ሐሰተኛ የቦንብ ሽብሮች ከ10 በላይ የሕንድ በረራዎችን አስተጓጎሉ

በሕንድ አየር መንገድ ጉዳዩ የተለመደ ቢሆንም ባለፉት ሁለት ቀናት በተደጋጋሚ እየቀረቡ የሚገኙ ጥቆማዎች ምንጭ ምን እንደሆነ አልታወቀም።

ባለፉት 48 ሰዓታት በሕንድ በረራዎች ላይ የቀረበውን ሐሰተኛ የቦንብ ሽብር ጥቆማዎችን ተከትሎ 10 በረራዎች እንደተስተጓጎሉ ተነገረ።

በትላንትናው እለት የሲንጋፖር አየር ኃይል ቦንብ ተጠምዶባቸዋል የተባሉትን አውሮፕላኖች በተዋጊ ጄቶች በማጀብ ሕዝብ ከሚሰበሰብባቸው አካባቢዎች ራቅ ብለው እንዲቀመጡ አድርጓል፡፡

ይህ ከመሆኑ ከሰዓታት በፊት የኢንዲያ ኤክፕረስ ንብረት የሆነ ከደልሂ ወደ አሜሪካ ቺካጎ ሲጓዝ የነበረ አውሮፕላን የቦንብ ስጋቱን ተከትሎ በካናዳ እንዲያርፍ ተገዷል፡፡

ሆክስ ቦምብ ትሬት ወይም ሐሰተኛ የቦምብ ማስፈራሪያዎች በብዛት ሕዝብ በሚበዛባቸው አካባቢዎች ፈንጂዎች ስለመጠመዳቸው ለፀጥታ አካላት የሚደረጉ ጥቆማዎች ናቸው።

በሕንድ አየር መንገድ ጉዳዩ የተለመደ ቢሆንም ባለፉት ሁለት ቀናት በተደጋጋሚ እየቀረቡ የሚገኙ ጥቆማዎች ምንጭ ምን እንደሆነ አልታወቀም፡፡

የአሁኑ ጥቃት ለየት የሚያደርገው ኤር ኢንዲያን ጨምሮ በሦስት የተለያዩ የአየር ትራንስፖርት በሚሰጡ ድርጅቶች ንብረት በሆኑ አውሮፕላኖች ላይ ተደጋጋሚ ጥቆማ መድረሱ ነው፡፡

በኤክስ (ትዊተር) ገጽ ላይ በአውሮፕላኖች ላይ ቦምብ ስለመጠመዱ አንድ ማስፈራሪያ ከተለጠፈ በኋላ መነሻቸውን ከሕንድ ሙምባይ ያደረጉ 3 ዓለም አቀፍ በረራዎች እንዲዘገዩ የተደረገ ሲሆን፤ ከጉዳዩ ጋር በተገናኘ የተጠረጠረ አንድ ታዳጊ በፖሊስ ተይዞ ምርመራ እየተደረገበት እንደሚገኝ ቢቢሲ ዘግቧል፡፡

በተመሳሳይ በኤር ኢንዲያ ንብረት በሆነ አውሮፕላን ላይ የበረራ ቁጥሩ ተጠቅሶ በተለጠፈ የቦምብ ስጋት 7 በረራዎች እንዲሰረዙ ተደርጓል፡፡

በበረራዎቹ መዘገየት እና መሰረዝ ከፍተኛ ኪሳራ እንደደረሰባቸው ያስታወቁት አየር መንገዶቹ ከሲቪል አቪዬሽን ደኅንነት ባለሥልጣናት እና ከፖሊስ ጋር በመተባበር ጉዳዩን ለማጣራት እየሠሩ እንደሚገኙ ገልጸዋል፡፡

የቀረበውን ስጋት ተከትሎ ተሳፋሪዎች ከነሻንጣቸው እና በካርጎ ከተጫኑ ጭነቶች ጋር እንዲወርዱ ከተደረገ በኋላ የኢንጂነሪንግና የደኅንነት ቡድኖች አውሮፕላኑ ድጋሚ ወደ አየር ላይ ከመውጣቱ በፊት አስፈላጊውን ማጣሪያ የሚያደርጉ ሲሆን በዚህ ሂደት አየር መንገዶች በሺህ ዶላሮች የሚቆጠር ኪሳራ ያጋጥማቸዋል፡፡

በጋዜጣው ሪፖርተር

አዲስ ዘመን ጥቅምት 7/2017 ዓ.ም

Recommended For You