የዛሬዋ ዓለማችን እጅግ ተለዋዋጭ ከመሆኗ ጋር ተያይዞ በየሽርፍራፊ ሰከንዱ አዳዲስ ለውጦች ይመዘገባሉ።ጠዋት የነበረው ከሰዓት፣ ቀን የነበረው ማታ ላይ ይቀየራል። የለውጡ ሂደት እጅግ ፈጣን ከመሆኑ የተነሳ ለመገንዘብ እንኳ አዳጋች መሆኑ ለማንም ግልጽ ነው።
ከዚህ የዓለም ተለዋዋጭ ሁኔታ ጋር አብሮ ለመጓዝና በዚህ ሂደት አሸናፊ ሆኖ ለመውጣት ተቀያያሪውን የዓለም ሁኔታ በንቃት መከታተል፣ መረዳትና ሁነኛ የመፍትሔ አቅጣጫ ቀይሶ መስራት እንደ ግለሰብ፣ እንደ ዜጋና እንደ ሀገር እጅግ አስፈላጊ ጉዳይ ነው። በዚህ መልኩ ካልተንቀሳቀሱ ውጤቱ ኋላቀርነትና ተሸናፊነት መሆኑም አያጠራጥርም።
ይኼ ጉዳይ በተለይም ሀገርኛና ህዝብን ለሚመሩ ፓርቲዎች እጅግ ወሳኝ ሆኖ ይገኛል። ምክንያቱም የፖለቲካ ፓርቲዎች የዓለምን ተቀያያሪ ሁኔታ በፍጥነት ተረድተው ለዚሁ የሚመጥን ፖሊሲ፣ ስትራቴጂና ፕሮግራም ካልነደፉ ውጤቱ ሀገርንና ህዝብን ክፉኛ ይጎዳል። በሌላ አነጋገር “በቆሞ ቀር” ፓርቲዎች የሚመራ ህዝብና አገር መጨረሻው ቆሞ ቀርነት ይሆናል ማለት ነው።
አሁን አሁን አንዳንዶቹ ቀድሞ የተናገሩትን እየረሱ አሊያም ቃል አባይ እየሆኑ እንጂ፤ አገራችንን እየመራ ያለው ገዥ ፓርቲ ቆሞ ቀርነት ለሀገራችን ትልቅ አደጋ መሆኑን ሲያስገነዝብና የዓለምን ተቀያያሪ ሁኔታ በመረዳት የሀገራችንን ተጨባጭ ሁኔታ እያገናዘቡ ተራማጅ ፖሊሲዎችንና ስትራቴጂዎችን መንደፍ ይገባል ሲል ነበር።
እውነት ነው! ዛሬ ያለው የኢትዮጵያ ህዝብ በ1983 ወይም በ1997 እና በ2000 ዓ.ም ከነበረው በብዙ መልኩ ይለያል። አስተሳሰቡ፣ ፍላጎቱና እውቀቱ ፍጹም በሚባል ደረጃ የተቀየረ ህዝብ ነው ያለው። ስለሆነም ለ1983 ወይም ለ1997 ነባራዊ ሁኔታ በተቀረጸ ፖሊሲና ስትራቴጂ አሁን ያለውን ነባራዊ ሁኔታ ማስተዳደር፤ የህዝብ ፍላጎትንም ፈጽሞ ማሟላት አይቻልም። ስለሆነም ለዘመኑ ትውልድ የሚመጥን አማራጭ ፖሊሲና ስትራቴጂ መንደፍ የውዴታ ሳይሆን የግዴታ ጉዳይ ነው።
ከዚህ አንጻር የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ (ዶ/ር) ያስመረቁትና አማራጭ ሃሳቦችን የያዘው ‹መደመር› መጽሐፍም ሆነ ኢህአዴግን ለማዋሃድ የቀረበው ጥናት ከቆሞ ቀርነት የመውጣትና የተራማጅነት መገለጫ ነው ማለት ይቻላል። በተለይም ደግሞ ለሀገራችን ችግር መፍትሔው ሀገርኛ መሆን አለበት ተብሎ መነሻ መደረጉ ይበል የሚያሰኝ ነው።
የችግሩን መንስኤ ማወቅ ከመፍትሄው ግማሽ ያህሉን እንደመጓዝ ይቆጠራል እንደሚባለው፤ የሀገራችን ወቅታዊ ችግር ምንድነው? ለዚህስ ምን አስተዋጽኦ ብናበረክት የተሻለ ነገር ይፈጠራል? የሚል እሳቤ መያዙ በራሱ እጅግ የሚያስወድስ ነው። ከዚህ አንጻር ጠቅላይ ሚኒስትሩ አገርን እንደሚያስተዳድር አንድ መሪ የድርሻቸውን ተወጥተዋልና ምስጋና ይገባቸዋል። ያነሱትን ሃሳብ ማየት፣ ለአዎንታዊ አስተሳሰብ እውቅና መስጠት፣ ለጉድለቱ አማራጭ ሃሳብ መጨመር፣ ከዚህ የተሻለ ሃሳብ አለኝ የሚል ደግሞ ሃሳቡን ይዞ መቅረብ ይኖርበታል።
ከዚህ ውጪ ቆሞ ቀር በሆነ አስተሳሰብ ውስጥ ሆኖ ለዚህ ዘመን የማይመጥን ያረጀ አማራጭን ይዞ እየቆዘሙ አዲስ ሃሳብና አማራጭ ይዞ የመጣን አካል ለመተቸት መሮጥ ከትዝብት ውጪ የሚፈይደው ምንም ነገር አይኖርም። ይልቁን ለመተቸትና ለማጣጣል የሚባክነውን ጊዜና ጉልበት ለአማራጭ ሃሳብ ማቅረቢያነት ማዋል ለራስም ለሀገርም ትርፉ ብዙ ነው።
ስለሆነም አማራጭ ሃሳቦች ከየትም አቅጣጫ ይብዙ፤ ይባዙ። አዲስ አማራጭ ይዞ የመጣን ወገን መተቸትና ማጣጣል አላዋቂነት ነው። በትችትና በአሉባልታ የሚባክነው ወርቅ ጊዜያችሁን የምታባክኑ ኃይሎችም፤ውሃ ከማይቋጥር ተግባራችሁ ተቆጥባችሁ የተሻለና አሸናፊ አማራጭ ሃሳብ ይዛችሁ የእውነተኛና የመጨረሻ ዳኛ ከሆነው ህዝብ ፊት ቅረቡ!
አዲስ ዘመን ጥቅምት 12/2012