ምክክር ለኢትዮጵያ አማራጭ የሌለው ምርጫ

ዜና ሐተታ

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በሶማሌ ክልል ጅግጅጋ ከተማ የአጀንዳ የማሰባሰብ የምክክር ምዕራፍ መድረክ እያካሄደ ነው።

ምክክሩ ከዚህ በፊት በአዲስ አበባ እና በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደሮች እንዲሁም በሐረሪ፣ በአፋር፣ በሲዳማ፣ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ ጋምቤላ እና በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልሎች መካሄዱም የሚታወስ ነው።

ሆኖም በሀገራዊ ምክክር ሂደቱ እጅግ ተማምነው የራሳቸውን አስተዋፅዖ ለማበርከት ከሚታትሩት መሳ ለመሳ የምክክሩን ፋይዳ በጥርጣሬ የሚያዩትም አልጠፉም።

ለመሆኑ ለኢትዮጵያ ከሀገራዊ ምክክር የተሻለ አማራጭ ይኖራታል?

ገራድ መሐመድ ገራድ ኩልምዬ የሀገር ሽማግሌ እና በሶማሌ ክልል ዋና የጎሳ መሪ ናቸው።

እርሳቸው እንደሚሉት ባለፉት 100 የሚሆኑ ዓመታት እንደ ሶማሌ ሕዝብ በጥይት እሩምታ የተሰቃየ ክልል የለም። ለዚህ መንስዔው የምክክር በር አለመከፈቱ ነው፡፡

የምክክር በሮች ክፍት አለመሆናቸውን ተከትሎም በንግግር መፍትሔነት ላይ ተስፋ የቆረጡ ብዙ ወንድሞቻችን የትጥቅ ትግልን መርጠዋል የሚሉት ኩልምዬ፤ ሀገራዊ ምክክር በሠላም አብሮ ለመኖርም ሆነ ስለዕድገት ለማሰብ አማራጭ የሌለው ምርጫ መሆኑን ይጠቁማሉ፡፡

የሶማሌ ክልል ሕዝብ፣ ኢትዮጵያ ሶማሌን ያካተተ መልክ እንዲኖራት ይፈልጋል ያሉት ዋና የጎሳ መሪው፤ የክልሉ ሕዝብ ጥቅምም እኩል ሊከበርለት እንደሚገባ ያነሳሉ።

ሕዝቡ ከሌሎች ወንድም ሕዝቦች ጋር ተባብሮና ተከባብሮ ለመኖር እንደሚፈልግ በመግለፅ፤ ሀገሪቱ አርብቶ አደር አርብቶ አደር የሚሸት ፖሊሲ እንዲኖራት ማድረግ እንደሚገባ ይናገራሉ። ይህንን ለማድረግ የሚቻለውም ምክክር ሲኖር ነው ባይ ናቸው፡፡

ኩልምዬ እንደሚሉት፤ የሱማሌ ክልል እኔን የማይመስል ሀገር ነው እያለ ወደ ትጥቅ ትግልና ግጭት በመግባት የተለያዩ ችግሮች የማይጠፉበት አካባቢ ሆኖ መቆየቱ የሚታወቅ ነው። በዚህም ምክንያት የሰው ሕይወት ሲጠፋ ቆይቷል።

እንደዚህ ዓይነት ችግሮችንም ለመፍታት ሀገራዊ ምክክሩ በወሳኝ ጊዜ የመጣ ነው ሲሉም ያስረዳሉ። እንዲያውም መቅደም ነበረበት ይላሉ፡፡

ሁሉንም ኢትዮጵያዊ የሚመስል ሀገረ መንግሥት እና ሀገር እንዲኖረን ሀገራዊ ምክክሩ እጅግ አስፈላጊ ነው ብለውም፤ ለዚህም ሁሉም የየድርሻውን ለመወጣት በመረባረብ ለስኬት ሊያበቃው ይገባል ሲሉ ጥሪያቸውን ያቀርባሉ፡፡

ሀገራዊ ምክክሩ የሀገራችን አጀንዳ ነው የሚሉት የሀገር ሽማግሌው፤ እንደ ኢትዮጵያዊነታችን በምክክሩ ያገባናል ብለዋል።

መመካከር ሲቻል የሶማሌን ክልል መልክ ያካተተ ሀገር እንዲመሠረት፤ ፖሊሲና ሕጎቿ የሱማሌን ክልል ሕዝብ ግምት ውስጥ ያስገባ ሀገር እንዲኖር እና ጠንካራ ሀገረ መንግሥት ግንባታ እንዲካሄድ መንገዶች ይኖራሉ ሲሉም ያስረዳሉ፡፡ ከወንድም ሕዝቦች ጋርም በሠላም ለመኖር የሚያስችል መንገድ መፍጠር የሚቻለው በምክክር እንጂ በግጭት አለመሆኑን መረዳት እንደሚገባ ነው የሚናገሩት።

ባለፉት 100 የሚሆኑ ዓመታት የክልሉ ሕዝብ በግጭቶች የተነሳ በርካታ መከራዎችን እንዳየ ጠቅሰው፤ ችግሮች በዚህ መንገድ የሚፈቱ ቢሆን ኖሮ ቀደም ብለው ሊፈቱ ይችሉ እንደነበር ጠቁመዋል።

ሆኖም በአሁኑ ወቅት ችግሮች መቶ በመቶ የሚፈቱት በመወያየት እና በሠላማዊ መንገድ መሆኑን በማመን ትጥቅ ትግል ሲያደርጉ የነበሩ ኃይሎች ሁሉ ወደ ሠላማዊ ትግል ገብተዋል ብለዋል። ይህም ምክክሩ የፈጠረው ተስፋ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

ሌሎች ክልሎች ከዚህ ትምህርት ሊወስዱ እንደሚገባ ጠቅሰው፤ ሰው ከሞተ እና ንብረት ከወደመ በኋላ ለውይይት ከመቀመጥ ሰው ሳይሞት እና ንብረት ሳይወድም ችግሮችን በጠረጴዛ ዙሪያ መፍታት ይገባል ሲሉም ያሳስባሉ። እንደ ሀገርም ከውይይት የተሻለ አማራጭ የለም ሲሉ ያክላሉ።

ሀገራዊ ምክክር ለምን አስፈለገ የሚል ጥያቄ ሁሌ ይነሳል የሚሉት ደግሞ የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር መላኩ ወልደማርያም ናቸው።

“ሀገራዊ ምክክር ያላስፈለገ ለኢትዮጵያ ምን ሊያስፈልጋት ይችላል?” ሲሉም ጥያቄውን በጥያቄ ይሞግታሉ።

ኢትዮጵያ እንደሀገር ከዚህ የበለጠ ነገር ሊያስፈልጋት አይችልም ያሉት ኮሚሽነሩ፤ የምክክሩ ዓላማም እስከዛሬ እርስ በርስ ሲያጨራርሰን ከኖረው አዙሪት እንውጣ የሚል መሆኑን ያብራራሉ።

በኢትዮጵያ ውስጥ ከዚህ በፊት ከተሠሩ፤ አሁን እየተሠሩ ካሉ እና ለወደፊት ከሚሠሩ ፕሮጀክቶች ሁሉ የሀገራዊ ምክክር አጀንዳን የሚያክል አይኖርም ሲሉም ያስረዳሉ።

ምክክሩ ሀገራዊ መግባባትን ለማምጣት ይረዳል የሚሉት ኮሚሽነር መላኩ፤ ይህም አለመግባባትን፣ እንደሀገር ልጅ አለመተያዬትን እና በየጊዜው የሚፈጠሩ ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት የሚያስችል ነው ሲሉ ያስገነዝባሉ።

እንደ ኮሚሽነር መላኩ ገለፃ፤ ኢትዮጵያ በጦርነት እና በግጭት አዙሪት ውስጥ ነው ያለችው። ከዚህ አዙሪት መውጣት ይገባል።

ከአዙሪቱ መውጣት የሚቻለውም ሀገራዊ መግባባት መፍጠር ሲቻል መሆኑን በመግለጽ፤ ሀገራዊ መግባባት መፍጠርም የፀና ሀገረ መንግሥት ለመመሥረት ይጠቅማል ሲሉ በአመክኒዮ ያስረዳሉ።

በተጨማሪም በምክክር የሚፈጠር ሀገራዊ መግባባት አዲስ የፖለቲካ ሥርዓት ለመቅረፅ ያስችላል ሲሉ ነው ያሉት።

ከዚህም ባሻገር ሀገራዊ ምክክሩ ትክክለኛ የሆነ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ለመዘርጋት እንደሚረዳ በመግለፅ፤ ከሁሉ በላይ ግን ሀገራዊ ምክክር ኢትዮጵያ የተሰኘች ሀገር የሁላችንም ኢትዮጵያውያን እንደሆነች ለማረጋገጥ ያስችላል ይላሉ።

ይህች ሀገር የእኛ የኢትዮጵያውያን ሀገር ናት፤ ዜጎቿም እኛ ኢትዮጵያውን ነን የሚሉት ኮሚሽነሩ፤ ይህንን ለማረጋገጥ የሀገራዊ ምክክሩ ቁልፍ ሚና ይጫወታል ነው ያሉት።

ምክክሩ ሰዎች የማይሞቱባት፣ የማይፈናቀሉባት ይልቁንም ዜጎች ተምረው ለከፍተኛ ደረጃ የሚበቁባት በሁሉም ዘርፍ ተሠማርተው ያለምንም መሸማቀቅ እና ስጋት የሚኖሩባት ሀገር እንድትሆን የሚያስችል መሆኑንም ነው የሚያነሱት።

ምክክሩ ይሳካል፤ መሳካትም አለበት ያሉት ኮሚሽነር መላኩ፤ ከምክክር ውጪ ሌላ ምርጫ የለም ሲሉ አፅንዖት ይሰጣሉ።

ውብሸት ሰንደቁ

አዲስ ዘመን ጥቅምት 7/2017 ዓ.ም

 

Recommended For You