
ኢትዮጵያውያን የወደፊት ዕጣ ፈንታቸው ብሩህ እንደሚሆን በብዙ ተስፋ እና እምነት ተቀብለው የሚኖሩ ሕዝቦች ናቸው። ይህ እውነት በተለይም በክርስትና ሃይማኖት ተከታዮች በኩል አብዝቶ የሚነገር እና ተስፋ የሚደረግ ነው። ለዚህም የክርስትናን ሃይማኖት ቀድመን መቀበላችን፤ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ደጋግሞ ስማችን መጠቀሱን እንደ ምክንያት የሚያነሱ አሉ።
ይህ ከእምነት የሚመነጭ ነገን ብሩህ አድርጎ የመቀበል መነሳሳት እንደ ማኅበረሰብ ብዙ የሕይወት መጎረባበጦችን፣ ፈተናዎችን እና ተግዳሮቶችን በጽናት ለመሻገር አቅም የሚፈጥር ነው። ዛሬን አሸንፎ ለመውጣት በሚደረግ የማኅበረሰብ ትግል ውስጥ የሚኖረው አበርክቶም በቀላሉ የሚታይ አይደለም። ትውልድን ተስፈኛ በማድረግ፣ የተስፋ ቢስነትን ጫና ለመቋቋም ያለውም አስተዋፅዖ ብዙ ነው።
በርግጥ ከመንፈሳዊ አስተምህሮዎች እና ስብዕና የሚመነጩ ተስፈኝነቶች በራሳቸው የሚቆሙ ሳይሆኑ ለሃይማኖታዊ መርሆዎች የሚገዙ እና ተጨባጭ የሕይወት ልምምድን የሚፈልጉ ናቸው። ከተስፈኝነት ባሻገር ከፍ ባለ መንፈሳዊ ዲስፕሊን የሚመራ ማኅበረሰብ የዕለት ተዕለት የሕይወት ትጋትን የሚጠይቁ፣ ከትናንት መንገድ መመለስን የሚሹም ናቸው።
መንፈሳዊ ተስፋን ለመውረስ ባለተስፋ መሆን አንድ መስፈርት ቢሆንም ተስፋን በማሰላሰል ብቻ፤ ወይም የተስፋ ቃል ባለቤት በመሆን ብቻ የሚወረስ አይደለም። ከመንፈሳዊ እውቀት በሚቀዳ ስብዕና ላይ ቆሞ መራመድን፣ አስቦ መመላለስን፤ ከሁሉም በላይ ራስን በአግባቡ ማወቅን፤ አውቆም ከራስ ጋር እርቅ ማድረግን የሚጠይቅ ነው።
እኛም እንደሀገር በእምነት ተስፋ የምናደርገውን የወደፊት ዕጣ ፈንታችንን ተጨባጭ ለማድረግ፤ እንደ ክርስቲያን ለተቀበልነው የተስፋ ቃል፤ በእውነት እና በመንፈስ መታዘዝ፤ ይህን የሚሸከም ማኅበረሰባዊ ማንነት መገንባት ይኖርብናል። ወንድማማችነት፤ ዕርቅን እና ይቅር ባይነትን መለማመድ፤ ለዚህ የሚሆን እውነተኛ መሰጠት ያስፈልገናል።
ለጥፋት ከመቦዳደን መጥተን ለበጎ ሥራ መተባበር፤ ከበቀለኝነት ወጥተን ወደ ይቅር ባይነት፤ ከነፍሰ ገዳይነት ወጥተን ራስን ለሌላው መስዋዕት ወደማድረግ፤ ከማግበስበስ ወጥተን ወደ አካፋይነት፤ ከሌብነት እና ካለመታመን ወጥተን ወደ ታማኝነት፤ ከአሮጌ የትናንት ትርክቶች ወጥተን፤ ሕይወት ወደሚሆን አዲስ ትርክት ልንመለስ ይገባል።
በወንድም ደም የፍርድ ጩኸት ከሚፈጠረው ዕረፍት አልባ ሕይወት ወጥተን የወንድምን ተስፋ በሚያለመልም ፍቅር ውስጥ መገኘት፤ ወንድምን ከሚያጎሳቁል የከሳሽነት መንፈስ ወጥተን ወንድምን ወደሚያበረታ አለሁልህ ባይነት፤ የወንድምን ሞት እና ውድቀት ከሚፈልግ ክፉ ማንነት ወጥተን ስለወንድም ራስን ወደመስጠት የሚያሻግር የሕይወት መታመን ውስጥ መግባት ይጠበቅብናል።
ከነፍሰ ገዳይነት ፉከራ እና ቀረርቶ ወጥተን፤ የሕይወት ዜማ ወደምናዜምበት፤ ዛሬ ላይ ቆመን ነገን ከማፍረስ ወጥተን፤ ዛሬ ላይ ነገዎቻችንን ብሩህ እና የተሻሉ አድርገን መሥራት ወደሚያስችል የማንነት መለወጥ መምጣት፤ ከተስፋዎቻችን ጋር በብዙ ተቃርኖ ቆመን ዋጋ ካሰከፈሉን ትናንቶቻችን ብዙ ተምረን መመለስ አለብን።
በደረት ላይ መስቀል በትከሻ ጠብመንጃ ተሸክመን፤ የሀገር እና ሕዝብ ተስፋ ከማጎሳቆል፤ ነፃ ሳንወጣ ስለነፃነት ሰባኪ ከሆንበት ግራ መጋባት፤ በወንድማችን አስከሬን ላይ ቆመን ከመፎከር እና ከመሸለል መታበይ፤ የከፋ ጥፋት ምንጭ ከሆነው ዘረኝነት እና አክራሪነት መላቀቅ አለብን።
በተለይ ዛሬ ላይ የስቅለትን በዓል እና ከበዓሉ በስተጀርባ ያለውን ሃይማኖታዊ አስተምሕሮ ስናስብ፤ ራሳችንን እና አሁናዊ እውነተኛ ማንነታችንን ቆም ብለን ልናጤነው፤ እንደ ክርስቲያን ማኅበረሰብ ከእያንዳንዷ አስቸጋሪ የታሪክ ጉዟችን በስተጀርባ የነበሩ እና ያሉ ፈተናዎች እና የፈተናዎቹን የጉልበት ምንጭ ምን እንደሆኑ ልናስተውል ይገባል።
በየዘመኑ የነበሩ ትውልዶች ተስፋዎቻቸውን የራሳቸው እንዳያደርጉ ያስገደዷቸው ተግዳሮቶች እና ተግዳሮቶቹ አቅም የገዙባቸው የተሳሳቱ እሳቤዎችን ከየት እንዳመጣናቸው፤ የቱን ያህል እንደ ሀገር ዋጋ እንዳስከፈሉን ልናሰላስል፤ ከዚህ የጥፋት አዙሪት ለመውጣት ከራሳችን ጋር እርቅ ለመፍጠር በመወሰን ሊሆን ይገባል።
የመስቀሉ ሥራ ትናንቶችን መዋጀት፤ ተስፋ ያደረግናቸውን ነገዎች መውረስ የሚያስችል፤ የእውነት እና የሕይወት መታደስን የሚፈጥር፤ እውነተኛ ለውጥ እና መለወጥን የሚያመጣ፤ ከተበላሸ የትናንት ማንነት የሚታደግ፤ የለውጥ እና መለወጥ አልፋ እና ኦሜጋ ነው!
አዲስ ዘመን ዓርብ ሚያዝያ 10 ቀን 2017 ዓ.ም