የማዕበል ወፎችን የቀሰቀሰው ሞገደኛ ራሱ የማዕበል ወፍ ነበር። አንዱ ተነስቶ ሌሎቹን ሁሉ ከፍ ባደረገበት መጽሐፍ ውስጥ፤ ጸሐፊው ከመሃከል አንደኛው መሆኑን አሳይቶበታል። እድሜ ልኩን የብዕር በትሩን ይዞ በምድረበዳና በለምለም መስክ ላይ ሲያዘግም የቆየው ደራሲና ሃያሲ ዓለማየሁ ገላጋይ ከሰሞኑ ለረዥም ጊዜያት ከገበያ ላይ ርቀው የነበሩ ሦስት የመጽሐፍት እርግቦቹን በድጋሚ አሳትሞ ከመጽሐፍቱ ፊላ በላይ ለቋቸዋል።
ከእነዚሁ ሦስቱ ጋር በአራተኛነት ለዳግም ሕትመት የበቃች ሌላ አንድ ነጭና ውብ እርግብም አለችበት። ለአሁኑ ስንቅ የሆነችውን “ማዕበል ጠሪ ወፍ”ን ጨምሮ “ቤባኒያ”፣ “በፍቅር ስም” እና “ወሪሳ” የተሰኙት መጽሐፍቶቹ በአንድ ጀንበር እንደ አዲስ ተወልደው ብቅ ብለዋል። ሦስቱ በግብዣ ይያዙና ከ“ማዕበል ጠሪ ወፍ” ጋር የቻልነውን ያህል አብረን ለመብረር ድግ! ድግ! ብንል ይሻላል።
ብዕሩ ከቶ የማይቋረጥ፣ ብራናው የማይከደን ምተሀተኛው ደራሲ ዓለማየሁ ገላጋይ “ማዕበል ጠሪ ወፍ” ሲል ይህን መጽሐፍ ጽፏል። ደራሲው ሁሌም በአንድ ዓይነት መንገድና እይታ ውስጥ መቆየት የማያሰለቸው ስለመሆኑ ሥራዎቹ ይናገራሉ። ግራ ቀኝም፣ ኋላ ፊትም እያለ አዳዲስ ሥነ ጽሑፋዊ ፍኖቶችን በመቅደድ ከማስደመም ስለማይመለስ ከፊቱ ቆመን በገፍ አድናቆትና ክብር እንድንሰጠው ግድ ይለናል።
በእርሱ የድርሰት ሥራዎች ውስጥ ከዚህ ቀደም በርከት ያሉትን እንግዳ ብዕሮችን ተመልክተናል። አሁን 18ኛው መጽሐፍ ላይ ደርሷል። 18ኛው የብዕር ልጁም ማዕበል ጠሪ ወፍ ነው። እንዲሁ በጥቃቅኑና በስሱ ካልሆነ በስተቀር በመጽሐፍ ደረጃ ማንም ያልደፈረውን ደፍሮና ተጠቦ በአዲስ ጭብጥና አቀራረብ አሳምሮ ጽፎታል።
በመጀመሪያ ዓለማየሁ ጋር ሃሳብ ነበር። ሃሳቡ ውስጥ ብዙ ትዝታ ነበር። በትዝታዎቹ ውስጥ ደግሞ ቁጭት፣ ብዙ መብከንከንና የለውጥ ድጓ ነበር። ባለፈው ዘመን ውስጥ በሀገራችን አንቱ ከተባሉ ደራሲያንና የሥነ ጽሑፍ ሰዎች ጋር ሁሉ ለማለት በሚቻል ደረጃ አብሯቸው አሳልፏል። በአንድ ማዕድ ላይ ተቋድሰዋል። በአንድ ጠረጴዛ ዙሪያ ተቀምጠው ስለ ሀገራችን ሥነ ጽሑፍ እያወጉ ተጨዋውተዋል። ወግ ቢጤ ይዘው፣ ቀልዱንም ጣል አድርገዋል። እናም ያ ዘመንና የዘመኑ ፈርጥ ጸሐፊያን ልቡ ውስጥ አሉ።
አሁንም በዚህኛው ዘመን ካሉት ጋርም በወዳጅነትም በሙያዊ ደቀመዝሙርነትም አብሯቸው አለ። ከእነዚህ ሁሉ ጋር ያሳለፈው ሕይወትና ሥራዎቻቸው ማዕበል ጠሪ ወፍን እንዲከትብ አድርጎታል። ሁሉንም በወግ በወጉ አሰናድቶ ለመጽሐፍነት ካበቃው በኋላ፤ ለመጀመሪያ ጊዜ ያስነበበው ከዓመት በፊት ነበር። ይሁን እንጂ መጽሐፉ ግን ቀድሞውን ለዓመታት በልቡ አዝሎት የኖረው ነው። ባያስነብበውም እርሱ ግን በውስጡ ደጋግሞ ሲያነበው ቆይቷል። ከዛሬ 20 ዓመት በፊት ሊጽፈው ጀምሮ መልሶ ብዕሩን ከድኖ አስቀመጠው። ተከድኖ በልብ የቆየ ነገር ሙክክ ብሎ መብሰሉ አይቀርምና በርግጥም በስሎ ነበር የወጣው።
መጽሐፉ ከውስጥም ከውጭም በብዙ አዳዲስ ነገሮች የተከበበ ነው። የሄደበትና በረዥሙ በተጓዘበት መንገድ ብቻም ሳይሆን አቀባበሉም የሚለይ ነበር። ለመጀመሪያ ጊዜ በመጋቢት 28/2016 ዓ.ም ተመርቆ በዚያው ዕለት ከአንባቢያኑ ጋር ተገናኘ። በተመረቀበት ዕለት ለንባብ የበቃ የመጀመሪያው መጽሐፍም ጭምር ያደርገዋል።
ከዚህም ከዚያም የሚያውቃቸው በርካታ ነገሮች ቢኖሩም በቂና የልብ የሚያደርስ መስሎ አልታየውምና አስቀድሞ ጥቂት ምርምር አዘል ጥናቶች አድርጎበታል። ከዚህ ስር የወጣው መጽሐፉ አሁንም ለሌላ የምርምር ፈለግ ዱካውን ያስቀመጠና መንገዱን አመልካች ሆኖ የቆመ ሥራ ነው። በመጽሐፉ ውስጥ የተካተቱት ሃሳቦች “ፍየል ወዲህ ቅዝምዝም ወዲያ” መስለው ብትንትን ያሉና ከአንዱ ወደ አንዱ የሚዘሉ በመሆናቸው፤ ኧረ እንዴትስ አድርጎ ለመጽሐፍነት አበቃው? የሚያስብል ነው። እነዚህን በጊዜና ቦታ፣ በታሪክና ባለታሪክ ፍርስርስ ብለው በየፊናው የተበተኑትን ጉዳዮች ገጣጥሞ ወደ አንድ ሙሉዕ አካልነት ለማምጣት የተለየ ችሎታና ተሰጥኦ የሚጠይቅ ነበርና በሚገባ አሳክቶበታል። የማዕበል ጠሪ ፍኖት ቀያሽና ዘዋሪ ብዕሩን በሁለት አቅጣጫዎች ላይ አሳርፎታል። በሁለት ጎራዎች ለይቶ በምዕራፎች ከፋፍሎታል።
ያስቀመጣቸው ተደራሲያን እጅግ በርካታና እጅግ ብዙ ጉዳዮቻቸውን እያነሳ የሚዳስስላቸው ናቸው። የታላላቅ ደራሲያኑን ሕይወት ደርሶ ሳይሆን አጠገባቸው ሆኖ ከተመለከታቸውና ከተጋራቸው ነገሮች ዳራ ላይ ተንጠላጥሎ እናገኘዋለን። በፈጠራና በገጸ ባህሪያት የተጎነጎነ ልቦለድ ባይሆንም የዚያኑ ያህል ስሜትን ቁጥርጥር አድርጎ መያዝ የሚችል አድርጎ ሰርቶታል።
በእነዚያ ያለፉ 20 ዓመታት ውስጥ ከሚያየውና ከሆኑ ነገሮች ውስጥ ቆንጠር አድርጎ ሲጽፋቸው የነበሩትን ነገሮች አሰናስኖ ዛሬ “ማዕበል ጠሪ ወፍ” ሲል ለማወቅ የምንፈልጋቸውንና የሚያስፈልገንን አስነብቦናል። አለማየሁ ገላጋይ ለዚህ መጽሐፍ መሠረትና ምሰሶ ወጋግራ የሆኑት ማዕበል ጠሪ ወፎች በዓይነ ህሊናው ውስጥ ነበሩ። ከሥነ ጽሑፍ እስከ ደራሲያኑ ድረስ ብዕሩን ሲያስረዝም እያንዳንዱ የሚያነሳቸው ሰዎችና ልዩ ልዩ ሥራዎች ማዕበል ጠሪ ወፍ ተደረግው ተሰይመዋል።
በማዕበል የተከበበ ደራሲ፣ በማዕበል የተከደኑ የሥነ ጽሑፍ ሥራዎች ከዚያ ዓይነ ህሊናው ውስጥ ቁልጭ ብለው ይታዩታል። ሥራዎቻቸውን ምናልባትም አንዳንዶቻችን እናስታውስና እናነሳቸው ይሆናል። ነገር ግን በእሳት ነበልባል ውስጥ እየነደዱ፣ እረመጡ እየፈጃቸውም በእሳት በጋመው የባህር ማዕበል ላይ ሆነው ሥራውን ያበረከቱልንን ጀግኖች ከስማቸው በዘለለ ማናቸውንም ዘንግተነዋል። ሻማ እየቀለጠ ስለሰጠን ብርሃን እንጂ ስለሻማው ከናካቴው ትዝም አላለን።
ማዕበል ጠሪዎቹ እነርሱ ናቸው። መጽሐፉ ፈትፍቶ እያነሳ የሚያጎርሰን አንድም ስለ እነርሱ ነው። ምናልባት ስለ ስብሐት ገ/እግዚአብሔር አውቃለሁ እንል ይሆናል፣ ጸጋዬ ገ/መድህንን አልረሳሁትም ብለን እናስብ፣ በዓሉ ግርማንም እንጠቅስ ይሆናል…ግን ከማዕበሉ ወዲያ አለማወቃችንን እናውቀው ይሆናል።
በሁለት ክፍሎች የተሰናዳው ማዕበል ጠሪ ወፍ፤ በመጀመሪያ ክፍሉ ውስጥ ሥነ ጽሑፋዊ ዳሰሳና ጉብኝቶች ናቸው። የግዕዝ ቋንቋን ጫፍ ይዞ እስከ አማርኛው ሥነ ጽሑፍ ድረስ በምልክታ ይጓዛል። በሀገራችን የድርሰት ሥራዎች ብቅ ማለት ከጀመሩበት ጊዜ አንስቶ የተከሰቱ ጣጣና የተንሸዋረሩ እይታዎች በሥነ ጽሑፍ ውስጥ የከሰቱትን አንዳንድ ጉዳዮችንም ያነሳል።
በአሮጌውና በአዲሱ ትውልድ መካከል የተፈጠረው ጭንጋፍና ግርዶሽ ምን መልክ እንዳሳየ ያስመለክተናል። በሁለቱ ዘመን ደራሲያን ሰንሰለታማ ተራራዎች ላይ እየዳኸና እየቧጠጠ ውስጥ ውስጡን ከጥያቄ ጋር ሲሄድ እንመለከታለን።
ጸሐፊው ስለ ደራሲያኑና ሥራዎቻቸውን ብቻ ሳይሆን ሲጽፉበት ስለነበረው ቋንቋና ስለ ቋንቋው ሁዳዴ እያበጠረ ያስቀምጠዋል። በጥንታዊቷ ኢትዮጵያ ውስጥ እልፍ የብራና ላይ ጽሑፎች የተከተቡት በግእዝ ቋንቋ ነው። ለዛሬው የአማርኛ ሥነ ጽሑፍ መሠረትና መነሻውም ይኸው የግእዝ ቋንቋ ነው። ከኛ አልፎም ለብዙ የውጭ ሀገር ጸሐፊያን ማማውን መወጣጫ ሆኖላቸዋል።
ዓለማየሁ በማዕበል ጠሪ ወፍ ውስጥ በሌላኛው ምዕራፉ የሚጀምረው ከዚሁ ሃሳብ ላይ ነው። ግእዝን ከአማርኛው ጋር መሳ ለመሳ አቁሞ ያላወቅናቸውን አሊያም ልብ ያላልናቸውን ነገሮች ከማወቅም እንድንመሰጥባቸው አድርጎ ይነግረናል። በአንድ የሥነ ጽሑፍ ሥራ ውስጥ ደራሲው እስከቻለበት ድረስ ውብ በሆነ መልኩ ከመደበኛው የቋንቋው አጠቃቀም የማፈንገጥ መብትና ነፃነት አለው። በየዘመናቱ ጉምቱ ብዕረኛ የነበሩትን የአብዛኛዎቻቸውን ሥራ ከተመለከትን በዚህ መብትና ነፃነት ውስጥ እየተንሳፈፉ አዳዲስ ነገሮችን ለመፍጠር የቻሉ ናቸው። በራሳቸው የአጻጻፍና የቋንቋ ፍኖት ውስጥ ፈሰው እናገኛቸዋለን። ታዲያ ከምን ተነስተው ወዴትና ምን አዳዲስ ነገሮችን ለመፍጠር እንደቻሉ እያነሳሳ ይበልጥ ሥራዎቻቸውን እንድንወድና እንድናደንቃቸው ያደርገናል።
በ250 ገጾች የተዋቀረው መጽሐፍ ሁለተኛው ክፍል ማዕበል ጠሪዎቹን ይዞ ይነሳል። በኢትዮጵያ የሥነ ጽሑፍ ታሪክ ውስጥ እንደ ፀሐይ ሲያበሩ ከፍ ብለው በዘመናት ሁሉ ከወዲያኛው እስከዚህኛው ትውልድ የነገሱትን ደራሲያንን ሥራዎች መራርጦ ያነሳል። አብዛኛዎቻችን ሠሪውን ተመልክተን ስለሥራው የምናወራ ነን። ያ የእኛ እውነታ ቢመስልም፤ እውነታው ግን ሠሪውን መግለጥ ያለበት ሥራው ነው። ሠሪውን እየተመለከትን ስለ ሥራው ባወራን ቁጥር ሁሉ አንዲቷን ጫፍ ብቻ ይዘን ከማይወጡበት የስህተት መቀመቅ እንወርዳለን።
ዓለማየሁ ገላጋይም ይህን አሰቦ ይመስላል ከጸሐፊያኑ አስቀድሞ ሥራዎቻቸውን በክፍል አንድ ማስነበቡ። ቀጥሎም በሁለተኛው ክፍል ራሳቸውን ይዞ መጣ። ከሥራዎቻቸውና ካላቸው የታላቅነት ማዕበል በመነሳት እንዴት ያሉ ድንቅ ወፎች መሆናቸውን ያሳየናል። ሥራዎቻቸውን እያጣቀሰ አቁሞ ምስክሮች ያደርጋቸዋል። በዚህ ምልከታው ውስጥ ቀደም ሲል በሥራ ያየናቸው ሰባቱ ጉምቱ ደራሲያን ተካተውበታል።
ከግጥም ሥራዎቹ እስከ ቲያትር መድረኮች ድረስ የነገሰው ሎሬት ጸጋዬ ገ/መድህን አንደኛው ነው። እንደ ሻማ ቀልጦ፣ እንደ ጧፍ ነዶ ከሞት በላይ ስምና ሥራውን ያኖረው በዓሉ ግርማ በዓለማየሁ ገላጋይ ብዕር ውስጥ ምስሉ ተስሏል። ለሥነ ጽሑፍ እንደኖረላት ሳይኖር የሄደው ደበበ ሰይፉ ከማዕበሉ ላይ ቆሞ ታንኳዋን በግጥሞቹ ሲጨብጥ እንመለከታለን። ከሰለሞን ደሬሳ የብዕር ጫፍ ላይ አዲስ መልክና ቀለም ያለው መስመር ተሰምሮ ይታያል።
በሀገራችን የልቦለድ ታሪክ ውስጥ ምሁራኑን ሳይቀር በጎራ ለይቶ እስከማሟገት ያደረሰውን “አደፍርስ”ን የጻፈው ዳኛቸው ወርቁ ሌላኛው ማዕበል ጠሪ ወፍ ነው። አፈወርቅ ገ/ኢየሱስም በሌላ አቅጣጫ ከተፍ ይላል። ስሎ በስዕሉ፣ ጽፎ በግጥሙ ዛሬም ድረስ አፍ የሚያስከፍተን ገ/ክርስቶስ ደስታን በዚህ መጽሐፍ ውስጥ እጅ እንነሳዋለን። ሰባቱ የማዕበል ወፎች ከፍ ብለው ሲበሩ እየተመለከትን ፈገግ እንላለን። ደግሞ ክንፋቸው እየተሰበረ መሃል ላይ ለመውደቅ ቁልቁል ሲምዘገዘጉ እንደ አዲስ እንደነግጣለን። ከባህሩ ማዕበልና ሞት ጋር ፊት ለፊት እየተያዩ ለመዳን ሲውተረተሩ እናዝናለን። የሆነው ሁሉ ሆኗልና መጥፎውንም ጥሩውንም ትዝታ ከእውነታው ጋር እንቀበለዋን። ዓለማየሁ ከልቡ ጽፎታል። ከልባችን እናነበዋለን።
ጸሐፊው ግን አሁንም ይቀጥላል። ያልታዩ ምስሎች፣ ያልተነበቡ ገጾችን ይገልጥልናል። ምን ትልቅ ብንሆን፣ ምን ተራራ ንደን ባቢሎን በጥበብ ብንገነባ ማናችንም ፍጹማን አይደለንም። የማይሳሳቱም የማይሰሩ ብቻ ናቸው። እስከሰራን ድረስ አንዲት ጉድለት፣ ጥቁር ነጥብ አይታጣም። ምን ቢጠቁር ግን የሠራነውን አያደበዝዘውም። ከሳትነው የሰጠነው ይበልጣል። ያቺን ጥቁር ነጥብ አግዝፈን እንደ ተራራ ከተመለከትናት አልፈን መቼም አንሻገረውም። በይሉኝታና ቸልታ ለማለፍ ስንሞክርም የዋዛ አይደለምና አደናቅፎ ይጥለናል። ሥራውን በቀኝ ይዘን፣ በግራ ነጥቧን ነቅሰን ለማረም ስንወድ ግን ጉዟችን ሁሉ የሰመረ ይሆናል። በውዳሴና እልልታ ብቻ ገነት አይገባም። ጉምቱዎቹን ከፍ አድርጎ የሰቀላቸው ዓለማየሁ ገላጋይ በከፍታው ውስጥ ሊያስመለክተን የወደደው ነገር ነበረው።
በውዳሴ ታላቅነታቸውን ጽፎ ጽፎ ሲያበቃ ነጥቧን ነካ አደረጋት። የያዘው አንድም የሥነ ጽሑፍን መንገድ ጥርጊያ ነውና እንደምን ለማለፍ ይቻለዋል? በሙግት ራሱን አሞግቶ ቢኖሩ ኖሮ አሜን ብለው ሊቀበሉት የሚችሉት ትችት ውስጥ ይሸጎጥባቸዋል። ያልደፈርነውን አጥር ዘሎ ያሳየናል። ይህን ሲያደርግ “ሙት አይወቀስም” ስለሚባል ብቻ ሳይሆን በነገሮቹ ውስጥ የሚያነሳቸው የእውነትም ያለ ወቀሳ ነው። አውቀንም ሆነ ሳናውቅ አለባብሰን ያለፍነውን በማረም መንፈስ ውስጥ ሆኖ ነው። ሥነ ጽሑፋችን ከረዥም እንቅልፉ ውስጥ እንዲነሳ ከወደድን ይህን ማድረግ ግድ ነው። ጥበብ ያለ ሂስ የምትገነባው ኃያል ቅጥር አይኖራትም። ያለ ቅን ትችት ሠርታ የምታቆመው ቤት የላትም። ከመሰለንም የገባን ዕለት ተንዶ በላያችን የፍርስራሽ ክምር ይሆናል።
ዓለማየሁ ይህን ለመጻፍ ስለምን ወደደ? ከማንበባችን መልስ መጽሐፉን ከድነን ይህን ጥያቄ ለራሳችን መጠየቅ ይኖርብናል። ጸሐፊው ለመጻፍ የነሸጠውን ጉዳይ እንድናነበው ካስነሸጠን ነገር ውስጥ ፈልገን ማግኘት ይኖርብናል። የጻፈው ስለ ደራሲያኑ፣ ያስነበበን ስለ ሥራዎቻቸው ቢሆንም፤ ውስጡ ግን እነርሱ ብቻቸውን አይደሉም። እኛ አንባቢዎችና ስለ ሥነ ጽሑፍ ያገባኛል የምንል ሁሉ አለንበት። የቱ ጋር ነኝ? ብሎ መጠየቅና መምረጥ ግን የኛ ፋንታ ነው። ሁላችንም ለማወቅ የሚገባን አንድ ነገር ቢኖር ግን፤ “ማዕበል ጠሪ ወፍ” መጽሐፍ ስለሆነ ብቻ አንስተን የምናነበውና ከደነን የምናስቀምጠው አለመሆኑን ነው። እንደ ልቦለድ ተመስጠንበት ስናበቃ “ይገርማል!” ብለን ብቻ አናስቀምጠውም። እንደ አንዳንድ ኢ-ልቦለዶችም ዕውቀት ሸምተንበት እንደምንወረውረው ፌስታል አይደለም። ይልቅስ በክብር ከግርግዳው ላይ የምንሰቅለው ዘንቢል እንጂ። እንደገና ነገም የምንፈልገው ንብረታችን ነው። ስለምንወዳቸው ደራሲያንና ሥራዎቻቸው ማወቅ ብቻ በቂ አይደለምና ተዝናንተንም ሆነ ሸምተን ስናበቃ ብዙ ጥያቄ፣ ብዙ ምላሽ ፍለጋ መውጣት ግድ ይለናል። ወርቁን እስከምናገኘው ድረስ ሳንታክት መቆፈር ይኖርብናል።
የሀገራችን ሥነ ጽሑፍ እንደ ግመል ሽንት ስለምን ወደኋላ አፈገፈገ? ለምንል ምላሹ ከማዕበል ጠሪ ወፍ ላይ ተጀምሯል። ጸሐፊው ስለ ሀገራችን የሥነ ጽሑፍ እድገትና መቀጨጭ ግድ ብሎት ማሰላሰል የጀመረው በዚህ መጽሐፍ ውስጥ አይደለም። ከወዳጆቹም ጋር ይሁን በየሚዲያው ስለዚህ ጉዳይ ሳያነሳ አያልፈውም። ማሰስና መጠየቁም አይሰለቸውም። ስለ ሥነ ጽሑፍ እድገት በመጨነቅ እንቅልፍ ከማይወስዳቸው ደራሲያን መሀከል አንደኛው ነው። እናም በውል የሚያውቃቸውን 20 ዓመታትን በልቡ አዝሎ መኖሩም ለዚሁ ነው። ለመጻፍ ሲል ብቻ አልጻፈውምና ለማንበብ ብቻ ስንል አናነበውም። ስናነበው እንጠይቃለን። እንፈትሻለን። ዘመንን ከዘመን፣ ትውልድን ከትውልድ ጋር እያነጻጸርን “የቱ ጋር ነው የተሰበርነው?” ብለን እንጠይቃለን። አንወቅስም፤ ግን እየተቸን ስብራቱን እንጠግናለን። ወደቀልባችን ተመልሰን ራሳችንን እንጠይቃለን። የእውነትን ዳና ተከትለን እንወጣለን። መዓዛዋን እያሸተትን እንሄዳለን። እየሄድን ከሥነ ጽሑፍ ማማ ላይ እንደርሳለን። ደርሰን ከከፍታው ሰገነት ላይ እንቆማለን። ቆመንም፤ ያለፍነውን ትናንት፣ የቆምንበትን ዛሬ እየተመለከትን “አበጀን!” እንላለን። ያን ጊዜ፤ ሥነ ጽሑፋችን ዓለምን ሁሉ አሸንፋ በጥበብ ኒሻን ትንቆጠቆጣለች።
ሙሉጌታ ብርሃኑ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 7/2017 ዓ.ም