የ137 ዓመት የእድሜ ባለጸጋዋ አዲስ አበባ መልኳን እየለወጠች ነው። አዲስ አበባ የዓለም የዲፕሎማሲ መዲና፣ የአፍሪካ ሀገራት ዋና ከተማ፣ የኢትዮጵያ ዋና ከተማ፣ የኢኮኖሚና የማኅበራዊ እንቅስቃሴ መናኸሪያ እንደ መሆኗ ይህን የሚመጥን ልማት እየተከወነላት ይገኛል።
ከፒያሳ እስከ አራት ኪሎ፣ ከአራት ኪሎ እስከ ቦሌ ድልድይ፣ ከቦሌ ድልድይ በመገናኛ ወደ ሲኤምሲ፣ ከቦሌ ተርሚናል ወደ ጎሮ፣ ከሜክሲኮ ወደ ወሎ ሠፈር፣ እንዲሁም ከእንግሊዝ ኤምባሲ ወደ አራት ኪሎ የሚወስዱ ኮሪዶሮች ባማረ መልኩ ተገንብተው ለአገልግሎት በቅተዋል።
በአምስት አቅጣጫዎች የተከናወነው የመጀመርያው ዙር የኮሪዶር ልማት ከተማዋን ከመሰረቱ የቀየረ ነው። የተሽከርካሪ መሄጃ አስፋልቱን እና የእግረኛ መንገዱን ስፋት ለተመለከተውም ዓለም አቀፍ ደረጃን ባሟላ መልኩ የተገነባ መሆኑን በቀላሉ መረዳት ይቻላል።
የኮሪዶር ልማቱ በተበሰረበት ወቅት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ‹‹አዲስ አበባ ከጥቂት ዓመታት በኋላ በአፍሪካ ካሉ ዋና ከተማዎች ከኬፕታውን በስተቀር የሚወዳደራት ከተማ እንደማይኖር በተግባር የምናሳያችሁ ጉዳይ ነው።›› ሲሉ አዲስ አበባ እንደስሟ ውብ እና አዲስ የምትሆንበት ጊዜ መቅረቡን መናገራቸው የሚታወስ ነው። አሁን እየታየ ያለውም የሚያረጋግጠው ይህንኑ ሀቅ ነው።
የአዲስ አበባ ዘመናዊነት መገለጥ ጀምሯል። ከፒያሳ እስከ አራት ኪሎ ያሉት መንገዶች እጅግ ባማረ ሁኔታ ተገንብተዋል። ዛሬ ፒያሳንና አራት ኪሎን የተመለከተ ኢትዮጵያ ውስጥ መኖሩን እስኪጠራጠር ድረስ መገረሙ አይቀሬ ነው። የአስፋልቱ ጥራት፤ የእግረኛ መንገዶቹ ስፋትና ጥራት፤ የመናፈሻዎቹ እና አረንጓዴ ሥፍራዎቹ ውበትና ድምቀት፤ የዘንባባዎቹ ማራኪነት በሙሉ እጅን አፍ ላይ ለመጫን የሚያስገድዱ ናቸው።
ለወትሮው በአቧራና በእርጅና ብዛት ተጎሳቁለው የነበሩ ሕንጻዎችና ፎቆች ዛሬ ታድሰው ሙሽራ መስለዋል። በየስርቻው ተወትፈው የነበሩ ቅራቅንቦዎች ተወግደው የፒያሳና የአራት ኪሎ ውበት ወለል ብሎ እንዲታይ ሆኗል። ብዙዎች እሪ ይሉበት የነበረው እሪ በከንቱም ዛሬ ስሙን አድሶ ሰላምና ውበት ፈሶበታል።
አፍን በሚሰነፍጥ ሽታው የሚታወቀው ከፒያሳ እስከ አራት ኪሎ ያለው መንገድም ጽዳቱ ተጠብቆለታል፤ ዘመናዊ መጸዳጃ ቤቶችም ተገንብተውለታል። በአጠቃላይ በኮሪዶር ልማቱ አማካኝነት ዓለም ከደረሰበት የዘመናዊ ከተማ መስፈርት አንጻር አዲስ አበባም መሰለፍ ጀምራለች።
በተመሳሳይም በሁለተኛው ዙር የኮሪዶር ልማት ከመጀመርያው ሰፋ ያለ አካባቢን በሚሸፍን መልኩ ተግባራዊ እየተደረገ ነው። ካዛንቺስን የመሳሰሉ አካባቢዎች ደግሞ ግንባታቸው ተጠናቆ ለምርቃት በቅተዋል። ሌሎቹም ልማታቸው እተፋጠነ ነው።
ሆኖም ከአዲስ አበባ መዘመን ጋር እኛ ነዋሪዎቿ ምን ያህል ዘምነናል ? ወይም ለመዘመን ተዘጋጅተናል? የሚለው ሊነሳ የሚገባው ጥያቄ ነው። ይህንን ጥያቄ ልናነሳ የቻልነው ደግሞ ከልማቱ ጎን ለጎን የታዘብናቸው ጉዳዮች ስላሉ ነው።
በተለይም በመጀመርያው ዙር የተገነቡ የኮሪደር ልማቶች በአጠቃቀም እና አልፎ አልፎም ሆን ተብሎ በሚመስል ሁኔታ ብልሽት እየገጠማቸው መሆኑን ለመታዘብ ችለናል። መንግሥት ከፍተኛ ወጪ አውጥቶ ለሕዝቡ ያስረከበውን ልማት ጠብቆ እና ተንከባክቦ ለትውልድ ማስተላለፍ ሲገባ በግዴለሽነት እና አውቆ አጥፊ በሆኑ ግለሰቦች ምክንያት ተበላሽቶ ሲታይ እንደ ዜጋ የሚያስቆጭ ነው። ከታዘብኳቸው ጉዳዮች ውስጥ ጥቂቱን ላንሳ።
የመጀመርያው ጉዳይ የጽዳት ጉዳይ ነው። አንዲት ከተማ ዘመናዊ የሚባለው ወይንም ደግሞ ነዋሪዎቿ ዘምነዋል የሚባሉት ለጽዳት ትኩረት ሲስጡ ነው። ጽዳት ዘመናዊነት መገለጫ ነው። ከዚህ አንጻር እየዘመነች ባለችው ከተማ በተቃራኒ ከተማዋን የሚያቆሽሹና ውበቷን የሚያጎድፉ ተግባራት አሁንም ይስተዋላሉ።
ውብ በሆኑት እነዚህ ጎዳናዎች በየቦታው የሚሽኑ ሰዎች አጋጥመውኛል። እንኳን ለመሽናት ቀርቶ ለመራመድም በሚያሳሳው ጎዳና ያለምንም ሀፍረት ቆመው የሚሸኑ ሰዎች ዛሬም አልጠፉም።
የኢትዮጵያ ዋና ከተማ፤ የተለያዩ ዓለም አቀፍና አኅጉር አቀፍ ተቋማት መቀመጫ፤ የአፍሪካ መዲናና ከኒዮርክና ጄኔቫ ቀጥላ ሶስተኛዋ የዲፕሎማቲክ ከተማ በሆነችው አዲስ አበባ በየሜዳው መጸዳዳት እንዲሁ በቀላሉ የሚታይ አይደለም።
ከተሞች ለአኅጉራዊና ዓለም አቀፋዊ መቀመጫነት ሊመረጡ የሚችሉት ጽዱና ውብ ሲሆኑ ብቻ ነው። ጽዱና ውብ ያልሆኑ ከተሞች ለማንኛውም አገልግሎት ተመራጭ አይሆኑም። ስለዚህም ከ50 ዓመታት በላይ የአፍሪካ ሕብረት መቀመጫ ሆና የቆየችው አዲስ አበባ በጽዳቷ ምክንያት መቀመጫነቷ ጥያቄ ውስጥ ሊገባ ይችላል ማለት ነው።
በአጠቃላይ ባዶ ሜዳ ላይ መጸዳዳትና አካባቢን መበከል በርካታ የሆኑ ውስብስብ ችግሮችን የሚያስከትል ነው። ባዶ ሜዳ ላይ የሚጸዳዳ ማኅበረሰብ ክብር የለውም። የሰው ልጅ ተደብቆ ወይም ተከልሎ ከሚያደርጋቸው ተግባራት መካካል አንዱና ዋነኛው መጸዳዳት ነው። ከዚህ ውጭ ሲሆን ክብርን ያጎድፋል፤ ከሰው ልጅ ተርታ አስወጥቶ ከእንስሳት ተርታ ያሰልፋል።
ቀደም ባለው ጊዜ አብዛኞቹ የፍሳሽ ማስወገጃ ቱቦዎች የተቀበሩት ከከተማዋ ምስረታ ጋር በተያያዘ በመሆኑ ከማርጀታቸውም ባሻገር አሁን ያለውን የሰው ቁጥር የማስተናገድ አቅም ለማስተናገድ የሚያስችሉ መጸዳጃ ቤቶች አልነበሩም። በዚህም ላይ በየጊዜው በሚሰሩ ግንባታዎች አማካኝነት ፍሳሽ ማስወገጃ ቱቦዎቹ ለብልሸት ስለተዳረጉ በአግባቡ ፍሳሽን የማስወገድ አቅም አልነበራቸውም ።
በዚህም ምክንያት አካባቢዎቹ በየጊዜው በሚፈነዱ መጸዳጃ ቤቶች የሚጥለቀለቁና አፍንጫ በሚሰነፍጥ ጠረናቸውም የሚታወቁ ናቸው።አግባብ ባይሆንም ሰዎች የቆሸሹትን የአዲስ አበባ ጎዳናዎች ለማቆሸሽ ብዙም ሞራል ጥያቄ የሚያነሳባቸው አልነበረም።
ዛሬ ግን ዘመናዊ መጸዳጃ ቤቶች እየተገነቡ ነው። ከፒያሳ እስከ አራት ኪሎ ባለው ኮሪዶር እንኳን በርካታ መጸዳጃ ቤቶች ተገንብተዋል። ስለዚህም በየቦታው መጸዳዳት በተለይም አሁን ባለው ሁኔታ ከአዲስ አበባ ዘመናዊት ጋር የሚሄድ አይደለም። ስለዚህም እየዘመነች ካለችው ከተማ ጋር አብሮ ለመጓዝ እራስን ማስተካከል ይገባል፤ በየቦታው መጻዳዳትም ነውር መሆኑን መረዳት ያስፈልጋል።
ከዚሁ ከጽዳት ጋር በተያያዘም ሶፍት፤ ወረቀት፤ የውሃ መያዣ ፕላስቲክ (በተለምዶ ኃይላንድ) የመሳሰሉትን በየቦታው መጣልም ከእንግዲህ ወዲያ በቃ ሊባል ይገባል። በተዋቡ የኮሪዶር ልማት መናፈሻዎች ላይ ጫት መቃም እና መተኛት የመሳሰሉ ተግባራትም አስተውያለሁ። በሳር እና በሚያማሩ አበቦች ያሸበረቁ የመንገድ አካፋዮች እየረገጡ እና እየጨፈላቁ ማለፍም አሁንም ያልተሸገርነው ችግር ነው።
የአዲስ አበባ ጎዳናዎች ክእንግዲህ ወዲያ አበቦችንና አትክልቶችን እንጂ ቆሻሻዎችን መሸከም አትችልም። ስለዚህም ቆሻሻዎችን እየተዘጋጁ ባሉ የቆሻሻ ማስቀመጫዎች ውስጥ በመጣል የከተማዋን ጽዳት መጠበቅ የሁሉም ነዋሪ ግዴታ ሊሆን ይገባል።
በሌላም በኩል የሚያድጉ አበቦችን እና አትክልቶችን መቁረጥ፤ ከሥራቸው መንቀል፤ ለመፋቂያ እያሉ መዘንጠፍ እና እየታከኩ ማለፍ የመሳሰሉ ችግሮች አሁንም ሊታረሙ የሚገቡ ጉድለቶችን ናቸው።
ሌላው እየዘመነች ያለችውን ከተማ ውበቷ እንዳይጎላና ጎዳናዎቿ እንዳያምሩ እንቅፋት እየሆነ ያለው ተሽከርካሪዎችን በዘፈቀደ ማቆም ነው። ከፒያሳ እስከ አራት ኪሎ ያለው ሰፊ ጎዳና መኪኖችን እንደልብ የሚያንሸራሽርና ለመኪናዎች መቆሚያም የራሱ የሆነ ፓርኪንግ ታስቦ የተሰራለት ነው።
ሆኖም ከቀድሞው ባሕል ያልወጡ አሽከርካሪዎች በየቦታው መኪናቸውን በመገተር የትራፊክ ፍሰቱን ሲያስተጓጉሉና እነሱም ለቅጣት ሲዳረጉ ማየት የተለመደ ሆኗል። በየትኛውም ዓለም ቢሆን ከመኪና መቆሚያ ውጭ እንደፈለጉ አቁሞ መሄድ የሚፈቀድ አይደለም። የእኛዎቹ አሽከርካሪዎች ግን ከዘመናዊነት በተፋታ መልኩ ዛሬም መኪናቸውን በሰፋፊ ጎዳናዎች ላይ ከማቆም ባሕል አልተላቀቁም፤ ከዘመናዊነት ጋር አልተዋወቁም። የኮሪደር ልማቱን መሰረተ ልማቶች ገጭቶ መሰወር እና ማፈራረስም አሁንም በአሽከርካሪዎች በኩል ከሚፈጸሙ ጥፋቶች ውስጥ የሚጠቀሱ ናቸው።
በእግረኞች በኩል የሚታዩ ክፍተቶች ደግሞ በሰፊው እና ባማረ መልኩ የተሠሩ እግረኛ መንገዶችን ትቶ በመሃል አስፋልት መጓዝ አሁንም ያልተላቀቀን አባዜ ነው።
የአዲስ አበባ ኮሪዶር ልማት ሲከናወን ለእግረኛ መንገዶች ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቷል። በርካታ ሰዎችን አዝናንቶ እንዲጓዙ የሚያደርጉ ስፋታቸው ከ10 ሜትር ያላነሱ የእግረኛ መንገዶች ተገንብተዋል። እነዚህ መንገዶችም በአአቦችና በዘንባባ ዛፎች ያጌጡ ናቸው። ሆኖም አንዳንድ እግረኞች ይህን ያማረ ቦታ ለቀው አስፋልት ውስጥ ሲጓዙና እራሳቸውንም ለአደጋ ሲያጋልጡ ተመልክተናል።
በትራፊክ አደጋ ዙርያ የተደረጉ ጥናቶች እንደሚያመላክቱት እስከ 84 በመቶ የሚደርሱ አደጋዎች የሚከሰተቱት ከእግረኞች ጋር በተያያዘ ነው። ይህ ደግሞ እግረኞች የተፈቀደላቸውን መንገድ ትተው የተሽከርካሪ መስመር ውስጥ በመግባታቸው የሚፈጠር ችግር ነው።
ዛሬ ግን ይህ ችግር ተቀርፏል፤ በቂ የእግረኛ መንገዶች ተሰርተዋል። ስለዚህም አንድ እግረኛ የተፈቀደለትን መንገድ ለቆ አስፋት ውስጥ ገብቶ እንዲሄድ የሚያደርገው አስገዳጅ ሁኔታ የለም፤ አያድርገውና አደጋ ከተከሰተም ጥፋቱ የእግረኛው ብቻ ነው የሚሆነው።
በመሰረተ ልማት ላይ የሚደርሱ ጥፋቶችም እንዲሁ አንዱ ትኩረት የሚያሻው ጉዳይ ነው። የቴሌ ገመዶችን፤ የኤሌትሪክ ሽቦዎችን፤ እና ለተለያዩ አገልግሎቶች የተዘረጉ መስመሮችን የሚቆርጡ ልማት ጠል ሰዎችም እንዳሉ ታዝቤያለሁ። ከፍተኛ ወጪ የወጣባቸው የስልክ፤ የኤሌትሪክ፤ የኢንተርኔት እና መሰል ዝርጋታዎች ተገቢውን አገልግሎት ሳይሰጡ በጥፋት እጆች ተቆርጠው ሲጣሉ አይተናል።
ይህ ደግሞ የሀገሩን እድገት ከሚወድ እና ዘመናዊነትን ከሚናፍቅ ዜጋ የሚጠበቅ አይደለም። ለሀገር ተቆርቋሪ ዜጎች መሰረተ ልማቶችን መንከባከብ እና በመሰረተ ልማቶች ላይ ጉዳት የሚያደርሱ ሰዎችንም አሳልፈው ለሕግ አካላት ሊሰጡ ይገባል።
ይህ ሲሆን ነው አዲስ አበባ እንደ ስሟ አዲስ እና ዘመናዊ መሆን የምትችለው። ያለበለዚያ በሌሎች ሀገራት ዘመናዊ ከተሞች ከመቅናት እና አርቆ ከመናፈቅ በዘለለ የምንመኛትን ውብ ከተማ ማየት አንችልም።
በአጠቃላይ እየዘመነችው ካለችው ከተማ ጋር አብሮ ለመጓዝ ዘመናዊ አስተሳሰብና ተግባራት ያስፈልጋሉ። በተለይም ከጽዳት፤ ከፓርኪንግ እና ከእግረኛ መንገድ አጠቃቀም ጋር ያሉ ኋላ ቀር አስተሳሰቦችንና ተግባራትን ማስወገድና ከዘመኑ ጋር አብሮ መጓዝ የግድ ይላል።
እስማኤል አረቦ
አዲስ ዘመን ሐሙስ ሚያዝያ 30 ቀን 2017 ዓ.ም