በፊደል ገበታ የንባብ አፋቸውን አፍታተው ወደ መደበኛ ትምህርት የሚሸጋገሩ ታዳጊ ሕጻናት በመጀመሪያ የሚፋጠጡት ከአራቱ መሠረታዊ የሂሳብ ስሌቶች ጋር ነው። ከመደመር፣ ከመቀነስ፣ ከማባዛት እና ከማካፈል ጋር። የኒኩልዬር ሳይንስ ትንተና ከዘርፉ ውጭ ለሚገኙ በርካታ ቀለም ጠቀስ ጎልማሶች እንቆቅልሽ የመሆኑን ያህል የመደመር ስሌትም እንዲሁ በመጀመሪያዎቹ ቀናት በጨቅላ ሕጻናቱ አእምሮ ገዝፎ የሚያስጨንቃቸው ከረቂቁ የፊዚክስ ጥበብ ባልተናነሰ ደረጃ ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም።
ድምሩ አሥር ሲሞላ አንድ አለኝ፣ ሃያ ሲደርስ ሁለት አለኝ፣ ወደ ሰላሣ ሲሸጋገር ሦስት አለኝ የሚለው የመደመር “ረቂቅ ሕግ” ምሥጢሩ እስኪገባቸው ድረስ እንኳን ስሌቱ “አለኝ” የሚለው ተደጋጋሚ ቃል በራሱ እንደሚያሰለች በዕድሜ ርዝመት አባቶች ነን ለምንለው ዜጎችም ሳይቀር ትዝታው የሚዘነጋ አይደለም።
ለፊደል አንጋቾቹ ታዳጊ ሕጻናት የመቀነስ ስሌት ጥበብም ከመደመር ስሌት ባልተናነሰ እንደሚፈታተናቸው ይታወቃል። ጎረቤት ከሚገኝ ማንኛውም ቁጥር “አንድ ስንበደር ወደ አስር ይለወጣል” የሚለው የስሌት ሕግ ጨቅላዎቹን ግራ ማጋባት ብቻ ሳይሆን “አእምሯቸውን አጡዞ ለልጅነት ነስርም” ሊዳርጋቸው ይችላል። የነስሩን የልጅነት ታሪክ ያጫወተኝ በልጅነቱ የመቀነስ ስሌት ጉድ የሠራው የዛሬው ኢንጂነር አብሮ አደግ ጓደኛዬ ነው። ይህ የዕድሜና የቀለም ጓደኛዬ ስለ አራቱ የሂሳብ ስሌቶች ባነሳን ቁጥር ደጋግሞ የሚናገረውን አንድ አባባል ወደኋላ አስታውሳለሁ።
ከመማሪያ ደብተራችን በስተጀርባ በሚገኘው የጊዜ ቤት ሰንጠረዥ ላይ አፍጥጠን 2 ጊዜ 2 = 4፣ 3 ጊዜ 3 = 9 እያልን የምንሸመድደውና ወደ ማባዛቱ ስሌት ስንገባም አንድ አለኝ፣ ሁለት አለኝ፣ ሦስት አለኝ፣ አራት አለኝ እያልን የምንቀምረው የሂሳብ ስሌት ምሥጢሩ እስኪገለጥልን ድረስ በሕጻንነት ዕድሜያችን ያስከፈለንን ዋጋም በቀላሉ የምንረሳው አይደለም። በማካፈል ስሌት ውስጥ የሚገኙት ተቀናሾችና ተደማሪ ቁጥሮች “ረቂቅ ጥበብም” እንዲሁ ለታዳጊ ሕጻናቱ ሞጋችና እንቅልፍ እስከ መንሳት የሚያደርስ ሞገደኛ የስሌት ሕግ ነው። ወደ ፍራክሽን ስሌት ደረጃ መሸጋገርማ “ጨረቃ ላይ የማረፍ” ያህል እንደምን ዠት ሆኖ ሕጻናቱን እንደሚያባንን እንኳን በትምህርት ጅማሮ ግብ ግብ ላይ ለሚገኙ ብላቴኖቻችን ቀርቶ የዛሬ ጎልማሶችና አዛውንቶችም ሳይቀሩ ትዝታቸውን ለማውጋት መሽቀዳደማቸው አይቀርም።
ከላይ በእማኝነት የጠቀስኩትና ዛሬ በአንቱታ ደረጃ ላይ የሚገኘው መሃንዲሱ አብሮ አደግ ጓደኛዬ በዕለት ተዕለት ሕይወቱ ውስጥ ተግዳሮቶች ሲገጥሙት እኛ የዕድሜ እኩዮቹን ፈገግ እያስደረገ የሚፅናናው “እንኳን ይህንን ችግር ይቅርና አራቱን የሂሳብ መደቦችና የፍራክሽንንም ፈተና ተቋቁሜ አልፌያለሁ” በሚለው የተዘወተረ አባባሉ ነው።
በልጅነት ገጠመኝ እያዋዛሁ የተንደረደርኩበት የአራቱ የሂሳብ መደቦች ትውስታ “ከሀገራችን ታሪክ ጋር ምን አገናኘው?” በማለት አንባቢው ቸኩሎ ይህንን ጥያቄ ቢጠይቅ መብቱ ነው። የእኔ መልስ በአጭሩ “ምንም አያገናኛቸውም። ነገር ግን በአናሎጂ ወይንም በተመሳስሎ ለጉዳያችን ማዋዣነት ብናስታውሳቸው ክፋት የለውም” የሚል ይሆናል። ደግሞስ “መደመር” የጊዜያችን ገናናና ወርቃማ የመሪ ቃልም አይደል።
ሀገሬ በረጅም ዘመናት ዕድሜዋ ውስጥ መደመርን፣ መቀነስን፣ ማባዛትንና ማካፈልን ያስተናገደችባቸው ታሪኮቿ የትዬለሌዎች ናቸው። እያንዳንዱ ክስተትም በወቅቱና በጊዜው ያሳደረው ሀገራዊ ተጽእኖና አትሞ ያለፈው አሻራም በቀላሉ ተተርኮ የሚያበቃ ብቻ አይደለም። ያውም በጋዜጣ ጽሑፍ? “አባይን በጭልፋ” ማለቱ ይቀላል። በልጅነት ዕድሜ አራቱ የሂሳብ ስሌቶች ጭንቅላታቸውን አዙሮ እስከ “ነስር የዳረጋቸው” ጓደኛዬን መሰል የዛሬዎቹ ጎልማሳ ዜጎች ትዝታቸውን የሚተርኩት በታሪክነቱ ካልሆነ በስተቀር “የለም በጨቅላነት ዕድሜዬ ለነስርና ለጭንቀት የዳረጉኝን ያንን/ያቺን የአራቱን መደብ የሂሳብ መምህር/ት ፈልጌ ዛሬ መበቀል አለብኝ” ብሎ ማሰብ “ወይ ጉድ!” ተብሎ ብቻ በመገረም የሚታለፍ ሳይሆን የሚበጀው በሽተኛውን “ወደ አማኑኤል ሆስፒታል” ወስዶ እርዳታ ማድረጉ ነው።
እንደ ማንኛውም ሀገረ መንግሥት ምሥረታ የሀገራችን ዳርና ድንበርም በረጅሙ ታሪካችን ውስጥ ሲደመርና ሲቀነስ፣ ሲሰፋና ሲጠብ መኖሩ እውነት ነው። እንደ የአዲሱ የመደመር መጽሐፍ ደራሲ ዐብይ አሕመድ (ዶ/ር) አገላለጽ “የኢትዮጵያ ሀገረ መንግሥት ምሥረታ ከሰሜን ወደ ደቡብ በተደረገ ባህላዊ የግዛት መስፋፋት የመጣ ነው። ይህንን የመስፋፋት ሂደት የኢትዮጵያ የፖለቲካ ልሂቃን ከቅኝ ግዛት፣ ከብሔራዊ ጭቆና፣ ከሀገረ መንግሥት ግንባታ አንፃር ይመለከቱታል።” (ገጽ 115) ይሉናል።
የመጽሐፉ ደራሲ “ከሰሜን ወደ ደቡብ” ብለው በአጭሩ የቀጩት ገለጻ ከደቡብ ወደ ሰሜን፣ ከምስራቅም ወደ ሰሜን የሚል ጥቁምታም ቢያክሉበት ኖሮ አይከፋም ነበር። የሆነው ሆኖ ግን ሀገረ መንግሥት እየተለጠጠና እየተሸበሸበ የሚሄደው በግዛት ድንበር ስፋትና ጥበት ብቻ ሳይሆን በሉዓላዊ ክብር ጭምር መሆኑ ሊሰመርበት ይገባል። ይህቺ ታላቅ ሀገር ኢትዮጵያ በዘመናት ውስጥ ለታሪኳ ድምቀት የሚሆኑ በርካታ ተደማሪ ክስተቶችን የማስተናገዷን ያህል በአንፃሩም ክብሯንና ዝናዋን እየሸራረፉና እየቀናነሱ ያሳነሱባትን ታሪካዊ አጋጣሚዎችንም ማስታወሱ አግባብ ይሆናል።
እንደ የታሪክ ባለሙያው ግዛው ዘውዴ አገላለጽ “የእርስ በእርሱን መተሻሸትና የሥርዓተ መንግሥት ለማማከልና ለማጠናከር የተደረጉትን መስፋፋቶች ትተን፤ ሀገርና ወገንን በጋራ በመከላከል ረገድ ከቱርኮች፣ ከዐረቦች፣ ከድርቡሾች/መሃዲስቶች፣ ከግብፆች፣ ከእንግሊዞች፣ ከኢጣሊያኖችና /ከሱማሌዎች/ ጋር በየዘመኑ ጦርነቶች ተካሂደዋል። የነፃነት ታሪካችን የተቀረጸው እነዚህን ወራሪዎች በመመከት ውጣ ውረድ ውስጥ በመሆኑ የአርበኝነትን ዋጋና ታሪካዊ ቦታ እጅግ ከፍ ያደርገዋል።” ይለናል (ዝክረ አርበኝነት 1933 – 2008፤ ገጽ 11)
የትኛውም ሀገረ መንግሥት የተመሰረተው የየዘመናቸው መሪዎችና ሕዝቦች በቀይ ምንጣፍ ላይ እየተረማመዱ የድንበር መስመር በማስመር ተፋቅረውና ተማምነው “እኔ ከዚህ ወዲያ፤ አንተ ከዚያ ወዲህ” እየተባባሉ እንደ አብርሃምና ሎጥ መከባበር በሰፈነበት ስምምነት ዳርቻቸውን ወስነው አይደለም። በፍጹም። ቢመርም ቢኮመጥጥም መስፋፋትና ቅኝ ግዛት የቀዳሚ ዘመናት የሀገረ መንግሥት መመስረቻ ተቀዳሚ ስልቶች ነበሩ። ይህንን ስልት ለመተግበር ደግሞ አንዱ መንግሥት ወራሪ፣ አንዱ ተወራሪ፣ አንዱ አባሪ፣ አንዱ ተባራሪ እየሆኑ መፋለም የተለመደ የዓለም ሀገራት ሁሉ ታሪክ ነበር እንጂ የኢትዮጵያ ብቻ ነበር ብሎ መሞገት ጅልነትም፤ ልጅነትም ነው።
እንኳን “ቡና በሚጣጡ” የአንድ ሀገር ቤተሰቦችና ጎረቤታማቾች ቀርቶ ከሩቅና ከማዶ ጦር እየሰበቁ በሚመጡ እብሪተኛ ወራሪዎች ሳይቀር በርካታ ሀገራት የመስዋዕት በግ የሆኑባቸው ታሪካዊ አጋጣሚዎችን ማስታወስ አይገድም። ጸሐፊው ይህን መሰሉን አካሄድ አጠንክሮ የሚገልጸው እንደ ጽድቅ ይቆጠር ለማለት ሳይሆን የብዙ ሀገራት ታሪካዊ እውነታ መሆኑን በሚገባ አስምሮ ለማለፍ ስለፈለገ ብቻ ነው።
አንዱን የዓለማችንን የታሪክ አንጓ ለአብነት እናስታውስ ብንል እንኳን እውነታው ይህንን ይመስላል። እ.ኤ.አ በ1885 ዓ.ም በበርሊን ከተማ የተሰበሰቡት የወቅቱ ኃያላን የአውሮፓ ሀገራት መሪዎች አፍሪካን እንደ ቅርጫ ሥጋ ለመቀራመት የወሰኑት በምክንያታዊ ሰበብ ሳይሆን በእብሪትና በአልጠግብ ባይነት እንደሆነ ታሪክ አስረግጦ ይነግረናል። የዚህን መሰሉ ስብሰባቸው ውጤት ወደ ተግባር እንዲለወጥ ከውሳኔ ላይ የደረሱት ሁሉንም የአፍሪካ ሀገራት የቅርጫ ድርሻ እንደሚከተለው በመከፋፈል ነበር። ፈረንሳይ 34%፣ ታላቋ እንግሊዝ 32%፣ ጀርመን 7%፣ ቤልጂዬም 7%፣ ስፓኝ 7%፣ ፖርቹጋል 6%፣ ጣሊያን 5%፣ ነፃ የሚባሉ መንግሥታት የተሰጣቸው ኮታ 2% ብቻ ነበር።
እየዋለ እያደረ ግን እብሪተኛዋ ኢጣሊያ ከሊቢያ፣ ከሶማሊያ እና ከኤርትራ የደረሳት የቅርጫ መደብ ቁጥር አነስተኛ መሆኑን ስታሰላስልና የሀገራቱ አብዛኛው ክፍልም ቆላማና በረሃማ መሆናቸውን ስታጤን ለማካካሻ እንዲሆናት ዓይኖቿን በኢትዮጵያ ላይ ጥላ “ጠብ ያለሽ በዳቦ” የወረራ ውሳኔ ላይ ደረሰች። ወሳኔዋን ለመተግበርም ቋምጣ ጦሯን ሺህ በሺህ አሰልፋ በሀገራችን ላይ ብታዘምትም በ1888 ዓ.ም አድዋ ላይ፣ ከአርባ ዓመት በኋላም ከ1928 – 1933 ዓ.ም በፋሽስት ወራሪዎቿ ላይ የደረሰባቸው ውርደት የሚዘነጋ አይደለም። የትኛውም ሀገረ መንግሥት በተመሠረተበት ወቅት ይህንን መሰል ታሪክ ያጣል ብሎ ማሰብ የሚቻል አይደለም። የጦርነት ድልና ሽንፈት የሀገራችን ድንበር ያሰፋልም ያጠባልም፤ ይደምራልም ይቀንሳልም የሚባለው ስለዚሁ ነው።
የርሃብና የድርቅ ታሪካችንም በሰፊዋ ዓለማችን ፊት እንደምን ሀገራዊ ክብራችንንና የዜጎቻችንን ስብዕና በማዋረድና በመቀነስ ስሌት ሰብሮ እንዳዋረደንና እስከ ቅርብ ጊዜያት ድረስ መሳቂያና መሳለቂያ እንዳደረገን ከሩቅ እስከ ቅርብ ያለውን ታሪካችንን በመጥቀስ ዋቢ ማመላከት አይግድም። የሕዝባችን ክብር ብቻ ሳይሆን ቁጥራችንም ሲበዛ ብቻ ሳይሆን ሲቀነስም የኖረው በጦርነት፣ በወረርሽን፣ በመፈናቀል፣ በስደት ወዘተ… መሆኑም አይዘነጋም።
ሀገሬ በመቀነስና በመደመር ስሌት ብቻ ሳይሆን በማካፈል ረድዔትም ብዙ ሀገራትን ታድጋለች። የአድዋ ድል ለዓለማችን ጥቁር ሕዝቦች የአርነት መገለጫ ብቻ ሳይሆን ቀና ብለው በሰብዓዊነታቸው እንዲኮሩ ጭምር ክብሯ ክብራቸው ሆኗል። ብዙዎቹ እንደ ተረት ቆጥረው ቢሳለቁበትም የሰንደቅ ዓላማዋን መሠረታዊ ሦስት ቀለማትን ረቂቅ ትርጉምንም ለበርካታ የአፍሪካ ሀገራት አካፍላለች። የቅርብ ዘመናቱን ታሪክ እናስታውስ ብንል እንኳ ማንዴላን ጨምሮ በርካታ የአፍሪካ አርነት ታጋዮች በኢትዮጵያ ምድር እየተገኙ የተካፈሏቸው ቁሳዊ፣ ሞራላዊና መንፈሳዊ ሀብቶች በወረቀት ብር የሚተመኑ አይደሉም። ክብሯን፣ ሀብቷንና ዕሴቶቿን በዘመናት ውስጥ ለብዙ ሀገራትና ሕዝቦች በቸርነት አካፍላለች፤ የቸርነቷንም አድማስ እያሰፋች ለብዙ ሀገራት በዘርፈ ብዙ ተራዳኢነቷ ስታባዛ ኖራለች።
የሩቁን ታሪክ እያመሳከርንና የቅርቡንም ታሪካችንን እያስታወስን በኩራት የምንተርካቸው ሀገራዊ ጉዳዮቻችን “ብዙ ነበሩ” ተብሎ ብቻ በሁለት ቃላት ገላጭነት የሚወከሉ አይደሉም። ደግነቱ ታሪካዊ፣ ባህላዊና ሃይማኖታዊ ቅርሶቻችንን ለመጎብኘት የሚመጡ የዓለም ቱሪስቶችን ለዓለም ሕዝቦች የደመርነውን፣ ያካፈልነውንና ያባዛነውን ቸርነቶቻችንን እየለዩ እንዲመሰክሩ እድል ስለማንሰጣቸው እንጂ “እህ” ብለን ጆሯችንን ብናውሳቸው ከአንደበታቸው ብዙ መስማት ይቻላል። በሀገራቸው ስለሀገራችን ምን እንደሚባልም ሊመሰክሩልን ይችላሉ።
ይህ የገዘፈና የደመቀ የሀገራችን ታሪክ ዛሬ ዛሬ በራሷ ልጆች፣ የእኔ በምትላቸው ውላጆቿ ሲዋረዱና መዘባበቻ ሲሆኑ መመልከት እንደምን መንፈስን እንደሚያውክና ውስጥን በቁጣ እንደሚሞላ መገመት አይገድም። መገመት ብቻም ሳይሆን አሳፋሪነቱን ማሰብ በራሱ ከአካላዊ ጉዳት የከፋ መሆኑን ለመመስከር አፍ አይዝም።
በክፉ ቀን ሸሽተው ሀገር የካዱ “ሆድ አምላኩ” ዜጎች ቀን ወጣልን ብለው በአደባባይ፣ በግላጭና በብዙኃን መገናኛዎች ሲቀባጥሩ መስማት ያማል። ይጠዘጥዛል። አንተ ማነህ ቢባሉ “እከሌ!” የሚያሰኝ የሚያኮራ ታሪክ የሌላቸውና ሊኖራቸው የማይችል ግለሰቦች ነጋ ጠባ እየተነሱ ታሪክ በራሱ የጉዞ ዛቢያ የደመራቸውን፣ የቀነሳቸውን፣ ያባዛቸውንና ያካፈላቸውን ታሪኮችና አፈ ታሪኮች እንደ ትኩስ እየቀሰቀሱ ለጦርነትና ለአመጽ ዜጎችን ሲያነሳሱ ማስተዋል ከጀመርን ውለን አድረናል።
የመከራ ዝናብ ካልዘነበ እያሉ መማፃናቸው ሳያንስ በአንደበታቸውና በድርጊታቸው ቀስቃሽነት በሚፈጠሩ ግጭቶች በሚፈሰው የንፁሃን ደም እጃቸውን ሲለቃለቁ እያስተዋልን የመከራ ምስክሮች ሆነናል። ቀዳሚዎቹ የሀገራችን መሪዎች በሀገረ መንግሥት ምሥረታ ላይ የተጫወቱትን ክፉም ሆነ በጎ ተግባር በታሪክነቱ ከማስታወስና መጥፎው ደግሞ እንዳይፈጸም፣ መልካሙ እንዲበረታታ የግልን አስተዋጽኦ ከማበርከት ይልቅ ወጣቱ “ሰይፍና ጎመድ” ይዞ በመውጣት እንዲተላለቅ መቀስቀስና ለንብረት መውደም ምክንያት እንዲሆን መጎትጎት ሰይጣናዊነትና ከሃዲነት እንጂ ሌላ ስም ሊሰጠው አይችልም።
በእጅጉ የሚያሳዝነው ግን በከንቱ ከሚያሳብዱት ከንቱዎች ጋር ያለ ዕውቀት የሚያብደው የወጣቱ ጀማ ድርጊት መቼ በቅሎ መቼ ለፍሬ እንደበቃ እንኳ ለመገመት አዳጋች እየሆነ መምጣቱ በራሱ አሳሳቢነቱን ያከፋዋል። ለውጡ ያስገኘው ፍሬ የጎመዘዛቸው፣ ሀገሪቱ የጀመረችው የተስፋ ጉዞ እነርሱን ያሳነሰ የመሰላቸው ዓላማ ቢሶች ድርጊታቸው እንደ አያያዛቸው የሚቀጥል ከሆነ የውርደታቸው ገበና መልሶ እንጦሮጦስ እንደሚያወርዳቸው ነቅተው በጊዜ ቢገነዘቡ ሳይጠቅማቸው አይቀርም።
“እብሪትና ትዕቢት የሞሉት አናት፣
ሰይፍና ጎራዴ የመቱት አንገት፣
አይገላገሉም እንዲህ በቀላሉ፣
እመሬት ላይ ወድቀው ሳይንከባለሉ።”
እንዳሉት ከበደ ሚካኤል ንክ እብዶችን ቼ! በማለት ከኋላ እየገፉና እያንደረደሩ ለጥፋት የሚማግዱ ጊዜ የገለጣቸው ባለጊዜዎችም ህሊናቸውንና ህዝቡ የሰጣቸውን ውክልና ቢያስቡና ከሴራ ቅንብራቸው ቢገቱ ለእነርሱም ሆነ በእነርሱ ዙሪያ ላሉት ሳይጠቅም አይቀርም። እንደነዚህ ዓይነት ወበከንቱዎች ያልገባቸውና ሊገባቸው የማይችለው “ግልጥ ምሥጢር” ኢትዮጵያ ከእነርሱ መፈጠር በፊት መኖሯ፣ ሕዝቦቿም በመከራና በደስታ ለሺህ ዘመናት ተከባብረውና ተረዳድተው መኖራቸው፤ በጋብቻ ቃልኪዳን፣ በአብሮ መኖር ትስስር በጥብቅ የተቆራኙና የተጋመዱበት ገመድም ማንም ሊበጥሰው አለመቻሉን ነው። ሕግ አስከባሪ አካላትም ቢሆኑ “ለወገኔ ይጠቅማል” ከሚል የአድሎአዊ ፍርድ ሚዛናቸውን አጽድተው ፍትሕን ቢያሰፍኑልን ከህሊናቸው እርካታ፣ ከሕዝባቸው አክብሮት ያተርፋሉ አንጂ የሚጎድልባቸው ነገር የለም።
እስካሁን በዝርዝር የጠቃቀስኳቸውን ሃሳቦች በጥቂት ገላጭ ቃላት ላጠቃልል። እውነት ነው እንደ አራቱ መደብ የሂሳብ ስሌቶች ኢትዮጵያ በረጅም ታሪኳ ውስጥ ድንበሯ ሲደመር ብቻ ሳይሆን ሲቀነስም ኖሯል። ሉዓላዊነቷን የደፈሩ ወደረኞቿን አሳፍራ የመለሰቸውን ያህል ስሟና ክብሯም በተፈጥሮና ሰው ሰራሽ ክስተቶች የጎደፈባቸውና ከገናናነቷ ታሪክ እየተቆረሰ የተከፈለበት ዘመናትም ነበሩ። በሕዝቦቿ ታላላቅ ተጋድሎዎችም ለዓለም ጥቁር ሕዝቦች ብቻ ሳይሆን ለነጩም ሆነ ለቢጫው የሰው ዘር በሙሉ ጥበቧንና ጀግንነቷን እያባዛች የኖረችባቸው ዓመታትም አይዘነጉም። ኢትዮጵያ ይህቺ ነች። ኢትዮጵያ “ሳይሞቅ ፈላ” ጉዶች እንደሚያስተዋውቋት አይደለችም።
ኢትዮጵያ ነበረች፤ አለች ወደፊትም በልጆቿ ታፍራና ተከብራ ትኖራለች። ከተያያዘችው የለውጥ ሀዲድ ላይም ማንም ኃይል እንደ ቅዱስ መጽሐፉ ሶምሶን በፀጉሩ ጉንጉን እየጎተተ ለማውረድ ቢሞክር የልቡንም ሆነ የእጁን ውጤት ሳይውል ሳያድር ማዝመሩ አይቀርም። የሀገራችን ፅኑ ታሪክ “የነስር ምንጭ” ሆኖ የሚያሰቃያቸው ህሙማን የሚፈወሱት ከታሪክ እውነታ ጋር ሲታረቁ ብቻ ነው። ሁሌም እንደምለው “ከታሪክ እንክርት ላይ አመዱን ትተው እሳቱን ብቻ መጫር” እስካልቻሉ ድረስ እብደታቸው ጤና አይሰጣቸውምና ህሊናቸውን ቢያዳምጡ መልካም ይሆናል። ሰላም ይሁን!
አዲስ ዘመን ጥቅምት 19/2012