ኢቢሲ፡- ሩሲያ ሶቹ ግብፅና ኢትዮጵያ በህዳሴው ግድብ ዙሪያ ያላቸውን ልዩነት በንግግር ለመፍታት መስማማታቸውን ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ አስታወቁ፡፡
የኢትዮጵያ ብሮድካስት ኮርፖሬሽን እንደዘገበው፤ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚነስትር ዶክተር አብይ አህመድና የግብፁ ፕሬዚዳንት አብዱል ፈታህ አልሲሲ በሩሲያ ሶቹ ከተማ ተገናኝተው ውይይት አድርገዋል፡፡
ሁለቱ መሪዎች ከሩሲያ- አፍሪካው የጋራ የኢኮኖሚ ፎረም የጎንዮሽ መድረክ ላይ ትናንት ባደረጉት ውይይት ግብፅ ወደ ቀድሞው የድርድር መድረክ እንደምትመለስ ፕሬዚዳንት አልሲሲ እንዳረጋገጡላቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ ለኢቢሲ ተናግረዋል፡፡ የአገራቱን ግንኙነት እያሻከረ ያለው የግብፅ ሚዲያዎች ዘገባ በመሆኑ ሁለቱ መሪዎች በጉዳዩ ላይም መክረውበታል፡፡
በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ላይ ከዚህ ቀደም የነበረው የሶስቱ አገራት ቴክኒካል ኮሚቴ መድረክም ተጠናክሮ እንዲቀጥልና ፖለቲካዊ መፍትሄ የሚያሻቸው ጉዳዮችን ደግሞ በፖለቲካዊ ውይይት ለመፍታት ከስምምነት መድረሳቸውን መሪዎቹ ተናግረዋል፡፡
ሁለቱ አገራት የአባይን ወንዝ በፍትሃዊነትና በአስተማማኝ ሁኔታ ለመጠቀም የአካባቢ ጥበቃ ስራዎችን አጠናክሮ ለመስራትም ከስምምነት ደርሰዋል፡፡
ግብፅ ከዚህ ቀደም በተለያዩ ደረጃዎች ኢትዮጵያና ሱዳን ያሉበትን በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ዙሪያ ሲደረግ የነበረውን ድርድር ማቋረጧን ተከትሎ ኢትዮጵያም ከንግግር ውጭ የውስጥ ጥቅሜን አሳልፌ አልሰጥም ማለቷ ይታወቃል፡፡ ግብፅም በአደራዳሪነት ሶስተኛ ወገን እንነጋገር የሚለውን ሀሳብ በኢትዮጵያም በኩል ተቀባይነት ሳያገኝ ቆይቷል፡፡
አዲሰ ዘመን ጥቅምት 14/2012
ጌትነት ምህረቴ