የመጽሐፉ ርዕስ ፡-መደመር
ደራሲ፡- ዐብይ አሕመድ (ፒ.ኤች.ዲ)
የገጽ ብዛት፡- 280
የታተመበት ጊዜ፡-
መስከረም 2012
የመሸጫ ዋጋ፡- 300 ብር
(በጥቁር ገበያ ከብር 350 – 400)
ዳሰሳ፡- ፍሬው አበበ
«መደመር» የሚለው ቃል በፓርላማ መድረክ የተሰማው ከ19 ወራት በፊት ዶ/ር ዐብይ አሕመድ ለጠቅላይ ሚኒስትርነት በተሾሙበት ዕለት ባደረጉት ንግግር ወቅት ነበር። ከዚያ በኋላ ንግግሩ ወደ ህብረተሰቡ ወርዶ በክፉም በደጉም የመወያያ አጀንዳ ሆኖ ከርሟል። «ተደምረሃል፣ ተደምረሻል፣…አልተደመርኩም» መባባልም የቢሮ ወግ ሆኖ ቆይቷል። አንዳንዶች ቃሉ ከተሰማ በኋላ መደመር «የእገሌ ነው… ከእገሌ የተቀዳ ነው» ከሚለው ጀምሮ «የመደመርን ካልኩሌተር የሰራነው እኛ ነን» እስከሚል ብዙ ተሰምቷል።
በሌላ በኩል መደመር ምንድነው? ርዕዮተ ዓለም ነው፣ የፓርቲ ማኒፌስቶ ነው፣ መመሪያ ነው፣ ፍልስፍና ነው?…የሚሉ ማባሪያ የሌላቸው ክርክሮች መሬት ረግጠው ሀሳብ ሲንሸራሸርባቸው ከርመዋል። የመደመር መሐንዲሱ ዐብይ አሕመድ (ፒ.ኤች.ዲ) በመጽሐፋቸው ለእነዚህ ሁሉ መልስ የሚሆን ስንቅ ይዘው መጥተዋል።
ደራሲው የመደመር ሀሳቡ በውስጣቸው የተጠነሰሰው በልጅነት ዕድሜያቸው ስለመሆኑ በመጽሐፋቸው ላይ ማንሳታቸው አስተሳሰቡን ሊነጠቋቸው ለቋመጡ ሁሉ ጥሩ አፍ ማዘጊያ ሆኗል። በመጽሐፋቸው መቅድም ላይ «የመደመር ዕሳቤ የእኛ ነው» ሲሉ ነገሩን ፍርጥ ያደርጉታል። አያይዘውም እንዲህ ይላሉ።
«የመደመር መምህሬ ተፈጥሮ ናት። ጠመኔዋ ደግሞ የልጅነት መንደሬ በሻሻ፣ ሰሌዳዋም የልጅነት አእምሮ….የመደመር ዕሳቤ ስለሕይወት ማሰብ ከጀመርኩበት ጊዜ አንሥቶ አብሮኝ ያደገ ነው። ልጅ ሳለሁ እንደኔ ልጅ ነበር፤ ወጣት ስሆን አብሮኝ ፈረጠመ፤ እነሆ ስጎለምስና ዐዋቂ ሆኜ ሀገራዊ ኃላፊነትን በተለያየ ደረጃ ስቀበል አብሮኝ እየበሰለ በላቀ ደረጃ ለማገለግላት ሀገር የምመርጠው አስተሳሰብ ለመሆን በቃ…»ይላሉ።
ደራሲው የመደመር ገባሮቹንም ሹክ ይሉናል። «የመደመር ዕሳቤ የእኛ ነው። ያመነጩትም ሆኑ ያዳበሩት ገባሮቹ ሁለት ናቸው። አንዱ በዘመናት ታሪካችን ውስጥ የነበሩና ያሉ ሀገራዊ ባህሎቻችንን አምጠው የወለዷቸው የህብረተሰባችንን የልብ ትርታ የተቃኘባቸው ዕሴቶቻችንን ሲሆኑ፤ ሌላው ደግሞ የተፈጥሮ ሕግ ነው። ለዚህም ነው፤ ለቁልፍ ችግሮቻችንን ቁልፍ መፍትሔዎችን እንደሚያቀብል የማምነው።…»
መደመር ምንድነው? ምንድነው የምንደምረው?
«የአለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ መዝገበ ቃላት «ደመረ» የሚለው ቃል መጨመር፣ ማግባት፣መግጠም፣ ማገናኘት፣ መዋሐድ፣ አንድ ማድረግ መቀላቀል፣ መደባለቅ» ይለዋል። የኢትዮጵያ ቋንቋዎች ጥናትና ምርምር ማዕከል በ1993 ዓ.ም ያዘጋጀው መዝገበ ቃላት መደመር የሚለው ቃል «ድምር» ከሚለው ዓምድ ቃል ወይንም «ደመረ» ከሚለው ግስ የሚገኝ እንደሆነ ይገልጻል። በዚሁ መሠረት ደመረ ማለት «አከበ፣ አከማቸ፣ ሰበሰበ፣ አንድ ላይ አጠቃለለ» የሚል ትርጓሜ ይሰጠዋል። በተመሳሳይ የአለቃ ደስታ ተክለወልድ መዝገበ ቃላትም «ሰበሰበ፣አከበ፣ አከማቸ፣አንድ ላይ አደረገ፣ ባንድነት አቆመ፣ጠመጠመ» ብሎ ይተረጉመዋል።»
ደራሲው ለጥቀውም «..ክሡትነትን እየፈጠርን ህልውናችንን ለማስጠበቅ ሐሳባችንን፣ ገንዘባችንን፣ ዕውቀታችንን፣ ተግባራችንን፣ ኑሯችንን ወዘተ… በጠቅላላው መሰብሰብ፣ ማከማቸት እና ማካበት ያስፈልገናል። በፈቃደኝነት በዚህ ሒደት ውስጥ ራስን ማሰለፍና ክሡትነትን ማረጋገጥ ነው «መደመር» የምንለው።….መደመር ስንል ዝም ብለን ከተውነው ለህልውና አደጋ የሚዳርገንን፣ ቀስ በቀስ እየሰበሰብን እንድንጠፋ የሚደርገንን የብቸኝነት ጉድለት ለመሙላት በዚህም ክሡትነታችንን እያረጋገጥን ህልውናችንን ለማስቀጠል እንችል ዘንድ አቅም የምናገኝበት የፖለቲካና የኢኮኖሚ ወረት ማፍሪያ መንገድ ነው…» ይሉናል።
መደመር ፍልስፍና ወይንስ ሌላ?
ደራሲው መደመር ኢትዮጵያዊ ፍልስፍና ስለመሆኑ ይጠቁሙናል። «…ከኢትዮጵያዊን መሠረታዊ ሥሪት የሚነሣ፣ ችግሮቻችንንም ሊፈታ የሚችል፣ እኛው እያቃናነውና እያሟላነው የምንሄደው፣ ከዓለም አቀፍ ነባራዊ ሁኔታ ጋር የተገናዘበ፣ ሁላችንንም ሊያግባባና ሊያስተሳስር የሚችል አንዳች ሉአላዊና ኢትዮጵያዊ ፍልስፍና ያስፈልገናል። በዓለም ላይ የሚቀነቀኑ ፍልስፍናዎች በመዳሰስ ቁምነገራቸውን ብቻ እንዳስ ፈላጊነቱ እየወሰድን ራሳችንን የምንፈትለው ችግር ፈቺ ዕሳቤ ያስፈልገናል።…»
መደመር በልኬት የሚታይ ፍልስፍና ነው። ለዚህ ፍልስፍና ያለን ቅርበት በመደመር ሜትር የሚለካና ከፍልስፍናው ሁለንተና ጋር ባለን ቅርበት መጠን የሚገለጽ ነው። ለመደመር ያለን ቅርበትም የመደመር ሳንካዎች በምናልፍበት መጠን ላይ የሚወሰድ ይሆናል።…»
የመደመር ተነሣሽነት
«..ተነሣሽነት ማለት ማንኛውም ግለሰብ ወይንም ንዑስ ሥርዓት ከካባው ጋር በሚያደርገው ግንኙነት ውስጥ የግንኙነቱ ለኳሽ መሆን ማለት ነው። በርን ዘግቶ በለውጥ ዕጦት በብቸኝነት ጉድለት ውስጥ ከመበስበስ ይልቅ፣ የጎረቤትን በር ማንኳኳት ማለት ነው። ተነሣሽነት ከእልህ፣ ከኩርፊያ፣ ከጠባቂነት እና ከፍዝ ባህርይ ወጥቶ ለመጀመሪያ ግንኙነት እጅን መዘርጋት ማለት ነው።»
«…መደመር የልሂቃንና እነሱ የሚመሩትን ሕዝብ ፍላጎትና ተነሣሽነት የሚፈልግ ሒደት ነው። ቃሉም ሌሎችን መሳብ ሳይሆን የራስ መሄድን ታሳቢ የሚያደርግ ነው። አባቶች ሲያስታርቁ «እስኪ ባንተ ይቅር» እንደሚሉት ሁሉ «በእኔ ይቅር» ብሎ ለግንኙነት መነሣሣትን የሚያመለክት ነው። ስለዚህም በመደመር ውስጥ ነገሮችን በሌላው ወገን ማላከክ ትርጉም የለውም። «አልመጣ ብሎኝ ነው» ከሚል ክስ ተላቅቀን የራሳችንን መሄድ ያስፈልጋል። በዚህ ተነሣሽነት ውስጥ ነው መደመር ዕውን የሚሆነው።..»
የመደመር ምሰሶዎች
«የመደመር ዕሴቶች በአጠቃላይ በኢትዮጵያ ላይ እንዲገነቡ የምፈልጋቸውን ዕሴቶች ታሳቢ ያደረጉ ጥልቅ ዕሴቶች ናቸው። እነዚህ ዕሴቶች የመደመር ምሰሶዎች ናቸው። ዕሴት ማለት ከነገሮች የምንሰጠው አንጻራዊ ዋጋና ሁኔታዎችን የምንመዝንበት መስፈርት ማለት ሲሆን፤ ይህም መስፈርት ጥልቅ ወይንም ዝርዝር ሊሆን ይችላል። የመደመር ዕሴቶች ከብቸኝነት ጉድለት ለመውጣትና ክሡትነትን እያረጋገጡ ለመሄድ እንችል ዘንድ ቅድሚያ የምንሰጣቸው ጥቅል ጉዳዮች ናቸው።
ከመደመር ዕሴቶች መካከል ሀገራዊ አንድነት፣ የዜጎች ክብር እና ብልጽግና ዋና ዋናዎቹ ስለመሆናቸው ደራሲው ዘርዝረዋል።
ስለ ልሂቃንን ሚና በጨረፍታ
“..ለገዥዎች የጭቆና መንገድ አንዱ ምክንያት የኢትዮጵያ ልሂቃን ሥሪት ነው። የኢትዮጽያ ልሂቃን በተለያዩ ታሪካዊና መዋቅራዊ ምክንያቶች ለማሰላሰል የራቁ ናቸው ብሎ ለማሰብ የሚያስደፍሩ አጋጣሚዎች አሉ። ብዙዎች ያነበቡትን እንደምግብ ዝግጅት በቀጥታ ለመተግበር ያልማሉ እንጂ ነባራዊ ሁኔታውን አገናዝበው ለመጓዝ የሚያደርጉት ጥረት ደካማ ነው።
ጉዳዩ ከትምህርት፣ ከባህል ዳራ የሚመነጭ መዋቅራዊ ገጽ ቢኖረውም የልሂቃኑ ንዝህላልነትና ስንፍና ከተጠያቂነት የሚያድናቸው አይደለም። ገዥዎች ከዚሁ የልሂቃን ባህል የሚመነጩ በመሆናቸው ድርጊቶቻቸው ከልሂቃኑ ብዙ የራቀ አይደለም።…”
ዘረኝነትንና ጎጠኝነትን ስለማስወገድ፣
“…ክብር የጋራ ጥቅምና ስጋትን የማስጠበቅ መርህ ነው። ሰዎች ሁልጊዜም ወደግብ መቅረቢያ መንገድ ሳይሆን ራሳቸው ግቦች እንደሆኑ የማመን እሴት ነው። የሰዎች ክብር በሁሉም ሰብዓዊ ፍጡር፣ በቡድን እና በግለሰብ ደረጃ ሊታይ ይችላል። ሌሎች ማናቸውንም እሴቶች የሰዎችን ክብር የሚያረጋግጡ መሆን አለባቸው። በሥራዎቻችን ሁሉ ዜጎችን አክብሮ ማገልገል፣ በማናቸውም ጉዳይ ላይ በክብር ማማከርና መያዝ ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባ ጉዳይ ነው። መደመር ከዚህ አንፃር ዘረኝነትንና ጎጠኝነትን በማስወገድ “ሰው” ሰው በመሆኑ ብቻ ክብሩና ነፃነቱ እንዲከበር ዘብ መቆም ማለት ነው። መደመር በዚህ ጊዜ ግለሰባዊ ነፃነትና ማኀበረሰባዊ ደኀንነት ማቀንቀን ይሆናል።..”
የመደመር ቀይ መስመሮች
እና ዋልታ ረገጥነት
ዶ/ር ዐብይ በመጽሐፋቸው የግብር ሳንካዎቹ የመደመር ፍልስፍና ቀይ መስመሮች ናቸው ይላሉ። “ምንም እንኳን መደመር በአጠቃላይ የልኬት ፍልስፍና የሚታይ ቢሆንም የግብር ሳንካዎቹን ማለፍ የታችኛው ወለል መሥፈርት ነው። ይኸም ማለት የጉዞውን ኃይል የሚገቱና የሚገዘግዙ ድርጊቶች፣ የተጓዦችን ልብ የሚያዝሉና ስግብግብነትን የሚያፋፉ ተግባሮችን፣ ለግለሰቦችና ለጥቂቶች ጥቅም ሲባል የብዙኃኑን የሀገርን ህልውና የሚገዳደሩ ልማዶችና ጥፋቶችን በፍጥነት በማያዳግም ሁኔታ ማስወገድን ታሳቢ ያደርጋል። በተለይ በላሸቀ ሞራል የሚደረጉ ዝርፊያዎችንና የተደራጁ ሌብነቶችን የሚታገስበት ጎን የለውም።”
“እንዲሁም በስንፍናና በዳተኝነት ያለብቃት ከሚደረጉ ድፍረቶች የሚከሰቱትን ውጤት አልባና ዝርክርክ አሠራሮችና ብክነቶች አይቶ እንዳላየ የሚያሳልፍበትና የይለፍ ፍቃድ የሚከለክልበት ግልጽ የሆነ ቀይ መሥመር ያሰምራል። መደመር ሁለት ነገሮች ውስጥ የተዘፈቀ ሰው ለመደመር ራሱን ከእነዚህ ነገሮች የግድ ማጽዳት ይኖርበታል፤ ከኀሊና ቢስነት እና ልግመኝነት።”
“ዋልታ ረገጥነት በመደመር ውስጥ መሰብሰብን የሚያሰናክልና የሚገታ አስተሳሰብ ነው። በሀገራችን በተለያየ አቅጣጫ በብቸኝነት ጉድለት ውስጥ የሚበሰብሱ ሐሳቦችንና ጉልበቶችን ሰብስቦ ወደወረትነት ለመቀየር ይቻል ዘንድ ዋልታ ረገጥነትን ማስወገድ ያስፈልጋል።
ዋልታ ረገጥነት የሚያጠፋው አንዱ መፍትሔ መሠረታዊ የአስተሳሰብ ሽግግር ማድረግ ነው። የአስተሳሰብ ሽግግር ጎራ የለሽ የልኬት ዕይታን የሚያዳብር ነው። ይኽም ማለት ነገሮችን ለመረዳት የፈጠርናቸው የተቃርኖ ምድቦች አስተሳሰባችንን እንዳይቀፈድዱት ማድረግ ነው።…”
እንደመውጫ
ጠ/ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ በሥልጣን ላይ በቆዩባቸው 19 ወራት የመደመር ፍልስፍናን አስመልክቶ በየአጋጣሚው፣ በየመድረኩ ገራሚ ሀሳቦችን አጋርተ ዋል። ጥቂቶቹን እንጠቀሳቸው።
“• ክፉን የማይጋራ የለም ባይባልም፤ ክፉን የማይጋራው ከበዛ ግን ክፋት መክኖ ይቀራል። አደገኛው ነገር አንድ ክፉ ሃሳብ ከአንድ ቀና ልቦና ከሌለው ሰው ሲፈልቅና ብዙዎች ሲጋሩት ለጥፋት ይውላል። የሚጋራው ያጣ እንደሆነ ግን እዚያው ግለሰብ ልብ ውስጥ መክኖ ይቀራልና ክፉ ክፉውን የማንጋራ፣ መልካም መልካሙን የምንደምርና የምንደመር እንድንሆን ያስፈልጋል።
• የመደመር ምሥጢር በፍቅር ለይቅርታ ብቻ ይሁን። ለክፋት፣ ለመግደል አንደመርም። የእኛ መደመር ለሌሎች ተስፋ እንጂ ጭንቀት አይሆንም።
• ብዙዎች የመደመር ፍልስፍናን ከመሠረታዊ የሂሳብ መሪ ቀመር ጋር ያገናኙታል። ይሁንና የእኛ የመደመር መሪ ሃሳብ ከስሌታዊ ንድፈ ሃሳብ በመጠኑ ከፍ አድርገን ልንመለከተው ይገባል። ምክንያቱም በማቲማቲክስ ፕሪንስፕል ቦዲ ማስ ይባላል። መጀመሪያ ቅንፉን ማፍረስ፣ እኛ ግንቡን ማፍረስ ነው። የእኛ የመደመር ዕሳቤ ከሂሳቡ ስሌት መሠረት የላቀ ነው። በዚህም የእኛ የመጀመሪያ ቅንፍ ሰበራው የጥላቻ ግንብን ማፍረስ ነው።
• መደመር ከተራው የሂሳብ ስሌት የሚልቅበት ዋናው ሃሳብ እኔና አንተ፣ እኔና አንቺ ስንደመር እንደ ሂሳብ ስሌቱ ሁለት አንሆንም። እኛ ነው የምንሆነው።
• የእኛ የመደመር መሪ ሃሳብ የሚቀንሰው በደል፣ ቂም፣ ክፋት፣ ጥላቻ፣ ስንፍና፣ ቀማኛነት፣አገር አለመውደድ፣ ሕዝብን አለማገልገል ይቀነሳሉ። የመቀነሻው መሣሪያ ደግሞ የማስሊያው መሣሪያ ደግሞ ይቅርታ፣ ምህረት፣ ደግነት፣ ፍቅር ይባላሉ።
• የእኛ የመደመር መሪ ሃሳብ ማካፈልም አለው። የምናካፍለው ፍቅር፣ በጎ ቃል፣ ጥበብ፣ ነዋይ ይሆናል።
• መልካሙን ስናካፍል፣ መልካሙን ስናብቃቃ መከፋፈል ሳይሆን መደመር ይሆንልናል። ክፉ ተግባር ቀንሰን ተባዝተን በጎ በጎውን አካፍለን በአፍሪካ ቀንድ ስንደመር መደመር ለእኔ ሳይሆን፤ ለእኛ ነውና ሁሌም እኛ ከእኔ ይልቃል።
• የምንደመረው ነገን በጋራ ለማነጽ፣ እንግዶቻችንን በፍቅር ለመቀበልና ለማስተናገድ፣ ደካማውን ለማገዝ፣ ያለንን ለማካፈል፣ ተግተን ለመስራት፣ የበደሉንን ይቅር ለማለት፣ በፍቅር ሁሉን ለማሸነፍ፣ የወደፊት ዕጣ ፈንታችን ከመበላላት መረዳዳት፤ ከመገፋፋት መተቃቀፍ እንዲሆንልን ነው።
• በመደመር ዛሬን ብቻ ሳይሆን ነገን እንሰራለን። ሳንደመር ስንቀር ኪሳራው ብዙ ነው።
• መልካችን፣ ፍቅራችን፣ ደግነታችን፣ ጀግንነታችንም አንድ ዓይነት ነው። ነገር ግን የእኛ መደመር ለሌሎች አፍሪካ ወንድሞቻችን ስጋት ሳይሆን ተስፋ፤ ጦርነት ሳይሆን ልማት፤ የሚቀንስ ሳይሆን የሚጨምር ነው።
• ጤንነታችን እንዳያመልጠን፣ ዴሞክራሲያችን እንዳያመልጠን፣ ሰላማችን እንዳይወሰድብን ሁላችንም በአንድ ልብ ተደምረን ዘብ ልንቆም ይገባል። ምክንያቱም አንድ ሰው ቤተሰብ አይሆንም፤ አንድ ቤተሰብ ብቻውን ከተማ ሊሆን አይቻለውም። አንድ ቡድንም እንዲሁም ሙሉ አገር ፈጽሞ ሊሆን አይቻለውም። አንድ አገርም ያለ ሌላ አገር ብቻውን አገር ተብሎ ሊጠራ አይቻለውም። ሌላ ድንበር የለምና።”
የዚህ መጽሐፍ ታትሞ መውጣት በተለይ ጠ/ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ በሥልጣን ላይ በቆዩበት ያለፉት 19 ወራት የመደመር ዕሳቤያቸውን አስመልክቶ የሰጧቸው መሰል ንግግሮችና ማብራሪያዎች በመነ ሳት “ይኽ ስለመደመር ፍልስፍና ለማስረዳት በቂ አይደለም” በሚል ሲሞግቱ ለነበሩ ወገኖች ጥሩ የምሥራች እንደሚሆን አልጠራጠርም። “ፈረስ ያደርሳል እንጂ አይዋጋም” እንዲሉ ጠ/ሚኒስትሩ በቀና ልቦና እነሆ መንገዱ ብለውናል፤ በመንገዱ መጠቀም የእኛ ኃላፊነት ነው። መንገዱን የመጠበቅ፣ ለሁሉ እንዲዳረስ የማስረዘም፣ የማስፋፋት ጉዳይ በእኛ ብርታትና ጥንካሬ የሚወሰን ይሆናል።
በመጨረሻም ሳልናገር ማለፍ የማልፈልገው ሚጢጢዬ፤ ግን ደግሞ ወሳኝ ነጥብ ቢኖር የመጽሐፉ የቋንቋ አጠቃቀም ምጥቀት፣ ከቃላት ግድፈት መጽዳት ለሌሎች ደራሲያን አርአያ ሊሆን የሚችል በመሆኑ የመጽሐፉን አርታኢ በአክብሮት እጅ እነሳለሁ።
አዲስ ዘመን ጥቅምት 19/2012