ደቡብ ኮሪያን በድሮን ድንበር ጥሳ ትንኮሳ ፈጽማለች የሚል ክስ ያቀረቡት የሰሜን ኮሪያ መገናኛ ብዙኃን 1 ነጥብ 4 ሚሊዮን ገደማ ወጣት ሰዎች ጦሩን ለመቀላቀል መመዝገባቸውን በዛሬው እለት ገልጸዋል።
ጦሩን ለመቀላቀል ማመልከቻ ያስገቡት ተማሪዎችን እና የወጣቶች ማኅበር አመራሮችን ጨምሮ ወጣቶች ጠላትን ለመደምስስ በሚደረገው “የተቀደሰ ውጊያ” ለመሳተፍ ቁርጠኛ መሆናቸውን ሮይተርስ ኬሲኤንኤን ጠቅሶ ዘግቧል።
ኬሲኤንኤ ይፋ ባልሆነ ቦታ ወጣቶች ማመልከቻቸውን ሲፈርሙ የሚያሳዩ ፎቶዎችን ለቋል። ሰሜን ኮሪያ በርካታ ወጣቶች እንዳሏት ይፋ ያደረገችው በኮሪያ ባሕረሰላጤ ያለው ውጥረት ከፍተኛ ደረጃ ላይ ከደረሰ ከሁለት ቀናት በኋላ ነው።
ሰሜን ኮሪያ ከዚህ በፊትም በቀጣናው ውጥረቶች በሚያይሉበት ወቅት እንዲህ አይነት መረጃዎችን በመልቀቅ ትታወቃለች። ባለፈው ዓመት የሀገሪቱ መንግሥት መገናኛ ብዙኃን አሜሪካን ለመዋጋት 800ሺ ወጣቶች መመዝገባቸውን ይፋ አድርጋ ነበር።
የስትራቴጂክ ስተዲስ ዓለምአቀፍ ኢንስቲትዩት መረጃ እንደሚያመለክተው ከሆነ ሰሜን ኮሪያ 1 ነጥብ 28 ወታደሮች እና 600ሺህ ተጠባባቂዎች አሏት።
ሰሜን ኮሪያ በድንበር አካባቢ ያለውን ምሽጓን ለማጠናከር ሁለቱን ኮሪያዎች የሚያገናኘውን ሙሉ በሙሉ እንደምታፈርስ አሳውቃ ነበር።
በጋዜጣው ሪፖርተር
አዲስ ዘመን ጥቅምት 7/2017 ዓ.ም