ሀገሪቱ በ2016 በጀት ዓመት በተለያዩ ዘርፎች ውጤታማ አፈጻጸሞችን ማስመዝገብ ችላለች። ውጤቶቹ የተመዘገቡት ደግሞ በብዙ ውጣ ውረዶች ውስጥ ታልፎ መሆኑ ነው። መንግሥት ይህን አፈጻጸም በተለያዩ ወቅቶች በተለያዩ መንገዶች ሲገልጽ ቆይቷል። አዲሱ የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ታዬ አፅቀ ሥላሴ በቅርቡ በተካሄደው 6ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትና የፌዴሬሽን ምክር ቤት 4ኛ ዓመት የሥራ ዘመን የመክፈቻ ስብሰባ ላይም ጠቅሰውታል።
ይህ ውጤታማ አፈፃፀም ከተመዘገበባቸው ዘርፎች መካከል የግብርናው ዘርፍ አንዱ ነው። ፕሬዚዳንቱ እንዳስታወቁት፤ በግብርናው ዘርፍ በበጀት ዓመቱ 6ነጥብ 9 በመቶ እድገት ተመዝግቧል፤ 700 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ከዋና ዋና ሰብሎች ማግኘት ተችሏል። የስንዴ ምርት እጅግ የሚያኮራና ልምድ የተቀመረበት መሆኑን ፕሬዚዳንቱ ጠቁመው፣ ስንዴ በመኸር 122 ሚሊዮን ኩንታል፣ በመስኖ ደግሞ 107 ሚሊዮን ኩንታል ማምረት መቻሉንም አመልክተዋል። የዚህ የስንዴ ልማት ስኬት ሀገሪቱ በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ስንዴ ለሁለተኛ ጊዜ ለውጭ ገበያ መላክ ያስቻለ መሆኑን ጠቅሰው፣ የበቆሎና የሩዝ ምርታማነትን ለመጨመር እየተሠራ መሆኑንም አስታውቀዋል።
በግብርናው ዘርፍ ለተመዘገበው ውጤት በርካታ ምክንያቶች ሊጠቀሱ ይችላሉ፤ ከእነዚህ መካከልም በዘር የሚሸፈነውን መሬት ማስፋፋት አንዱ ነው። በዚህም በኩልም ትልቅ ለውጥ መታየቱን ፕሬዚዳንቱ አስታውቀዋል። ፕሬዚዳንቱ እንዳሉትም፤ በ2015 በጀት ዓመት የታረሰው መሬት 20 ሚሊዮን ነጥብ 3 ሄክታር ነበር፤ ይህን አኃዝ በ2016 በጀት ዓመት በአምስት ሚሊዮን ሄክታር በማሳደግ ከ26 ነጥብ ሁለት ሚሊዮን በላይ ሄክታር መሬት ታርሷል።
መንግሥት ይህን ዕድገት በ2017 በጀት ዓመትም ለማስቀጠል በትኩረት እንደሚሠራ ፕሬዚዳንቱ አስታውቀዋል። ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር የግብርና ዘርፍ ለመገንባት ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሠራ አስታውቀው፣ በእዚህም በተለይ ለመስኖ ልማት ትኩረት በመስጠት የመስኖ ሜካናይዜሽን ሥራዎች እንዲጠናከሩ እንደሚደረግ አመልክተዋል።
መንግሥት በዘርፉ የተመዘገበውን ዕድገት አድንቆ፣ በቀጣይም በግብርናው ዘርፍ ላይ ውጤታማ ሥራ ለመሥራት አቅጣጫ ማስቀመጡ የዘርፉን ምርትና ምርታማነት ይበልጥ ለማሳደግ ያለውን ቁርጠኝነት አጠናክሮ መቀጠሉን ያመለክታል። የዘርፉን ምርትና ምርታማነት በሜካናይዜሽን አገልግሎት ይበልጥ ለማረጋገጥ፣ የመስኖ ልማቱን አጠናክሮ ለመቀጠልም ምቹ ሁኔታን ይፈጥራል።
እስከ አሁንም በመንግሥት ቁርጠኝነትና ክትትል የመኸርና የበልግ የግብርና ሥራን በማጠናከር፣ በመኸርና በበልግ ተወስኖ የኖረውን የግብርና ሥራ በመስኖ ይበልጥ እንዲጠናከር በማድረግ በዘርፉ በአጭር ጊዜ ውስጥ ታሪክ ማስመዝገብ ተችሏል። በስንዴ ልማት በመኸርና በመስኖ እየተገኘ ያለው ምርት ለእዚህ በአብነት ይጠቀሳል። በዚህም ብዙ የውጭ ምንዛሪ ተመድቦ ከውጭ ይመጣ የነበረውን ስንዴ በሀገር ውስጥ የስንዴ ምርት መተካት ተችሏል። ሀገሪቱ የውጭ ምንዛሪ ይዛም ስንዴ ለመግዛት እንዳትችል ጫና ይደርስባት እንደነበር ይታወቃል። በስንዴ ላይ የታየው ለውጥ ይህን ጫናም ማስቀረት ችሏል። የስንዴ ፍላጎትን በራስ አቅም መሸፈን የመቻል ነፃነትን አጎናጽፏል።
ይህ ምርታማነት የመጣው መንግሥት ለዘርፉ ያደረገውን ድጋፍና ክትትል ተከትሎ ነው። ይህን ዘርፍ በመደገፍ ብዙ ማትረፍ እንደሚቻል መንግሥት በጽኑ ይታመናል። ለእዚህም ማዳበሪያ በድጎማ እያቀረበ ያለበት ሁኔታ፣ በሜካናይዜሽን ማሽነሪዎች እና በብድር አቅርቦት ላይ በትኩረት የተሠራበት ሁኔታ በአብነት ይጠቀሳሉ። ሀገር በውጭ ምንዛሪ እጥረት በተፈተነችባቸው ባለፉት ዓመታት ለግብርናው ዘርፍ ምን ያህል ቅድሚያ በመስጠት ማዳበሪያ ሲያቀርብ እንደነበር ይታወቃል።
መንግሥት እንዳለፉት ዓመታት ሁሉ በዚህ ዘርፍ ላይ ትኩረት አድርጎ ለመሥራት አቅጣጫ ማስቀመጡ የምግብ ዋስትናን ከማረጋገጥና የውጭ ምንዛሪ ማስገኘት አንድ ነገር ሆኖ የተረጂነትን አመላካከትንም ለመስበር ለተያዘው አቅጣጫም አቅም ይሆናል። የስንዴ መስኖ ልማቱ ተጠናክሮ ይቀጥላል። እንደ ሩዝ ባሉት ሰብሎች ላይም የስንዴውን ታሪክ ለመድገም እየተሠራ መሆኑ ይታወቃል። በእነዚህ ምክንያቶችና ዘርፉ ገና ብዙ ሊሠራበት የሚችል ብዙ እምቅ አቅምም ያለው ከመሆኑ ጋር በማያያዝ በተቀመጠው አቅጣጫ መሠረት መሥራት ከዘርፉ አካላት ሁሉ ይጠበቃል።
ሀገር እጅ አጥሯት በውጭ ምንዛሪ እጥረት ሳቢያ ያላከናወነቻቸውን የግብርናውን ዘርፍ ሥራዎች ለመሥራት አሁን ምቹ ሁኔታ እንዳለ ይታሰባል። በቅርቡ ወደ ትግበራ የገባው የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ የዘርፉን ልማት ለማፋጠን የሚያስፈልገውን የውጭ ምንዛሪ ለማግኘት ምቹ ሁኔታን እንደሚፈጥር ይጠበቃል። በዚህም ለሜካናይዜሽን አገልግሎት በወሳኝ መልኩ መስፋፋት መሥራት ያስፈልጋል። ይህ ሲሆን የዘርፉን እቅድ ማሳካትም ብቻ ሳይሆን ከተቀመጠው እቅድም በላይ ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ ይቻላል።
አሁን ባለው ተነሳሽነት፣ ቁርጠኝነትና ክትትል ላይ ይህም ማድረግ ሲቻል ባለፉት ዓመታት በአስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥ ምርትና ምርታማነትን ሲያሳድግ የቆየው የግብርናው ዘርፍ ውጤታማነቱ ከእስከ አሁኑም የላቀ ሊሆን እንደሚችል ጥርጥር የለውም። በተለይ ለዘርፉ ምርትና ምርታማነት እድገት ወሳኝ ሚና ለሚጫወተው የሜካናይዜሽን አቅርቦትና ለሌሎች የመስኖ ልማት ሥራዎች ለሚያስፈልጉ ቴክኖሎጂዎችና ለመሳሰሉት የውጭ ምንዛሪ ማቅረብ ቅድሚያ ሊሰጠው ይገባል።
አዲስ ዘመን ጥቅምት 7/2017 ዓ.ም