‹‹… ዘመዶቼ ሆይ! እኔ የማገባት ሴት መልኳን ሳላይ፣ ጠባይዋንና ዕውቀቷን ሳልመረምር የማገባ ይመስላችኋልን? እርሷስ ጠባዬን፣ መልኬን ሳታይ ዕውቀቴን ሳትመረምር እኔን ባል አድርጋ ለመኖር የምትችል ይመስላችኋልን? የእናንተ ዓይን ለእኛ ምናችን ነው?›› ይላል የብላቴን ጌታ ኀሩይ ወልደ ሥላሴ ጽሑፍ!
ይህን ከፍ ሲል በትእምርተ ጥቅስ የሰፈረውን ቃል የተናገረውም ደራሲው ገጸ ባሕርይ ያደረጉት ‹‹ዐወቀ›› የተባለው ሰው ነበር፡፡ ብላቴን ጌታ ኀሩይ ወልደ ሥላሴ ‹‹አዲስ ዓለም›› በተሰኘው ልብ ወለድ መጽሐፋቸው ለብሌን እማኝነት ያበቁት ጥራዝ አደባባይ የዋለው በ1925 ዓ.ም ነው፡፡
በነገራችን ላይ‹‹ ጎሕ ጽባሕ›› በተሰኘ መጠሪያ የግል ቤተ ኀትመት በማቋቋም የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ ሊሆኑ ይበቁ ዘንድ ብኩርና የተቀዳጁት ብላቴን ጌታ ኀሩይ ወ/ሥላሴ የኢትዮጵያ ሥነ ጽሑፍ መዛግብት በሚመረመሩበት ጊዜ ሁሉ ባለ ውለታ መሆናቸውን ለአፍታ እንኳ መዘንጋት የሚቻል አይደለም፡፡ ይህም ውለታቸው ከኢትዮጵያ አልፎ ባሕር ማዶ የተሻገረ ነው፡፡
መቼም ‹‹ ነገርን ነገር ያነሣዋል›› እንዲባል ነውና ጥቂት ብንዳስሰው የሥነ ጽሑፍ ጉዳይ ከተነሣ ዘንድ፣ እንዲሁም የባለ ውለታነት ነገር ከታሰሰ ዘንድ እንደ አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ፣ እንደ ብላቴን ጌታ ኀሩይ ወልደ ሥላሴ፣ እንደ ብላቴን ጌታ ማኀተመ ሥላሴ ወልደ መስቀል፣ እንደ ኀሩያን የአማርኛ ቋንቋ መጻሕፍት ደራስያን እንደ አለቃ ታየ ገብረ ማርያም፣ እንደ አለቃ ተክለ ማርያም ፋንታዬ፣ እንደ ብላታ መርስዔ ኃዘን ወልደ ቂርቆስ ያሉ እና ሌሎችም መሰል ታላላቅ ሰዎች እንዲሁም ተስተው መቅረታቸውና ለውለታቸውም የሚታወሱበት፣ መረሳት ሳይገባቸው እንዲረሱ የተደረጉበት ሁኔታ ሲታሰበኝ ‹‹መሥራት ለምኔ ማድረግስ ለምኔ›› አሰኝቶ የቀሩትም ሰዎች ከመሥራትም ከማድረግም ተቆጥበው ትውልድ እንዳያፈሩ በሠሩት እንዲያፍሩ፣ እንዳልነበር ሆነው እንዲቀሩ በር ይከፍታል:: ይህ እጅጉን የሚያሳዝን ነው፡፡
በውኑ በዛሬ ጊዜ ያለው የኢትዮጵያ ደራሲያን ማኀበር ለዚህ ነገር ተገቢ የአስታዎሽነት ሚና ይጫወት ዘንድ ዓይነተኛ ድርሻ ያለው ይመሰለኛል፡፡ ስለዚህ ለጉዳዩ ቢያስብበት የተሻለ ሳይሆን አይቀርም፡፡
ወደ ብላቴን ጌታ ኀሩይ ማንነት እንመለእና ለዚህ ነው ጀርመናዊው ሊቀ ሊቃውንት ዩገን ሚትቮህ ከእኒሁ በዚያን ዘመን የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትርነት መንበረ ሥልጣን ከያዙት፣ እጅግም ከከበሩ ማእምረ ልሳን ጋር በሀገረ ጀርመን ያደረጉትን የረጅም ጊዜ ቆይታ በተመለከተ ሲጠቅሱ ‹‹ሕያው ሆኖ የሚኖር ጥበባዊ ትውስታ›› በማለት በክብር ያዘከሩት፡፡ የኀሩይን ታላቅነት ያወሱ ሌሎችም አያሌ ርዕሳነ ማእምራን አሉ፡፡ ይህም ለኢትዮጳያችን ታላቅ ክብር ነው፡፡ ይህን ያህል ስለ ዕውቁ ደራሲ በመጠኑ ካልኩ ዘንድ የዛሬው ጽሑፌ ወደተነሣበት ጉዳይ ላምራ፡፡
ደራሲው ገጸ ባሕርይ አድርገው ያስቀመጡት ዐወቀ ዘመዶቹ ያጩለትን ሚስት አላገባም ስለማለቱ፣ ይህንን ያለበትን ምክንያትም አሳማኝ በሆነ መልክ ዘርዝሮ ስለ ማተቱ በሚገባ ተርከው ያስተማሩበት በጥበብ የተጌጠ ድርሰት መሆኑን ለመካድ የሚቻልበት ሁኔታ የለም፡፡ በዚህ የብላቴን ጌታ ኀሩይ ወ/ሥላሴ ድርሰት እጅግም ሐታትያን ሒስ የሰጡበትን ወቅት አላስታውሰውም:: ይሁንና ድርሰቱ በአስተማሪነቱ የማይናቅ አስተዋጽኦ ማበርከቱን አንክድም፡፡
የጽሑፉም አደራረስ ስናየውና የተጻፈበትን ዘመን ስናሰላው፣ እንዲያ ሲልም ከዛሬው ጊዜ ጋር አገጣጥመን፣ እያነጻጸርን ስንፈትሸውና ወቅትን ከኩነት ስናመላክተው ‹‹ዛሬስ?›› የሚለው ጥያቄ ድቅን እያለ ምላሽ የሚያስፈልገው መሆኑን ይጠቁመናል፡፡ የዛሬ ሰማንያ ዓመት ገደማ ደራሲው የተቃወሙት አሰተሳሰብ ዛሬም መታየቱ አልቀረምና!
አንዳንድ የዋሕ ሰዎች ይህን መሰል አመለካከት ጭርሱን ሞት እንደተቀበረ አድርገው የሚያስቡ አይጠፉ ይሆናል፡፡ እውነቱ ግን እንዲህ እንደሚታሰበው አይደለም፡፡ አመለካከቱ ታሞ ሊሆን ይችላል፡፡ ሞቶ ግን አልተቀበረም፡፡
በእርግጥ እንደ ጥንቱ የሀገራችን ልማድ ከሆነ ሁለቱም ተጋቢዎች ፈጽሞ ሳይተዋወቁ፤ የፍጥምጥሙ ዕለት ሊሆን ጥቂት ጊዜ ሲቀረው ለወንድየው ተነግሮ በዚያው ነገሩ ያልቅ ነበር፡፡ ሴቷ ወትሮውንም ከወላጆቿ፣ ከቤተ ዘመዶቿ ፈቃድ የማትወጣ፣ የምትዳርም ብቻ ሳትሆን የምትሰጥ ዕቃ ሆና የምትገመት ያህል ነችና!
እርሷን ከቁም ነገር አግብቶ የሚያዋያት ‹‹ትወጃለሽ፣ አትወጂም›› ብሎ የሚጠይቃት ‹‹ጨዋ ሰው›› አልነበረም:: ‹‹ጨዋ›› ሊባል የሚበቃው እንደ ዕቃ አንሥቶ የሚሰጥ ሆኖ የቆየ ነበርና!
ይሁንና ይህ ሸበቶ ወግ ዛሬም ‹‹ሞቶ ተቀብሯል›› ብሎ እርም ማውጣት የሚቻልበት ደረጃ ላይ አልደረስንም:: ተጋቢ ወጣቶች በትምህርት ቤት፣ በተግባር ገበታ ወይም በሌላ የሆነ ሥፍራ ተዋውቀው ወይም በጊዜ ወለዱ ‹‹ፌስቡክ›› አድራሻ ከነምስሉ ተለዋውጠው ቢገኙም ‹‹ላግባሽ›› ብሎ የጋብቻ ፍላጎቱን ከገለጠ አማላጅ ለወላጆቿ መላክ የግድ መሆኑን አይተናል፡፡
ሌላው ቢቀር ‹‹ለወጉ›› ሲባል እንኳ የአማላጁ ነገር የሚቀር አልመሰለም፡፡ የዚህ ጽሑፍ አቅራቢ በተደጋጋሚ ወቅት ለዓይን ምስክርነት የበቃባቸው ሁኔቶች እውነታን በእውነታ ለማረጋገጥ ችለዋል፡፡
ሊጋቡ ያቀዱ ጥንዶቹ እንዲያውም አንዳንዶቹ አብረው በአንድ ጣሪያ ሥር አንሶላ ሲጋፈፉ፣ ገና ከማለዳው የወደፊት አነዋወር ዕቅዳቸውን ሲነድፉ፣ ሲደምሩ፣ ከዕለት ድግሳቸው ቀደም ካለው የመሰናዶ ጊዜ አንሥቶ እስከ ሠርግና እሱን ከመሳሰለው፣ እንደዚያም ካለው የመሰናዶ ጊዜ አንሥቶ እስከ ዋናው ሠርግና መልሱ ያለውን ወጭ ሳይቀር ጥቁርና ነጭ አድርገው ሲጽፉ፣ ሲደምሩ፣ ሲቀንሱ ይከርሙና ሠርጉ ሲቃረብ እርሷ ‹‹እንድትሰጥ›› ወደ ወላጆቿ ቤት ሄዳ ጥቂት ዕለታት ያህል አማላጆች ወደ ወላጆች ተልከው ‹‹ልጃችሁን ለልጃችን›› በሚሉበት ጊዜ እዚያ ሄደው ‹‹ለወጉ›› የሚሰነብቱ አልታጡም፡፡
ወረደም ወጣ ‹‹አማላጅ›› የሚለውን ነገር እንደክብር የሚቆጥሩ ሴቶች ፈጽሞ እንዳልጠፉ ነው ብዙ ጊዜ የታዘብኩት፡፡ ‹‹የድሮው ቀረ›› ቢባል በተሐድሶ ገጽታውን ቀይሮ ብቅ ብሏል፡፡ ‹‹በበርኖስ ላይ ከራቫት›› መሆኑ ጥቂት ቢያስቅም ያንኑ አስቂኝነት እንደ ልዩ መታወቂያ ይዘው መታየትን የሚወዱ፣ የነገውን በአቻምናው የሚያቅዱ፣ የዛሬን በትናንት ወዲያው ሒሳብ ለማስላት የሚፈቅዱ ሴቶች የተትረፈረፉ ናቸው ማለት ያስደፍራል::
በሌላ በኩል ግን ስለ ‹‹እኩልነት›› ብዙ ሲያወሩ፣ በየመድረኩ የሌለ ታሪክ ሲቀምሩ ይስተዋላሉ፡፡ ለመሆኑ አንድ ሰው ‹‹እኩልነት›› ከተባለ እንደ ‹‹ዕቃ›› መቆጠርንም ይጨምራል ማለት ይሆን? ለዚህ ዓይነቱ ጥያቄ ምላሻቸው ያው ‹‹ወጉ!›› የሚል ሲሆን ይህ ደግሞ የባሰ ያጠያይቃል፡፡ እንደ ‹‹ወግ ዕቃ›› መቆጠራቸውም እንጂ ‹‹ወግ እንደ ደረሰው ሰው›› ብቻ ሊታያቸው አለመቻሉ ይህም ስላልተገለጠላቸው ዘወትር የሚገርመኝ ነው፡፡
እዚህ ላይ ለአብነት ያህል የአሁኑን በሀገራችን ያለውን ነባራዊ እውነታ ብንቃኝ በሥልጣን ላይ ካሉት ከፍተኛ ሹማምንት፣ ማለትም ከሚኒስትርነት አንስቶ ዝቅ ሲልም እስከ ሚኒስትር ደኤታ ማእረግ ያሉትን ሰዎች ብናይ በርካታ ሴቶች ተሹመው ይገኛሉ፡፡ እንግዲህ እነዚህ ከፍተኛ ሹማምንት ለመቶ ሚሊዮን ሕዝብ ተጠሪ ሆነው የተቀመጡ ናቸው፡፡ ይሁንና አንድ ወንድ ለትዳር ጓደኝነት ቢፈልጋቸው ‹‹በቅድሚያ አባቴን በአማላጅ አስጠይቀህ እንጂ አለዚያ አይሞከርም›› የሚሉ መሆናቸውን በየአጋጣሚው ተገንዘበናል፡፡
እናስ ያንን ያህል የሀገር ባለ አደራነት የት አደረሱት? ምላሹ ያው ‹‹ ባህሉ፣ ወጉ.. ወዘተ›› የሚለው ይሆናል፡፡ ፈጽሞ ተቀባይነት ሊኖረው የማይችል ምክንያት!!
በመሠረቱ አንድ ባህል ‹‹ባህል ነው›› ተብሎ ሲነገር የአንድን ኀብረተሰብ ሲወርድ ሲዋረድ የመጣ የአነዋወር ዘዬ፣ ሥርዓት፣ ሕይወት፣ ልማድ፣ ወግ የሚያመለክት ነው፡፡ ይህ ማለት ግን ‹‹ባህል›› ከተባለ በጥቅሉ ሁሉም የማይሽረው፣ ጊዜ የማይለውጠው እስከ ተፍጻሚተ ዓለም ከብሮ፣ ተከብሮ የሚኖር ነው ማለት እንዳልሆነ ግልጽ ሊሆንልን ይገባል፡፡ ‹‹ሲወርድ፣ ሲዋረድ›› ከተባለ አዋርዶ መቅረትንም ይጨምራል ማለት አይደለም፡፡
ከጊዜው ጋር የሚሄድ፣ ከሥልጣኔ ጋር የሚዋሐድ፣ በአንድነት የሚራመድ ባህልም ወግም አለ፡፡ በአንጻሩ ደግሞ ከጊዜ ጋር የማይሄድ፣ ከሥልጣኔ ጋር የማይዋሐድ፣ በአንድነትም የማይራመድ፣ ይልቁንም ለሥርዓተ ህላዌ መሰናክል የሆነ፣ በኋላ ቀርነት የደነደነ ባህልም ወግም መኖሩን መርሳት የለብንም፡፡
ሀገራችን ኢትዮጵያ ቁጥር ሰፍር የሌለው፣ በአኩሪነቱ የሚዘከር ባህልም ወግም እንዳላት ሁሉ የሰውን ልጅ መብት የማይጠብቅ፣ ክብር የማያስጠብቅ፣ እንዲያውም የሚያስጨንቅ አንዳንድ የአነዋወር ዘዬ፣ ወግና ልማድ ያላት መሆኑንም መዘንጋት የሚገባን አይመስለኝም፡፡
ሆኖም ሰውን እንደ ‹‹ዕቃ›› አንሥቶ ከመሰጠት የበለጠ አዋራጅ ነገር ‹‹አለ›› ቢባል በሰብዓዊው ክብርና መብት ጥቂት እንደ መቀለድ ይመስለኛል፡፡ የተዳሪውን ፈቃደኝነት ጠይቆ ይመስለኛል፡፡ የተዳሪውን ፈቃደኝነት ጠይቆ፣ በሥነ ሥርዓት አዘጋጅቶ፣ ወይም እንደ አስፈላጊነቱ የአቅምን ያህል አሰናድቶ መዳር እንደ ‹‹መስጠት›› የሚያሳፍር ኩነት አይደለም፡፡ ይህ በሀገራችን ብቻ ሳይሆን በአህጉረ አውሮፓም ዛሬ፣ ዛሬ ጭርሱ እየቀረ ሄደ እንጂ እስከ አለፈው ምዕተ ዓመት መደምደሚያ ድረስ ይሠራበት ነበር፡፡ በሀገራችን ግን አሁንም እንደ ጥንቱ እየሠራንበት ነው፡፡
ይህ ስለተባለ ግን ወላጆች አይከበሩ፣ ይደፈሩ፣ ሥነ ምግባር ይነቀፍ፣ አኩሪ ሥነ ሥርዓት አይደገፍ ለማለት የተሞከረ እንዳልሆነ አንባቢ እንዲረዳልኝ እወዳለሁ:: ይህም ልብ ሊባል የሚያሻ ነውና! በተረፈ እንደ ጥንቱ እያሰብን ዛሬም በዘመኑ እንኖራለን ብሎ መነሣት ከጥቅሙ ጉዳቱ ብቻ የሚያመዝን መሆኑን ዘወትር ማስታወስ ይገባናል፡፡
‹‹ወግ ማክበር›› ሲባል ‹‹የወግ ዕቃ›› መሆንም እንዳልሆነ ልብ እንበል!!
አዲስ ዘመን ጥቅምት 15/2012
አሸናፊ ዘደቡብ