በመዲናዋ በከተማ ግብርና ከአንድ ሺህ 300 በላይ ዜጎች የሥራ ዕድል ተፈጥሯል

– ከ120 ሚሊዮን በላይ እንቁላል ተገኝቷል

አዲስ አበባ፡- በመዲናዋ ባለፉት ሦስት ወራት በከተማ ግብርና ከአንድ ሺህ 300 በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ ዕድል መፈጠሩን፤ ከዘጠኝ ሺህ ቶን በላይ የሥጋ ምርትና ከ120 ሚሊዮን በላይ እንቁላል መገኘቱን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የአርሶ አደርና ከተማ ግብርና ልማት ኮሚሽን አስታወቀ፡፡

በኮሚሽኑ የኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ወንደሰን አካሌ ለኢፕድ እንደገለጹት፤ በ2017 በጀት ዓመት በእንስሳትና በዕፅዋት ሃብት ልማት በግለሰብ፣ በማኅበራት እና በተቋማት ሰፋፊ የከተማ ግብርና ሥራዎች እየተሠሩ ይገኛል፡፡

በአዲስ አበባ በከተማ ግብርና ዘርፍ በሩብ ዓመት ለሦስት ሺህ ዜጎች የሥራ ዕድል ለመፍጠር ታቅዶ ባለፉት ሦስት ወራት ለአንድ ሺህ 330 ዜጎች አዲስ የሥራ ዕድል እንዳገኙ ጠቁመው፤ በዚሁ ዘርፉም ሰባት ሺህ 628 ቶን የሥጋ ምርት ለማግኘት ታቅዶ ከዘጠኝ ሺህ 378 ቶን የሥጋ ምርት መገኘቱን ተናግረዋል፡፡

እንዲሁም 132 ሚሊዮን 941 ሺህ በላይ እንቁላል ለማግኘት ታቅዶ ከ120 ሚሊዮን በላይ ማግኘት መቻሉን አመልክተው ፤ 900 ቶን የዶሮ ሥጋ ለማግኘት ታቅዶ አንድ ሺህ 442 ቶን ሥጋ ማግኘት ተችሏል ብለዋል፡፡

በተጨማሪም በወተት፣ በማር ፣ በዓሣ ምርት፣ በግቢ፣ በማሳና በጓሮ አትክልት ልማት ከእቅድ በላይ መከናወኑን አቶ ወንደሰን ጠቁመዋል፡፡

የሥራ ዕድሉ የተፈጠረው በእንስሳት እርባታ፣ በጓሮ አትክልትና ፍራፍሬ ልማት እንዲሁም በተለያዩ የግብርና ሥራዎች መሆኑን አስረድተዋል።

ኮሚሽኑ ወደሥራ ለሚሰማሩ ዜጎች የተለያዩ ሙያዊ ድጋፎችን እንደሚያደርግ አውስተው፤ በግብርና ዘርፍ የሥራ ዕድል ተጠቃሚ መሆን የሚፈልግ ማንኛውም ዜጋ ተደራጅቶ በመምጣት ምቹ ሁኔታውን ሊጠቀም እንደሚገባ አንስተዋል፡፡

በከተማ ግብርና የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ኮሚሽኑ በትኩረት እየሠራ መሆኑን ገልጸው፤ በቀጣይ በዘርፉ እየተሰጡ ያሉ የአቅም ግንባታ ሥልጠና፣ የግብዓትና ቴክኖሎጂ አቅርቦት፣ የሙያና ቴክኒክ ድጋፍና የልምድ ልውውጦች ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አመላክተዋል፡፡

በዶሮ እርባታ፣ በወተት ላም፣ በከብት ማደለብ፣ በአትክልት ልማት፣ በችግኝ ማፍላትና በሌሎች የሥራ መስኮች ዜጎች በምርጫቸው ወደ ቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች በመግባት የክህሎት መር ሥልጠና እንዲወስዱና ወደሥራ እንዲሠማሩ እየተደረገ መሆኑን አቶ ወንደሰን አስረድተዋል።

አማን ረሺድ

አዲስ ዘመን ጥቅምት 7/2017 ዓ.ም

 

Recommended For You