ኢትዮጵያ የአፍሪካ ዋንጫን ለማዘጋጀት በይፋ ጥያቄ አቅርባለች

ኢትዮጵያ የ2029 አፍሪካ ዋንጫን ለማዘጋጀት ለአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) በይፋ ጥያቄ ማቅረቧ ታውቋል:: ኢትዮጵያ በቅርቡ 46ኛውን የካፍ ጠቅላላ ጉባኤና የአፍሪካ ከ20 ዓመት በታች የእጅ ኳስ ሻምፒዮናን ለማስተናገድ እያደረገች የሚገኘውን ዝግጅት በተመለከተ የባሕልና ስፖርት ሚኒስቴር፣ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽንና የእጅ ኳስ ፌዴሬሽን ከትናንት በስቲያ መግለጫ ሰጥተዋል::

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ኢሳያስ ጂራ በመግለጫው ላይ እንደተናገሩት፣ መንግሥት የ2029 የአፍሪካ ዋንጫን ለማዘጋጀት ፍላጎት እንዳለው ለካፍ በደብዳቤ ጠይቋል:: ካፍ የኢትዮጵያን ጥያቄ መቀበል አለመቀበሉንም በሚቀጥለው ዓመት ሞሮኮ በሚያካሂደው ጠቅላላ ጉባኤ ላይ እንደሚወሰን አቶ ኢሳያስ ጠቁመዋል::

ካፍ በቀጣዩ ሳምንት ጠቅላላ ጉባዔውን አዲስ አበባ ላይ ሲያደርግ ኢትዮጵያ በመድረኩ የ2029 የአፍሪካ ዋንጫን የማዘጋጀት ፍላጎትን በማሳየት ዕድሉ እንዲሰጣት ቅስቀሳ እንደሚደረግም አቶ ኢሳያስ ገልጸዋል:: የካፍ ፕሬዚዳንትና ምክትሎቻቸው በዚህ ጉባኤ ለመታደም ሲመጡም በተናጠል ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር ውይይት እንደሚያደርጉም ተጠቁሟል::

አቶ ኢሳያስ የዘንድሮውን የካፍ ጠቅላላ ጉባዔ በተመለከተ በሰጡት ማብራሪያ፣ ጉባዔው ወደ አዲስ አበባ የመጣው የኢትዮጵያ መንግሥት የአፍሪካ ዋንጫውን ለማዘጋጀት እንቅስቃሴ ከጀመረ በኋላ መሆኑን አስረድተዋል:: 46ኛው የካፍ ጠቅላላ ጉባኤ ኮንጎ ኪንሻሳ ላይ እንዲካሄድ በሥራ አስፈጻሚ ተወስኖ

እንደነበር እና በወረርሽኝ ምክንያት ተሰርዞ መንግሥት ባሳየው ፍላጎት ወደ ኢትዮጵያ ሊመጣ እንደቻለም አቶ ኢሳያስ ተናግረዋል::

ጉባኤውን ለማዘጋጀት በቀረበው ጥያቄ መሠረት ናይሮቢ በተካሄደ የካፍ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ስብሰባ የተወሰነ ሲሆን፣ የጉባኤውን ወጪ የሚሸፍነው መንግሥት ቢሆንም ኢትዮጵያ የሌላ ሀገር ዝግጅት በመውሰዷ፣ መንግሥትና ካፍ ግማሽ ወጪ በመጋራት ጉባኤው በአዲስ አበባ እንደሚካሄድ ፕሬዚዳንቱ ገልጸዋል::

ኢትዮጵያ በዚህ ወር የካፍን ጠቅላላ ጉባዔና የአፍሪካ ከ20 ዓመት በታች የእጅ ኳስ ሻምፒዮናን ለማስተናገድ ዝግጅቷን እያጠናቀቀች እንደምትገኝም በጋዜጣዊ መግለጫው ላይ ተጠቁማል:: የካፍ ጠቅላላ ጉባኤና ከጥቅምት 10 ጀምሮ እስከ 12 በስካይ ላይት ሆቴል እንደሚካሄድ የተገለፀ ሲሆን፣ የአፍሪካ ከ20 ዓመት በታች እጅ ኳስ ሻምፒዮና ደግሞ ከጥቅምት 23 እስከ 27/2017 ዓ.ም ድረስ ይደረጋል::

የሁለቱም ስፖርታዊ ኩነቶች የቅድመ ዝግጅት ምዕራፍ የሚገኝበትን ደረጃ አስመልክተው ባሕልና ስፖርት ሚኒስቴር፣ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን እንዲሁም የእጅ ኳስ ፌዴሬሽኖች መስተንግዶዎቹ ስኬታማ እንዲሆኑ በቅንጅት እየሠሩ እንደሚገኙ አስታውቀዋል::

የባሕልና ስፖርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ሻዊት ሻንካ እንደገለፁት፣ በዚህ ዓመት ከስፖርት ዲፕሎማሲ አኳያ ስኬታማ ሥራዎች ተሠርተዋል:: ካለፈው ዓመት ጀምሮ ኢትዮጵያ ትልልቅ ዓለም አቀፍና አሕጉር አቀፍ ውድድሮችን ማስተናገዷን በማስታወስም በዚሁ ጥቅምት ወር መጀመሪያ አንስቶ ኢትዮጵያ የአፍሪካ ጠረጴዛ ቴኒስ ሻምፒዮና እና ጠቅላላ ጉባኤን እያስተናገደች እንደምትገኝ ተናግረዋል:: በተጨማሪም የካፍ ጠቅላላ ጉባኤና የአፍሪካ ከ20 ዓመት በታች እጅ ኳስ ሻምፒዮናንም ለማስተናገድ ዝግጅቶች መጠናቀቃቸውን አክለዋል::

እንደ ሚኒስትሯ ማብራሪያ፣ ስፖርታዊ ዝግጅቶቹ በኢትዮጵያ መካሄዳቸው በሀገር ገጽታ ግንባታና በኢኮኖሚ ረገድ የውጭ ምንዛሪ ለማመንጨት ትልቅ ሚና አላቸው:: ለዚህም ዝግጅቶቹን የተሳካ ለማድረግ በመንግሥት ከፍተኛ አመራሮች የሚመራና የቴክኒክ ባለሙያዎችን ያካተተ ዐቢይ ኮሚቴ ተቋቁሞ ሥራዎችን እያከናወነ ይገኛል:: የሚሠሩት ሥራዎች በልዩ ሁኔታ እየተገመገሙም ይገኛሉ:: በተለይም የካፍ ጠቅላላ ጉባኤን ስኬታማ ለማድረግ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የሚመራና የተለያዩ ሚኒስትር መሥሪያ ቤቶች የተካተቱበት ኮሚቴ ተቋቁሞ እየተሠራ ይገኛል:: በተመሳሳይ የአፍሪካ ከ20 ዓመት በታች እጅ ኳስ ሻምፒዮናን የተሳካ ለማድረግ ከሚኒስትር መሥሪያ ቤቱና ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ የተውጣጣ ኮሚቴ ተዋቅሮ አስፈላጊው ዝግጅት እየተደረገ ነው::

በካፍ ጠቅላላ ጉባኤ ለመታደም ከ400 በላይ እንግዶች የሚመጡ ሲሆን ከፊፋና ከሌሎች አሕጉራት ኮንፌዴሬሽኖችም እንግዶች ተጋብዘዋል:: እንግዶቹ ከሀገራቸው ለጉባኤው ወደ ኢትዮጵያ ሲመጡም የቪዛ ወጪ ከክፍያ ነፃ የተደረገ ሲሆን፣ ሥራዎችም በተቋቋመው ኮሚቴ እየተገመገሙ ነው::

የቴክኒክ ቡድኑ ሥራውን ቀደም ብሎ በመጀመሩ እንግዶቹ ነገና ከነገ በስቲያ ወደ አዲስ አበባ እንደሚገቡ ይጠበቃል:: ከዋናው የካፍ ጉባኤ አስቀድሞ እሁድ ቀኑ ሙሉ እና ሰኞ ጠዋት የየዞኑ ኮንፌዴሬሽኖች ስብሰባዎች በተናጠል ከካፍ ፕሬዚዳንት ፓትሪስ ሙሴፔ ጋር ይካሄዳሉ:: በመቀጠልም ሰኞ ከ4፡00 ሰዓት ጀምሮ እስከ ቀን 7፡00 ሰዓት የካፍ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ስብሰባ ከተደረገ በኋላ በተሳታፊዎች መካከል የወዳጅነት ጨዋታ በአዲስ አበባ ስታዲየም ይደረጋል::

ማክሰኞ ከ4፡00 ሰዓት እስከ 7፡00 ሰዓት ድረስ ዋናው የ46ኛው የካፍ ጠቅላላ ጉበኤ የሚካሄድ ሲሆን፣ ከተጠናቀቀ በኋላም የካፍ ፕሬዚዳንት ፓትሪስ ሙሴፔ ለመገኛ ብዙኃን መግለጫ የሚሰጡ ይሆናል::

ዓለማየሁ ግዛው

 አዲስ ዘመን ጥቅምት 7/2017 ዓ.ም

 

 

 

Recommended For You