በርካታ የዱር እንስሳት በትልቅ ጫካ ውስጥ አብረው ይኖሩ ነበር።ቆይቶ ጫካውን በሚያስተዳድሩት እንስሳት ደስተኛ ያልነበሩ ጥቂት ጎረምሳ እንስሳት አምጸው በተለያዩ ጋራዎች ላይ በሚገኙ ዋሻዎች መሸጉ።ከዚያም መሰሎቻቸውን እያሳመኑ ከጎናቸው በማሰለፍ ለዓመታት ከታገሉ በኋላ ድል ቀንቷቸው ጫካውን የማስተዳደር ዕድል ገጠማቸው።ጫካውን ለማስተዳደርም በትግሉ ወቅት ከፍ ያለ ሚና የነበራቸው አጋዘኖች፣ ዋልያዎች፣ ድኩላዎችና ኒያላዎች በጫካው ውስጥ የሚኖሩ ሌሎች ወዳጅ እንስሳትን አጋር አድርገው ጥምረት ፈጠሩ።
ጥምረቱ የተፈጠረበት መንገድ እንዲህ ነው። በቅድሚያ አጋዘኖች፣ ዋልያዎች፣ ድኩላዎችና ኒያላዎች በየበረታቸው መሪዎቻቸውን እንዲመ ርጡ ተደርገ።በመቀጠል ከየበረቱ የተመረጡት መሪዎች አንድ ላይ ሆነው የጋራ ምክር ቤት አቋቋሙ።በጫካው የሚኖሩ እንስሳትም “ወዳጅ” ተብለው ጥምረቱን እንዲያደምቁ ተደርጎ ጥምረቱ ጫካውን ማስተዳደር ጀመረ።
ጥምረቱ በረትን መሰረት አድርጎ የተዋቀረ ነበርና ከዚህ ቀደም በጋራ ይኖሩ የነበሩት እንስሳት ቀስ በቀስ በየበረታቸው ተወሰኑ።እንደ ቀድሞ ከራስ በረት ውጭ እንደ ልብ መፈንጨት ቀረ።እያንዳንዱ እንስሳም ለበረቱ ብቻ ተቆርቋሪ የመሆን አዝማሚያ ታየበት።እንዲያውም በጊዜ ሂደት ቀደም ሲል በሌሎች እንስሳት በረት ውስጥ ይኖሩ የነበሩ ሁሉ እየተባረሩ መሰሎቻቸው ወዳሉበት በረት እንዲሄዱ ተደረገ።ይህም በጋራ መኖርን የለመደውን ሰፊውን እንስሳ አስቆጣ።
ብዙ ጉዳት ከደረሰ በኋላም ቢሆን ጥምረቱን በመሰረቱት እንስሳት የእርጅና ዘመን በየበረት ሆኖ ጫካውን ማስተዳደር ጎጂ መሆኑን የተረዱ ወጣት እንስሳት ረጅም ጊዜ የወሰደ ትግል ካደረጉ በኋላ ጫካውን ማስተዳደር ቻሉ።ወጣቶቹ ሰፊውን እንስሳ የጎዳውና ጫካውን ለምለምና ምቹ እንዳይሆን ያደረገው እያንዳንዱ እንስሳ በየበረቱ መታጠሩ መሆኑን በመግለጽ እያንዳንዱ በረት ፈርሶ ጫካው የጋራ በረት መሆን አለበት ብለው ወሰኑ።
ነገር ግን ውሳኔው ቀደም ሲል በጥምረቱ ውስጥ ብርቱ ከነበሩት አጋዘኖች ጠንካራ ተቃውሞ ገጠመው።አጋዘኖች ውህደቱን ክህደት አድርገው ቆጠሩት።እርግጥ ነው አጋዘኖች ሎሎች እንስሳትን ለትግል በማነሳሳት ጉልህ ሚና ነበራቸው ፤ ድኩላዎችንና ዋልያዎችንም አበጅተዋቸዋል።ነገር ግን አዲሱ የእንስሳቱ ትውልድ ይህን የአጋዘኖች ውለታ እንደ በደል እንጂ እንደ እዳ አይቆጥረውም፡፡
የሚያራምዱት አቋም ምንም ይሁን በአጋዘኖች በረት ውስጥ የተሻለ አንድነትና ህብረት አለ።በለውጥ ማዕበል ወስጥ ካለፉት ድኩላዎች ፣ ሚዳቆዎችና ዋሊያዎች የተሻለ ልምድ ያላቸው ስብስቦች መሆናቸው የአደባባይ ምስጢር ነው።ፍላጎታቸውን ለማስፈጸም ምን ማድረግ እንዳለባቸው ከተሞክሯቸው ያውቃሉ።ለዚህ ይመስላል አዲሶቹ የጫ ካው አስተዳዳሪዎች በበቂ ሁኔታ እስኪደራጁ ድረስ አጋዘኖችን በትዕግስት ስም መለማመጥ የመረጡት።
“ወዳጅ እንስሳት” እየተባሉ የሚጠሩት ሎሎች እንስሳት ደግሞ በርቀት ሲመለከቱት በቆዩት ማዕድ ላይ እኩል ተሳታፊ ሆኖ ለመቅረብ ቋምጠው የቅልቅሉን ፉጨት በመጠባበቅ ላይ ናቸው።እስካሁንም አጋዘኖች ፣ ድኩላዎች ፣ ኒያላዎችና ዋልያዎች ጫካውን ሲያስተዳድሩ “ወዳጅ እንስሳት” ተብለው እየተጠሩ ዳር ላይ ሆነው ተመልካች በመሆናቸው ከፍ ያለ ቁጭት ተሰምቷቸዋል።
ጫካውን የጋራ በረት ለማድረግ በሁሉም እንስሳት መካከል በተደጋጋሚ የተደረጉት ውይይቶች አመርቂ ውጤት እየተገኘባቸው ቢሆንም ከውስጥም ከውጭም ፈተና ተጋርጦበታል።በተለይ የዋልያዎች ወጠጤ አመራሮች ወደ አዲሱ በረት ጉዞ በሚደረግበት ሰዓት በየፌርማታው የተቀሩትን እንስሳት የሚያስቆጣ ሀሳብ እየሰነዘሩ ውዝግብ በማስነሳት መግባባት እንዳይኖር እያደረጉ ነው።የሚናገሩት አምጠው ይሁን አምልጧቸው አይታወቅም።
በሌላ በኩል ቀድሞም በነበረው ጥምረት ውስጥ ምንም አይነት ሚና ያልነበራቸው ተኩላዎች “ጭር ሲል አልወድም”ን እየዘፈኑ ነው።በየዕለቱ አዲስ ደንቃራ በማኖር የአዲሱን አካታች በረት ምስረታ ለማደናቀፍ ላይ ታች ማለት ይዘዋል።ተኩላዎች አራቱ እንስሳት በየበረታቸው በነበሩበት ወቅትም ምክንያት እየፈጠሩ እርስ በእርስ ግጭት ውስጥ እንዲገቡ በማድረግ ጠቡ በሚፈጥርላቸው ዕድል ምግባቸውን በቀላሉ ሲያገኙ ኖረዋል።
አሁን ግን እንስሳቱ በአንድ በረት ውስጥ ለመኖር ስለወሰኑ እንደቀድሞ እርስ በእርስ አናክሰዋቸው ቀለባቸውን ማግኘት አይችሉም።ስለዚህ የኢዲሱን በረት ምስረታ ለማስቀረት ከአኩራፊዎቹ አጋዘኖችና ከወንዝ ማዶ ካሉት ዝሆኖች ጋር ተባብረው እየሰሩ ነው።እንስሳቱ በሚኖሩበት ጫካ ትልቅ ወንዝ አለ።ከወንዙ ማዶ የሚኖሩት ዝሆኖች የእንስሳቱ መኖሪያ ሰላም እንዲሰፍንበት ስለማይፈልጉ እንስሳቱ በየበረታቸው እንዲቆዩ ይመርጣሉ።ምክንያቱም ምንጊዜም ቢሆን የማያባራ ግጭት ውስጥ እንዲቆዩ አጥብቀው ይሻሉ።ስለዚህ ተኩላዎችንና አጋዘኖችን በተለያየ መንገድ ይደግፋሉ።
እንስሳቱ ሰላም ከሆኑ ከወንዙ ስለሚጠጡ የመጠጥ ውሃ እጥረት ይገጥመናል ብለው ይሰጋሉ።ስለዚህ በአንድ በኩል እርስ በርስ እንዲጋጩ አበክረው ይሰራሉ።በሌላ በኩል እንስሳቱ ከወንዙ ከመጠጣት ይልቅ በየአካባቢያቸው ካሉ ምንጮች እንዲጠጡ ፤ ከወንዙ ለመጠጣት ከመረጡም ዝሆኖች ከፍተኛ የውሃ መጠን ስለሚያስፈልጋቸው በጥቂቱ እንዲያደርጉት በወዳጅነት መንፈስ ይደራደራሉ።
ተኩላዎች ከዝሆኖችና አጋዘኖች በሚደረ ግላቸው ድጋፍ እየታገዙ እንስሳቱ በጋራ በረት መሰባሰባቸው አደጋ እንደሚደቅንባቸው እየገለጹ በፍርሃት ሊያጠምቋቸው ይጥራሉ።አዲሱ በረት የጋራ የሚል ስም ተሰጠው እንጂ በጉልበተኞች የሚዘወርና የአንድ ወገን የበላይነት የሚሰፍንበት እንደሆነ ደጋግመው በመናገር እንስሳቱ ወደዚያ እንዳያመሩ ሰፊ ቅስቀሳ በማድረግ ላይ ናቸው።አሁን አሁን ደግሞ የአዲሱ በረት ምስረታ አይቀሬ መሆኑን እየተገነዘቡ በመምጣታቸው የተኩላዎች ጭንቀት ከመቼውም ጊዜ በላይ ጨምሮ ጡዘት ላይ ደርሷል።
ጫካውን የጋራ በረት ለማድረግ ከተደረጉ ውይይቶች በአንዱ፤ አንድ አንጋፋ ሚዳቋ ተነስቶ “በጋራ በረት ውስጥ የምንኖር ከሆነ አንደኛችን ሌላኛችንን እንቀበላለን።እናም በየበረታችን ሆነን የምንሰብከውን መለያየት ወደጎን ብለን ተፈጥሯችንንና በተናጠል ያዳበርነውን ማህበራዊ ባህላችንን መለያያ ከማድረግ ይልቅ እንደውበት ቆጥረነው በጋራ አብረን እንድንቆም ያደርገናል።
በጋራ በረት ውስጥ መኖራችን ስለ እያንዳንዳችን የሚነገሩ አሉታዊ አስተሳሰቦችን አርመን አንድነታችንን ይበልጥ እንድናጠናክር ይረዳናል።ለምሳሌ ስለኛ ስለሚዳቆዎች ብዙ ያልተገቡ ታሪኮች ይነገራሉ።“የቀን ጠማማን ሚዳቋ አትዘለውም” ይባላል።እኛ ሚዳቋዎች እዚህ የደረስነው ልክ እንደ እህት እንስሳቶች ሁሉ ብዙ ጠማማ ቀናትን በትጋት ተሻግረን ነው።
ተበድረን እንደማንከፍል ተደርጎም የሚነገር ታሪክ አለ።ብታውቁትም ታሪኩን ልንገራችሁ ።አንዲት ሚዳቋ ከመሬት ገንዘብ ተበድራ አልከፍልም ትላለች።ከዚያም ከእለታት አንድ ቀን መሬት አፍ አውጥታ ብድሬን መልሽ ትላታለች።ሚዳቋዋም ደንግጣ ከነበረችበት ቦታ ፈትለክ ብላ ወደ ተራራ ጫፍ ላይ ከወጣች በኋላ እፎይ ያበዳሪዬን ድምጽ ከዚህ በኋላ አልሰማም አለች።መሬትም በይ ብሬን ክፈይኝ ብላ ዳግም ጠየቀቻት።እንዴ ይህች መሬት የሌለችበት የት አገር ልሂድ ብላ ሚዳቋ ወደ ማይታወቅ ቦታ አፈተለከች።ከዚያ በቃ አሁንስ አታገኘኝም ስትል መሬት ጮክ ብላ እየጠበኩሽ እኮ ነው ገንዘቤን መልሺልኝ ብላ አንባረቀችባት።ሚዳቋም መሬት የሌለችበት አገር ለመድረስ ስትሮጥ ስትሮጥ ሳንባዋ ፈንድቶ ሞተች።ይህ ስማችንን ለማጠልሸት የተፈበረከ ታሪክ ነው።በዚህ የሀሰት ትርክት ምክንያት ለዘመናት እኛ ሚዳቋዎች ሌሎች እንስሳት የለፉበትን ሀብት የምንዘርፍ ቀማኞች ተደርገን ተስለናል” አለ።
ለጫካው የሚጨነቁ ገለልተኛ እንስሳት የሚሰጡት አስተያየት እንደሚያመለክተው አዲሱ በረት ዘለቄታ ያለው ሰላም የሚያስገኝና ወደ እድገትና ብልጽግና የሚወስድ መንገድ ነው።እንስሳቱ ያልተበከለ አየር ፣ ለምለም የግጦሽ ሳርና ንጹሕ የምንጭ ውሃ ለማግኘት ወደ ሌላ አገር የሚያደርጉትን ስደት ያስቀራል፡፡
ተኩላዎች ህልውናቸው የሚረጋገጠው እንስሳቱ በየበረታቸው ሲቆዩ ብቻ ስለሆነ ጫካው አንድ በረት እንዳይሆን ታላቅ ዘመቻ ላይ ናቸው።ወጣቶቹ እንስሳት ጫካውን በረት ለማድረግ በዝግታ ጉድጉድ ማለታቸውን ቀጥለዋል።ማንኛቸው እንደሚሳካላቸው ጊዜ ይነግረናል !
አዲስ ዘመን ጥቅምት 19/2012
የትናየት ፈሩ