የአፍሪካ መዲና በአፍሪካ ወጣቶች ዕይታ

ዜና ሐተታ

ከሰሞኑ ለሦስት ቀናት የቆየ የአፍሪካ አንድ ሺህ የወጣቶች ጉባዔ በአዲስ አበባ ተካሂዷል። ትኩረቱን የምግብ ሥርዓትና አግሮኢኮሎጂ ላይ ያደረገው ጉባዔ ላይ ለመታደም ከተለያዩ 45 በላይ የአፍሪካ ሀገራት የመጡ ከ250 በላይ ወጣቶች አዲስ አበባ ገብተዋል፡፡

ወጣቶቹ በጉባዔው በአፍሪካ የተረጋገጠ የምግብ ዋስትና እንዲኖር የመከሩ ሲሆን በቆይታቸው በከተማዋ የተሠሩና በመሠራት ላይ የሚገኙ የተመረጡ የልማት ሥራዎችን ጎብኝተዋል።

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅትም የልማት ሥራዎቹን ሲጎበኙ ያገኛቸውን የላይቤሪያ፣ ጋናና የኬንያ ወጣቶችን በጎበኟቸው የልማት ሥራዎች ዙሪያ ያላቸው አስተያየት ጠይቋል፡፡

ኦሊቪያ ፒ ሊቪንግስቶን ጉባዔው ላይ ለመሳተፍ ከላይቤሪያ የመጣች ወጣት ናት፤ ኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ እንደመጣች የገለጸችው ኦሊቪያ፤ በአዲስ አበባ ያለው የሕንጻ ግንባታዎችና በከተማዋ እየተሠራ ያለው የኮሪደር ልማት እንዳስደነቃት ትናገራለች፡፡

ኦሊቪያ፤ አዲስ አበባ በጣም ውብና በከተማዋ በተለያዩ ቦታዎች የተገነቡት ፓርኮች እና የመዝናኛ ቦታዎች ለነዋሪዎችም ሆነ ለጎብኚዎች በጣም ሳቢ መሆናቸውን ገልጻ፤ የላይቤሪያ መንግሥት በከተሞች በማስዋብ ረገድ ይህን ተሞክሮ ከኢትዮጵያ ወስዶ ተግባራዊ ሊያደርግ ይገባል ብላለች፡፡

በጉባኤው ላይ ሲነገረን የነበረውን ኢትዮጵያ የአረንጓዴ ዐሻራ ችግኝ ተከላ ንቅናቄ በጉብኝቴ ወቅት ከጠበኩት በላይ ሆኖ አግኝቼዋለሁ የምትለው ኦሊቪያ፤ ወደ ሀገሬ ይዤ የምመለሰው አንደኛው ተሞክሮ ነውም ብላለች፡፡

አረንጓዴ ዐሻራ ንቅናቄው በተለይም ትኩረቱን ለምግብ የሚሆኑ ችግኞች ላይ አድርጎ ከሠራ ኢትዮጵያ በምግብ እራሷን ለመቻል እያረገች ያለችውን ጥረት ያሳካል፡፡ ንቅናቄው በዋናነትም በአሁኑ ጊዜ በዓለም ላይ ያለው የአየር ንብረት ለውጥ ቀውስ ለመከላከል ትልቅ ሚና ይኖረዋል ስትልም ተናግራለች፡፡

ከአስር ዓመት በፊት ወደ ኢትዮጵያ እንደመጣችና የአሁኑ ለሁለተኛ ጊዜ እንደሆነ የምትናገረው ደግሞ ኬኒያዊቷ ወጣት ናስታሲያ ቲ ባውድ ኒጄንጋ ናት፡፡ ከተማዋ ላይ ካለፈው ጊዜ ካየችው ብዙ መሻሻሎችና እድገት መመልከቷንም ገልጻለች፡፡

ከጉብኝቴ ሁሉ በተለየ ያስደነቀኝ የኢትዮጵያ ታሪኮችና ባሕሎች በአግባቡ ተሰንደው መቀመጣቸው ነው ያለችው ወጣቷ፤ በተለይም ኢትዮጵያ በቅኝ ላለመገዛቷ ማሳያ የሆነው የዓድዋ ድል መታሰቢያ ሙዚየም አስደንቆኛል ብላለች፡፡

ኢትዮጵያ ከሌሎች አፍሪካ ሀገራት ልዩ የሚያደርጋት በርካታ ነገሮች አሏት፡፡ የአፍሪካ ኅብረት መቀመጫ መሆኗ፣ ምግቦቿ እንዲሁም የበርካታ ብሔሮች መገኛ መሆኗ ዋነኞቹ ናቸውም ትላለች፡፡

ሌላኛው በጉብኝት ወቅት ያገኘነው ከጋና የመጣው ንዪግማ ኦፓክፓጆር ጀምስ በበኩሉ፤ ወደ ኢትዮጵያ ሲመጣ የመጀመሪያው እንደሆነና ከጉብኝቱ በርካታ ዝርያ ያላቸው ዕፅዋቶችን መመልከቱ እንዳስደሰተው ገልጿል፡፡

ከተማዋን አረንጓዴ ለማድረግ እየተሠሩ ያሉ ሥራዎች የሚበረታቱ ናቸው ያለው ጀምስ፤ በተለይም በአንድነት ፓርክ ሁሉንም ብሔሮች ለመወከልና ለማስተዋወቅ የተሠራው ሥራ አስደንቆኛል፡፡ ይህም ኢትዮጵያ አንድነቷ የጠነከረ መሆኑን እንድረዳ አድርጎኛል ይላል፡፡

የተሠሩ የልማት ሥራዎች ለጎብኚዎች ምቹና የቱሪዝም ኢንዱስትሪው እንዲያድግ የሚረዳ ነው ያለው ወጣቱ፤ የኢትዮጵያ መንግሥት ፕሮጀክቶችን ሲሠራ የኢትዮጵያን ብሎም አፍሪካን ታሪክና ባሕል በሚወክልና በሚገልጽ መልኩ መሆን አለበት ሲል አስተያየቱን ሰጥቷል፡፡

የአፍሪካ ሀገራት የቱሪዝም ዘርፉን ለማሳደግ ያለውን ቢሮክራሲ ማቅለል እንደሚያስፈልግና በሁሉም የአፍሪካ ሀገራት ተዟዙሮ መጎብኘት ለሁሉም ዜጋ ቀላል መሆን አለበትም ይላል ጀምስ፡፡

ዳግማዊት አበበ

አዲስ ዘመን ጥቅምት 7/2017 ዓ.ም

 

Recommended For You