ዶ/ር ሂፖሊቴ ፎፋክ በአፍሬክስም ባንክ ዋና ኢኮኖሚስት፤ የጥናት ምርምርና ዓለም አቀፍ ትብብርም ዳይሬክተር ናቸው። በዚህ ሳምንት የሩሲያና አፍሪካ ስብሰባ በሩሲያዋ ሶቺ ከተማ መካሄዱን ተከትሎ በአዲስ መልክ ብቅ እያለ ያለውን የሩሲያና አፍሪካ ግንኙነት ከፍተኛ ትርጉምና ፋይዳ በተመለከተ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል። የዶክተሩም ሀሳብ እንዲህ ለንባብ ቀርቧል።
ሩሲያ ለአፍሪካ አዲስ መጤ ወዳጅ አይደለችም። አብዛኛዎቹ የአፍሪካ ሀገራት በቅኝ ግዛት በሚማቅቁበት ወቅት ሩሲያ ከፍተኛ እገዛና እርዳታ ስታደረግ የኖረች ሀገር ነች። አዲሱ ትውልድ ይሄንን የቀደመ እውነት እንዲያውቅ አልተደረገም። ለምሳሌም በሩሲያ ውስጥ በአፍሪካዊው ታጋይ ፓትሪስ ሉሙምባ ስም የተሰየመ ታዋቂ ዩኒቨርሲቲ አለ። በአፍሪካ ውስጥ ግን ማስታወሻ አልቆመለትም። ሩሲያ ከበርካታ የአፍሪካ ሀገራት በተለያየ ዘመን ተማሪዎችን በመቀበል አስተምራለች። አስመርቃለች። ሀገራቸውንና ሕዝባቸውን እንዲያገለግሉ አድርጋለች። በሩሲያ ፌዴሬሽንና በአፍሪካ መካከል ያለው ግንኙነት ዘመን የተሻገረ ነው።
በዚያን ዘመን ሶቭየት ሕብረት የአፍሪካ ሀገራት ለነጻነትና የራሳቸውን እድል በራሳቸው ለመወሰን በሚያደርጉት ትግል ታክቲካልና የሎጅስቲክ እርዳታ ትሰጥ ነበር።
በቅርብ ዓመታት ምናልባትም ዓለም አቀፉን ርእዮተ አለማዊ ሁኔታ በሚያንጸባርቅ መልኩ ይህ የአሁኑ በሩሲያና በአፍሪካ መካከል የተፈጠረው የኢኮኖሚ ትብብር ከፍተኛ ፍላጎትን አሳድሮአል። ለምሳሌም ያህል ባለፈው አስር ዓመት በሁለቱ አጋሮች (ሩሲያና አፍሪካ) መካከል ያለው የንግድ ግንኙነት ከ140 በመቶ በላይ አድጓል። በ2018 (እኤአ) 20.4 ቢሊዮን ደርሷል። ከሩሲያ የሚመጣው ኢንቨስትመንት በማደግ ላይ ይገኛል። የበለጠ ለማስፋት ሰፊ አማራጮችም አሉ።
በሩሲያና በአፍሪካ መካከል ታሪካዊ ግንኙነቶቻቸው ሲታዩ አብሮ ለመስራት ያሉት እድሎች የበለጠ ለመስራት የሚያስችሉ ናቸው። ሩሲያ በቴክኖሎጂ፤ በኢነርጂ፤ በመሰረተ ልማት የደረሰችበት ታላቅ የእድገት ደረጃ ለአፍሪካ ኋላቀር መሰረተ ልማት እጅግ በጣም ጠቃሚና አስፈላጊ ነው። በተለይም በአፍሪካ ስር የሰደደ የኃይል ማመንጫና ማከፋፈያ ችግር አለ። ልማትና እድገት ለማምጣትና ለማስፋፋት ዋነኛ ማነቆ መሆኑ ተለይቷል።
የሩሲያ ውሁድ የሆነ የተፈጥሮ ሀብት አያያዝ እውቀት አፍሪካ አህጉር ካላት የተትረፈረፈ የተፈጥሮ ሀብት አንጻር ተጠቃሚ እንድትሆን ይረዳታል። አፍሪካ በሸቀጦች ላይ የተመሰረተ ኢንዱስትሪላይዜሽን እንድትመሰርት የኢኮኖሚና የንግድ ትብብር በተመጣጠነ መንገድ እንድታራምድ ያስችላታል።
ባለፈው ሰኔ በሞስኮ በተካሄደው በአፍሪካ ‹ኤክስፖርት ኢምፖርት ባንክ› (አፍሬክሲም) ዓመታዊ ስብሰባ ላይ ኦፊሴላዊ በሆነው የመክፈቻ ንግግራቸው የሩሲያው ጠቅላይ ሚኒስትር ዲሚትሪ ሜድቬዴቭ ግሎባላይዜሽን በታዳጊ ሀገራት ውስጥ የልማት ተዋናዮችን አሰላለፍ ለውጦታል፤ አፍሪካን የሩሲያ በጣም ጠቃሚ አጋር አድርጓታል ሲሉ ተናግረዋል። አክለውም ከሩሲያ በርካታ አስርት ዓመታትን ካስቆጠሩ የቆዩ የንግድና የቢዝነስ የኢንዱስትሪ ተሞክሮዎች አፍሪካ ተጠቃሚ በመሆን እድሎቹን በማስፋት የምርት አቅሟን ማሳደግና ማስፋፋት አለባት ብለዋል።
በተመሳሳይ መልኩ ፕሮፌሰር ቤኔዲክት ኦራማህ የአፍሬክስ ባንክ ፕሬዚደንት በሁሉም የዓለም ክፍሎች የሚገኙ አጋሮች የአፍሪካን እድገትና እርምጃ፤ የአፍሬክስ ባንክ ራእይ የሚደግፉ ሁሉ ኃይላቸውን አቀናጅተው ለአፍሪካ አዲስ አጀንዳ ግፊት ሊያደርጉ ይገባል ሲሉ ጥሪ አድርገዋል።
አፍሪካ ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት በአማካይ 4.5 በመቶ ጠንካራ የሆነ የኢኮኖሚ እድገት አስመዝግባለች። ይህም በዓለም ደረጃ ካለው 3.8 ከመቶ በላይ ነው። አህጉሩ በዓለማችን ውስጥ ጥቂት ፈጣን የኢኮኖሚ እድገት ያስመዘገቡ ኢኮኖሚዎችንም የያዘ ሲሆን በኢንቨስትመንት ከፍተኛ ገቢ አግኝቷል። አፍሪካ ለታዳጊዎቹም ሆነ ላደጉት ኢኮኖሚዎች ለሁለቱም የዓለም አቀፍ ኢንቨስተሮችን ከፍተኛ ትኩረት የመሳብ ኃይል ፈጥራለች።
አሁንም የአህጉሩ የእድገት ምንጭ ተለዋዋጭ በሆነው ዓለም አቀፍ የንግድ መልክአ ምድር ላይ የንግድ አጋሮችን በመሳብ ብዝሀነትን በስፋት ማንጸባረቅ ችሏል። የደቡብ ዓለም በአፍሪካ ከፍታውን እየጨመረ መጥቷል። ቻይና ሕንድና ሁለት የብሪክስ ሀገራት ከሩሲያ ጋር በመሆን የአፍሪካ የመጀመሪያና ሁለተኛ ነጠላ ግዙፍ የንግድ አጋሮች ናቸው።
ሆኖም ግን ዓለም አቀፉ ንግድ በሚመረቱ ሸቀጦችና እያደገ በመጣው ቴክኖሎጂ የበላይነት በሚመራበት ሁኔታ ውስጥ በአፍሪካ ተከታታይነትና ቀጣይነት ያለው ግዙፍ የኢኮኖሚ እድገት ለማስመዝገብ፤ ከዓለም ኢኮኖሚ እንዲዋሀድ ለማድረግ በሀይል፤ በቴክኖሎጂና በፈጠራ ኢንቨስትመንትን በከፍተኛ ደረጃ ማስፋፋት ይጠይቃል። ከኢንቨስትመንቱ በተጨማሪ በግንባታዎች፤ የኢኮኖሚ መሰረተ ልማት ዝርጋታዎችን በማሳደግ ምርቶችን በከፍተኛ ደረጃ ማስፋፋትን ይጠይቃል። በዚህ ማዕቀፍ የአፍሪካን የመሰረተ ልማት ክፍተት በመሙላት ምርትን በከፍተኛ ደረጃ ማስፋፋትና ማሳደግ በተለይ ወሳኝ ይሆናል።
የሩሲያ ኢንቨስትመንት ቁልፍ በሆኑት ስትራቴጂካዊ ክፍሎችና ኢንዱስትሪዎች በተለይም በፔትሮኬሚካል፤ በአቪየሽንና በባቡር መስመር ዝርጋታ በመላው አፍሪካ የኢኮኖሚ መስፋፋትን ብቻ አይደለም የሚያመጡት። የአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጠናን የማፋጠንና የመጨመርም እምቅ አቅም አለው።
በአፍሪካ ለኢኮኖሚ እድገትና መስፋፋት ወሳኝ የሆነው መሰረተ ልማት ገና አላደገም። ያሉትን ማነቆዎች በመጋፈጥ ለመሰረተ ልማት መስፋፋትና ማደግ የተለየ ትኩረት በመስጠት መስራትን ይጠይቃል። የአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጠና በሸቀጦችና በአገልግሎት አሰጣጥ ረገድ በዓለም አቀፍ ደረጃ ብቸኛው ግዙፍ ገበያ በመሆን፤ አዲስ የንግድ ግንኙነት በመፍጠር ፤ ለመሰረተ ልማት እድገትና መስፋፋት፤ ምርቶችን ለማምረት፤ ቀጥተኛ የውጭ ኢንቨስትመንትን በመሳብም ረገድ ወሳኝ በመሆን የጨዋታውን ሕግ ይቀይረዋል ተብሎ ይታሰባል። ይህንንም በተሳካ ሁኔታ ተግባራዊ ማድረጉ ወሳኝ መሆኑን የዶ/ር ሂፖሊቴ ፎፋክ የሩሲያ አፍሪካ ግንኙነት ምልከታ አስረድተዋል።
አዲስ ዘመን ጥቅምት20/2012
ወንድወሰን መኮንን