ጥንታዊቷ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ከፍቷታል፡፡ በተለይ ባለፉት ሁለት እና ሶስት ዓመታት መልኩን እየቀያየረ ቤተክርስቲያኗ እና አገልጋዮችዋ ላይ የሚፈጸመው ጥቃት እንዲቆም በተደጋጋሚ ያቀረበችው ጥያቄ በቂ የተግባር መልስ ማጣት አባቶችን አሳዝኗል፡፡
በመንግሥት በኩል ችግሩ ከአጠቃላይ የሠላምና ጸጥታ መደፍረስ ጋር የተያያዘ መሆኑን በማስረዳት ችግሩ በተናጠል ሳይሆን አብሮ ለመፍታት እየሰራ ስለመሆኑ መናገሩ የሚታወስ ነው፡፡
በተጨባጭ ሁኔታው ቅር የተሰኙ የቤተክርስቲያኗ ምዕመናን በዋና ከተማው አዲስአበባ ባለፈው ወር ሊያካሂዱት አቅደው የነበረው ሰላማዊ ሰልፍ ከመንግሥት ጋር ተቀራርቦ በመነጋገር ለመፍታት በተደረሰው ስምምነት መሰረት ለጥቅምት 30 ያራዘሙት ቢሆንም ባለፉት ሳምንታት በአማራ ክልል የተለያዩ ከተሞች ደማቅ የተቃውሞ ሰልፎች ተካሂደዋል፡፡
በነሐሴ ወር 2010 ዓ.ም ቤተክርስቲያኗ እንዲህ ብላ ነበር፡፡ መንግስት እያሳየ ያለው ከመጠን ያለፈ ትዕግስት ለሀገሪቱ አንድነትና ለዜጎች ደህንነት አደጋ መደቀኑን ገልጻለች።
“በቅርብ ግዜያት ውስጥ በተፈጠሩ ግጭቶች ዘጠኝ አብያተ ክርስትያናት ሲወድሙ አምስት ካህናት በአሰቃቂ ሁኔታ ተገድለዋል።
በባሌ፣ በሻሸመኔ፣ እንዲሁም በጣና በለስ እንዲሁም በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ያለውን ሁኔታ ትኩረት ሰጥታ የተመለከተችው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን በተለይ በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል በሰው፣ በአብያተ ክርስትያናትና በንብረት ላይ የደረሰ ጥቃቶችና ዘረፋዎች ተዘርዝረዋል።
በፓትሪያሪክ አቡነ ማቲያስ በተነበበው የቤተክርስቲያኒቱ መግለጫ 9 አብያተ ክርስትያናት ከነሙሉ ንብረታቸው መውደማቸውን፣ አምስት ካህናት በአሰቃቂ ሁኔታ ሲገደሉ ፣ሰባት ካህናት ደግሞ ከፍተኛ ጉዳት ደርሶባቸዋል።
ከዚህም በተጨማሪ በርካታ ምዕመናን መጎዳታቸውን ንብረቶች መውደማቸውንና ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስተያን ውጪ ያሉ ክርስትያኖች ላይ ተመሳሳይ ጥቃት መፈጸሙን ፓትሪያሪክ ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ዘርዝረዋል ።
መንግስት ለሃገራዊ መግባባት ሲል የሚያሳየው ከልክ ያለፈ ትዕግስት የሐገሪቱን አንድነት እንዲሁም የዜጎችን ደህነት አደጋ ላይ መጣሉንም መግለጫው ዘርዝሯል።”
በሌላ በኩል ከትላንት በስቲያ ሐሙስ ዕለት ዓመታዊ መደበኛ ስብሰባውን እያካሄደው ቅዱስ ሲኖዶስ የሶስት ቀናት ጸሎትና ምህላ ማወጁን አስታውቋል፡፡ የቅዱስ ሲኖዶስ መግለጫ ምን ይላል?
ቅዱስ ሲኖዶስ እንዳለው በአገራችን እንኳንስ ሊደረጉ ቀርቶ ሊታሰቡ የማይገባቸው ጎሣንና ሃይማኖትን መሠረት ያደረጉ መጠነ ሰፊ ግጭቶች በተለያዩ ክልሎች እየተስፋፉ መኾኑ በእጅጉ ያሳሰበው ቅዱስ ሲኖዶስ፣ ከዛሬ ጥቅምት 13 ቀን 2012 ዓ.ም. ጀምሮ ለሦስት ቀናት ጸሎት እና ምሕላ እንዲደረግ ዐወጀ፤ ከመንግሥት የጸጥታ ኀይሎች አንሥቶ ሁሉም አካላት እና ዜጎች በየድርሻቸው ለአገራዊ ሰላም፣ አንድነት እና ተግባቦት የድርሻቸውን እንዲወጡ የሰላም ጥሪ አስተላለፏል፡፡
ዓመታዊ መደበኛ ስብሰባውን በማካሔድ ላይ የሚገኘው ምልአተ ጉባኤው፣ የምሕላ ዐዋጁንና የሰላም ጥሪውን ያስተላለፈው፣ ኀሙስ፣ ጥቅምት 13 ቀን 2012 ዓ.ም. ረፋድ፣ በወቅታዊ አገራዊ ጉዳይ በሰጠው አስቸኳይ መግለጫው ነው፡፡
የበርካቶች ሕይወት ከጠፋባቸውና ንብረት ከወደመባቸው፣ ዜጎች ለከፋ እንግልትና እርዛት ከተዳረጉባቸው የቀደሙ ግጭቶች ባለመማር፣ አሁንም በኦሮሚያ ክልልና በአዲስ አበባ ዙሪያ ከተሞች እንዲሁም በሌሎችም ክልሎች፣ በአገራችን ላይ ከፍተኛ ጥፋትና ድህነት የሚያደርሱ መጠነ ሰፊ ግጭቶች መበራከታቸው በእጅጉ እንዳሳሰበው ገልጿል፡፡
የአማራ እና የቅማንት፣ የአማራ እና የጉሙዝ፣ የአማራ እና የትግራይ፣ የሶማሌ እና የአፋር፣ የኦሮሞ እና የአማራ፣ ወዘተ. እየተባሉ የተደረጉ ግጭቶች ሁሉ፣ “ምክንያታዊ ባልሆኑ ጉዳዮች መነሻነት” የተከሠቱ እንደ ሆኑ ምልአተ ጉባኤው በመግለጫው አስፍሯል፡፡
ከእውነታ የራቁ፣ የሕዝቡን የአንድነት እና የአብሮነት ባህል የሚጎዱ፣ ታሪክን የሚያፋልሱ ሐሰተኛ ትርክቶች ለግጭቶች መንሥኤ እንደሆኑ ጠቅሶ፤ የፖለቲካ ኀይሎች፣ የብዙኀን መገናኛዎች፣ የሶሻል ሚዲያው ተጠቃሚዎች እንዲሁም ምሁራንና የመንግሥት የሥራ ሓላፊዎች፣ ብሔርንና ሃይማኖትን መሠረት ካደረጉ የትንኮሳ ቃላት ተቆጥበው፣ ከልዩነትና ግጭት ይልቅ ለሀገራዊ አንድነትና ተግባቦት የድርሻቸውን እንዲወጡ ጥሪውን አስተላልፏል፡፡
የጸጥታ እና የፍትሕ አካላት፣ ግጭቶች እና አለመግባባቶች ከመከሠታቸው በፊት፣ ቅድመ መከላከልን መሠረት ያደረገ የጸጥታ ሥራን በመተግበር የሰው ሕይወት መጥፋትንና የንብረት ውድመትን በማስቀረት የተጣለባቸውን ሓላፊነት እንዲወጡ ቅዱስ ሲኖዶሱ በአስቸኳይ መግለጫው ጠይቋል፡፡
ያለሀገር ሰላም እና አንድነት እንዲሁም ፍቅር እና ተግባቦት መኖር የማይቻል በመሆኑ፣ ሁሉም እንደየ እምነቱ እና የሃይማኖቱ ሥርዓት፣ ከጥቅምት 13 ቀን ጀምሮ ለሦስት ቀናት ያህል በጸሎት እና በሐዘን፣ ስለ ሀገር ሰላም በአንድነት ለመናውን ለፈጣሪ ያቀርብ ዘንድ፣ ጸሎት እና ምሕላ እንዲያደርግ ማወጁን ምልአተ ጉባኤው በአስቸኳይ መግለጫው አስታውቋል፡፡
የአማራ እና የቅማንት፣ የአማራ እና የጉሙዝ፣ የአማራ እና የትግራይ፣ የሶማሌ እና የአፋር፣ የኦሮሞ እና የአማራ፣ ወዘተ. እየተባሉ የተደረጉ ግጭቶች ሁሉ፣ “ምክንያታዊ ባልሆኑ ጉዳዮች መነሻነት” የተከሠቱ እንደ ሆኑ ምልአተ ጉባኤው በመግለጫው አስፍሯል፡፡
ከመንግሥት ጋር የተጀመረው ምክክር ምን ደርሷል?
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን፣ ካህናት እና ምእመናን ላይ በተለያዩ አካባቢዎች የሚደርሰው ጥቃት እንዲቆም የሚንቀሳቀሰው የአዲስ አበባ አስተባባሪ ኮሚቴ መስከረም 02 ቀን 2012 ዓ.ም በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ፣ በየጊዜው የሚኖረውን የውይይት ሒደት እና ውጤት፣ ለሕዝበ ክርስቲያኑ ለማሳወቅ በገባው ቃል መሠረት የመጀመሪያውን መግለጫ መስጠቱ ይታወሳል፡፡ ኮሚቴው ያከናወናቸው ዋና ዋና ተግባራት በተመለከተ በድጋሚ ጥቅምት 7 ቀን 2012 ዓ.ም ሒደቱን አስታውቋል፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የአብያተ ክርስቲያናት የይዞታ ማረጋገጫ ጥያቄዎች ተግባራዊ ምላሽ የመስጠቱ ሒደት በተጠናከረ ሁኔታ ቀጥሏል፡፡
በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ክልል እንዲሁም በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር የተገቡ ቃሎች ትግበራ በተቻለ ፍጥነት እንዲሔድ እና ተግባራዊ ምላሽ ለመስጠት ከተማ አስተዳደሩ እና ክልሉ እያደረጓቸው ያሉ ጥረቶች አሁንም በተጠናከረ ሁኔታ ቀጥለዋል፡፡ የእዚህን ያህል ባይሆንም ከኦሮሚያ ክልል በስተቀር በሌሎች ክልሎችም ተስፋ ሰጪ ጅምሮች እና እንቅስቃሴዎች አሉ፡፡
የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት በክልሉ የተፈጠሩ እና እየተፈጠሩ ያሉ ችግሮችን ለመፍታት ለዘብተኝነት እያሳየ ነው፡፡ ኮሚቴው ከክልሉ ከፍተኛ አመራሮች ጋር በችግሮች ላይ በተወያየበት ወቅት ‹‹በክልላችን መዋቅራዊ ጥቃቶች አሉ ብለን ባናምንም በግለሰቦች የሚፈጠሩ፣ ችግሮች ስለሚኖሩ እነዚህን ችግሮች በማጣራት መፍትሔ እንሰጣለን››ብሎ ቃል ቢገባም እስካሁን ምንም ተጨባጭ መፍትሔ ሊያመጣ እንዳልቻለ ጠቅሷል፡፡
ከመስቀል በዓል ጋር በተያያዘ የፌዴራል ፖሊስ በሰጠው መግለጫ ምክንያት የታሰሩ ኦርቶዶክሳውያን እንዲፈቱ ተደርጓል፡፡ ከፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ጋርም በተደረገው ውይይት በመስቀል በዓል አከባበር ላይ በአንዳንድ የጸጥታ ኃይሎች እና ሕገ ወጥ ቡድኖች ምክንያት የተፈጠረውን ችግር ከክልሎች የፖሊስ ኮሚሽነሮች ጋር በመገምገም የመፍትሔ አቅጣጫ ለማስቀመጥ እና አስፈላጊውን እርምት ለመውሰድ ከስምምነት ላይ ተደርሷል፡፡
በክልሎች ደረጃ የተደረጉ ውይይቶችን አፈጻጸም በቅርበት ለመከታተል እና ቀጣይ ችግሮች እንዳይፈጠሩ በቅንጅት ለመሥራት ከመንግሥት እና ከየአህጉረ ስብከት የተውጣጡ አካላት ያሉበት የጋራ ኮሚቴ በየዞኖቹ ተቋቁመው በክልሎቹ በተቋቋሙት የጋራ ኮሚቴዎች አስተባባሪነት፣በየዞኖቹ በመንግሥት እና በቤተ ክርስቲያን ተወካዮች መካከል ውይይቶች መካሔድ ጀምረዋል። በአንዳንድ ዞኖች የትግበራ ዕቅድ አውጥተው በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛሉ፡፡ በዚህ አጋጣሚ ሕዝበ ክርስቲያኑ በየዞኖቹ የተቋቋሙ ኮሚቴዎች ውስጥ በንቃት እንዲሳተፍ፣ መረጃዎችን እንዲሰጥ እና ተገቢውን ድጋፍ በመስጠት ክርስቲያናው ግዴታውን እንዲወጣ ጥሪ አቅርቧል፡፡
በዚህ አጋጣሚ የፌዴራል ፖሊስ የመስቀል በዓልን አስመልክቶ በዋዜማው ዕለት የሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ እና መግለጫውን ተከትሎ አረንጓዴ፣ ቢጫ ቀይ ቀለማት የተዋቡ አልባሳትን በለበሱ ምእመናን ላይ ፖሊስ ይፈጽመው የነበረው የማንገላታት እና የማመናጨቅ ተግባር አግባብነት የሌለው በመሆኑ ሊታረም ይገባል፡፡ መግለጫው ምእመናን ወደደመራ በዓሉ እንዳይወጡ፣ የወጡትም በስጋት እንዲያሳልፉ ከማድረጉም በላይ በአንዳንድ አካባቢዎች በዓሉ በሰላም እንዳይከበር እና ሁከት እንዲፈጠር ያደረገ በመሆኑ በጉዳዩ ላይ የፌዴራል ፖሊስ ቃል በገባው መሠረት ገምግሞ አስፈላጊውን እርምት እንዲወስድ ጠይቋል፡፡
የመስቀል በዓል በታላቅ ድምቀት የሚከበር የዐደባባይ አገራዊ እና ዓለም አቀፋዊ በዓል ሆኖ ሳለ በአንዳንድ አካባቢዎች ሕዝበ ክርስቲያኑን ለግጭት በሚያነሣሣ መልኩ በጸጥታ አካላት አላስፈላጊ እርምጃዎች ሲወሰዱ ተስተውሏል፡፡ እንዲህ ዓይነት ድርጊቶች ወዳልተፈለገ ግጭት የሚያመሩ እና በዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ፊትም የአገርን ገጽታን የሚያበላሹ ከመሆናቸውም በላይ በሕዝበ ክርስቲያኑ ትዕግሥት እና ማስተዋል ታክሎበት እንጂ የከፉ ችግሮች እንዲፈጠሩ የሚጋብዙ ስለሆኑ በአስቸኳይ እርምት ሊደረግበት ይገባል፡፡
በኦሮሚያ ክልል አንዳንድ አካባቢዎች ከመስቀል በዓል አከባበር ጋር በተያያዘ በዝምታ ሊታለፉ የማይችሉ ችግሮች ተፈጥረዋል፡፡ በደብረ ዘይት ከተማ የመስቀል ደመራ በዓል ላይ የሰንበት ትምህርት ቤት ወጣቶች የለበሳችሁትን ዩኒፎርም አውልቁ መባላቸው፣ በዚሁም ምክንያት የመስቀል ደመራ በዓል ሳይከበር መቅረቱን እና ደመራው ሌሊት በሕገ ወጥ ቡድኖች መቃጠሉ፤ በጅማ ከተማ ለመስቀል ደመራ በዓል የወጡ ምእመናን መደብደባቸው፣ በሻምቡ ከተማ በዓሉ ሊከበርበት ከነበረው መስቀል ዐደባባይ ውጭ ሌላ ቦታ አክብሩ ተብለው መከልከላቸው ቤተ ክርስቲያናችንን በእጅጉ ያሳዘኑ ታሪካዊ ስሕተቶች ናቸው፡፡ በእነዚህ አካባቢዎች ምእመናን በዓሉን በሰላም እንዳያከብሩ ክልከላዎችን ያደረጉ፣በሕዝበ ክርስቲያኑ ላይ ድብደባ የፈጸሙ እና ምእመናንን እና አስተባባሪዎችን በማሰር እና በማንገላታት የበዓሉን ድባብ ሰላማዊ እንዳይሆን ያደረጉ የመንግሥት አካላት ሊታረሙ እና አስፈላጊው እርምጃ ሊወሰድባቸው ይገባል፡፡ በተጨማሪም ከግሸን ደብረ ከርቤ ክብረ በዓል የሚመለሱ ምእመናን በየመንገዱ በተደራጁ ወጣቶች እብሪት የተሞላበት የጥቃት ተግባር ተፈጽሞባቸዋል።
የክልሉ መንግሥትም ይህንን ነውረኛ ድርጊት በዝምታ በመመልከት መንግሥታዊ ሚናውን ሳይወጣ ቀርቷል፡፡ አሁንም በአንዳንድ የክልሉ አካባቢዎች ሃይማኖታዊ ጫናዎች እና ማንገላታቶች ቀጥለዋል፡፡ የቤተ ክርስቲያን ይዞታዎችን መውረር፣ መጋፋት እንዲሁም ቤተ ክርስቲያንን እና የኦርቶዶክሳውያን ቤቶች እና ሱቆች ማፍረስ ተባብሶ ቀጥሏል፡፡ መንግሥት በእነዚህ ሕገ ወጥ ድርጊት ፈጻሚዎች ላይ እርምጃ አለመውሰዱ ጥፋቱ እንዲባባስ አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡ የክልሉ መንግሥት ይህን እያደረጉ ባሉ ቡድኖች እና የመንግሥት አካላት ላይ አስፈላጊውን እርምጃ እንዲወስድ፣ እየተፈጠሩ ላሉ ችግሮችም በአፋጣኝ መፍትሔ እንዲሰጥ እንጠይቃለን ሲል መግለጫው ያትታል፡፡
በአንዳንድ ሚዲያዎች እና ግለሰቦች በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ላይ እየተሰነዘሩ ያሉ ጸያፍ እና ከፋፋይ የሐሰት ትርክቶች፣ የቤተ ክርስቲያንን አስተምህሮ የማጉደፍ እና የማጣጣል ድርጊቶች እንዲሁም ቤተ ክርስቲያንን ባልዋለችበት በማዋል የከበረ ስሟን በሐሰት የማጥፋት ዘመቻዎችን በማውገዝ በሕግ ለመጠየቅ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመነጋገር ላይ እንደሚገኝ ጠቅሷል፡፡
እንደመሰናበቻ
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ትልቅና ለኢትዮጵያ ጥንታዊ ታሪክና ስልጣኔ መሰረት የጣለች ቤተክርስቲያን ናት፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የፖለቲካ አጀንዳ ያነገቡ የተለያዩ ኃይሎች ይህቺን ቤተክርስቲያን ዒላማ አድርገው መንቀሳቀሳቸው እና ለመጉዳት መሞከራቸው በቀላሉ የሚታይ አልነበረም:: ሆኖም መንግሥት ድርጊቱን በራሱ መንገድ እንዲፈታ ቤተክርስቲያኗ ያሳየችውን ትዕግስት እንደድክመት በመቁጠር አሁንም ጥቃቱ የመቀጠል አዝማሚያ ማሳየቱ በምንም መልኩ ተቀባይነት አይኖረውም:: እናም መንግስት ሕግና ሥርዓትን ለማስከበር፣ ቤተክርስቲያኗ ከተጨማሪ ጥቃት ለመታደግና የምዕመናንን ቁጣ ለማለዘብ ይበልጥ በትኩረት ሊሰራ ይገባል፡፡
(ማጣቀሻዎች፡- ማኀበረ ቅዱሳን፣ ሐራ ተዋህዶ፣ የቅዱስ ሲኖዶስ መግለጫ…)
አዲስ ዘመን ጥቅምት 15/2012