በታሪክ የመጀመሪያ የሆነው የሩሲያ-አፍሪካ ስብሰባ በሩሲያ የጥቁር ባህሯ ሶቺ ከተማ ትናንት ጥቅምት 12 2012 ዓ.ም እንደሚካሄድ መርሐ ግብሩ ያሰረዳል፡፡ በዚሁ ስብሰባ ላይ የሩሲያና አፍሪካ ግንኙነትን በተመለከተ በርካታ ጉዳዮች ይነሳሉ ተብሎም ይጠበቃል፡፡ ስብሰባው እንዲካሄድ ተነሳሽነቱን ያሳዩት የሩሲያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን ናቸው፡፡ ይህ የፑቲን ‹‹አፍሪካን የማገዝና ከምዕራባውያን ምዝበራ መታደግ›› የሚል ራዕይ በወቅቱ የአፍሪካ ሕብረት ፕሬዚዳንትና የግብጽ አረብ ሪፐብሊክ ፕሬዚዳንት አብደል ፈታህ አልሲሲ ተቀባይነት አግኝቷል፡፡
ዝግጅቶቹ ያተኮሩት በሩሲያ ፌዴሬሽንና በአፍሪካ አህጉር ውስጥ ባሉት አገራት መካከል ያለውን ግንኙነት ለማጎልበት ነው፡፡ አብዛኛዎቹ የአፍሪካ አገራት መሪዎች ስብሰባውን ይካፈላሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ከስብሰባው ጎን ለጎን የቢዝነስ ፎረም ተወካዮች በተለያዩ ዘርፎች ላይ በጋራ ለመሥራት ያሉትን አማራጮች ይቃኛሉ፡፡ ስብሰባው ኢንተር ፓርላሜንተሪ ሩሲያ አፍሪካ ኮንፈረንስ በሚል በመጪው ሐምሌ 3 2019 በሞስኮ የሚካሄድ ሲሆን የአፍሪካ መንግሥታት የፓርላማ አፈጉባኤዎችም ይጋበዛሉ፡፡
ሶቺ ከተማ በሩሲያው መሪ ፑቲን ተባባሪ ሊቀመንበርነት የሚመራው የሩሲያና አፍሪካን ስብሰባ ታስተናግዳለች፡፡ በሩሲያና በአፍሪካ አህጉር ግንኙነት ውስጥ ይህ የመጀመሪያው ግንኙነት ሲሆን ሁሉም የአፍሪካ መንግሥታት መሪዎችና የአህጉሩ ዋነኛ ማህበራትና ድርጅቶች መሪዎችም እንዲሳተፉ ተጋብዘዋል፡፡
በስብሰባው ላይ የተለየ ትኩረት የሚሰጠው ሩሲያ ከአፍሪካ አገራት ጋር ያላትን ግንኙነት በፖለቲካው፣ በኢኮኖሚ፣ በቴክኒካልና በባሕላዊ ትብብር ለማስፋትና ለማጠናከር ነው፡፡ ስብሰባው እጅግ በጣም ሰፊ የሆኑ ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮችንም ለመወያየት ዕቅድ ይዟል፡፡ ከዕቅዶቹ ውስጥ ለአዳዲስ አደጋዎችና ፈተናዎች የሚሰጠው የጋራ ምላሽና የአህጉሩን ሰላምና መረጋጋት ማጎልበት (ማጠናከር) የሚሉ ይገኙበታል፡፡ በስብሰባው ማጠቃለያ ተሳታፊዎቹ በሩሲያና አፍሪካ ግንኙነት ዋነኛና ቁልፍ በሆኑት ጉዳዮች ዙሪያ የጋራ ፖለቲካዊ መግለጫ ያወጣሉ ፡፡፡
ሁለት ቀናት በሚወስደው ስብሰባ የሩሲያና የግብጽ መሪዎች፤ የሩሲያና የአፍሪካ ባለሥልጣናት እንዲሁም ዋነኛ የንግድ ተወካዮች የሚሳተፉበትን ኢኮኖሚ ፎረም ይከፍታሉ፡፡ ይህንን ከፍተኛ ፎረም ተከትሎ በንግድ በኢኮኖሚና በኢንቨስትምንት ዙሪያ ስምምነት ይፈረማል፡፡
ከ47 አገራት የተውጣጡ መሪዎች በቀጣዩ ሳምንት በሶቺ ከተማ የሚካሄደውን የሩሲያና የአፍሪካ ስብሰባ ይካፈላሉ ሲል የክሬምሊን ቃል አቀባይ የሆነው ዲሚትሪ ፔስኮቭ ለሪፖሮች መግለፁን ታስን ( የሩሲያውን የዜና ወኪል ) ጠቅሶ ኤፒኤ የዜና ወኪል ዘግቦአል፡፡
ዲሚትሪቭ ፔስኮቭ እስከ አሁን 47 የአፍሪካ መሪዎች በሶቺው ስብሰባ የሚገኙ መሆናቸውን አረጋግጠዋል ብሎአል፡፡ አንዳንድ አገራት ለስብሰባው ተወካዮቻቸውን ይልካሉ፤ 8 ግዙፍ የአፍሪካ ማህበራትና ድርጅቶችም ይሳተፋሉ ፡፡
እንደዘገባው ፕሬዚዳንት ፑቲን ከአፍሪካ መሪዎች ጋር ስብሰባ ካደረጉ ከቀናት በኋላ ሩሲያ በአፍሪካ ተጽዕኖ እንዲኖራት ሞስኮ ‹‹ከመዝባሪው የምዕራቡ ዓለም በአፍሪካ ላይ በሚደርሰው ጫናና በደል የተነሳ ለአፍሪካ አገራት ከፖለቲካዊ ሁኔታዎች ውጭ ዕርዳታ ትሰጣለች›› ማለታቸውን ከሞስኮ ሮይተርስ የዜና ወኪል ዘግቦአል፡፡ በአፍሪካ ላይ ተጽዕኖ ለማሳደርና የንግድ ግንኙነት ለመፍጠር ከፍተኛ ፍላጎት አለ ብሎአል ሮይተርስ፡፡
በዚህ ረገድ ብላድሚር ፑቲን በጣም ግልጽ የሆነ መልዕክትና ማስጠንቀቂያ አስተላልፈዋል፡፡ ይህም በአፍሪካ ላይ ከፍተኛ ውድድርና ሽሚያ ያለ መሆኑን የሚገልጽ ነው፡፡ ፕሬዚዳንት ፑቲን ‹‹አሁን ምዕራባውያን አገራት ምን ያህል ነፃ የሆኑ የአፍሪካ አገራትን እንደሚገፉ፤ እንደሚያስፈራሩ፤ ስም የማጥፋት ዘመቻ እንደሚያካሄዱ እያየን ነው›› ሲሉ ከታስ የዜና ወኪል ጋር ባደረጉት ቃለምልልስ ገልፀዋል፡፡ ፑቲን የተወሰኑ አገራትን ስም ባይጠቅሱም በአህጉሪቷ የቅኝ ገዢ ኃይል አይነት እየሆኑ ያሉትን ምዕራባውያን አገራት ማለታቸው እንደሆነ ግልጽ ነው፡፡
እነዚህን ዘዴዎች በመጠቀም ቀደም ሲል ያጡትን ተጽዕኖ ፈጣሪነትና ጫና በቀድሞ ቅኝ ግዛቶቻቸው ላይ ለመጫን በአዲስ መልክ ለመመለስ “እጅግ ከፍተኛ ትርፍ ለማግኘትና የአህጉሪቱን የተፈጥሮ ሀብት ለመመዝበር ተዘጋጅተዋል›› ሲሉ ፑቲን ይጠቅሳሉ፡፡ ሞስኮ ከአፍሪካ ጋር ያላት ግንኙነት እያደገ መሆኑን ለዚህም የወታደራዊና ቴክኒካዊ ሕብረት ስምምነትን በተመለከተ ሩሲያ ከ30 በላይ ለሆኑ የአፍሪካ አገራት የጦር መሣሪያ እንደምታቀርብ ገልፀዋል፡፡
አንቶን ኮብያኮቭ የሩስያው ፕሬዚዳንት አማካሪ ሲሆኑ ፕሮፌሰር ቤኔዲክት ኦራማህ ደግሞ የአፍሪካ ኤክስፖርት ኤምፖርት ባንክ (አፍሬክሲም ባንክ) የዳይሬክተሮች ቦርድ ሊቀመንበር ሲሆኑ በሞስኮ የንግድ ስብሰባ አድርገዋል፡፡
ስብሰባው በዋነኛነት ያተኮረው በቀጣይ በሚካሄደው በአፍሬክሲም ባንክ ባለድርሻዎች ዓመታዊ ስብሰባ ላይ ሲሆን ሩሲያ ውስጥ እ.ኤ.አ በ2019 ይካሄዳል፡፡ በሌሎችም የሩሲያ አፍሪካ ግንኙነቶች ላይ ተወያይተዋል፡፡
ፑቲን ከታስ የዜና ወኪል ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ሩሲያ ኢትዮጵያ ያለባትን ዕዳ በተመለከተ በቅርቡ እልባት እንደምትሰጥ ገልፀዋል፡፡ ከሶቭየት ሕብረት በኋላ ባለው ጊዜ ሩሲያ አፍሪካ አገራት ያለባቸውን 20 ቢሊዮን ዶላር ዕዳ ሰርዛለች፡፡ እጅግ በጣም የሚደገፍ እርምጃ ነው፡፡ ስለዚህ አሁን ለሁላችንም የሚጠቅመው ግንኙነታችንን ‹ሀ› ብለን ከታች መጀመር ነው ብለዋል ፑቲን፡፡ በዚህም መልኩ ኢትዮጵያ ከሩሲያ ላይ የተበደረችውና ያለባት ቀሪ የ163.6 ሚሊዮን ዶላር ዕዳ እንደሚሰረዝ ይጠበቃል፡፡
አዲስ ዘመን ጥቅምት 13/2012
ወንድወሰን መኮንን