ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ባለፈው ቅዳሜ በሚሊኒየም አዳራሽ በተዘጋጀው” መደመር “ ፅንሰ ሀሳብ መፅሐፍ ምረቃ ስነ ስርዓት ላይ “ ‘ መደመር ‘ን እንደ መነሻ ፣ መሰረት foundation ወስደን በእሱ ላይ መገንባት ፣ መጨመር ለዓለም ማስተዋወቅ ያስፈልጋል:: ስንተችም ከእነ አማራጩ ከእነ መፍትሔው ሊሆን ይገባል “ ባሉት መሰረት ፤ ከአክብሮት ጋር በፅንሰ ሀሳቡም ሆነ በመፅሐፉ ስያሜ ላይ ሰዋሰዋዊና አለም ዓቀፍ ቅርፅ ለማስያዝ ያግዛል ያልሁትን የመነሻ ሀሳብ ማቀበል ፈለግሁ ፡፡
ከሁሉም በላይ አኩሪና ሙሉኡ የሆነውን ቱባ ቱባ ሀገር በቀል ዕውቀቱንና ባህሉን ችላ ብሎ ደጅ ደጁን ሲቀላውጥ ለኖረ ምንጅላት ፣ ቅድመ አያት ሆነ የ60ዎቹም ወይም የዛሬው ትውልድ ሀገረኛ ( ሀገር በቀል ) የአመራር ፣ የአስተዳደር ፅንሰ ሀሳብና ፍልስፍና ይዞ መምጣት በራሱ ትልቅ እውቅናና ክብር ሊቸረው የሚገባ መሆኑን ያለንፍገት ፣ ያለስስት መቀበል ያሻል ፡፡
ከ3ሽህ እስከ 5ሽህ አመታት የዘለቀ የሀገረ መንግስት ልምምድና ታሪክ አለኝ እያለ በእነ አክሱም በእነ ያሬድ ፣ በእነ ዘርዓ ያዕቆብ በእነ ምኒልክ ፣ በእነ … ለሚመካ ፣ ለሚቆዝም ሕዝብ የ “ መደመር “ ፅንሰ ሀሳብ ታሪክን የሚዋጅ ትውልዱንም በኩራት ቀና ብሎ እንዲራመድ የበኩሉን አስተዋጾ የሚያበረክት ታላቅ ስጦታ ነው ማለት ይቻላል ፡፡
ቅኝ ያልተገዛች ፣ የሰው ልጅ መገኛ ፣ የአድዋ ድል ባለቤት የሆነች ሀገር ላይ በትክሻዋ በሰላም የኖቤል አሸናፊና ተሸላሚ በሆነ ጠቅላይ ሚኒስትር የምትመራ እና የራሷ ሀገር በቀል የአስተዳደር ዘይቤ የቀመረች ሀገር የሚለው በወርቅ ዘቦ የተንቆጠቆጠ ካባ ስትደርብ በራስ መተማመን እና ኩራት ላይ ስንት ካራት እንደሚጨምር ስሌቱን ለአንጥረኛው ልተወው ፡፡
ስለሆነም በቅድሚያ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድን በማስከተል ይህ ሕልማቸው እውን እንዲሆን ከጎናቸው የነበሩ ሰዎችንና ተቋማትን እንደ አንድ ሀገር ወዳድ ዜጋ ከልብ ማመስገን እፈልጋለሁ ፡፡
በቀጣይ መፅሐፉ እጄ ሲገባ አቅሜ በፈቀደ በዚሁ ጋዜጣ ግምገማዬን ለማስነበብ ቃል እየገባሁ ለዛሬው ግን በፅንሰ ሀሳቡ ስያሜና በቀላሉ ለማስፋትና ለማስተዋወቅ ስለሚያግዙ አላባውያን ትንሽ እላለሁ ፡፡
ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር “ መደመር “ን ለመበየን ዋቢ ያደረጉት የደስታ ተክለወልድም ሆነ እኔ በማመሳከሪያነት የተጠቀምሁበት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ ቋንቋዎች ጥናትና ምርምር ማዕከል ያዘጋጀው የአማርኛ መዝገበ ቃላት መደመርን ፦ 1.መሰብሰብ 2 . ማከማቸት 3 .ማካበት ሲል ይበይኑታል ፡፡ አቻ ብያኔው መሰብሰብ ወይም ማከማቸት ወይም ማካበት መሆኑን ያሳያል ፡ ፡ እዚህ ላይ ራሳቸውን የቻሉ አማራጭ ፣ አቻ ፍችዎች መሆናቸውን ልብ ይሏል ፡፡ መደመር ሶስት የተለያዩ ትርጉሞች እንዳሉት ያሳያሉ እንጂ እርስ በርሳቸው ሂደታዊ ወይም ባህሪያዊ ግንኙነት የላቸውም ፡፡ ይበልጥ ግልፅ ለማድረግ “ መደመር “ ፦ መጀመሪያ መሰብሰብ ቀጥሎ ማከማቸት ከዚያ ማካበት ማለት አይደለም ፡፡
ሆኖም ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ አዲስ አመትን ምክንያት በማድረግ ከሸገር ኤፍ ኤም 102 . 1 ሬዲዮ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስም ሆነ ከዚያ በፊት ሆነ ሰሞኑን ሌሎች አመራሮች በተለያዩ መድረኮች “ መደመር “ በሚል ርዕስ ስለታተመው የክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር መፅሐፍ የሚሰጡ ማብራሪያዎች ፤ መደመር ትላንትን በማከማቸት ዛሬን በመሰብሰብ ነገን በማካበት የሚያስተሳስር ፍልስፍና ፣ ፅንሰ ሀሳብና ስልት ስለመሆኑ በስፋት እየተነገረ ነው ፡፡
ይሁንና የቃሉ እማሬዊ ወይም የተለመደው ፍቺ ከፍ ብሎ ለመግለፅ እንደሞከርሁት ፅንሰ ሀሳብነትን ፣ ፍልስፍናነትንና ስልትነትን አይገልፅም ፡፡ ከዚህ በላይ ቃሉ በቁሙ ወሰን ፣ ድንበር ፣ ዘር ፣ ሀይማኖት ፣ ጾታ ፣ ማንነት ፣ ጎሳ ፣ ወዘተ .ተሻጋሪነትን አያሳይም ፡፡ ስለሆነም እነዚህን ጎደሎዎች ለመሙላት ቃሉ ላይ የተወሰነ የሰዋሰውና የቅርፅ ለውጥ ማድረግ ያስፈልጋል ፡፡
ምክንያቱም ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር በመደመር መግለፅ የፈለጉት የመሰብሰብ ፣ የማከማቸትና የማካበት ፍልስፍናን ፣ ፅንሰ ሀሳብን ወይም ስልትን እንጂ ዘርን፣ ቀለምን ፣ ጎሳን ፣ ሀይማኖትን ፣ ዕምነትን ፣ ጾታን ፣ መደብን ፣ ወሰንን ፣ ድንበርን ወዘተ . አይደለም ፡፡ ለዚህም ነው የተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት ወጣት መሪዎች ድንበር ፣ አይዶሎጂ ፣ ማንነትና ባህል ሳይወስናቸው ፍልስፍናውን ወደ ሀገራቸው ወስደው በመቀመር ስራ ላይ ለማዋል ፍላጎት ማሳየታቸውን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከሸገር ኤፍ ኤም ሬዲዮ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ የነገሩን ፡፡
ሆኖም ከፍ ሲል ለማብራራት እንደሞከርሁት“ መደመር“ የሚለው ቃል በራሱ ፣ በቁሙ ፤ ፅንሰ ሀሳብ ፣ እምነት፣ አመለካከት ፣ ንድፈ ሀሳብ ፣ አላማ ፣ ፍልስፍና ወዘተ . መሆኑን አያሳይም ፡፡
ስለሆነም “ መደመር “ የሚለውን ቃል እነዚህን መግለፅ እንዲችል ሰዋሰዋዊ እግረ መንገድም አለም አቀፋዊ ቅርፅ መስጠት ያስፈልጋል ፡፡ ቅርፁን ራሱ “ መደመር “ እሚለው ቃል ላይ ወይም ፍልስፍናውን፣ ፅንሰ ሀሳቡን ወይም ስልቱን ለመጀመሪያ ጊዜ ያስተዋወቁት ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ ስለሆኑ የመጀመሪያ ስማቸውን እንዳለ ወስደን የቅርፅ ለውጥ አድርገን ልንጠቀምበትም እንችላለን ፡፡
በተለይ በሰላም የኖቤል 100ኛው አሸናፊና ተሸላሚ መሆናቸው ለዚህ ታሪካዊ አጋጣሚም ሲሳይም ነው ፡፡ የስማቸውን አለም አቀፋዊ ተቀባይነት (ብራንድነት) በእጅጉ ከፍ ስለ አደረገው መደመርን በእሳቸው ስም ማለትም “ ዐቢይ “ ላይ የሰዋሰው ቅርፅ ለውጥ አድርገን ብንጠቀምበት በአጭር ጊዜ ውስጥ ቀጣናዊ ፣ አህጉራዊና አለማ አቀፋዊ ተቀባይነትን ያገኛል ፡፡
“ መደመር “ ወይም “ ዐቢይ “ ከሚሉት ስሞች አንዱን ከመረጥን በኋላ ከፍ ሲል ለማሳየት እንደሞከርሁት አመለካከትን የሚገልፅና አለም አቀፍ ቅርፅና ትርጉም ለመስጠት ከሁለቱ በአንዱ ስም ምዕላድ / ክፍለ ቃል / ማከል ያስፈልጋል ፡፡
ለመሆኑ ምዕላድ ( affix ) ምንድን ነው ?
ምዕላድ ፦ ሰዋሰዋዊ ምድቡ ስም ሲሆን ፤ ትርጉም ኣዘል የሆነና ኣነስተኛ ወደ ሆነ ሌላ ትርጉም ኣዘል ትርጉሞች ሊከፈል የማይችል የመጨረሻ ንኡስ ኣሃድ ወይም ክፍል ነው፡፡ ለምሳሌ “ ሆድ “ ራሱን የቻል ቃል ወይም ምዕላድ ሲሆን “ ሆዳም “ ግን የ”ሆድ “ እና የቅፅል መስራች “…ም” ጥምረት ማለትም የሁለት ምዕላዶች ጥምረት የፈጠረው ቃል ነው ፡፡) ምዕላድ በዋናነት ባዕድ መነሻ ( prefix ) እና ባዕድ መዳረሻ ( suffix ) በሚል በሁለት ይከፈላሉ::
ባዕድ መድረሻ ፦ በስርወ ቃሉ ላይ ያልነበረ ፤ ከውልድ ቃል በስተመድረሻ በኩል በቀጣይነት የሚገባ እስር ምዕላድ ነው ፡፡ ያ – ህ – መስሪያ ፣ ሰራህ ፤ እግረ መንገዴን ስለ ባዕድ መነሻ ትንሽ ልበልና ወደ አስረጂዬ አልፋለሁ ፡፡
ባዕድ መነሻ ፦ ደግሞ መጀመሪያውኑ በስረወ ቃሉ ወይም በኣንድ የቃል መነሻ ስር ላይ ያልነበረ ፤ በእርባታ ጊዜ ከውልድ ቃል በስተመነሻ በኩል በተቀጣይነት ገብቶ የውልድ ቃሉ አካል ሆኖ የሚያገለግል እስር ምዕላድ:: መ – ቢ – ኣ ( ለምሳሌ ስራ ብሎ – መስሪያ ፣ ቢሰራ ፣ ኣሰራር ፣ …)
ለምሳሌ ሶሻል የሚለው ቃል ትርጉም ማህበራዊ፣ ካፒታል ወረት ፣ ሊበራል ነፃ አሳቢ መሆንን ሲገልፁ እንደ ቅደም ተከተላቸው መዳረሻ ምዕላድ ማለትም -ኢዝም ሲጨመርባቸው ግን ሶሻሊዝም ፣ ካፒታሊዝም፣ ሊበራሊዝም ሲሆኑ ፍቻቸው ይሰፋና ፍልስፍናን ፣ ፅንሰ ሀሳብን ፣ አመለካከትን ፣ ስርዓትን ፣ ወዘተ . የሚገልፅ ይሆናል ፡፡
ዳርዊን ፣ ሌኒን ፣ ማርክስ ፣ ማኦ ፣ ወዘተ . በቁማቸው እንደማንኛችንም ስሞች የተፅኦ ስሞች ናቸው ፡፡ – ኢዝም የሚል በዓድ መዳረሻ ሲጨምርባቸው ግን ዳርዊኒዝም፣ ሌኒኒዝም ፣ ማርክሲዝም ፣ ማኦይዝም ይሆናሉ:: በዚህም ፅንሰ ሀሳብን ፣ አመለካከትን ፣ ስርዓትን ፣ ፍልስፍናን ፣ ወዘተ ይገልጻሉ ፡፡
ስለሆነም ከፍ ብለን እንደተመለከትነው “ መደመር “ ወይም “ ዐብይ “ ፍልስፍናን ወይም ፅንሰ ሀሳብን እንዲገልፅልን ባዕድ መድረሻ ( suffix ) በላዩ ጣል ማድረግ አለበን ፡፡ ፍልስፍናውን “ መደመር “ እንዲገልፅልን ከወሰን “ መደመሪዝም “ ልንለው ወይም “ ዐቢይ “ ፍልስፍናውን ወይም ስልቱን በላቀ ደረጃ ይገልፅልናል ካልን ( በነገራችን ላይ የእኔ ምርጫ ይህ ነው፤ ) “ ዐቢይዚም “ ልንለው እንችላለን ፡፡
መደመርም ሆነ ዐብይ የሚለው – ስም – እምነትን፣ ፅንሰሀሳብን ፣ አመለካከትን ፣ ንድፈ ሀሳብን ፣ አላማን ፣ ፍልስፍናን ፣ ስልትን ፣ ወዘተ . እንዲገልፅልን – ኢዝም የሚል ባዕድ መድረሻ መጨመር ሰዋሰዋዊ አግባብ የsyntax ግዴታ ነው ፡፡ የምንፈልገውን ፅንሰ ሀሳብ በሙላት እንዲገልፅልን ወደ “ መደመሪዝም “ ወይም “ ዐቢይዚም “ ማሻሻል ያስፈልጋል ፡፡
ለአንድ ቁሳዊ ሆነ መንፈሳዊ ወይም ሀሳባዊ አልያም ለሰው የምናወጣለት ስም ወይም የምንሰጠው ስያሜ ቀድመን የምንልከው ነገር ስለሆነ ትኩረትንና ጥንቃቄን ይጠይቃል ፡፡ ብዙ ነገራችንን ይወስናልና:: ዛሬ ቤተኛ የሆኑን የቁስ ፣ የሀሳብ ፣ የመጠን ፣ ወዘተ . መጠሪያዎች እንዲሁ በአጋጣሚ ፣ በድንገት የተሰጡ አይደለም ፡፡ መጠሪያ ይዞ የሚመጣው ትርጓሜ ፣ ውጤትና ፍፃሜን ቀድሞ የሚያመላክት ሊሆን ይችላልና::
ኢትዮጵያን ፣ አዲስ አበባን ፣ ቶዮታን ፣ አፕልን፣ አማዞንን ፣ ኮካን ፣ ዴሞክራሲን ፣ ካፒታሊዝምን ፣ ኮምኒዝምን ወዘተ . ብንወስድ በአቦ ሰጥ ወይም ባፈተት የወጡ ስሞች አይደሉም ፡፡ ከፈጠራው ከእሳቤው ባልተናነሰ ሁኔታ ነገን በማለም የብዙዎች አእምሮ ተጨንቆባቸዋል ፡፡ እኛም መደመርን ከዚህ አኳያ ልናየው ይገባል ፡፡
አንድን ፍልስፍና ሆነ ፅንሰ ሀሳብ አልያም ግኝት በስፋት ለሚሊዮኖች ከፍ ሲልም ለቢሊዮኖች በማስተዋወቅ ተቀባይነት እንዲያገኝ ፤ በእያንዳንዱ ህይወት ቦታ እንዲያገኝ ለማስተዋወቅ ብራንድ ለማድረግ የምንከተለው ስትራቴጂያዊ ስልት ወሳኝ ነው ፡፡ ከዚህ አንጻር “ መደመር “ ላይ ከሚያስፈልገው መጠነኛ የስያሜ ማስተካከያ እና ፅንሰ ሀሳቡን ፍልስፍናውን በአጭሩ ከሚገልፅ ቃል ወይም ሀረግ አልያም ዓረፍተ ነገር ( motto ) ካለመካተቱ ባሻገር ቅርፁ እፁብ ድንቅ ነው ማለት ይቻላል ፡፡ መሰብሰብን ፣ ማከማቸትን እና ማካበትን እንዲገልፁ ሆነው የቀረቡ ሶስት ቀለበቶች ተንሰላስለው በሕብረ ቀለም የቀረቡበት የመደመር ምልክት ፣ አርማ ( logo ) በቀላሉ በሰው አእምሮ ተቀርጾ የሚቀርና የሚታወስ ነው የሚል እምነት አለኝ ፡፡
ሌላው አንድን ፅንሰ ሀሳብ ፣ ፍልስፍናንና ርዕዮት አለምን የሚወክል ፣ የሚገልፅ ቃል ወይም ሀረግ ለምሳሌ ሶሻሊዝም ፣ ካፒታሊዝም ፣ ሊበራሊዝም ፣ ወዘተ . ወደ ሌላ ማህበረሰብ ሲወሰድ የቅርፅ ለውጥ ይደረግበታል እንጂ መተርጎሙ አይመከርም ፡፡ ስያሜው የወል ነውና::
“ መደመሪዝም “ም ይሁን “ ዐቢይዝም “ ፍልስፍና ፣ ፅንሰ ሀሳብ ስለሆነ ርዕሱ ከአማርኛ ወደ አፋን ኦሮሞም ሆነ ትግረኛ አልያም ወደ ሌሎች የውጭ ቋንቋዎች ሲተረጎም ርዕሱ የወል ስም ስለሆነ ባይተረጎም ይመከራል:: በመፅሐፉ የተመለከትሁት የኦሮምኛ ትርጉም ርዕሱ “ IDA’AMUU “ በሚል ተመልክቻለሁ ፡፡ ርዕሱ በሁሉም ቋንቋዎች ተመሳሳይ ተቀራራቢ ቢሆን ይመረጣልና ፡፡ የትርጉም ሳይንስም ይሄን ነው የሚመክረው ፡፡
እንደ ማሳሰቢያ
ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር በመፅሐፉ የምረቃ ስነ ስርዓት ላይ ፅንሰ ሀሳቡ መነሻ ፣ መሰረት መሆኑን ገልፀው ኢትዮጵያውያን እንዲሔሱት ፣ እንዲተቹት ጋብዘው ከትችቱ ከሒሱ ጋር ግን አማራጭ አጎላማሽ ሀሳብ እንዲያቀርቡ አሳስበዋል ፡፡ ስለሆነም ልሒቃን ፣ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትና የመንግስት ፣ የፖሊሲ አማካሪዎች /think tank/ የጎደለውን በማከል ያለውን እውቅና በመስጠት እንደሚያጎለብቱት ተስፋ አደርጋለሁ::
ሌላው ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ ነገር የተከበረውን የትግራይ ሕዝብ ያላካተተ መደመር ሙሉኡ ሊሆን ስለማይችል የለውጥ ኃይሉም ሆነ መላ ሕዝቡ በዚህ ረገድ ያለበትን ታሪካዊ ኃላፊነት በማስተዋልና በጥበብ ይወጣል የሚል ዕምነት አለኝ:: በቀጣይም መፅሐፉ ወደ ትግረኛና ሌሎች ሀገረኛ ቋንቋዎች እንደሚተረጎም ተስፋ አደርጋለሁ ፡፡
ፈጠሪ ኢትዮጵያንና ሕዝቧን አብዝቶ ይባርክ !!!አሜን ፡፡
አዲስ ዘመን ጥቅምት 15/2012