜሪካ ሴናተሮች የዋና ሥራ አስፈጻሚውን ማብራሪያ ከሰሙ በኋላ፤ “ኩባንያው የተሳፋሪዎችን ደህንነት ከማረጋገጥ ይልቅ ትርፉን አስቀድሟል” ሲሉ ቦይንግን ወንጅለዋል። አክለውም፤ “ኩባንያው ትርፉን ብቻ በማስላት አውሮፕላኖቹን ቶሎ ወደ ሥራ ለማስገባት መጣደፉ ከባድ ችግር ነበር” ሲሉ ወቅሰዋል።
ሴናተሮቹ ለሁለቱም አደጋዎች ምክንያት የሆነውን የአውሮፕላኑን ችግር ቦይንግ ቀደም ሲልም ያውቅ ነበር በሚለው ላይም በግልፅ ሃሳባቸውን ያስቀመጡ ሲሆን፤ ሴናተር ሪቻርድ ብሉሜንዛል እንዳሉት “ቦይንግ ይሁንታ አግኝቶ ቶሎ ወደ በረራ እንዲገባ ኩባንያው ነገሮችን በጥድፊያ አከናውኗል” ሲሉ ድርጊቱን ኮንነዋል።
አያይዘውም፤ “ይህ የሚያሳየው ቦይንግ ከተሳፋሪዎች ደህንነት ይልቅ ትርፉን ማስቀደሙን ነው።” በማለት ከአደጋው ምርመራ ጋር በተያያዘም ቦይንግ በተደጋጋሚ ሆን ብሎ መረጃዎችን ሲያሳስትና ሲዋሽ እንደነበርም ገልፀዋል።
የአሜሪካ የሕግ አውጭ አካላት ቦይንግ 737 ማክስ 8 አውሮፕላን ለመብረር ስለጠየቀ ብቻ እንዲበር ፈቃድ መሰጠቱን ሆን ተብሎ ታቅዶበት እንዲደበቅ በማድረጉ በቦይንግ ዋና ስራ አስፈጻሚ ላይ ክስ እንዲመሰረትበት መደረጉንም ገልጸዋል።
ሥራ አስፈጻሚው ዴኒስ ሙለንበርግ በበኩላቸው፤ “በድምሩ ለ346 መንገደኞች ህይወት መጥፋት ምክንያት የሆነው በሁለቱ 737 ማክስ 8 አውሮፕላን ላይ የደረሰው የመከስከስ አደጋ በኛ ስህተት የደረሱ አደጋዎች መሆኑ እሙን ነው። ከሁለቱም አደጋዎች ተምረን መደረግ ያለባቸውን ለውጦች ለይተን አውቀን ለውጦችን እያደረግን ነው” ሲሉ ተናግረዋል።
በሌላ በኩል፤ በአደጋው የሞቱት ሰዎች ቤተሰቦች የአደጋውን ሰለባዎች ፎቶ ግራፎች ይዘው በችሎቱ የተካፈሉ ሲሆን፤ ብዙዎቹ ሥራ አስፈጻሚው ችግሩን ለማድበስበስ ሲሰሩ እንደነበር ገልጸው በዚህም ከኃላፊነታቸው ሊነሱና ለፍርድ ሊቀርቡ እንደሚገባ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ከነዚህ መካከል በኢትዮጵያው አየር መንገድ አውሮፕላን በደረሰው አደጋ ሰበብ እህቷን ያጣችው አድናን ስቱሞ፤ “ዋና ስራ አስፈጻሚው አውሮፕላኑ ችግር እንዳለበት እያወቁ የመጀመሪያው አደጋ ከደረሰ ከአምስት ወራት በኋላ በኢትዮጵያው አየር መንገድ 157 ሰዎች ህይወታቸውን ሲያጡ ነው አውሮፕላኑ እንዳይበር እገዳ ያስተላለፉት። ስለዚህ የ346 ሰዎችን ህይወት በቸልተኝነት እንዲጠፋ በማድረጋቸው ከኃላፊነታቸው ተነስተው ሊታሰሩ ይገባል” ብላለች።
“ዋና ስራ አስፈጻሚው ኃላፊነት የማይሰማቸው ሰው ናቸው። በአደጋው ህይወታቸውን ላጡት 346 ሰዎች ኃላፊነቱን ሊወስዱ ይገባል። ምክንያቱም አውሮፕላኖቹ የደረሰባቸው የመከስከስ አደጋ በቀላሉ ቀድሞ መቆጣጠር የሚቻል ነበር” በማለት ለቢቢሲ የተናገሩት ደግሞ፤ በኢትዮጵያው አየር መንገድ አውሮፕላን በደረሰው አደጋ አምስት የቤተሰብ አባላቸውን ያጡት ፓውል ንጆሮጌ ናቸው።
ቦይንግ ሁለቱ አደጋዎች ከደረሱ በኋላ የአውሮፕላኑን የበረራ ሶፍትዌሮችን እያስተካከለ መሆኑን ሴናተሮቹ ጠቁመው፤ ነገርግን የበረራ ማረጋገጫው መዘግየት ከፍተኛ ጥርጣሬ እንዳስከተለ ተናግረዋል፡፡ እንዲሁም፤ ባለፈው ከተከሰቱ አደጋዎች በፊት ስለኤም.ኤስ.ሲ ስርዓት ለተቆጣጣሪዎች ወይም ለአውሮፕላን ካፒቴኖች ስልጠና ባለመስጠቱ ቦይንግን ኮንነዋል፡፡
ሴናተር ማሪያ ካንዌል በበኩላቸው፤ “በአውሮፕላኖቹ ብቻ ሳይሆን በመኪኖች እና በሌሎች የመጓጓዣ ዓይነቶችም በጣም የተለመዱ እየሆኑ የመጡ አውቶማቲክ ስርዓቶች በስፋት መመርመር አለባቸው። ምክንያቱም፤ ባለፈው ከደረሱ ሁለት አሰቃቂ አደጋዎች በመማር ችግሮችን ቀድሞ መፍታት ካልተቻለ ኃላፊነት በጎደለው ሥራ የብዙዎች ህይወት ዳግም አደጋ ላይ ይወድቃል፤” ሲሉ አሳስበዋል።
በአምስት ወራት ልዩነት በላዮን አየር መንገድና በኢትዮጵያ አየር መንገድ የቦይንግ ማክስ 8 አውሮፕላኖች ላይ በደረሰው የመከስከስ አደጋ በጥቅሉ 346 ሰዎች ህይወታቸውን ማጣታቸው ይታወሳል።
ምንጭ:- ቢቢሲ
አዲስ ዘመን ጥቅምት21/2012
ሶሎሞን በየነ