የዴሞክራሲዊና ሰብዓዊ መብቶች መጓደልና የፍትህ እጦት የአገራችንን ህዝቦችን አስቆጥቶ ያለፉት ሁለት ሶስት ዓመታት ህዝባዊ እምቢተኝነትና አመጽ አገሪቱን ክፉኛ ሲንጧት እንደነበር የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነው። ኢህአዴግ አገሪቱን በመራባቸው 27 ዓመታት በኢኮኖሚው መስክ አስገራሚ ስኬትን ቢያስመዘግብም በሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች አከባበር ግን ሁሌም ስሙ በክፉ ሲነሳ እንደነበርም የማይታበል ሀቅ ነው።
እርግጥ ነው ሀገራችን በሃሳብ ደረጃም እንኳ ቢሆን ሥልጣን የሚገኘው ከምርጫ ኮሮጆ ነው የሚለውን አስተሳሰብ ይዛ ተግባራዊ እንቅስቃሴ የጀመረችው ከፊውዳላዊው ሥርዓት ጀምሮ ነው። በደርግ ዘመነ መንግስትም የይስሙላ ምርጫ ተካሂዶ የሸንጎ አባላት መመረጣቸውም አይዘነጋም። ይሁንና በሁለቱም ሥርዓተ መንግስቶች የተደረገው ምርጫ ባልተስተካከለ ሜዳና ፈረስ የተከናወነ ከመሆኑም በላይ የህዝቡን በነጻነት የመወሰን መብት ያላረጋገጡ በመሆናቸው ውሎ አድሮ በህዝባዊ አመጽና በትጥቅ ትግል የሙጥኝ ያሉትን ስልጣን እንዲለቁ ተገደዋል።
በዘመነ ኢህአዴግ ከሽግግር መንግስቱ ማብቂያ አንስቶ በ1994፣ በ1997፣ በ2002 እና 2007 ሀገር አቀፍ ምርጫዎች ቢካሄዱም አካሄዱ ግን እንዳያማህ ጥራው እንዳይበላ ግፋው ዓይነት እንደነበር ህዝብና ተፎካካሪ ፓርቲዎች ደጋግመው ሲገልጹ ተስተውሏል። በተለይም ምርጫው በተስተካከለ ሜዳ ላይ እንዲከናወን የማድረግ የፊታውራሪነት ሚና የተጣለበት የብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ከመንግስት ገለልተኛ አለመሆን፣ ተፎካካሪ ፓርቲዎች በነጻነት ተንቀሳቅሰው ፕሮግራምና ዓላማቸውን ለህዝብ እንዳያደርሱ ከገዢው ፓርቲ አባላት የሚደረጉ ጫናዎች ተአማኒና ሁሉን የሚያስማማ ምርጫ እንዳይከናወን እንቅፋት እንደሆኑባቸው ብዙዎች ሲያማርሩ ታይቷል።
በ1997 ዓ.ም በተደረገው አገር አቀፍ ምርጫ ከድምጽ መስጫ ቀናቶቹ በፊት በነበረው ብርቱ ፉክክር ኢትዮጵያ በዓለም የዴሞክራሲ መድረክ ልዕልናን ልትጎናጽፍ ተቃርባለች የሚል ተስፋን ቢያጭርም በድምጽ መስጫው ቀን በተስተዋሉ ህጸጾች ምክንያት ግን ውጤቱ ከዚሁ በተቃራኒ ለሰላም መደፍረስ፣ ለብጥብጥ፣ ለእስርና ሞት ምክንያት ሆኗል። የሀገራችን ገጽታ በትልቁ የተጎዳበት ሁኔታም ተፈጥሯል። ይህ ምርጫ ቁርሾና ቂም እንዲሰፋ፣ በርካቶች እንዲሰደዱ የመንግስት ተዓማኒነት በከፍተኛ ሁኔታ እንዲመናመንና የሸቀጦች ዋጋ ከሚገባው በላይ እንዲንር በአጠቃላይ ህዝብ በዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታና በዴሞክራሲዊ ምርጫ ተስፋ እንዲቆርጥ አድርጎ አልፏል ማለት ይቻላል።
ከዚህ ሁኔታ ጋር ተያይዞ የ2002 ምርጫን ዴሞክራሲያዊና ፍትሃዊ ለማድረግ በሚል መንግስትና ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች በምርጫ ህግና በምርጫ ቦርድ አደረጃጀት ላይ ውይይት ቢያደርጉም ሂደቱ አሳማኝ አይደለም እንዲሁም መንግስት ከልቡ አምኖ እያደረገው ያለ ነገር አይደለም በሚል ምክንያት የተወሰኑት ከሂደቱ አቋርጠው ሲወጡ እስከ መጨረሻው ተጉዘው የስምምነት ፊርማቸውንም ያኖሩትም ቢሆኑ ፍጻሜው ውጤት አልባና ጉንጭ ማልፋት ብቻ እንደነበር የገለጹበት ሁኔታ ታይቷል።
በዚህ ሁኔታ የተከሰተው የፖለቲካ ምህዳር መጥበብና የዴሞክራሲያዊና ሰብአዊ መብቶች መታፈን ህዝብ በገዢው ፓርቲ ኢህአዴግ ላይ የመረረ ትግል እንዲያካሂድበትና ከሥልጣን ባይወርድም ከድርጅቱ የጠነከረ አቋም አንጻር ይሆናል ተብሎ የማይታሰብ ሁለንተናዊ ለውጥ እንዲያደርግ አስገድዶታል። ከዚህ ለውጥ ማግስትም የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዓብይ አህመድ አገሪቱ ያላት ብቸኛ ምርጫ አንድም የአውነት ዴሞክራሲ ማስፈን አልያም በአምባገነናዊነት ጎዳና አቅንቶ መበታተን መሆኑን ገልጸዋል። ይሁንና መንግስታቸው የመረጠው መንገድ ፍጹም ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን ማስፈን መሆኑንና ለዚሀም በሀገር ውስጥ ሆነ በተለያዩ የዓለም ሀገራት የሚገኙ ተፎካካሪ ፓርቲዎችና አክቲቪስቶች ያለፈውን በመርሳት ለቀጣዩ ስራ በጋራ እንረባረብ ሲሉም መልዕክት አስተላልፈው ነበር። በአሜሪካና በጀርመን በመዘዋወርም በተለያዩ ምክንያቶች አኩርፈውና ሸሽተው የነበሩ ፖለቲከኞችን ወደ አገራችሁ ግቡና በሃሳብ ተወዳድረን ያሸነፈ ይምራ የሚል ጥሪ አቅርበዋል።
በሽብርተኝት ለተፈረጁ ፓርቲዎችም ፍረጃውን በማንሳት፤ የብሎገሮችና ድረ ገጾች እንዲሁም ፕሮግራማቸውን በሀገሪቱ እንዳያሰራጩ ታግደው የነበሩ መገናኛ ብዙሃንን እገዳ በማንሳት ጥሪው ከልብ የመነጨ መሆኑን አሳይተዋል። በነጻ የምርጫ ሜዳ ላይ ተወዳድረን ህዝብ ካልፈለገንና ከተሸነፍን እንደ መንግስት ለአንዲትም ቀን እንኳን በስልጣን ላይ የመቆየት ፍላጎት የለንም ሲሉም ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተለያዩ መድረኮች ተናግረዋል።
ተፎካካሪ ፓርቲዎችን ጨምሮ በብዙዎች ዘንድ ተቀባይነት ያገኙትን ግለሰብ ለብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ በማድረግም መንግስት ለዴሞክራሲዊ ሥርዓት ግንባታ የሰጠው ትኩረት ከአንገት በላይ አለመሆኑን አስመስክሯል። የምርጫ ቦርድ ጽህፈት ቤት ተአማኒነትን በተላበሰና በገለልተኛነት የሚሰራበትን ምቹ ሁኔታ ለመፍጠርም የሚመለከታቸውን አካላት ሁሉ ባሳተፈ መልኩ ተጨባጭ እርምጃዎችን ለመውሰድ እየተንቀሳቀሰ ነው።
የሃሳብ ብዝሃነት የሚንጸባረቅባቸውን መገናኛ ብዙሃን በፍጹም ነጻነት እንዲንቀሳቀሱም ምቹ ሁኔታ ተፈጥሮ መገናኛ ብዙሃኑ እንደ አሸን እየፈሉና ሃሳቦች ያለምንም መሸማቀቅ ገበያ ላይ እየዋሉም ይገኛሉ። ህዝብ ይሄን ባነብ እንዲህ ይደረስብኝ ይሆን ከሚል ፍራቻ ተላቆ የሚፈልገውን መርጦ እያዳመጠ፣ እየተመለከተና እያነበበ ይገኛል። ማሻሻያው የእናቴ መቀነት አደናቀፈኝ ዓይነት ምክንያቶች በማይፈጠሩበት ደረጃ እንደሚከወንም ጥርጥር የለም።
በአጠቃላይ ሜዳውና ፈረሱ ለውድድሩ በመልካም ሁኔታ እየተዘጋጁ ነው። መንግስት እያከናወነ ካለው ተጨባጭ እርምጃ አንጻር ጨዋና ኃላፊነት የሚሰማቸው ህዝብና ፓርቲ ከተገኙ ዓለምን አስደማሚ ነጻ ምርጫ እንደሚካሄድም ለመተንበይ አያዳግትም። ስለሆነም እንደ ህዝብም ሆነ እንደ ፓርቲ በህዝብ ዘንድ ተቀባይነትን ያተረፉ አጀንዳዎችን በመያዝ የህግ የበላይነትን በማክበርና ከሴራ በመራቅ ታሪክን ለመጻፍ መዘጋጀት ጊዜ የማይሰጠው ተግባር ሊሆን ይገባል እንላለን!
አዲስ ዘመን ታህሳስ 19/2011